ብቸኛና ፍጹም ሀይማኖት(9… )

የእግዚአብሄር ፈቃድ

​​​​​​​​ዕብ.3:1 ‘’ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ’’
እውነተኛ ሃይማኖት ከአይሁድ እምነት ይጀምር እንጂ ፍጻሜውን ያገኘው በኢየሱስ የመስቀል ስራ አማካይነት በተሰጠን እምነት ነው፤ የዚህ ሃይማኖት ሊቀካህናትና የሃይማኖቱ ሃዋርያ ራሱ ጌታ ነው፤ አይሁድ የተቀበሉት ህግ ሊመጣ ለነበረው በእምነት ለሚገኘው ለክርስቶስ ጽድቅ እንደ ጥላ ነበረ። ይህም እምነት አብረሃም እግዚአብሄርን አምኖ ጽድቅ ሆኖ በተቆጠረለት ጊዜ በእምነቱ ለአህዛብ ሳይቀር አባትነትን እንዳገኘ እናያለን፣ እንዲህ ይላል ቃሉ፦
‘’እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።’’ (ገላ. 3:3-8)
እግዚአብሄር አንድ ፍጹም የሆነ ሰውን ለማዘጋጀት ፍጹም የሆነ እምነት ሰጥቶአል፤ ይህ እምነት በጌታ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ላይ መሰረቱን የጣለ ነው። በዚህ እምነት ሃዋርያቶች ለአለም አዋጅ አውጥተው ደቀመዛሙርት ጌታን እንዲከተሉት አድርገዋል።
‘’ በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤’’ (ሮሜ. 1:16-18)
​​​​​​​​ቃሉ የሰው ዘር በሞላ ኃጢአትን እንደሰራና የእግዚአብሔር ክብር እንደጎደለው አስረግጦ ይናገራል፤ ሰው ከፍርድ ማምለጥ ባለመቻሉ እርሱን የሚወድ ፈጣሪ አምላክ በራሱ መንገድ ተገልጦአል፤ ስለዚህ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው እንድንጸድቅ ልጁን በመስቀል መስዋእት እንዲቀበል አድርጎአል። ​​​​​​​​በሮሜ.3:25-26 ላይ ሲያረጋግጥም፦
‘’እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥​​​​​​​​ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።’’ ይላል።
የእግዚአብሄር ወዳጅና የእምነት አባት የሆነው አብረሃም የተቀበለውን ተስፋ ለዘሩ እንዲሁም ለአህዛብም ጭምር ያሳልፍ ዘንድ በእምነት በኩል ከእግዚአብሄር ጽድቅን ተቀበለ፦
‘’ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።’’ ​​​​​​​​(ሮሜ.4:16-17)
ወደ አብረሃም እምነት የሚጠራውን የምስራች የሚቃወሙ አሉ
​​​የወንጌል እውነት ቅንነትና ልብን መስጠት ይፈልጋል፤ ሆኖም በአይሁድ በኩል ሲፈጠር የነበረው ውዥንብር ለሰዎች ሁሉ የተሰጠውን ፍጹም ሃይማኖት ለማሳት በር የከፈተና ጠማማ እውቀትን ያስፋፋ ነበር፤ እውነትን ባልተረዱ ሰዎች መሃል አይሁዳዊና አሕዛብ በሚል መለያየት ፈጥረው ሰዎች እንዳይቀራረቡና የጌታ ጸጋ በሰዎች ዘንድ እንዳይሰራ የሚለኩሱትን የጥፋት እሳት እንዲያጠፋና እንዲሽር ሃዋርያው ጳውሎስ ብዙ ደክሞአል፤ የሚዘዋወሩ ከንቱ ትምህርቶችና ውዥንብሮች ይጠሩ ዘንድ ሃዋርያው ያስተምር ነበር፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስራ ሁለቱ ወገኖች አንድ ወደ መሆን እንዲመጡ ሲያሳስብ በ​​​​​​​​ኤፌ2:10-16 ላይ እንዲህ ይላል፦
