ብቸኛና ፍጹም ሀይማኖት(3… )

የእግዚአብሄር ፈቃድ

እምነት በሃይማኖት ትምህርት ላይ መመስረት ይጠይቃል። ሃይማኖት መንፈሳዊ ትምህርት እንጂ ቁሳዊ አይደለም፣ መደመርና መቀነስ ስሌት የሚመራውም አይደለም፣ ትምክህቱም ሳያይ መዘርጋት እንጂ ማስተማመኛ ሰብሳቢ አይሆንም፣ እምነትና ማስረጃ አብረው አይሄዱም፣ አማኝ የሰማውን መለኮታዊ ቃል ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል እንጂ ምረመራ አድርጎ ማረጋገጫን አያቀርብም።
‘’እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።’’(ዕብ. 11:1-3)
የአንድ ሰው እምነት የሚፈጠረው በሌላ አካል ላይ መተማመንን ሲመጣ ነው፤ ከምንሰማውና ከምናየው ተነስተን በንግግሩ እምነት መጣል ሲመጣ እውነተኛ እምነት በልባችን ያድራል፦
እውቀት፦ አንድ ሰው እምነት ከማግኘቱ በፊት ስለእምነት ሊነገረውና እርሱም ሊሰማ ያስፈልጋል፤ እውነተኛው እምነት ከኢየሱስ የሚመነጭ መሆኑን ሰው መስማት አለበት፤ ኢየሱስን ለማመንም እርሱ የተናገረውን (በብሉይም በሃዲስ ኪዳንም ጭምር) መቀበል፣ ማመና እውነትነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እውቀት የሚባል መሳሪያ የእምነት ቁልፍ ነው፤ ምክኒያቱም አምላክ በድንግዝግዝ እንደ ጣኦታት፣ እንዲሁም እንደ አጋንንት በድብቅ ሊመለክም ሆነ ሊጠራ አይፈቅድም፤ ስለዚህ ስታምኑኝ ቅድሚያ አውቃችሁኝ ይሁን ይላል።
‘’ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።’’ (ሮሜ. 10:16-17)
አንዳንድ ጊዜ እምነት ይጨመርልን ዘንድ እንመኛለን፣ ባለን ነገር ላይ የበለጠ ነገር እናይ ዘንድ ከእግዚአብሄር ከፍ ያለ እምነት እንመኛለን፣ ከእግዚአብሄር ብዙ መቀበል ስለምንሻ። እምነት ከፍ የሚለው ወደ እርሱ በእውቀት ስንጠጋው ነው፤ የቃሉ ምስጢር በበራልን መጠን ማንነቱን እያወቅን ስለምንሄድ በርሱ ላይ ያለን እምነት እየጠነከረ ይሄዳል። ሁልጊዜ ከማመን በፊት ሰው የሚያምነውን አምላክ ማወቅ ስለሚቀድም።
አምኖ መቀበል ይጠበቃል፦ይህ የእምነት ገጽታ አንድ ሰው ያየውንና የሰማውን ለማመን እውነቱን መቀበል እንዲገባው ያሳያል፤ የእግዚአብሄርን ቃል ስንቀበል በእግዚአብሄር ላይ ያለን እምነት ይነሳሳል፣ ይጨምራል፤ እንዲሁ ሰዎችም ኢየሱስ እንዳለ ካመኑ በሁዋላ እንዴት እንደሚያድን ማወቅ አለባቸው።
ደግሞ እግዚአብሄር እንዳለ ማመን ብቻ አያድንም፦ ሲጨንቀንና ተስፋ ስንቆርጥ እግዚአብሄር ስላለ ነው እንላለንና። በምን መንገድ እንደሚያድን ማወቅና ያን ማመን ግን አስፈላጊ ነው፣ የምናምነው ህያው ስለሆነ እንጂ ከእኛ ፍላጎት ጋር አያይዘን ስለእርሱ ስለተናገርን ለውጥ አያመጣልንም (አጋንንት እኮ የእግዚአብሄርን ህልውና ያምናሉ፣ እምነታቸው ፍቅር፣ ትህትናና መታዘዝ ስለሌለው ከፍርድ አላዳናቸውም)።
ኢየሱስ ወደዚህ አለም እንደመጣ ማመን አስፈላጊ ነው፣ መጥቶስ? መጥቶ ሊያድነን እንደሞተ፣ በእርሱ ሞትም የኛን ሞት በመስቀል ላይ ድል እንደነሳው ማመን ያስፈልጋል፤ ቀጥሎስ? በስሙ ንሰሃና የሃጢያት ስርየት እንደሚሰጥ ማወቅ፣ ማመንና ከውሃና ከመንፈስ እንደሚወልደን የተናገረውን ቃል መቀበል ያድናል።
መደገፍ፦ኢየሱስ እንደሚያድን ማወቅ ተገቢ ሆኖ በርሱ ላይ ሁሉን ነገር መጣል የሚያስፈልግ ሰአት ላይ ያን ለማድረግ ልብ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ መደገፍ እንደሚችል ማረጋገጥ ተገቢ ነው፤ በእርሱ ላይ ከተደገፍን የኛን ፕሮግራም አውጥተን የርሱን ስለምናስገባ የኛ የሆነ መጠበቅና ጊዜን የመወሰን ነገር ያቆማል ማለት ነው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቼም ይሁን መቼ የለመንነው ይፈጸማል (እንደፈቃዱ መሆኑ እርግጥ ከሆነ)፣ የትኛውም ሰአት ይሁን ብቻ ያደርገዋል ብሎም በትእግስት እርሱን መቀበል ይጠይቃል። በእምነት ስር መስደድ፦
– የእምነታችን ማእከል ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣል
– የእምነታችን ማረጋገጫ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣልው
– የእምነታችን ውጤት ከጌታ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣል
– የእምነታችን መጨረሻም በጸጋው መዳን መሆኑን ያትማል።
‘’በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።’’ (ኤፌ. 2:9-11)
ከእምነት ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ቃላት በተለይ በእንግሊዘኛ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አሉ፤ እነዚህ ቃላት በተለይ በአማርኛ ቋንቋ ስንጠቀማቸው ትርጉዋሜያቸውን እንድናስተውል ቀጥሎ ተዘርዝረዋል፦
