ብቸኛውና ፍጹሙ ሃይማኖት መለኮታዊ ምንጭ ስላለው ከአህዛብ እምነት የተለየ ስራ ይሰራል፣ የተለየ ባህሪም ያለው ነው፤ ይህ ሃይማኖት በጌታ መገለጥ ፍጹ ሆኖ ልስ ልጆች ተሰጥቶአል ስለዚህ ይህ ሃይማኖት ወደ እኛ ሲመጣ፦
1.አዲስ ስርአትን ያበስራል
በብሉይ ኪዳን የነበሩት እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሄር ፊት የሚቀርቡበትን መንገድ ለውጦ በአዲስ መንገድ በመተካት የአብረሃምን እምነት ፍጹም የሚያደርግ ስርአት በጌታ ተገልጦአል።
አስቀድሞም ቢሆን ለአይሁድ ከተሰጠው የሙሴ ህግና ስርአት በቀር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እውነተኛ አምልኮ አልነበረም፤ ያ የብሉይ ኪዳን መንገድ ግን በጌታ መገለጥ አብቅቶአል። አህዛብ ቢከራከሩም ለእስራኤል ከተሰጠው ተስፋ በቀር ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኝ መንገድ አልነበረም፤ ጌታ ወደ ገዛ ወገኖቹ በመምጣት አሮጌውን መንገድ ሻረው፤ አዲስ መንገድ ሲከፍትም አስቀድሞ ህዝቡን ወደዚያ ጋብዞአቸዋል። ሃዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ተመርቆ የተከፈተውን አዲስ መንገድ በርሱም ያለውን አምልኮ የሚሰብክ የእግዚአብሄር አገልጋይ ሲሆን ወገኖቹ የሆኑትን አይሁዶች ሲያስብ ግን ብዙ ኀዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት ስለእነርሱ እንደነበረው ሲናገር ይታያል፤ ያም በሥጋ ዘመዶቹ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቹ ከክርስቶስ መለየት ያስጨንቀው እንደነበር በመልእክቱ አሳይቶአል (አዲስ ከተመረቀው መንገድ የተለዩ መሆኑ እያስጨነቀው ነበረና)፤ በዚያም ወደ ሁዋላ ተመልሶ እግዚአብሄር ስለአባታቸው አብረሃም እንዴት እንደተቀበላቸው በማስታወስ ሲቆጭም እናያለን፤ በእርግጥም በእነርሱ ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ አደራና ተስፋ ቃል እንደነበረ ቃሉ የሚያስረዳ ነው፤ ደግሞስ በእነርሱ ዘንድ የነበረው ያ አደራ፣ ተስፋና ቃልኪዳን ታላቅ አልነበረምን? ሃዋርያው እየተደነቀ ሲናገር ወገኖቹ እንደ አህዛብ የሚቆጠሩ ሳይሆኑ ከእግዚአብሄር ጋር ቃል ኪዳን የተጋባው አባታቸው አብረሃም ልጆች እስራኤላውያን ሲሆኑ እውነትን የተቀበሉ፣ እግዚአብሄር በክብሩ የተገለጠላቸውና የአምልኮ ስርአት የሰጣቸው፣ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት የተቀበሉ ታላቅ ህዝቦች እንደነበሩ እንመለከታለን፤ እነዚህ ህዝቦች የአብረሃም፣ የይስሃቅና የያእቆብ ዘር ሲሆኑ አምላካቸው ለአባቶቻቸው የገባው ተስፋ ለነርሱና ለምድር አህዛብ ይደርስ ዘንድ ክርስቶስ በነርሱ በኩል ይመጣ ዘንድ የተወሰነላቸውና የታደሉ ወገኖች ናቸው። እነርሱም ክርስቶስ በመጣ ጊዜ በስሙ በማመን እርሱን ይቀበሉት ዘንድ ሲጠበቁ ያ ሳይሆን በአሮጌው መንገድ ተይዘው ቀሩና አዲሱን የህይወት መንገድ ተቃወሙ፦
‘’ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።’’ (2ቆሮ.5:17-20)
እግዚአብሄር ራሱን ከሰው ጋር ለማስታረቅ አዲስ የደህንነት መንገድ ፈጥሮአል። ያም በብሉይ ኪዳን ስርአት አሮንና ልጆቹ ተሾመው እንደነበረው ያለ ስርአት ያለው አይደለም፤ ያንን ስርአት የሻረው ጌታ ፍጹም ያልሆነውን የሰው አገልግሎት በክርስቶስ ስጋና ደም ፍጹም በማድረግ ታላቅ የአምልኮ ስርአት ለኛ ሰጥቶአል፤ ይህን የተቀበሉ ሰዎች ለዘላለም ህይወት የታደሉ ናቸው። ቃሉም ሲያረጋግጥ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል ይላል።
