የጌታ ኢየሱስ ክብር በብርሃን የተገጠለት አገልጋይ፣ ማዳኑንና ምህረቱን ከእርሱ የቀመሰ በአንድ ወቅት ግን የአማኞች አሳዳጅና ጠላት የነበረ ከተለወጠና የጌታ ጸጋ ካገኘው በሁዋላ ደግሞ ከሁሉም ሃዋርያት አብልጦ የሮጠ፣ አብዝቶ የደከመም የእግዚአብሄር ሰው የኖረበትንና የሰበከውን ሃይማኖት ለተተኪው ልጁ በጽናት አስይዞ ይሰድደው ዘንድ በምክሩ ሲያበረታው በብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል እንመለከታለን፤ በዚህ ስፍራ የምንመለከተው ቃል ደግሞ እንዲህ ሲል ይንገራል፦
‘’በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም።’’ ይለዋል(1ጢሞ.1:2-3)።
በዚህ ቃል ላይ ሃዋርያው ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ አንድ አስፈላጊ ነገር ሲያመለክተው እናያለን፤ ይህም በእውነተኛ ሃይማኖትላይ የተነሳ ጠላት የሆነ ልዩ ትምህርት ላይ አትኩሮቱን እንዲያደርግ የሚያስገነዝብ ነው፤ ይህ ትምህርት በግልጥ በጌታ የተሰጠን መዳን ወደኋላ ሊስብ የሚችል፣ አማኞችን ሊያስት የሚችል፣ ጨርሶ መዳንን የሚያጠፋና የእግዚአብሄርን የዘላለም እቅድ የሚያበላሽ በመሆኑ በተገለጠው ሰማያዊ እምነት ውስጥ ስፍራ እንዳይኖረውና እንዲጠፋ ሊዋጋ እንዲገባው ያነቃዋል።
በጌታችንና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጀመረ፣ ፍጹም የሆነውና ሙሉ መዳን የሚሰብከውን ሃይማኖት አለም ልታውቀና ልትቀበለው የሚገባው የእያንዳንዱ ፍጥረት መጀመሪያና መፈጸሚያ ቃል በርሱ ዘንድ ስላለ ነው። ምድራችን ክርስትና በሚል ስም ብቻ ስንት ሺህ ሃይማኖት ተሸክማለች? ትክክለኛው ቁጥር ይሄ ነው ማለት አይቻል ይሆናል ግን እስከዚህ ሰአት ድረስ የክርስትናን ስም የያዘ ሃይማኖት (ከስሙ በስተቀር የህይወት ቃል በማያስተናግድ ሁኔታ ውስጥ ያለ) ያለከልካይ እየተፈለፈለ ይገኛል። በዘመናችን እያየን ያለው መንፈሳዊ ድቀትና ጥፋት መነሻ ምክኒያቱ ሃዋርያው አስቀድሞ ያስጠነቀቀው ነገር ቸል በመባሉ ነው። ሰዎች እውነትን በሚበርዝ ትምህርት እየተጥለቀለቁ ባለበት ወቅትና ሃይማኖተኞች በራሳቸው እውቀት ምድራዊ ሃይማኖትን ቀርጸው ሊዘውሩ በሚጣደፉበት ወቅት መጨረሻው እየቀረበና ጥፋት ወደ እኛ እየተጣደፈ ይገኛል። አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠው ሃይማኖት በምድር ላይ ተሰራጭቶ ሰዎች እንዲድኑ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የእውነት እውቀት እንዲጸና ያስፈልጋል፤ ይህም አስቀድሞ በአማኞች ዘንድ አንድነት እንዲኖር በማድረግ፤ እውነትን የሚቃወሙ የጽድቅ ጠላቶችን ነቅቶ በመለየትና በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ ሾልከው የሚገቡ ሃሰተኛ አማኞች ደቀመዛሙርት በሰይጣን ወጥመድ ይወድቁ ዘንድ የትምህርትን ነፋስ እንዳያነፍሱ በማስጠንቀቅ ነው።
ሮሜ.16:17-18‘’ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።’’ ይላል።
እውነትን ከመጠበቅና ጽድቅን ከማጽናት አንጻር ለገዛ ሆዳቸው ያደሩ ደፋሮች የህይወት ቃልን እንዳይበርዙ መጠንቀቅ ተገቢ ነው ይላል፤ እነዚህ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የማይገዙ አታላይና ተንኮለኞች በእምነት ያልበሰሉትን አታልለው በትምህርታቸው ሊጥሉ ስለሚችሉ ከነርሱ አማኞች ፈቀቅ እንዲሉም ማስጠንቀቂያ ቀርቦአል። እውነተኛ ሃይማኖት ሲጸና በቤተክርስቲያን፦
-የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱ እንዲከበር ይሆናልና
