የእግዚብሄር ተስፋ በእግዚአብሄር ላይ ላለን እምነት የጀርባ አጥንትና መሰረት ነው። እግዚአብሄርን የሚያምኑ እርሱን ተስፋ አድርገው ይጠብቃሉ፤ ተስፋ በሌለበት እምነት የለምና። ቃሉ የሚነግረን እንዲህ በማለት ነው፦
እብ.11:1-3 ‘’እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።’’
ተስፋ በማይታይ ግን ሊሆን ባለው ነገር ላይ ይሆናል በሚል መተማመን፣ በተለይ ተናጋሪው እግዚአብሄር ሲሆን እግጠኛ ሆኖ እስኪገለጥ አምነው የሚጠብቁት የታመነም ቃል ነው። እግዚአብሄር የተናገራቸው ቃሎች ውስጥ ተስፋ ህያው ሆኖ ይኖራል፤ ያው ተስፋምነው በእምነታችን ላይ ህይወት የሚዘራው። አማልክት ከህያው እግዚአብሄር የሚለዩት በዋናነት በዚህ ነው፤ አማልክት ተስፋ የላቸውምና ተስፋ አይሰጡም። የራሳቸው ህልውና ራሱ የተረጋገጠ ስላልሆነ እነርሱን ተስፋ የሚያደርጉ እንደነርሱ ተስፋ የለሽ ናቸው፤ እግዚአብሄር ግን ዘመናት ተሻግሮ፣ ትውልድን አልፎ ለልጅልጅ የሚሆን ቃልን ይናገራል። የተናገረውን ይፈጽም ዘንድ ለሰዎች ያን ተስፋ ገና ነገሩ ሳይመጣና ሳይሆን ይሰጣል፤ ያን ቃል የጨበጡ እስከፍጻሜው ይከተሉታል፤ የተናገረውን አምነው ይጠብቁታል፣ በወሰነው ጊዜ መጥቶ የተናገረውን ይፈጽምናም ተስፋውን ይሞላል።
ዕብ.6:11-15 ‘’በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፦ በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤ እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።’’
ቃሉ እንደሚያሳየው ተስፋችንን በእምነትና በተግስት ደግፈን እስከ ፍጻሜው ልናደርሰው ተገቢ ነው፤ እምነታችን በዳተኝነት እየተሳበ ቢጎተትም ጨክነን በእምነታችን በመትጋት የተስፋውን መሙላት ማየት ይገባል። አማኝ በተስፋ ምክኒያት ህይወቱ ይለመልማል፤ ህይወት ጭፍግግ ቢል እንኳ፣ ነገሮች ጭልምልም ባሉ ሰአትና ምንም የሚታይ ተጨባጭ ነገር በሌለበት ወቅት እግዚአብሄር የተናገራቸውን የተስፋ ቃላት ከፍ አድርጎ ሲያነሳ ልቡ ይሞላል፣ ደስታው ይለመልማል፣ እምነቱ አቅም ያገኛል እንዲህ ስለሚል፦
‘’በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም። እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ።’’ (መዝ.118:5-7)
እግዚአብሄር የነገረኝ እስከሚሆን አስጨንቆ የተስፋዬን ጋሻ ሊያስጥል ያለው ጠላቴ ቢኖርም በትግስት አምላኬን እጠራለሁ፣ እግዚአብሄር አምላኬም ወደተስፋዬ የሚያስኬደኝን መንገዴን እያሰፋልኝ ወደ ፍጻሜው እደርሳለሁ፣ ስለዚህ ፊት ለፊቴ የተጋፈጥከኝ ጠላቴ ሆይ አልፈራህም አምላኬ በቀኜ ነውና።