2.የህግ ፍጻሜ የያዘ ሀይማኖት ነው
ለተስፋው ህዝብ የተሰጠ መመሪያ ሁሉ አንድ ቦታ ላይ የሚያቆም ነበር፣ ያም የሆነው ተስፋው ፍጻሜውን ስላገኘ ነበር፣ ሃዋርያው ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ጽፎአል፦
‘’በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።’’ (ሮሜ. 9:4-6)
የስጋ ዘመዶቹ ነገር ለምን አስጨነቀው? በስጋ ስለተበደሉ፣ ጥቅማቸው ሰተጓደለ፣ ወይስ የከሰሩበት ነገር ስለነበረ? እርገጥ ነው ከክርስቶስ (የተስፋው ሙላት) በፊት መያዣ የሆነ ብዙ ነገር ከእግዚአብሄር ተቀብለዋል፤ እነዚያ በነርሱ ዘንድ የነበሩት ሁሉ እስከ ክርስቶስ መወለድ ጊዜ ድረስ በነርሱ ዘንድ ሊጠበቁ ተገብቶአቸዋል፤ ሃዋርያው የተጨነቀበት ዋናው ምክኒያትም የተስፋውን ፍጻሜ አመልካች የነበሩትን ስጦታዎች ተሸክመው ወገኖቹ መቀመጣቸው፣ የጠበቁት ሲመጣ እርሱን ባለመቀበላቸው እንዲያውም ተስፋውን ያማያውቁት ምስኪኖች አህዛብ ክርስቶስን ማመናቸው እያስገረመው የወገኖቹ ሞኝነት ግን እያሳዘነው በቁጭት ይናገራል። አማኞች እየበዙ በሄደበት በሃዋርያት ዘመን እዚያው የብሉይ ኪዳን ትእዛዝ ላይ ተጣብቀው ሲያስቸግሩ ለነበሩ አይሁድ ሃዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ደጋግሞ ሲያስተምራቸው ነበር፤ በጢሞቲዎስ አገልግሎት ውስጥም ለተገለጡ ክርስቲያን አይሁድ መባል ያለበትን ለወጣቱ አገልጋይ አንዳንድ ነገሮች አስታውቆታል።
በ1ጢሞ.1:2 ላይ ‘’ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን’’ ሲል ያሳስባል፤ አዎ ህጉ በራሱ ቅዱስና መልካም ነው፣ ከጌታ የተሰጠ በመሆኑ። ነገር ግን ማንም የሰው ልጅ በህጉ በኩል ፍጹም መሆን አልቻለም፤ ህጉ ብቃት ሊሰጥ ስላልቻለ ሁሉ በህጉ ምክኒያት ሞተዋል። ከህግ ውጪ የተገለጠው አዲሱ መንገድ ግን ሰውን ፍጹም አድርጎ የሚያቀርብ ነው።
‘’እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና። አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል። ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና፦ እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ’’ (እብ. 8:5-8)
3.ብቸኛው ሃይማኖት አዲስ አምልኮ ፈጥሮአል
ጌታ ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን መንገድ ያስጨነቃትን ሳምራዊት አግኝቶ ያነጋግራት ነበር፤ በሚያዋራት ወቅት ሴትየዋ መጀመርያ አንድ ተራ መንገደኛ የተዋወቀች መሰላት፣ በቆይታ ስታጠናው አንድ ሃይማኖተኛ የአይሁድ ሰው ሆነባት፣ መነጋገር በቀጠለች ጊዜ አንድ ነቢይ የእግዚአብሄር ሰው ሆኖ ተገለጠላት፣ በመጨረሻ በጣም በቀረበችው ጊዜ የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑ በራላት። ይህን የተረዳች ሳምራዊት በልቧ የነበረን የዘመናት ጥያቄ እርሱም የብሉይ ኪዳን አምልኮ፣ መንገድና ስርአት ስለነበረው በጥርጣሬ አነሳችለት፣ እርሱም ጥርጣሬዋን ፈታላት፦
