ሃይማኖት በውጫዊና ውስጣዊ መገለጫዎች ይታወቃል
አንድ ሃይማኖት በእምነት ደረጃ ሲገለጥ መሰረቱ መንፈሳዊነት ሲሆን ከዚያ በመነሳት የውስጣዊ ህይወትን ከእግዚአብሄር ጋር በማገናኘትና በስጋችንም እግዚአብሄርን እያከበርን በቅድስና እንድንኖር የተፈጠረልን መንገድ ነው። ሆኖም በምድር ላይ የምናገኛቸው ሃይማኖቶች ከእውነተኛነታቸው ሌላ መንፈሳዊነት የሚገዛቸው ብቻ ሆነው አናይም፤ እጅግ ብዙ ሃይማኖቶች በዘመናችን ተፈጥረዋል፣ ስጋን የሚያገለግሉና መመሪያዎቻቸው በአእምሮ ውጤቶች ላይ መሰረት ያደረጉ ሆነው ይታያሉ። በሰው የተፈጠሩ ሃይማኖቶች እግዚአብሄር ከሰጠው አንድ ሃይማኖት ፍጹም ይለያሉ።
አገልግሎታቸውን መሰረት አድርገን ስናይ በሁለት መንገድ እናያቸዋለን፦
1. ውጫዊ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እምነት – እግዚአብሄርን ሳይሆን ሰዎችን የሚያገለግል፣ መንፈስ የማይነካ፣ ሰዎችን ብቻ የሚያስደስት፣ ታይታ ያለበት፣ በሰው ስርአት የታጠረ፣ እግዚአብሄር የማይከብርበት፣ እግዚአብሄር የማያውቀውና ከእግዚአብሄር ያልሆነም ነው።
ይህ ሰውን በማገልገል ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ሰዋዊ በመሆኑ ከእግዚአብሄር ጋር መጉዋዝ አይችልም፤ መሰረቱ የእግዚአብሄር ቃል ሳይሆን የሰዎች አእምሮ አውጥቶና አውርዶ፣ ደምሮና ቀንሶ ያልያም የእግዚአብሄርን ቃልና ሰብአዊ አሳብን በማቀላቀል የተፈጠረ እምነት ስለሚሆን እግዚአብሄርን ሳይሆን ስጋን የሚያስደስት ተልእኮ ያለው ነው።
ብዙ የሃይማኖት ክፍሎች በክርስትና ስም አሉ፤ እነዚህ ሃይማኖቶች ስማቸው ሳይሆን መንፈሳዊ ይዘታቸው ከክርስቶስ ትምህርት የተንሸራተተ በመሆኑ በራሳቸው ፈቃድ የሚነዱ ናቸው። እንዲያውም ወደ ክርስቶስ ከማቅረብ ይልቅ ፈቃዱን እየተቃወሙ ሰዎችን ወደ ስህተት የሚመሩ ናቸው።በስህተት መንፈስ አሰራር የተጠቁ ክርስቲያኖችም እውነተኛውን ሃይማኖት በመበረዝ ጥፋት ውስጥ እንደሚገቡ ቃሉ ያሳያል፦
‘’መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል’’ (1ጢሞ.4:3)
ከመናፍስት ጋር በሚፈጥሩት ግንኙነት በኩልም ሰዎች ሃይማኖት ይፈጥራሉ፣አጋንንትን ለማስደሰት ከነርሱ የሚሰጣቸውን ስርአት ይጠብቁ ዘንድ ያን ያደርጋሉ፤ ይህ አደገኛ እምነትና ሰዎችን የሚያዋርድ ሲሆን ከሰውነት ውጪ የሚያደርጉና አሳዛኝ ፍጻሜ ያላቸው ናቸው።
2. መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እምነት – የእግዚአብሄር መንፈስ የሚመራው፣ የእግዚአብሄር ቃልን መሰረት ያደረገ፣ የዘላለም ህይወትን መሰረትም ያደረገ፣ እውነተኛውን አምላክ የሚገልጥና እግዚአብሄር የሚከብርበት ነው።
‘’ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ።’’ (ይሁ. 1:3-5)
እግዚአብሄር በመንፈሱ የሚሰራው ስራ ውስጣዊ ህይወትን የሚደርስ፣ በመንፈስ ላይ ተጽእኖ ያለው፣ ሰዎች ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያደርግ ዘንድ መንገዱን ለሰዎች የሚገልጥበት ነው። እውነተኛ እምነት ከሌለ ግን መንገዱ አይገለጥም።