የተስፋ ነገር እንዲህ ነው፣ ደግሞ ከእግዚአብሄር የምንቀበለው ተስፋ የራሱ ባህሪያት ያሉት ነው፤እነርሱን በማስተዋል መረዳት ብቻ በእምነት መበርታትን ይፈጥራል፣ ብዙዎች የሚቀበሉትን ተስፋ ይዘው የማይቆዩት በተስፋው ምንነት ላይ ያላቸው መረዳት እንደ ቃሉ ስለማይሆን ነው።በእግዚአብሄር ላይ ያለን እምነት በሰዎች ላይ ካለን እምነት የሚለየው እግዚአብሄር የሚያሳምነን በሚሰጠን የተስፋ ቃል በኩል በመሆኑ ነው፤የተስፋ ቃል ደግሞ የፍጥረት ቃል አይደለም፦ የሰው ቃልና የመላእክት ቃል እንኩዋን ተስፋ ሲኖረው ብርቱ ነው፤ የእግዚአብሄር ግን ከዚያ እጅግ ይልቃል፤ የፍጥረት ቃል በሁኔታዎች መሃል ይቀያየራልና፤የእግዚአብሄር ቃል ግን የተስፋ ቃል ስለሆነ በሁኔታዎች ተጽእኖ አይቀየርም፤ አይዘገይም፤ አይጠፋምም። ዘመናት ይለፉ፣ ሁኔታዎች ይለዋወጡ፣ ከፍ ይበሉ ወይም ዝቅ ይበሉ በነርሱ ምክኒያት የተስፋው ቃል ከቦታው ፈቀቅ አይልም፣ ከልኩም አይዛነፍም።
ዕብ.6:16-18 ‘’ እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ’’
የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል በምንም ሁኔታ ምኪያት እንደማይለወጥ ስናስተውል ጨክነን የተስፋውን ፍጻሜ በእምነትና በጉጉት እንጠብቀዋለን፦ ንጋት ሲሆን ተስፋው በውስጣችን ይደምቃል፣ በመሸም ጊዜ ወደ መኝታ የምንሄደው ተስፋው በልባችን ረግቶና ተቀምጦ ነው፣ ዘመናት ወደፊት ሊገሰግሱና እኛን ወደኋላ ሊጎትቱን ይችላሉ፤ አይኖች ይፍዘዙ፣ ጅማትም ይሸብሸብ የተስፋው ቃል ሲገናኘን ሳይለወጥ ከአምላካችን እንደወጣበት አወጣጥ ሆኖ ይታያል፤ በእንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ላለፉ ወዳጆቹ እግዚአብሄር በክብር ይገለጥላቸዋል፤ እርሱ ተስፋ ያደረጉትን ሊገናኝ በእርግጥ ይመጣልና። አብረሃም እግዚአብሄር ተስፋ ከገባለት በኋላ ብዙ ዘመናትን ጨክኖና ታግሶ ሲጠብቅ ኖሮአል፤ ነገር ግን በቃ አበቃ የኔ ነገር እያለ ማቅማማት ላይ ሳለ እግዚአብሄር የተናገረውን የማይረሳ ነገር ግን የሚጠበቅ አምላክ መሆኑን አሳየው፦
ዕብ.6:13-14-15 ‘’እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፦ በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤ እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።’’ ይላል።
ተስፋ ሲደክም ግን ጥርጥር በእምነታችን ውስጥ ሰርጎ ይገባል፤ ካላስተዋልንና በውስጣችን ከከረመ እምነታችንን ቀስ በቀስ ይበላል ኋላም ይውጠዋል፤ እምነት ሲዋጥም የተነገረን ያ የተስፋ ቃል ማረፊያ አጥቶ ከልብ ይነቀላል። ያ ከመሆኑ አስቀድሞ እምነት እንዳይናጋ መጠበቅ ይገባል፣ የተስፋ ቃል ላይም ተጣብቆ መቆየት ያስፈልጋል።
የእውነተኛ አምልኮ ጀማሪ የሆነው አብረሃም ከእግዚአብሄር ዘንድ የእምነት አባት የሚል ስም ተቀብሎአል፤ እኛም በርሱ መንገድ እግዚአብሄርን ብናምን የአብረሃም ልጆች እንሆናለን። የአብረሃም እምነት በተስፋ ላይ የተመሰረተ ነበር፤ በመስዋእት ላይ የተደገፈም ነበረ፦
ሮሜ.4:16-22 ‘’ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው። ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። ስለዚህ ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ነገር ግን፦ ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም፥ ስለ እኛም ነው እንጂ’’