‘’ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ፦ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ፦ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።’’ (ዮሃ. 4:20-27)
መሲሕ ሲመጣ ይዞት የሚመጣው አዲስ የአምልኮ መንገድ እንዳለ ሳምራዊትዋ ማስተዋልዋ አስደናቂ ነገር ነበር፤ እርሱም እምነትዋን አረጋገጠላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አላት። ጌታ ኢየሱስ በሰጠው እምነት በኩል እግዚአብሄር ያለገደብ በመንፈስ የሚመለክበት ጊዜ መጣ፣ እኛም የዚያ አምልኮ ክፍል የመሆን እድል አገኘን።
‘’እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።’’ (ቆላ. 2:16-23)
4.አዲስ ወግና ልማድ አምጥቶአል
በህጉ ስርአት የተሰጡ በርካታ ትእዛዞች በእስራኤላውያን ዘንድ አሁን ድረስ እንዳሉ አሉ፤ እነዚህ ወግና ልማዶች በአዲስ ኪዳን ለተገለጠው እምነት ብዙ እንቅፋት ሲፈጥሩ የምናየው ነው። ከላይ በቆላ. 2:16-23 እንደተመለክትነው ብዙው ወግና ስርአት መሻሩን ያልተቀበሉ ወደ ክርስትና የመጡ አይሁድ ለሃዋርያት አገልግሎት ትልቅ ተግዳሮት ፈጥረው ነበር። ሃዋርያው ግን አጥብቆ ይህን ስርአት ሞግቶአል፤ ወጣት አስተማሪዎችም ትምህርቱን እንዲቃወሙና በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጠረውን ስርአት አጥብቀው እንዲይዙ አዞአቸዋል፤ ለቲቶ እንዲህ አለው፦
‘’የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል።የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ። የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸተኞች፥ ክፉዎች አራዊት፥ በላተኞች፥ ሥራ ፈቶች ናቸው ብሎአል።ይህ ምስክር እውነተኛ ነው። ስለዚህ ምክንያት የአይሁድን ተረትና ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን ሰዎች ትእዛዝ ሳያዳምጡ፥ በሃይማኖት ጤናሞች እንዲሆኑ በብርቱ ውቀሳቸው።ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል።እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።’’ (ቲቶ 1:10-16)
በሙሴ ህግ በታዘዘው መሰረት እስራኤላውያን ይጠብቁዋቸው የነበሩ እጅግ የበዙ ስርአቶች ህዝቡን ፍጹም ሊያደርጉዋቸውና ወደ እግዚአብሄር በፍጹም ህሊና ሊያቀርቡዋቸው ስለተሳናቸው ጌታ ኢየሱስ እነርሱን እንደ የአስፈላጊነቱ መለወጥ የተገባቸውን በመለወጥ፣ መሻር የነበረባቸውን በመሻርና መተካት የነበረባቸውን በመተካት ፍጹምና አዲስ ሃይማኖት ፈጥሮአል፤ አሁን ከባድ ሸክም የሆነው በአይሁድ ሊያውም በጌታ ኢየሱስ አምነው ክርስቲያን ከሆኑት ይመጣ የነበረው የተተወን እየሳቡ እንደ ወግና ልማድ አድርገው አማኞችን ሲያስጨንቁ መታየታቸው ነበር፤ ይህ ድርጊታቸው በብዙ ስፍራ እንቅፋት ሆኖበት ነበር፤ ሃዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፦
‘’እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።’’ (1ቆሮ. 11:1-2)
‘’ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥’’ (ገላ. 1:11-16)
‘’እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።’’ (ቆላ. 2:6-10)