ወደ መንገዱ የገቡም በመንገዱ ላይ ጸንተው በመጉዋዝ አምላካቸውን እንዲገናኙና በምህረቱ ውስጥ ኖረው የመንግስቱ ወራሽ እንዲሆኑ እግዚአብሄር ቃሉን ይሰጣል፣ መንፈሱንም እያወረደ ይባርካል። እግዚአብሄር እውነቱን እንዲያውጁና መንገዱን እንዲገልጡ የሾማቸውንም በመላው አለም ያሰማራል።
‘’ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር’’ (ሃስ. 19:8-11)
በእግዚአብሄር መጽሃፍ ውስጥ የተገለጠ አንድ ሃይማኖት ብቻ አለ፤ ቃሉም የሚሰራው ከዚህ እምነት ጋር ብቻ ነው፤ በየጊዜው የሚነሱ የራሳቸውን ሃይማኖት የሚፈጥሩ ተቋማት ቃሉን ይገልገሉበት እንጂ የሚደግፋቸው መንፈስ አይመጣላቸውም፣ ይህም ተቀባይነት እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡
‘’በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን እያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።’’ (ኤፌ. 4:4-8)
ከላይ ያነበብነው ቃል ስለ አንድ እውነተኛ ሃይማኖት የሚያሳየን ብርቱ ማስረጃ ያለው ነው፤ ሃይማኖት እውነት መሆኑ ማረጋገጫው በውስጡ የሚገለጠው እውነትና የሚመለከው አምላክ ከሆነ እንዴት ያለ እውቀትና አምላክ አንድ ሃይማኖትን እውቅና እንደሚያሰጠው በማስረጃ ማረጋገጥ የሚቻል ነው። ስለዚህ አንድ ሃይማኖት በእግዚአብሄር ዘንድ የታወቀ መሆኑን ስናረጋግጥ በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ያለው እውነት አንድ አካልና አንድ መንፈስ የሚገልጥ እንደሆነ፣ በመዳን እውቀት በኩል አንድ ጥምቀት የሚሰበክበትና የሚመለከውም አምላክ መገለጫ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት መሆኑን ማረጋገጫ ይሰጣል። ከዚህ ውጪ ያሉ በአለም ውስጥ ያሉ የበዙ ሃይማኖቶች ከእግዚአብሄር እውቅ፣ ሞገስና እይታ ውጪ ናቸው ማለት ነው።
ሀይማኖት በአለም ለምን ይበዛል?
የሃሰት አባት ሰይጣን እስካለ ድረስ የሃሰት ነገር ሁሉ መኖሩ አይቀርም፤ የእውነትን ነገር ለመናድ ሲል እንዲሁም የእውነትን ምንጭ ሊደፍን በማሰብ በተለያየ መንገድ ሃሰትን ያወጣል፣ ያሰራጭል፣ ያስፋፋል፣ በዚህ እንቅስቃሴው እጅግ የበዙትን ያደናግራል። በሃይማኖት እውነት ሰው ወደ እግዚአብሄር እንዳይደርስ እውነትን አስመስሎ ይሰራል፤ እግዚአብሄር ከሃሰት ጋር እንደማይሰራ ስለሚያውቅ ሰዎችን ወደ ስህተት በማስገባት ከአምላክ ጋር ያቆራርጣቸዋል።
ትውልዳችን ትኩረቱ በሃይማኖት ውስጥ መኖሩ ላይ እንጂ የትኛው ከአምላክ ጋር ያገናኛል የሚለውን ትኩረት ሳይሰጥ በተለያዩ የእምነት አይነቶች ውስጥ ራሱን አስገብቶ ወዲያ ወዲህ ይላል። እምነት ከፍርድ የማያድን ከሆነ ጊዜን በከንቱ ማባከን ምን ይጠቅማል? ሃይማኖት በእግዚአብሄር መንገድ ካልመራ ወደ አጋንንት መውሰዱስ እንዴት ይጠረጠራል?