እኛም እንደ አብረሃም የጠነከረ እምነት ላይ የምንመሰረትበት መሰረት በተስፋው ላይ የሚኖረን መጣበቅ ነው፤የእምነትም ምክኒያት እርሱ ነው። በዘፍ.22:17-18 ውስጥ ስለአብረሃም ተስፋ የሚናገር ክፍል አለ፤ እግዚአብሄር አብረሃምን፦
‘’የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።’’ አለው። በርሱ ዘመን የአብረሃም ወዲያው ቀጣይ የሆነው ዘር ይስሃቅ ሲሆን እርሱም በምድር የተገባለትን ተስፋ የሚሸከም ልጅ ሆኖ ተወለደ፤ ነገር ግን እግዚአብሄር ለገባው የዘላለም ተስፋ ፍጻሜው በመንፈሳዊ ዘር በክርስቶስ ሆነ። ክርስቶስ የአብረሃም የተስፋ ዘር ነው፣ ይስሃቅ ግን የስጋ ዘር። የአብረሃምን የምድር ስጦታ ይስሃቅ ወርሶአል፤ አብረሃም በመንፈስ የተቀበለው የተስፋ ቃል ደግሞ የመንፈስ ተስፋ ሆኖ የቃሉን ዘር ክርስቶስን በተስፋ ሲጠብቅ ኖሮ ሞተ።
አብረሃም አመነ ተብሎ ለምን ተጻፈለት? አብረሃም ባመነ ሰአት ከእግዚአብሄር የተቀበለው ነገር አልነበረም፣ የሆነለት ነገርም አልነበረም፤ አብረሃም ግን በእግዚአብሄር ማንነት እርግጠኛ ስለሆነ በገባለት ቃልኪዳን አልተጠራጠረም። በስጋ የሆነውን ብናይ እንኩዋን አብረሃም ይስሃቅ እስኪመጣለት 25 የመጠበቅ አመት አሳልፎአል። ሳራም ከዛሬ ነገ እንደምታረግዝና ልጅ እንደምትታቀፍ በጉጉት እየጠበቀች ያን ሁሉ ዘመን ተመላልሳለች፤ ነገሩ ቀላል አልነበረም፤ በጥበቃዎችቸው ውስጥ መሰልቸት ብልጭ ይል ነበር፣ ጥርጥር ይታገል ነበር፣ የስጋ ፈቃድ ጣልቃ ገብቶም ነበር፣ በዚያ መንገጫገጭ አካሄድ ውስጥ ስቶ ከእምነት መፈናቀል ሁሉ ሊኖር ይችል ነበር፤ ነገር ግን በሆነው ነገር ሁሉ ውስጥ፣ በተከታተላቸው ውጣ ውረድና የእምነት ግብግብ ውስጥ ተስፋ የሚባል ብርቱ ማሰሪያ ገመድ ነፍሳቸውን አጥብቆ ባያስር አብረሃምም ሳራም የተሳሳቱበት አጋጣሚም ነበር እኮ፤ ተስፋው ግን በደከሙበት ቅጽበት አልተዋቸውም፣ በተሳሳቱበት የስጋ ፈቃዳቸው ውስጥ፣እርዳታው እንዲረሱ አላደረጋቸውም፤ ተንሸራተው አልጠፉም፣ ነገር ግን ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ቆጥረዋልና አንድ ቀን የልጅ ጥበቃቸው እውን የሚሆንላቸው ጊዜ መጣ።
ተስፋውን የሚተካ ሰዋዊ አሳብ ይመጣል
ተስፋ የቱን ያህል ብርቱና የማይለወጥ የማይናወጥም ቢሆን እንኳን የሰው ልብ ግን በጥበቃ ብዛት ዝለት ሲያደክመው ወይ በዝንጉነትና በመታከት ሲሸነፍ የተቀበለውን ብርቱ ተስፋ አጥብቆ ከመያዝ ወደ ኋላ ሊል ይችላል፤ ይህ ሁኔታ እግዚአብሄር ታግሶ በተሰጠው ቃል ላይ እንዲጸና ያመለከተውን ማሳሰቢያ ቸል እንደሚል አመልካች ነው፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ውጊያ ልባችንን ሲያጠቃ የእምነታችንን ግለት የሚያቀዘቅዝበት ጊዜ መኖሩ እርግጥ ነው። በሌላ በኩል የጠበቅነው ነገር ከነባራዊው ሁኔታ አንጻር ፍጻሜው የማይቻል ሲመስል የራስ መፍትሄ ብልጭ የሚልልን ጊዜም አለ፣ እኛም ያን የራስ መፍትሄ ሳንመረምር ተቀብለን እናደርገዋለን፣ ዘግይቶም ይሁን መሳሳታችንን ባስተዋልን ጊዜ ተጸጽተን ወደ ስፍራችን ብንመለስም በዚያ ስህተት የማይቀለበስ ጠባሳ በህይወታችን የሚፈጠር ሆኖ እናገኘዋለን። አብረሃምን ስንመለከት ከሚስቱ ከሳራ ጋር ይዘው የዘለቁት ተስፋ በዘመን ርዝማኔ ከእጃቸው ሾልኮ ስህተት ውስጥ አስገባቸውና የማይሽር ፈተና ተቀበሉበት፣ ታሪካቸው እንደሚያሳየው የፈተናቸው ምንጭ የነበረው ተስፋቸውን ከመጠበቅ ዝለው ሳለ በራሳቸው የወሰዱት የስጋ መፍትሄ ያመጣባቸው ውድቀት ነበር።
