ብቸኛና ፍጹም ሀይማኖት(6… )

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የእውነተኛው ሃይማኖት ብቸኛ መሳርያ ወንጌል ነው፤ የወንጌል ምስጢርም ክርስቶስ። ወንጌል የጌታን ድል ስለሚያውጅ ነፍሳትን ወደ እግዚአብሄር መንግስት ይሰበስባል፣ ሃይል ያለው የትንሳኤ መንፈስ ስለሚሰራም ሃሰተኛ ትምህርቶችን ይዋጋል፣ በቃሉ አስተማማኝ ቃል-ኪዳን የገባ አምላክ ለሰው ልጆች አይዋሽምና በሙሉ የጸና የእምነት መሰረት ሆኖ ይኖራል። ወንጌል የሚታመን ዘላለማዊው የእግዚአብሄር አሰራር የተገለጠበትም አዋጅ ነው። ወንጌል በተለያዩ ዘመናት ከተነሱ የሃሰት ሃይማኖቶች በኩል ጥቃት ቢደርስበትም ባለመናወጥ እውነትን እየገለጠ በትውልዶች መሃል አልፎ ዛሬ ላይ ደርሶአል። ፍጹሙ ሃይማኖት በወንጌል በኩል ሙላቱ ታይቶአል። ሰዎች እውነተኛውን ሃይማኖት ይሹ ዘንድ ካሰቡ ወንጌልን በትክክል መስማት፣ ማስተዋልና መቀበል ይገባቸዋል። ቤተክርስቲያንም ወንጌል ባስተማራት እውነት የተወለደች አካል ነች፦ የክርስቶስ አካልና ከርሱ መለየት የማትችል፣ በርሱ ህይወት የምትኖር፣ ከርሱ ብቻ ሃይልን የምታገኝ፣ በርሱ ምሪት የምትመራም ነች።
የእውነተኛው ሃይማኖት መገኛ ቤተክርስቲያን ስትሆን እርሱዋ በሃዋሪያቶች ትምህርት ላይ የተመሰረተች ነች፤ ይህን እውቀት ጌታ ኢየሱስ አጽድቆታል ፡-
‘’ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።’’ (ማቴ.16:13-18)
ሃዋርያቶች የሰበኩት ወንጌል ከቤተክርስቲያን ህልውና ጋር የተያያዘ ነው፤ ምክኒያቱም ትምህርቱ ለማዳን የሚያስችል ምስጢር አለበት፣ ከዚያ በወጡትና ባፈነገጡት ላይ ግን የሞት ፍርድ አለ። ሃይማኖት ከወንጌል ይመነጫል፤ በአለም ላይ ያሉት ግን የተበረዙ ወይም የተፈጠሩ ናቸው፤ እውነተኛነታቸውን ለማጽደቅ ቢምሉ እንኳን ሰማይ አይቀበላቸውም፤ ያን የሚያውቅ ጌታ እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል ሲል ሰዎች የሃዋርያቶችን ትምህርት እንዲያከብርና እንዲቀበል ያስገድዳል። ሃዋርያቶችም ስለራሳቸው የሚናገሩት አላቸው፦
‘’በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።’’ ይላሉ (ኤፌ. 2:20-22)።
በሐዋርያትና በነቢያት እውቀት ላይ መታነጽ የሚገኘው እነርሱ ያስተማሩትን ወንጌል በመቀበል ነው፣ ይህም ሰዎች በዘመናችን ከሚያስተምሩት ሰዋዊ የእምነት አንቀጽ ፍጹም የሚለይ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ የሚያንጸን የእግዚአብሄር ማደርያ እንድንሆን በማሰብ ስለሆነ ሲያንጸን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በሆነው በራሱ ነው፤ በክርስቶስ የምንጋጠምና የምናድግ መንፈሳዊ ቤት እስካልሆንንና ሰዎች ያነጹን እስከ ሆነ ድረስ ግን የቅዱሱ አምላክ ማደሪያ መሆን አንችልም። ከዚህ ለመዳን በአለም ላይ የተኮለኮሉትን ‘‘ቤተ-ክርስቲያኖች’’ እርግፍ አድርገን በመተው በሃዋርያት ትምህርት ላይ መመስረት ያስፈልጋል።
በወንጌል የተለወጡ ነፍሳት በአንድ አካል ሆነው በወንጌል የሚመሩበት መንፈሳዊ ክልል አለ፤ በዚህ መንፈሳዊ ክልል ውስጥ እግዚአብሄር ይገኛል፣ ልጆቹን ይጎበኛል፣ ይባርካቸዋል፣ ይናገራቸዋል፣ ያስተምራቸዋል፣ ይገስጻቸዋል፣ ያርማቸዋል፣ ይቀድሳቸዋል፣ ፈቃዱን ይገልጥላቸዋል፣ ይፈውሳቸዋል። ቤተክርስቲያን ትክክለኛ የእግዚአብሄር ማደሪያ ስትሆን እነዚያ በረከቶች በመሃከልዋ ይገለጡና ነፍሳትን የምትስብ ትሆናለች። ቤተ-ክርስቲያን በመፈስ ስትበረታ ዘመኑን የሚዋጅ ትምህርት ከወንጌል አውጥታ ታስተምራለች፤ ነፍሳት የሚነቁበትንና አምላካቸውን የሚጠባበቁትን ጸጋ ታካፍላለች።
