ብቸኛና ፍጹም ሀይማኖት(10…)

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ሰው ያለፈጣሪው መኖር እንደማይችል የሚያውቅ ሰይጣን ሰዎች እርሱ አምላክ እንደሆነና መመለክ እንደሚገባው አድርጎ በተለያየ መንገድ ያሳምናቸዋል፣ በአገልጋዮቹ አድርጎ ይናገራል፣ ብዙዎችን አሳምኖም በሚታዩ ጣኦታት በኩል እንዲያመልኩት ያደርጋል፤ ይህን በተመለከተ ንጉስ ዳዊት እንዲህ ብሎአል፦
መዝ.96:4-5 ‘’እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።’’
ዋናው ነገር ሰዎች እነዚህን ጣኦታት ከልብና ከህይውት ካላስወገዱ እግዚአብሄር እንደማይጎበኛቸው እርሱንም በእውነትና በመንፈስ ሊያመልኩት እንደማይችሉ ማስተዋል ላይ ነው፤ ቃሉም ያን አስረጦ ያሳስባል፣ እንዲህ ሲል፦
ዘጸ.20:3-6‘’ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።‘’
ሰይጣን እግዚአብሄርን ለማስካድ የሰማይ አምላክ የሚባል ጨርሶ እንደሌለ ያስተምራል፣ አለ ብሎ በእምነት ለጸናው ደግሞ እንዲህ ይለዋል፦ አለ ግን እሱ ብቻ ሳይሆን ከርሱ ጋር ሌላ እኩያ አምላክ አለ። ይህን በሚመስል ሌላ እንግዳ እውቀት ገዳይ ስብከት ሰብኮ፣ ክፉ ትምህርቱን በልቡ አትሞም ይበክለዋል፤ ሁለቱም እውቀት ከእግዚአብሄር ጋር እንደሚያጣላ ስለሚያውቅ የማያውቀውን በማሳወር የሚያምነውንም በማደናገር ከመስመር ያስወጣል፤ የእግዚአብሄር ማስጠንቀቂያ ግን ጥብቅ ነው፦
ዘዳ.4:23-29‘’አምላካችሁም እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ አምላክህም እግዚአብሔር የከለከለውን በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና። ልጆችን የልጅ ልጆችንም፥ በወለዳችሁ ጊዜ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ በረከሳችሁም ጊዜ፥ በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል ባደረጋችሁ ጊዜ፥ ታስቈጡትም ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር በሠራችሁ ጊዜ፥ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ፤ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትቀመጡባትም። እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። በዚያም የማያዩትን የማይሰሙትንም የማይበሉትንም የማያሸቱትንም፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ።’’
ወደ ፍጹሙ ሃይማኖት ስንመጣ በዚያ ውስጥ እያንዳንዱ የእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ በግልጽ ተብራርቶ እናገኛለን፤ የእውነት አስተማሪዎች በዚያ አሉ፤ ለመንጋው የሚራሩ አስተማሪዎችም በእርግጥ በዚያ ያገለግላሉ። ቅን ወገኖች ቅዱሱን አምላክ ሲገልጡት እግዚአብሄር ለልጆቹ የመንግስቱን ምስጢር የሚያስተውሉበት መንፈስ ያፈስላቸዋል።
ሮሜ.8:13-15 ‘’እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።’’
እግዚአብሄርን የሚፈልግ ጸንቶ እስከ መጨረሻው እንዲጓዝ እምነቱ የጸናና ያልተበረዘ እንዲሆንም የግድና አስፈላጊ ነው። የእግዚአብሄር ቃል በእምነት ጸንቶ ለሚኖረው አማኝ የመጨረሻ ሽልማት እንደሚሰጠው ያሳያል፤ በውጪ ያሉት ግን የሚያገኛቸው ፍርድ አለ፤ በዚህም ትውልድ የክፋት ምንጭ የሆኑ አጋንንት የሚያስቷቸው ወገኖች ወደ ተወሰነው ታላቅ ፍርድ እየሄዱ ነው። ሁሉን የሚችል አምላክ ባሪያዎች ግን በየትውልዱ ሁሉ መዳን ይገኝ ዘንድ የማይለወጠውን ወንጌል አንዴ አኑረው አልፈዋል።
