ያለጥርጥር ሁሉ ሊቀበሉት የተገባ የነጠረ እምነት አለ፣ ያለክርክር ሁሉ ሊከተሉት የተገባ ጌታ አለ፣ ያለማወላወል እጃቸውን ሊሰጡና በምስጋና ወደርሱ ሊገሰግሱ የተገባ አምላክ አለ፤ ይሄ አምላክ እናደርገው ዘንድ የተገባውን ትእዛዝ በፊታችን ሲያኖርም እንድንና ዋስትና ባለው መንገድ ውስጥ እንድንመላለስ ነው።
በመጨረሻው ዘመን ግን ጨካኝ መንፈስ በግልጥም ተሰውሮም እየሰራ ስላለ ሃሰተኞች ሃይማኖቶች በእውነተኛ ሃይማኖት ላይ እንዲነሱ አድርጎአል፣ ብዙዎች ስተው ተከትለዋቸዋል። በመናፍስት የሚታገዙ የክፋት ስራዎች ጻድቃንን ከእግዚአብሄር ለይተው ከጸጋ ሲያጎድሉ ኖረዋል፣ ስጋውያንንም በዚያ ያበዛሉ። እነርሱ ለእውነተኛው ሃይማኖት ራሳቸውን አላስገዙም፣ ለእውነት መንገድም የሚለቅ ህሊና የላቸውም፤ ስለዚህ ለእውነት ፈተና ሆነዋል፤ ክፉ መንፈስም በጻድቃን ላይ ክፋትን ያነሳሳ ዘንድ በአመጸኞች በኩል እውነተኛውን ሃይማኖት ለማጥፋት ይሰራል። ይህን የተረዳው ሃዋርያ ህዝቡን የሚያነቃ ትምህርት በፊል1:27 ላይ ሰጥቶአል፦
‘’ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።’’
መዳን ግን አንድ መሰረት ያለው የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፤ መዳን አንድ ምንጭ ያለው ነው፤ መዳን አንድ አሰራር ያለው ነው፤ ሁሉም ግን የኢየሱስ ነው፣ ከኢየሱስ ነው። ሃይማኖቶች ለምን እንደበዙ ሲመረመር ከላይ የተዘረዘሩት የጌታ የሆኑት ነገሮች በአንድም በሌላም መንገድ ድርድር ውስጥ ስለገቡ ነው። እውነተኛውና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠው ሃይማኖት ግን ያለማወላወልና ያለጥርጥር እውነቱን ያሳያል። ሰለዚህ ቃሉ፦
‘’ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ።’’ ሲል ያሳስባል (1ቆሮ.16:13)።
አንድ መሰረቱ ከጥንት አባቶች የሚመዘዝ እምነት (አብረሃም ያመነው እምነት) አለምን ያድን ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም ተደርጎ ተገልጦአል፣ ይህ ሃይማኖት ጌታ ኢየሱስ ራሱን የሚሰብክ ሲሆን በትምህርቱ አለምን የሚወርስና ሃሰተኞችን የሚያሳፍር ነው። በዚህ እምነት በኩል ጌታችን ይሰራል፣ እርሱ ይታመናልና።
‘’ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦። በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ወይም በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው’’ (ሮሜ.10:6-12)
የተለያዩ አስተሳሰቦች እምነቶችና መላምቶች በገነገኑበትና ስር በሰደዱበት ባህል፣ ልማድና ሃይማኖት ውስጥ ሰብሮ የተገለጠ ህይወት ያለው እምነት መሰረቱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ስለዚህ መዳን ከተመኘን ጌታ በሰጠው በዚህ እምነት ላይ ጥርጥር አያሻም፣ አይገባምም፤ በርሱ የልብ ማመንታት ሊፈጠርም አይገባም።
ጌታ በስጋ የመጣው በአይሁድ ቤተሰብ በኩል ያውም የእግዚአብሄርን ጉብኝት ተስፋ አድርግው ሲጠባብቅቁ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ በመሃከላቸው እየተመላለሰ አስተማረ፤ መዳን ከአይሁድ ስለነበር የሚጸናውን አጽንቶ፣ የሚሻረውን ሽሮ፣ የሚጨመረውን ደግሞ ጨምሮ የአይሁድ ሃይማኖትን ፍጹም ሆኖ እንዲቆም አደረገው። በዚህ እምነት በኩል ትንሳኤ በመታወጁ ለሰው ልጆች ታላቅ ተስፋ ሆኖአል።
ሃዋርያቶች የሰበኩት የእምነት ቃል የሚያውጀው ክርስቶስን ሲሆን እርሱም መከራ የተቀበለው፣ የደማው፣ የሞተው፣ መቃብርም የወረደው እንዲሁም በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል ነስቶ የተነሳው ለደህንነታችን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤ ይህ ሃይላትና ስልጣናትን የሻረ የጌታ ስራ ለአለም የምስራች ይባል ዘንድ ካስፈለገ ብቸኛውና አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለሃዋርያት የተሰጠ ሃይማኖት በአለም ላይ ይገለጥ ዘንድ ይገባዋል፤ በኤፌ4:4-6 ውስጥ ያለው እውነት እንደሚያሳየው፦