-ጌቶች ከአገልጋዮቻቸው፣ ታላላቆች ከታናናሾች ሳይተቻቹና ሳይናናቁ ተከባብረው በመኖር አንድነት እንዲጸና ይሆናልና
-ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ሃሰተኛ ስፍራ ያጣል፤ ነገር ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት መጽናት ይሆናልና
-ከንቱ ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ የሚናፍቁ ሃሰተኞች እውነት በበረታበት ቤተክርስቲያን ስፍራ የላቸውምና
-በአለም ካለ ምኞት ርቆ በእግዚአብሄር ፈቃድ መኖር እዲቻል የሃዋርያው ዋነኛ ምክር ከነዚህ አሳቾች መራቅ እንደሚገባ ያሳስባል። ከዚህ ይልቅ ኑሮዬ ይበቃኛል የሚለውን እግዚአብሔርን በመምሰል የሚገኘውን ማትረፊያ መያዝ ተገቢ ነው።
1ጢሞ.6:1-6‘’…አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ። ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው’’ ስለሚል።
2ዮሐ.7-11‘’ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት።ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።’’
በእምነት የበረቱትን ለማሳሰብና ለመምከር ሃዋርያው የሚያስቀምጣቸው ብርቱ ምክሮች ለክርስቲያኖች በተለይ በበሰሉት ዘንድ ልብ ሊባል እንደሚገባ ቃሉ አመልካች ነው፦
‘’እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን’’ (ፊል3:15-20)
አንድ ጊዜ በጌታ ፈጽሞ የተሰጠውን ሃይማኖት ክፉው ይሰውር ዘንድ አሳችና አመጸኛ የሆነ ሰው ሁሉ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ አሁንም ቢሆን ከድሮ ጀምሮ ሲቀጣጠል የመጣ የክፋት ልምምድ ትውልድን አሸንፎ እንደቀጠለ ነው፤ ዲያቢሎስ በፈንታው ይህን ሰው ፈልጎ በመያዝ እየተጠቀመበትና ማሳሳቻ መንገዱን በርሱ በኩል በስውር እየዘረጋ ነው። የጥፋትና የማሳሳቻ ትምህርት ሁሌም ለስጋ አጋዥ ጥቅም ስላለው በተለይ ለዚህ የተመደቡ ሰዎች ስራዬ ብለው በክፋት እንዲቀጥሉ ውስጣቸውን ያደፋፍራል፤ ጽድቅን ወደኋላ ብለዋልና እግዚአብሄርን ሳይፈሩ ሆዳቸውን በዚህ ስራ አክብረውበታል።በልማዳቸው የጌታን ቃል ሲያጣምሙ አልፈሩም፤ ህያውን ቃል በትምህርታቸው ሲበርዙና ሲደልዙ ጌታ በአርያም ሆኖ እያየን ነው ብለው አላደነገጡም፤ ሆዳቸው አሸንፎአቸዋልና በስራቸው ክደውታል፣ ስሜታቸው ነድቶአቸዋልና የአምሮት ጥማታቸውን ሊያረኩበት ተጣድፈውበታል። ይሄ ሁሉ ሩጫ የስጋ ፈቃድን የሚሞላ ይምሰል እንጂ ማቆሚያ ነጥብ አለው፤ ጊዜ ሳለ ካልተመለሱበት በንሰሃ በኩል አመጻቸውን ካልተዉም የሚጠብቃቸው ዲያቢሎስ ላይ የተወሰነው የፍርድ መጨረሻ ይሆናል ማለት ነው።
ይሁ.1:16-21 ‘’… እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤እነርሱ:- በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
ፍጻሜ ሰማይና ምድር
የአለም ፍጻሜ እየደረሰ ባለበት ትውልድ መሃል የነገር ሁሉ ፍጻሜ እየቀረበ መሄዱ የግድ ነው፤ ፍጻሜው ደግሞ አምላካቸውን ተስፋ ላደረጉ ምህረት ለአመጸኞች ፍርድ ይዞ የሚያመጣ ነው፤ ያም በሆነ ጊዜመጽናት ያለበት እንዲጸና መሻር ያለበት ደግሞ እንዲጠፋ ፍጻሜው ይመጣል። የትውልዱ ስነልቦና በደነደነበት በአሁኑ ወቅት፣ ህሊና በተቃጠለበት ጊዜና አመጽ ስፍራዎችን በተቆጣጠረበት በዚህ ዘመን መጨረሻ ፍጻሜው ፍርድን ይዞ እየመጣ ነው።