ፍጻሜ እርኩስ መናፍስት
ይሁዳ ስለ ፍጹሙ ሃይማኖት በጻፈበት ስፍራ ክፉ መናፍስትን ስለሚያገኛቸው ፍርድም ተናግሮአል። እግዚአብሄር የሰውን ልጅ ባሳቱ የእግዚአብሄርንም ፈቃድ በተቃወሙ ክፉ መላእክት ላይ ይፈርዳል፤ ይህን የሚያስተውሉ በእውነተኛ ሃይማኖት ላይ የተመሰረቱ ብቻ ናቸው፦
‘’ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ።’’ (ይሁ. 1:5-8)
እግዚአብሄር በአመጽ፣ በሃጢያትና በመተላለፍ ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ (የወደቁ መላእክትና እውነትን ያልተቀበሉ የሰው ልጆች በሙሉ) ለፍርድ ማቅረቡ ጻድቅ አምላክነቱን የሚያመለክት ነው። የቃሉ እውነት የእሳት ባህር ለሰይጣንና ለመላእክቱ እንደተዘጋጀ እነዚህን ክፉ መናፍስት የተከተለ ማንም ሰው ቢኖር ግን ከነርሱ ጋር በዘላለም ቅጣት እንደሚቀጣ ያሳያል።
‘’ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው።ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።’’ (ራእ.20:7-10)
በእውነተኛ ሃይማኖት ለሚኖሩ ወገኖች እግዚአብሄር ጥበቃን፣ ምህረትን፣ ሰላምንና በረከትን ይሰጣል። በእምነት እየበረታን ጌታን ተስፋ እንድናደርግ፣ በርሱ እየኖርን ራሳችን ጭምር ብርሃን እንድንሆን ይፈለጋል፤ ፈቃዱን በማወቅ ከእርሱ የምንቀበለውን ጸጋ ይዘን እስከ መጨረሻው በመጓዝ ደግሞ እንድናለን። በሃዋርያት ዘመን እንደነበረው ያለ መታዘዝ ካለ እነርሱ የተቀበሉትን ጸጋ በዚህም ዘመን እንቀበላለን፣ የጌታ ሃይል ህይወታችንን እንዲለውጥና በእርሱ ፈቃድ እንድንመላለስ ስለሚያስችል ዘወትር በርሱ እንድንኖር መትጋት ይጠበቅብናል፦
‘’በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና፦ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ። በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ። በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።’’ (ሃስ.14:21-23)
በሃይማኖት ጸንተን በመኖር የጌታን ክብር ማሳየት፣ የክብር ወንጌሉን ላልዳኑት በፍቅር እያቀረብን ከጠላት የጥፋት መንገድ ወገኖቻንን ማስጣል እንዲሁም በመዳናችን ውስጥ የሌሎችን መዳን የምናይበት የከበረ ህይወት እየኖርን በዚህ ምድር ላይ መመላለስ ተገቢ ነው።
ቅዱሳን በሃውርያት ዘመን ልባቸውን በጌታ ላይ በማስደገፋቸውና በጠላት መንግስት ላይ ከፍተኛ የጽድቅ ተቃውሞ በወንጌል ስብከት በማስነሳታቸው ክፋት የጸናባትን ምድር አናውጠዋል፤ ይህም ለጌታ ኢየሱስ ክብር የሆነና የእርሱን ፈቃድ ለፍጥረት ያሳወቀ፣ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሆነ ህይወትም ነበር፤ ይህ ህይወት የተጋድሎ ሃይማኖት የሚያበረታውና የሚያጸናው ህይወት ነበረና ስለርሱ ሃዋርያቶች ማሳሰብን አልተዉም፣ሃዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ይል ነበር ፦
‘’ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።’’ (ፊል. 1:26-30)