‘’እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።’’
እግዚአብሄር አህዛብን ወደ አብረሃም ተስፋ ያመጣ ዘንድ የምስራች እንዲሰበክላቸው ደቀመዛሙርትን ተጠቅሞአል፤ ይህን የምስራች የተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙም ነበሩ፣ አሁንም ደግሞ አሉ፤ ተስፋ ያልነበረንን የዘላለም ህይወት ተስፋ እንደሰጠን በማመን ከጠበቅነውና ይህን አምላክ እስከመጨረሻው ከተከተልነው በፍጻሜው እናገኘዋለን። ያመኑትን ይበልጥ እምነታቸውን የሚያነሳሳና የሚያጠነክር እንዲሁም የሚደግፍ ቃል በሮሜ. 1:16-19 ሲናገር፦
‘’በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና።’’
ከሃይማኖት የሳቱትን ቃሉ በተግሳጽ ይናገራቸዋል፦
ቃሉ አስረግጦ እንዳወጀው ሃይማኖት አንድ ከሆነ ክዚህ አንድ ጊዜ በጌታ ፈጽሞ ከተሰጠ ሃይማኖት በየትኛውም መንገድ ወጣ ማለት ውጤቱ ልማት ሳይሆን ጥፋት ነው።
‘’መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦“ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ነገር ግን፦ እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦“እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ፦“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ “አለ።’’ (ሮሜ. 10:15-20)
ሃይማኖት መሰረቱ የህያው እግዚአብሄር ቃል ነው፤ ያን የተከተለ እምነት ፈጽሞ ሊስት አይችልም፤ የስጋ ፈቃና እውቀት ግን ያስታል፤ ፍልስፍናና አለማዊ እውቀት ግን ያስታል፤ አግንንታዊ ትምህርት ሾልኮ ከገባ ያስታል፤ ፍልስፍና ከተደባለቀም ያው ያስታል። ነገር ግን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ ሃይማኖት የማይናወጥ ጌታ ኢየሱስ ገንኖ የሚታይበት ነው። በተለያዩ እንቅፋቶች ምክኒያት የልጅነትን ስልጣን ያገኙ ወደ ኋላ ሲሉ፣ ተስፋውን የተቀበሉ ሲያፈገፍጉም ከእግዚአብሄር ፊት የሚያርቅ ስህተት ይይዛቸዋል፤ቃሉ ሲገስጻቸው እንዲህ ብሎ ነው፦
​​​​​​​​‘’የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ​​​ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።’’ (2ጢሞ. 3:5-7)
የአምልኮ መልክ በሃይማኖት ውስጥ መምጣቱ አይቀርም፤ የሃይማኖት ገጽ ብቻውን ያለ አካል ከተገለጠ ራቁቱን መውጣቱ አይቀርም፤ ህይወት የለበትምና፣ የታይታ ነገር ብቻ ነውና፤ ያም የሚሆነው ጸጋው የሚያካፍለውን ሃይል ሳይኖሩበትና ሳያምኑት ሲቀሩ ነው። እግዚብሄርን መፍራትና ንጹህ አምልኮ ሳይኖራቸው በሃይማኖት እንዳሉ ለማስመሰል ከፍ ያሉ ቃላትን በመናገር፣ በአስመሳይ አቀራረብ በመመላለስ ደካሞችን ያስታሉ። እንደነዚህ ካሉ አስመሳዮች ራቅ ይላል ቃሉ።
ፍጻሜ ጻድቃን
የአምልኮ መልክ የተላበሱ በክህደት እግዚአብሄርን እያሳዘኑ በሚቀጥሉበት ዘመን እውነት ላይ ተጣብቀው የሚመላለሱ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ አብልጠው በመጠጋት አካሄዳቸውን እያደሱ ይቀጥላሉ፤ በዚህ የጻድቃን መጨረሻ ደስታ እንደሆነ የተረጋገጠ ሆኖአል።