ሰው እምነቱ ሲናወጥ ተስፋውን የሚያሻሽልበት መላ ከስጋው ሊቀበል ይችላል፤አብረሃምና ሳራ በእንደዚያ ያለወቅት የተስፋውን ፍጻሜ በራሳቸው መንገድ ሊያስፈጽሙ ሞከሩና እስማኤል በተስፋቸው መሃል ጣልቃ ይገባ ዘንድ ብቅ አለ፤ የተፈራው አልቀረም የእስማኤል ልደት ከስጋ ፈቃድ ስለነበረ ለመንፈስ ፈቃድ እሾህ ሆኖ ኖረ፤ በእምነቱ ጨርሶ ያልደከመው አብረሃምም ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ተስፋውን አገኘ።
ዘፍ.16:1-4 ‘’የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት። ሦራም አብራምን፦ እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋ ግባ አለችው። አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች።’’
ተስፋው ምን ቢደነዝዝ ትዝታው ቃል ከውስጣችን ተፍቆ እስካልጠፋ ድረስ የወደቀ እምነታችን አንድ ቀን ይነሳል፤ ከብዙ መንገጫገጭ በሁዋላ መስመሩ ይገባል፤ ያኔም ቢሆን የጣልነውን እንድናነሳ ተስፋው ሃይል ይሆነናል። ስለዚህ ሁሉን ቻይ አምላክይችላል የሚል እምነት በአብረሃም ውስጥ እንዲፈጠር ብርቱ የሆነ የተስፋ ቃል ረዳው። የአብርሃምን እምነት ስንመለከት እምነቱን በእግዚአብሔር ሁሉን የመቻል ባሕርይ ላይ ያሳረፈ እንደሆነና የተስፋ ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን እንደተረዳ እንመለከታለን። እኛም ዛሬ የእምነት ጉዞአችን ማረፍ ያለበት በእርሱ ቃልና ማንነት ላይ መሆን ይገባዋል፣ የአብረሃም እምነት ወራሽ እስከሆንን ድረስ። ሃዋርያው ጳውሎስ ለመግለጽ እንደሞከረው አብረሃም እግዚአብሄር ማን መሆኑን ተረድቶ (እውነተኛና ቻይ መሆኑን አውቆ) ስለነበር የነገረውን የተስፋ ቃል አንድ ቀን ፈጽሞ እንደሚያስረክበው አምኖ ነበር እንጂ በጥርጣሬ አንድም ቀን ወደ ሁዋላ ብሎ አልተንሸራተተም።
ዘፍ.17:1-7 ‘’አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ።’’
ከእምነታችን ኋላ ሆኖ የሚደግፈን የተስፋ ቃል ምንኛ ብርቱ ነው? ከፊታችንስ ሆኖ ሩቅን አቅርቦ ሊያሳየን የሚችል፣ የእምነት አይናችንን የሚያበራና የሌለውን እንዳለ እንድንቆጥር የሚያደርግ የተስፋ ጉልበት እንደምን ብርቱ እንደሆነ ተመልክተናል?
አብርሃም ለሃያ አምስት ዓመታት ምንም ተጨባጭ ውጤት ሳያይግን ተስፋውን ሳይጥል በእግዚአብሔር ነገር ላይ አትኩሮቱን አድርጎ ተጉዞአል፣ ግዴለም አምላኬ ይችላልና ልታገስ ሲል ጠብቆአል። እኔ የማውቀው አምላክ አደርገዋለሁ ያለውን የሚፈጽም አምላክ ነው ሲል ራሱን አሳምኖ ጨክኖ ለዘመናት አምላኩን ጠበቀ። ለሃያ አምስት ዓመታት አብርሃም ያንን ቃል ኪዳን ጠብቋልና እምነቱን በሚጋፉት ምክኒያት ከመጣል ተቆጥቦአልና አሸንፏል!