የክፉ ሃይላት ምንም ቢበረቱ፣ ምንም ያህል የስጋ ክንድ ቢያስተባብሩም፣ ደቀመዛሙርት ግን ሃያል የሆነ አምላክ በሚያለብሰው የጸጋ ክብር ተረድተው ከድል ወደ ድል ተራምደዋል፣ አሁን ያሉትንም ያ ጸጋ ያራምዳቸዋል። መከራን የሚያስረሳ ሃይል እንዴት ያለ ሃይል ነው? መከራን የሚልቅ ደስታ በጌታ ኢየሱስ የሆነልን ልዩ የመንፈስ ደስታ እኮ ነው፤ መከራ እያለ መከራውን የሚረግጥ፣ ፈተና በርትቶ በፈተናው ላይ የመንፈስ ብርታት የሚያጎናጽፍ፣ ችግር እያንገላታም የችግሩ ዱላ የልብ ህመም እንዳይፈጥር የሚያደርግ የጌታ ኢየሱስ ጸጋ አለ። በእውነተኛ ሃይማኖት ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ለጽድቅ ያማጠኑ ይህን የክብር ህይወት ይቀዳጃሉ፤ የታመነውም አምላክ ብርታት ይሆናቸዋል።
‘’እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል።’’ (ቆላ.1:22-26)
እግዚአብሄር በወንጌል የሰጠን ምህረት፣ ይቅርታ፣ በረከትም ሆነ ጸጋ ጸንቶ እንዲኖር ከተፈለገ የተገለጠልንን ሃይማኖት እስከ መጨረሻው አጥብቀን መያዝ ነው።እንደ ዴማስ ሃይማኖትን ስለ አለም ተድላ ብለን ሳንተው፣ እንደ ሃዋርያት ዘመን አይሁድ ሃይማኖትን ሳናሳድድና ሳንክድ፣ በዚህ ዘመን እየሆነ እንዳለው በሰዋዊ እምነት ሳንዋጥ ለሃዋርያት አንዴ የተገለጠውን ሃይማኖት አጥብቀን እንያዝ፤ ከውጪ ያለን ወደዚያ ልባችንን እናዘንብል፣ ከውስጥ ያለን በያዝነው እንጽና ጌታ ጸጋውን ያበዛልናል።
(ቆላ. 2:6-8)‘’እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።’’
በሃይማኖት በርትቶ መቆም ከትምህርት ነፋስ ጋር እየተጋደሉ መጽናትን ይጠይቃል፣ እምነትም በውስጣችን ተተክሎና በአምላካችን ላይ ያለን መደገፍ ጸንቶ ያለድካም ለመኖር በእምነት መቀጠልና መቀጣጠል ይጠይቃል፤ የሃይማኖት ትምህርት አለም እንደፈጠረችው ያለ እምነትን የሚያራምድ ሳይሆን ኢየሱስን ጌታ ያደረገና በርሱ ጸጋ የሚመላለስ ነው፤ በአለም ላይ ያለ ሃይማኖት የቱን ያህል ይብዛ፣ ምንም ስለ ጌታ እንዲያምን ይናዘዝ፣ በጌታ ስም ቢሰብክም፣ ስሙን በአጋንንት ላይ ቢጠራም አንዴና ፈጽሞ በተሰጠው ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ወንጌል ሊሰብክ አይችልምና ፍጹም ጥንቃቄ ይሻል።ሃዋርያትም ይሄን ስለሚረዱ ትጠንቀቁ ይላሉ።
እንግዲህ አስቀድማችሁ በሃዋርያት ተሰብኮላችሁ ያመናችሁትን ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን ያኔ በልጅነታችሁ በየዋህነትና በእምነት እንደ ተቀበላችሁት፣ ዛሬ ምንም የተለያየ እውቀት ብትሰሙም ያለመናወጥና ያለመደነጋገር በርትታችሁ በመቆም በእርሱ ተመላለሱ ሲሉ ያሳስባሉ። በጌታ እምነት ላይ ሥር ሰዳችሁ መንፈሳዊ ቤት እንድትሆኑ በእርሱ ቃል ላይ በጸጋው ታነጹ፥ በሃዋርያት እጅ አስቀድማችሁ እንደ ተማራችሁም ሳትለዋወጡ ቁሙና በሃይማኖት ጽኑ፥ ያዳናችሁን የጸጋ ቃል ይዛችሁ፣ የጌታን ስም እየጠራችሁ፣ በመንፈስ እየተመላለሳችሁና በርሱ መንፈስ በደስታ ሆናችሁምስጋና ይብዛላችሁ ሲሉ ያስታውሱናል። ተጠንቀቁ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሰጠ ሃይማኖት ያገኛችሁትን እውነት የሚያስት የተለያየ እውቀት በአለምና በአጋንንት በኩል ያገኛችኋዋልና፤ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና የሚሰበከውን ትምህርት ተመልከቱ፣ ንግግርና ሰዋዊ ቃል ብቻ በሆነ ነገር ግን ህይወት ባልሆነ በዚህ አለም ትምህርት በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁም ይሉናል።