ነገር ግን አንድ እግዚአብሄር ከአንድ ሃይማኖት ጋር ከሰራ በቁጥር እጅግ የበዛውና በአይነት የተንቆጠቆጠው የሃይማኖት አይነት መጨረሻው ምንድነው? በእንዲህ ያለ ጥርጥር ውስጥ ስንገባ ማመንታትን ጨርሶ የሚያጠፋ በቃሉ ላይ የተቀመጠ እውነት አንዱን ሃይማኖት ብቻ በማሳየትና በመግለጽ ሌሎችን ከንቱ አድርጎ ያሳየናል፤ በእርግጥም በእግዚአብሄር ዘንድ ከአንዱ በቀር የቀሩት ስለማይታወቁ፣ ስለማይታሰቡም የእግዚአብሄርን ብቻ ለማግኘት መዘርጋት ያስፈልጋል።
በአንድ ተስፋ መጠራታችን አምነን ያ ተስፋ ወደ ሚመራን አንዱ የእስራኤል አምላክ ካልተመለከትን እውነትን አናገኝም፤ እውነቱ አንድ አምላክ የሚመለክበት ሃይማኖት የሚያበራና ከጌታ ኢየሱስ ጋር አንድ አካል የሚያደርግ ነው፤ ጌታም አካሉን በትክክለኛው የእምነት እድገት እንዲያድግ ይንከባከባል፣ ያሳድጋል። መጠራታችን ከያዝን በዚያ ያለውን ጌታ አግኝተን በስጦታው እንባረካለን፤ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን እያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን ስለሚል፡፡
ከዚህ የሚያክል ተስፋ ተንሸራትታ ቤተክርስቲያን ስትዳከም ግን ያዳናትን የጌታ ሞትና ትንሳኤ በሙላት ባለማመን፣ ባለመመስከርም ምክኒያት በጠላት ትጠቃለች፡፡ የትንሳኤው ሃይል በሃጢያትና በሃጢያት ምንጭ በሰይጣን ላይ የበቀል በትር ነው፤ የበትሩ ጉልበት ከባርነት ነጻ አውጥቶ በእግዚአብሄር ፊት የሚያመላልስም ነው፤ ቤተክርስቲያን ያን ስትተው ግን የረገጠችው ጠላት ቀና ይላል፤ የዲያቢሎስ መንግስት ይነሳባታል፤ በጌታ ሞትና ትንሳኤ አሰራር የወደቀላት ከበላይዋ ይቆማል።
‘’በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና’’ (ኤፌ. 2:3-7)
በአጋንንት መንግስት ውስጥ ለተያዘ ሰው አለም የምትሰጠው አንድ የአኗኗር ስርአት አለ፣ ይህ ስርአት ህይወትን በበደልና በኃጢአት ሙት አድርጎ የሚያኖር ነው፤ መንፈሳቸው ሙት የሆኑ ሰዎች የማይታዘዙ የአመጸኛው አባታቸው የሰይጣን ልጆች ተብለው በዚህ ክፉ አለም ይኖራሉ፤ የእግዚአብሄር መንፈስ ያለባቸው የእግዚአብሄር ልጆች አኗኗራቸውን ካልቃኙና በመንፈስ ካልተመሩ የመዋጥ አደጋ ውስጥ ይገባሉ።
የዲያቢሎስ መንግስት ግን ሰይጣንን ያነገሰ ነው፤ አጋንንትን ሰራዊት አድርጎ የሚያሰማራ መንግስት ነው፤ በዚህ መንግስት ውስጥ ክፉ ሰዎች ይመላለሱበታል፣ ምን እንደሚሰሩ ሳያስተዉሉ በሰይጣን እቅድ እየተመሩ በአጋንንት እየታገዙም ፈቃዱን ይፈጽማሉ፣ እንዲህ ተላልፈው በተሰጡ ሰዎች መሃከል በአለም ውስጥ ለመኖር የእግዚአብሄር መንግስት በመሃከላችን መኖር አለባት፣ ያለበለዚያ እግዚአብሄርን ማንገስ ያልቻለች ቤተክርስቲያን ጠላት የሆንዋት ሁሉ ይነሱና ያዳክሙዋታል። አማኞችም በአሳብና በድርጊት ከአለማውያን ጋር በመዛመድ ሲኖሩ እየደከሙና ከመንግስቱ እየራቁ ሄደው አደጋ ላይ ራሳቸውን ይጥላሉ።
‘’አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።ወይስ መጽሐፍ፦ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።’’ (ያእ. 4:4-10)