1.የአለም ፍጻሜ የያዘ ሀይማኖት
‘’እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።’’ (እብ. 9:23-28)
እውነተኛ ሃይማኖት ከሰው ልጆች የሚሰውረው፣ በሰው ልጅ ላይ የሚዋሸውም ሆነ ለነገ ብሎ የሚያቆየው ድብቅ እውቀት የለም። የሰውን ልጅ ስብራት የሚጠግን፣ ልቡን የሚያቀና ከአምላክ ጋር የሚያጣብቅ፣ ለመንግስቱ ወራሽነት የሚያበቃ ትምህርት ግን አለበት። በእውነተኛው ሃይማኖት ውስጥ ጎልተው የሚታዩ እውነቶች ስለጽድቅ፣ ኩነኔና የአለም ፍርድ የሚናገሩ ናቸው።
በእምነት በመኖር የተቀበልነውን መለኮታዊ ትምህርት ይዘን ከቀጠልን መንፈሳዊ ህይወት ስኬታማ ነው፤ በዚህ በእኩል ጸንተን በእምነትና በጸጋ በመታገዝና በሃይማኖት ላይ በመተከል ህይወትን እስከ መጨረሻው በጽድቅ ማኖር ያስችላል። አማኞች በተሰጣቸው የእምነት መገለጥ ላይ ተጣብቀው እምነታቸውን በዚያ መንገድ ከማነጽ ሌላ አማራጭ የላቸውም፤ ጌታ ኢየሱስ በደሙ ሃጢያታቸውን አጥቦ በበጎነትና በቸርነት ሊያጸና ስላቀረባቸው፣ በመከራና በሞቱ ሊታረቃቸው የሰራው ስራም በነርሱ በመጽናቱ፣ በሥጋው ሞት ግድግዳውን ስላፈረሰው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ስራ በመስራቱም የሰው ልጆች በእምነታቸው ላይ ተተክለው እንዲኖሩ ይረዳቸዋል።
ነገር ግን አማኞች በእምነት ሆነው ያለ ነቀፋ በቅድስናና በጽድቅ ይቀርቡ ዘንድ ከጌታ ኢየሱስ ምሪት ውጪ መሆን የለባቸውም። ከቃሉ ጸጋ ያላገኙ ሰዎች እምነት በልባቸው ስላላደገ፣ ህይወቱን ስላልኖሩ በዚህም በጎ የጸጋ ሥራ በነፍሳቸው ላይ ስላልተሰራም ልባቸው ይዝላል፣ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ የሚያሳድግ የጸጋው ሥራ በነርሱ ዘንድ እስካልተከናወነ ድረስም ሰዎች ነውር የሌለባቸው ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም።
አማኞች እንዲያድጉና ከጥፋት እንዲጠበቁ የጸጋ አስፈላጊነት መታሰብ አለበት፤ የቅዱሳን የመጨረሻ ጽናት በእምነትና በቅድስና እንዲጸና በእውነተኛ ሃይማኖት መኖር ተገቢ ነውና። ነገር ግን ከክርስቶስ ሞት፣ ዕርቅና የድል ፍጻሜ ይልቅ ሰዎች ወደ አለም ካዘነበሉ ግባቸው ጋ መድረስ አይችሉም።
ቤተክርስቲያን የተመሰረተችበትና የተደላደለችበትን ሰማያዊ እውቀት በሰዋዊ ጽድቅ መተካት አትችልም፤ በዘመናችን ያሉ በቤተክርስቲያን ስም የተጠሩ ቤተ-እምነቶች ግን አሸዋማ መሠረት ላይ ስለታነጹ ምድራዊ ነገር የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፤ ነገር ግን የገሃነም ደጆች የማይችሏቸው የእግዚአብሄር ልጆች በዓለቱ በክርስቶስ ላይ ስለተመሰረቱ እስከ መጨረሻው መጽናት የሚችሉና በፍፁም ሳይሰናከሉ፣ ስር ሰድደው በእርሱ የሚታነጹ ናቸው።
በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ወደ እግዚአብሄር በመቅረብ ከወንጌል ተስፋ ጋር እንዲጣበቁ ቃሉ ያሳስባል። በወንጌል ውስጥ እንደተቀመጠው የዘላለም ሕይወትና የመንግስቱ ተስፋ በቤተክርስቲያን እንዲጸና በክርስቶስ አካል መኖርና በጠንካራው መሠረት በክርስቶስ ላይ መቆም ይጠይቃል። የወንጌል ተስፋ የአማኞች የነፍስ መልህቅ ነው፣ የደህንነታችን እርግጠኛነትና ጽናት እርሱ ስለሆነ የርሱ የሆኑት ከርሱ ውጪ ሊሆኑ አይችልም።