Religion (አምልኮ፣ የእምነት ስርአት)
– Jew’s religion- የአይሁድ ስርአት
– our religion- አምልኮአችን
– Pure religion and undefiled before God- ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ
– vain religion- ከንቱ አምልኮ
የአምልኮ (Religion) አግባብነት
በእኛ ባህልና ማህበረሰብ ውስጥ Religion የሚለው ቃል ቡዙ ጊዜ በመልካም የማይነሳበት ምክኒያት አለው፤ ይህ ቃል ግን አምልኮ ከሚለው ትክክለኛው ትርጉም ጋር በመልካም የሚነሳ ነው። ከአይሁድ ስርአት ጋር ስናነሳው ትክክለኛውን የሃዋርያት እምነትና ስብከት በየስፍራው ሲዋጋ የነበረ እንደሆነ የምናስተውለው ነው፦
‘’በአይሁድ ሥርዓት ( in the Jews’ religion) በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥’’ (ገላ. 1:14-16)
‘’አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው (seem to be religious) ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው (this man’s religion is vain)። ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው ( Pure religion and undefiled before God)፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።’’(ያዕ 1:26-27)
እግዚአብሄር ከከንቱ አምልኮ አውጥቶ ንጹሕና ነውርም የሌለበትን አምልኮ እንድንለማመድ ስለረዳን የተመሰገነ ይሁን።
ከንቱ አምልኮ የአይሁድ አምልኮ ብቻ አይደለም፤ ሃዋርያቶች ያመለኩበትን መንገድና ስርአት የማንለማመድ ሁላችን በከንቱ አምልኮ ውስጥ እንዳለን በግልጽ መቀበል አለብን፤ ሃዋርያው ከዚያ አምልኮ ወደዚህ ወደ ንጹህ አምልኮ የገባው የእምነት ለውጥ አድርጎ እንጂ በልምምድ ከቶ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት (ሃስ.22)።
Faith (እምነት)
– faithful God- የታመነ አምላክ
– faithful in all his house- ሙሴ በእግዚአብሄር ቤት የታመነው
– children in whom is no faith- ያልታመኑ ልጆች
– faithful priest- የታመነ ካህን
– peaceable [and] faithful in Israel- ሰላምንና እውነትን በእስራኤል የሚወዱ
– the just shall live by his faith- ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል
የእምነት (Faith) አግባብነት
እምነት (Faith) በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች በእግዚአብሄር ላይ ስላላቸው እምነትና በርሱ ላይ መደገፋቸውን ያመለክታል። ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖርና በአብሮነት ለመጓዝ በአምላኩ ላይ እምነቱን መጣል አለበት፤ የማይታይ ግን የሚታመን አምላክ ከእኔ ጋር አለ ተብሎ በልብ ካላኖሩት ባለማመን ምክኒያት ይለያል፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ያደርግልኛል ተብሎ ካልታመነ አንዳች ነገር አያደርግም፤ ብጠራው ይሰማኛል፣ ብለምነው ይሰጠኛል ተብሎ ካልታመነ እንዲሁ አንዳች ነገር አይሰጥም፤ ምክኒያቱም እግዚአብሄር ሊታመን የተገባ አምላክ ነው።
‘’ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።’’ (ያዕ.1፡5-8)
እግዚአብሄር በሚታመኑበት ልጆቹ የሚደሰት አምላክ ነው፤ እንደ አባትነቱ በማክበርና በማመን ወደ እርሱ የምናደርሰው ምንም ነገር ተሰሚ ነው፤ ያን የማያስተውል ትውልድ በቃሉ ይነቀፋል፦
‘’ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ (faithful God) እንደ ሆነ እወቅ፤ የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል።’’ (ዘዳ. 7:8-9)
እግዚአብሄር እመኑኝ የሚለው የታመነ (እንደተናገረው የሚያደርግ) አምላክ በመሆኑ ነው፤ እርሱ ታማኝ፣ ህያው፣ ተስፋን የሚሰጥና የሰጠውንም ተስፋ የሚሞላ አምላክ ነው። ለአብረሃም እጅግ ታላላቅ ቃልኪዳን ሲነግረው እንዴት ይሆን ይሆን የሚያሰኝ ነበር፤ እግዚአብሄር ግን እንደተናገረው ሁሉንም ተስፋ በክርስቶስ ባደረገው ስራ አከናውኖታል፦
‘’እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት (merciful and faithful ) እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።’’ (እብ. 2:14-18)