‘’በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።’’
በአንድ ተስፋ የማይጠራ እምነት ወደ እውነተኛው ጌታ አያመጣም፤ ወደ ስህተት መንፈስ እንጂ ወደ መዳንም አያቀርብም።
የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል ይላልና።ነገር ግን እውነትን ያልተቀበሉ ልባቸው ዝግ በመሆኑ ልባቸው ውስጥ ያላደረውን፣ ያላመኑበትን ጌታ እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙት፣ ሰምተው ባልተቀበሉትስ የጌታ ቃል እንዴት ያምናሉ? የጌታን አገልጋዮች ያልተቀበሉ ያለ ሰባኪ እንዴት ይሰማሉ? ነገር ግን ወገኖቼ ብሎ ወደነርሱ የመጣላቸው አይሁድ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ለተቀበሉት ግን በስሙም ላመኑት ለነርሱ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣንን ሰጣቸው። ዛሬም ሊድኑ ያሉ ሁሉ በርሱ ያምኑ ዘንድ ተገብቶአቸዋል፣ ስለዚህ እምነት ከመስማት ሆኖአል፣ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል። ስለ ገዛ ወገኖቹ ስለእስራኤል እግዚአብሄር ሲናገር ግን፦ ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።
ለእምነት የታዘዙትን የሚያበረታ ህያው ቃል ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል፦
‘’እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥ ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።’’ (ሮሜ 16:25-27)
አለም በአብዛኛው በስህተት እንድትዋጥ ያደረገው ነገር በእምነት ጸንቶ ያለመኖርና በራሱ በሃሰት ሃይማኖት ተጽእኖ ምክኒያት ነው፤ በሃዋርያቶች ወንጌል የተሰበከ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተከደነ ደህንነት ይዳፈናልና፤ ከዘላለም ዘመን የተሰወረው በሃዋርያቶች ዘመን ግን የታየው ይህ በነቢያት አስቀድሞ የተናገረ የምስራች ሰዎች እንዲድኑበት እንጂ በሰዎች አሳብ እንዲድበሰበስ የእግዚአብሄር ፈቃድ አይደለም፤ እንዲሁም የዘላለም እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ወንጌል እንዲያበራና አህዛብ በብርሃኑ እንዲመላለሱ ፈቃዱ ነው፤ የወንጌል ባለአደራ ሃዋርያ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን የሚያምኑትን ሊያበረታና ሊተክል እደሚችል በማሳወቅ በዚህ ወንጌል እንድንጸና ያሳስባል።
እውነተኛ ሃይማኖት የወንጌል ሃይማኖት ነው
የወንጌል ሃይማኖት ጌታ ኢየሱስን ስለምሰብክ ሁልጊዜ ጌታ ከቃሉ ጋር ይሆናል፣ እንዲሁም ከቃሉ አገልጋዮች ጋር ይወጣል። ወንጌል ሲሰበክ መንፈስ ቅዱስ እውነተኛነቱን ይመሰክራል፤ በወንጌል ሃይማኖት በኩል የእግዚአብሄር ሃይልን ተለማምደናል፣ ድነናል፣ ተፈውሰናል። ወንጌል እግዚአብሄርን ገልጦልናል፣ ማንነቱን አብርቶልናል፣ ፈቃዱን አሳውቆናል። ስለዚህ የዚህ ሃይማኖት ምንጭ ገብቶን ከሆነ ለርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን።
ፊል1:27 ‘’ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።’’ ይላል።
በመጨረሻ ዘመን እየሆነ ካለው ክህደት በመነሳት መንፈሳውያን ከክፉ መናፍስት ጋር ትልቅ ተጋድሎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ቃሉ ያመለክታል፤ ሃይማኖቱ የያዘው ወንጌል የክርስቶስ ወንጌል ነውና አላስነካም፣ እንዲለወጥ አልፈቅድም፣ እኔም ከርሱ ውጪ አላምንም በሚል ጸሎት፣ በቃሉ ሙግትና ትግል ውስጥ እንድንገባ ውሳኔያችንን ይጠይቃል። ቅዱሳን የሰማይ ባላገሮች ኑሮአችንን ምድር ላይ ብናደርግም ልባችን ግን በሰማይ ባለው እግዚአብሄርና መንግስቱ ላይ በማድረግ በእምነት መጽናት ያስፈልገናል።