ወንጌል ከሰማይ በታችም ላለው ፍጥረት ሁሉ የተሰበከ ነው። ወንጌሉ በየቦታው የተሰበከው በጌታ በራሱ መንፈስ ስለሆነ በየስፍራው ያሉ አማኞች በዚያ መንፈስ መዳንን ያገኛሉ። በሩቅም በቅርብም በዓለም ሁሉ ዘንድ ለአሕዛብም ሆነ ለአይሁድ የተሰበከው ወንጌል ሰውን በአንድ ሃይማኖት የሚያኖር ነው።
2.የአለም ስርአት ፍጻሜን አብሳሪ ሃይማኖት
‘’እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።’’ (ቆላ. 1:27-28)
እውነተኛው ሃይማኖት መጨረሻችንን የሚያሳይና የሚያስተማምን መንገድ ያለው ነው፤ አለም ፍጻሜዋ ቅርብ ነው፤ የሰው ልጆችስ መጨረሻ ምንድነው? ይህን እውቀት ሰዎች መጨበጥ የሚችሉት በሃዋርያትና በነቢያት መሰረት ላይ የታነጸ ሃይማኖት ውስጥ ሲኖሩ ብቻ ነው።
‘’አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።’’(ራእ. 21:1-4)
3.የጽድቅ ፍጻሜ የያዘ ሀይማኖት
ትንሳኤው አዲስ ህይወት ፈጥሮአል፣ አዲስ ማንነት ፈጥሮአል። እግዚአብሄርን ወደ መምሰል ማደግም በክርስቶስ ኢየሱስ የተገኘ አዲስ ማንነት ውጤት ነው፤ በዚህ ማንነት የተቀረጹ ሰዎች እየበዙ ሄደው አለም ላይ ተጽእኖ በማሳደር ልዩ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ወደ መለኮታዊ እውቀት የሚያስገባ እውቀትን የሰጠ ጌታ ሲሆን ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ የሚደርሰው በእምነት በኩል ነው።
የጌታ ኢየሱስ መወለድ አዲስ የአለም ስርአት ፈጥሮአል፣ ይህም መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን የሰው ልጅ አስቀድሞ የማያውቀው ነገር ግን የእግዚአብሄርን የዘላለም አሳብ የገለጠው ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በሰው ዘንድ እየሆነ ያለውና የሚታየው የእምነት ይዘት መዛባት ሲሆን በዚህ ተጽእኖ የበዛ ሀይማኖት ሊፈጠር ችሎአል፡፡ ቁንጽል እውቀት ያበቀላቸው ሀይማኖቶች ብዙ ናቸው፤ ሰው ባገኘው ቁንጽል እውቀት ደፍሮ ሀይማኖትን ሲያቆም፣ ያላስተዋለውም በስሚ ስሚ ሲከተል፣ እውነት ሲዛባ፣ የበዛው ተከታይ በግምትና በጭፍን ጥብቅና ሲቆም፣ መገሰጽም ሲሳነው ተያይዞ ወደ ገደል መንደርደር በዝቶአል፡፡ አይን ሲጋረድ በተናጋ የሰው ህይወት ውስጥ አድብቶ የሚገባ ጠላት ጥፋትን ያፋጥናል፤ ይህ ጥፋት በሃይማኖት ትምህርት ጸንቶ መኖር እንዳይቻል፣ ከእውነት ማፈንገጥ እንዲሆን፣ እግዚአብሄርም እንዲቆጣ ፍርድን ይስባል ፦
‘’የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዓት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዓት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ። የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ። በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ።እግዚአብሔርም፦ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ። ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም።’’(2ነገ. 17:7-14)
እግዚአብሄርን የተከተለ ግን አንዱም አልወደቀም፣ ያመነውም እድሜው አላጠረም፣ እግዚአብሄር ለሚያምኑት ታማኝ አምላክ ነውና፣ በእምነት ለሚጠሩትም ቅርብ ነውና።