1ዮሐ.2:18-21 ‘’ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ። እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።’’
ፍጹሙ ሃይማኖት በጌታ የተሰጠው ተስፋ እውን እንደሚሆን ያበስራል፤ ተስፋ በተቆረጠለት ጊዜ የሚፈጸም የእግዚአብሄር ቃል ነው እንጂ ባዶ ንግግር አይደለም፤ በዚህ ቃል መሰረት የተስፋ ቃል ምድርና ሰማያት አልፈው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በእግዚአብሄር እንደሚፈጠሩ ያበስራል። በሌላ በኩል ስንመለከተው ደግሞ በጌታ የሚገለጠው ጽድቅ ደግ ደጉን፣ ለእኛ የሚጠቅመንን እንዲሁም ማየት የምንሻው ብቻ እንዲገለጥ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፤ ከእግዚአብሄር የሆነውን ሁሉ እንጠብቅ ዘንድ የሚያስተምር ነው። እውነቱን በይበልጥ ማገናዘብ ሳይኖር ከዚህ ውጪ አቋም በመያዛችን ምክኒያት ሊመጣ ያለውን ፍርድ ማየት፣ ልብ ብሎ መጠንቀቅም የጽድቅ ፍላጎትና የመታዘዝ መገለጫ ነው። ጸጋ የእግዚአብሄርን በጎነት እንደሚያመለክት ተናግረን ስናበቃ ከባድ የሆነውንና አስፈሪ የሚያደርገውን ፍርዱን አይተን ጨካኝ ልናደርገው ብንሞክር የጽድቅን መሰረታዊ አሳብ አላስተዋልነውም ማለት ነው፤ እግዚአብሄር ጻድቅ በመሆኑ ለቅኖች በጎነቱን ለክፉዎችም ፍርዳቸውን ይሰጣል፣ ይሄም የእውነተኛና የማያዳላ አምላክነቱ መገለጫ ነው። ጸጋም ፍርድም የርሱ ገንዘብ ናቸውና፣ እኛም መርጠን የምንወስዳቸው ሼልፍ ላይ የተደረደሩ እቃ አይደሉምና፣ በእኛ መቻል፣ ፍላጎት ወይም ፈቃድ የምንወስናቸው ከቶ አይደሉም፤ ነገር ግን በርሱ ምህረት ስለተገለጡልን የሚሻለውን መርጠን በመቀበል፣ በእምነት በመከተልም ለራሳችን በጎ ነገር እንቀበላለን፤ እንደ አሳቡ የምንኖራቸው እንደ ምህረቱ መጠን ተግተን የምንሻቸው የትኞቹ መሆናቸውን በተገለጠልን ቃል ስንለይና ገንዘባችን በማድረግ ጻድቁ አምላክ ሊገለጠው ካለው ብይን እንዲያተርፈን እንረዳለን።እውነተኛው ሃይማኖት የሚያስተምረን ይሄንን ነውና፣ እንዲህ ስለሚል፦
‘’እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለምሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤ ነገር ግን ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም ስለሕግም ከሚሆን ጠብራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስልሰው ራቅ። መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ።’’(ቲቶ 3:3-11)
የደህንነት ፍጻሜ የያዘ ሀይማኖት
ሃዋርያቶች ካመኑት ጌታ በቀር ሌላ የሚያድን እንደሌለ፣ ከስሙ በቀር ሌላ ስም ማዳን እንደማይችል እንዲሁም እርሱ ብቻ ሊነግስ የተገባው ጌታ እንደሆነ አውጀዋል፤ ከታናሹ እስከታላቁ ድረስ መዳንን በተመለከተ ሊያውቅ የሚገባውን ሲያመለክቱ እንዳሉት፦
‘’መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።’’ (ሐዋ.4:12)
በአለም ላይ የተፈጠሩ ሃይማኖቶች ይህን መዳን በግልጥ አይሰብኩም፣ ቢሰብኩ በእምነት ያይደለ፣ ወይ ሰዋዊ አሳብ የታከለበት፣ ያልያም ፍልስፍና የጠመዘዘውና መናፍስት ጣልቃ የገቡበት የጌታን የማዳን ስራ ጥርጥር ውስጥ ያስገቡበት አካሄድ ያለው ነው። እግዚአብሄርም እምነታቸው በድንቅና በታምራት በማጀብ ከነርሱ ትምህርት ጋር መሆኑን መስክሮአል፦
1ጢሞ.4:1-3‘’መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።’’ ይላልና ሃይማኖትን ከሚያስክድ የመናፍስት ትምህርት እንድንጠበቅ በሃዋርያት ትምህርት እንጽና።