​​​​​​​​ማቴ. 25:23፤ ‘’ጌታውም፡- መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ​ግባ አለው። ‘’
በጌታ ባለ ህይወት ላይ ተጣብቆ መኖር ከርሱ ዘንድ ያለውን የህይወት መንፈስ ይሰጣል፤ በርሱ ምሪት ላይ በተደገፈ ኑሮ ውስጥ መኖርም መልካም ባህሪ ተካፋይነትን በማስገኘት በእውነተኛ እምነት ውስጥ ያሳድጋል፤ ጌታ ኢየሱስ መጥቶ በዚህ ህይወት ውስጥ ያገኘውንም ይሸልማል። በዚህም የጻድቃን ፍጻሜ ወደ ጌታቸው ደስታ መግባት ነው፤ ይህም እውነተኛውን ሃይማኖት እስከመጨረሻው ስንጠብቅ የምንቀበለው ነው፦
‘’መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።’’ (2ጢሞ 4:7-8)
ፍጻሜ ሀጢአን
​​​​​እምነታችን ወንጌልን የሚመጥን ሲሆን እግዚአብሄር ይቀበለናል፤ ፍጹም ትሁት በሆነና አንድነትን በሚጠብቅ ልብ ሆነን ከሃዋርያት ትምህርትና ከወንጌል ሃይማኖት ጋር ህብረት በማድረግ ሳንላላ፣ ቸል ሳንልም አጥብቀን በመከተል፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ውጊያ ተጋድሎ እያደረግን አብረን በመስራት፣ ሳንለያይ፣ ሳንጉዋተትና ሳንገፋፋ በአንድ መንፈስ እንድንቆም የሃዋርያቶች ምክር ነው፤ እንዲህ ይላሉ፦
‘’ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።’’
በሃይማኖት እየተጋደልን ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ እንድንኖር ታዘናል። በሃይማኖት ሆነው እንዲህ በጽድቅ በመጋደል ተቃውሞ መግጠም አይቀርም፣ ነገር ግን ጠላት ሰዎችን ቢያንቀሳቅስም ከኢየሱስ የተነሳ ድል ስለምናገኝ በተቃዋሚዎች እንዳንዳነግጥ ቃሉ አስቀድሞ ያሳስባል ።
2ቆሮ.11:11-16 ‘’ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። ​​​​​​​​እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። እንደ ገና እላለሁ፦ ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ።’’
አንድ ጊዜ ፈጽሞ ከተሰጠ ሃይማኖት ያፈነገጠ ማን ነው? ከእውነት የሳተው፣ በእውነት ላይ የተነሳውም ነው፤ ራሱን ከእውነተኛ አገልጋዮች ጋር አመሳስሎ ነፍሳት የሚያጠምድ የጠላት መንፈስ መጠቀሚያ እርሱ ነው፤ እርሱ የዳኑትን አዳዲስ አማኞች ጭምር ከመንገድ ለማሳት በተንኮል ይሰማራል፣ ራሱን ይለውጣል፣ ያታልላል፣ ዋሽቶ ይናገራል፣ የጽድቅ አገልጋዮችን የሚያስነቅፍ የተንኮል ስራ ይሰራል፤ እነዚህን ሁሉ በዘመናችን አይተናል፣ ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ግን በርሱ የተደገፉትን እንዴት አድርጎ እንዲጠብቅ ያውቃል። የእግዚአብሄር ልጆች ከአንድ ሃይማኖት ውጪ በእግዚአብሄር የሚታወቅ ሃይማኖት እንደሌለ አውቀው በተፈጠሩ ምድራዊ ሃይማኖቶች እንዳይደክሙ፣ እንዳይሸነገሉና እንዳይስቱ ሊጠነቀቁ ይገባል።
​​​​​​​​2ተሰ.2:9-12 ‘’ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።’’