(ማቴ.4:23-25) ‘’ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። ‘ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።’’
በጌታ በኢየሱስ ትምህርት በኩል በልብ በሚፈጠር እምነት መዳን ለብዙዎች ሆኖአል። ከህያው አምላክ የወጣ የህይወት ቃል ፈውስ አምጥቶ ለህዝብ ነጻ መውጣት መንገድ ሲሆን እናያለን፤ እውነት ሁሌም አርነት ያወጣልና በዚህም ዘመን በርሱ ላይ ብቻ ባለን እምነት እርሱን በህይወታችን ማንገስ እንደምንችል ልናምን ይገባል።
የጌታ ደቀመዛሙርት በእግዚአብሔር ለተመረጡት ወገኖች እምነት እንዲሆንላቸው፣ በርሱ ተደግፈው በእምነት ይበረቱ ዘንድም በወንጌል ያለውን ምስጢር ይገልጡላቸው ነበር፤ በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁና በጽናት እንዲቆሙ ይህ ብርሃን ለህይወት መሰረት ነውና።
እንዲሁም በህያው አምላክ ላይ ለተደገፉ ትምክህት የሚሆነውን ይህ የህይወት ተስፋ የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሰጥቶአል፤ በዘመኑም ጊዜ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ የወንጌል አደራ ለሃዋርያት በተሰጠ ስብከት ለህዝቡ ገለጠ፤ ቃሉ በሃይማኖት ኅብረት ህዝቡን አንድ በማድረግ ከአምላኩ ጋር እያኖረ ያለ ነው፤
በሃይማኖት ህብረት አማኞችን በአንድ አሳብና በአንድ ልብ ያቆም ዘንድ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርትም እንድንጸናና ተቃዋሚ መንፈስን በመዋጋት በርሱ ድል እንድንመላለስ ጸጋው ረድቶናል።
ብዙ ትምህርቶች በአለም ላይ ተፈብርከው ወደ ጆሮአችን ቢገቡም ህይወት ሊሆኑ ስለማይችሉ ወደ መንፈሳችን አይደርሱም፤ ወንጌል ግን እውነት በመሆኑ የተታለሉ ወገኖችን ወደ አምላክ ይመልሳል፣ በከንቱ ፍልስፍና፣ ባእድ አምልኮና በመሳሰለው አጋንንታዊ ተጽእኖ ውስጥ የሚመላለሱ ተፈትተው ወደ መዳን እንዲመለሱ ይረዳል፤ እውነት ሁሌም አድራሻ አለውና፣ ያም ጌታ ኢየሱስ ከሚገለጥበት እምነት ውስጥ ይገኛል።
1ዮሐ.2:24-29 ‘’እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።’’
የእውነት ፍጻሜ የያዘ ሀይማኖት
ሃዋርያቶች አጠንክረው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድንጋደል ለመምከር መልእክቶችን አዘጋጅተዋል፤ ይህ ያለ ምክኒያት አትኩሮት ያልተሰጠው ተጋድሎ በእኛም ዘንድ ይዘቱን ሳይለቅ በጥብቅና በጥልቅ ታስቦበት እርምጃ እንዲወሰድበት እንዲሁም በጠላት አሰራር ውስጥ ከመውደቃችን በፊት እንድንረዳው የተሰጠ ማስገንዘቢያና ጠንቀቂያ ነው።
ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ ሃይማኖት ስለመዳን ብቻ ሳይሆን ስለፍርድና ስለነገሮች ፍጻሜም ያስተምረናል፤ በዚህ እውቀት ላይ ሆነን ወደፊት ሊመጣ ያለውን እንድናስተውል እንድንወስንም የሚያደርግ ነው። ፍጥረታት በእግዚአብሄር እንደተፈጠሩ ሁሉ መጨረሻም ተበጅቶላቸዋል። እጅግ የበዙ የፍጥረት አይነቶች በአጋንንት በረከሰች ምድር ላይ ይኖራሉ፤ ምድር ከሰው የተነሳ ተረግማ የምትጠፋበትን ጊዜ የምትጠብቅ መሆንዋ ብቻ ሳይሆን በላዩዋና በውስጥዋ ያሉ በሙሉ ከርስዋ ጋር የሚጠፉበት ጊዜ ተቃርቦአል።
2ጴጥ.3:9-14 ‘’ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።’’
ነቢያት በጥንት ዘመን ስለመምጣቱ ትንቢት ተናግረው ነበር፣ ጌታ ራሱ ዳግመኛ እንደሚመጣ ገና በምድር ሳለ ተናግሮአል፤ በዚያን ወቅት ስለአለም መጨረሻ ለሃዋርያቱ እያብራራ ነግሮአቸዋል፤ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እያሉ ግን በቃሉ ላይ የሚዘብቱ ስለመምጣቱም ጥርጥርን የሚዘሩ ሃሰተኞች ኖረዋል አሁንም አሉ፣ ጌታ ግን እንደተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ይመጣል፤ በሰማይና በምድር ላይ የተናገረው ፍርድም ይፈጸማል፤ የጌታን ቃል የሚቀበል ግን እርሱ ሊመጣ ካለው ጥፋት ያመልጣል።