ሰው በእምነት ወይም በሃይማኖት በኩል የሚያመልከውን አምላክ ይጠጋል፣ ይከተላልም። ማንም ያለ ሃይማኖት መኖር አይችልም፣ ምክኒያቱም ለአምልኮ የተፈጠረ ማነንት በውስጡ ስለያዘ። ያ ማንነት መንፈሳዊ በመሆኑ ሁልጊዜ በመንፈስ ያስሳል፣ የሚያረካውንም ነገር ይፈልጋል። የሰው ተፈጥሮ ስጋ፣ ነፍስና መንፈስ እንደያዘ ቃሉ ያስተምራል፤ በስጋው በኩል ከግኡዙ አለም ጋር ይገናኛል፣ በመንፈሱ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ አለምን ይገናኛል። በሰው ስጋዊ ተፈጥሮ ውስጥ ያለው የመብላትና የመጠጣት ረሃብ እንዳለ ሁሉ በመንፈሱ በኩል መለኮታዊ ስጦታዎችን ካላገኘ በተመሳሳይ ስሜት ሲባክን ይኖራል። ስለዚህ ሁልጊዜ ከማሰስ የማይመለስ መንፈሳችን እውነተኛውን አምላክ እስኪያገኝ በጭንቅ ሆኖ እርግጠኛውን ነገር ለመያዝ ይጥራል፤ ያለእውነተኛ አምላክ እስካለም ድረስ በሃሰተኛ መናፍስትና በሰዋዊ እውቀት ቁጥጥር ስር ወድቆ ይንከራተታል። ታላቁ ሃዋርያ ጌታ ሳያገኘው በፊት በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ ነበር፣ አምላኩ ግን ተገናኝቶ መንገዱን ቀየረለት፣ ከዚያ በሁዋላ ስለቀድሞው ማንነቱ፣ እምነቱና ትምህርቱ ያረጀና ያፈጀ ስለመሆኑ በአጽኖት እያስረዳ ሰዎችን አዲስ በተመረቀው የሃይማኖት መንገድ እንዲገቡ ይሰብክ ነበር፦
‘’ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም… በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ ነገር ግን፡- ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።’’ (ገላ. 1:15-24)
በአይሁድ ሥርዓት (Jews’ religion) ከመጠን ይልቅ ተውጦ ሲንቀሳቀስ በግል የአብረሃም አምላክን መጠጋት ያውም የተስፋ ህዝብ ለሆነው እንደ ጳውሎስ ላለ ሰው የማይገባ ሲሆን በእንዲያ ያለ ስርአት ለተቆጣጠረው እምነት ጊዜና ጉልበቱን መስጠቱም አሳዛኝ ልምምድ ነበር።
ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ (more exceedingly zealous of the traditions of my fathers) ሲል ለነበረበት የአይሁድ ሃይማኖታዊ ስርአት እንደተሙዋገተ፣ ከህያው አምላክ ቃል ይልቅ የርሱና የአይሁድ የሚሆኑ አባቶቻቸው በየትውለዳቸው ሲቀባበሉ ቆይተው ለርሱ ያወረሱትን ሰዋዊ ስርአት እንደተከተለ በጸጸት ያስታውሳል።
በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ለተወለደ ሰማያዊ ማህበር (the church of God) ጌታ አንድ ብቸኛ መዳን እንደሰጠና እርሱም ይህን ጌታ የሚሰብክ ሃይማኖት እንደተቀበለ፣ ከአባቶች ወግ ትረካ ዞር እንዳለና ወደ ተቀበለው አዲስ ሃይማኖት እንዳዘነበለ፣ በዚያ ተግቶም እንዳገኙት ለህዝቡ ይመሰክራል። አስከትሎም ስለዚህ ሃይማኖት አቀባበል ሃዋርያው የሚናገረው አለው፣ እንዲያውም የዚያ ሃይማኖት አድራሻ ከየት እንደሆነ ሲያመለክት እንዲህ ይላል፦
‘’ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።’’ (ገላ.1:11-13)
በእርግጥ ሃይማኖት እምነት ነው። ከእግዚአብሄር የተሰጠ ሃይማኖት ደግሞ አለም ላይ የተንሰራፋውን አሳሳች የተመሳሰለ እምነት፣ ኋዋላ ቀር ወግና ከንቱ የሆነ ልምምድን የሚሽር ነው፡፡ መለኮታዊ ሀይማኖት አለማዊ እይደለም፣ ፈጠራም አይደለም፤ ስጦታ ነው፣ የእግዚአብሄርና አንድ ብቻም ነው። ደግሞ ሰዋዊ አይደለም (ሰው ያቁዋቁዋመው ተቁዋም አይደለም)፣ የእግዚአብሄርን ማዳን፣ ጸጋ፣ ትእዛዝና ፍርድ የያዘ ነው፡፡
‘’በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።’’(ኤፌ.4:4-6)
ፍጹሙ ሃይማኖት በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ላይ የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ ጌታ በሞቱ ያረጀውን መንፈሳዊ ስርአት አፍርሶአል፣ ተቀብሮ በተነሳ ጊዜም የሞቱትን ነገሮች ሲቀብር መነሳት ያለባቸውን ተስፋዎች ግን በሙሉ አንስቶአቸዋል፡፡ ጌታ በትንሳኤው አዲስ ነገርን ፈጠረ፡፡
አንድ ጌታ ተገለጠ፣ ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ አዲስ ሰውን ፈጠረ፣ አንድ ሃይማኖትን ሰጠ። በዚያ ሃይማኖት ውስጥ አንድ ጌታ ብቻ አለ፣ ከጌታ ወጥቶ ወደ ህዝቡ ህይወት የሚፈስ አንድ መንፈስም አለ፣ በህዝቡ መሃል በመንፈሱ የሚመላለስ ይህ ጌታ በስጋ የተገለጠው አምላክ ነው።
ሃይማኖት ሞቱና ትንሳኤው ከሌለበት የአለምን መንገድ በሌላ መንገድ ያስቀጠለ አዲስ የእምነት ስርአት ብቻ ነው የሚሆነው እንጂ የጌታ ፈቃድ ያለበት እምነት አይሆንም፡፡ አንዱና ብቸኛው ሀይማኖት ወንጌል የሚባል መመሪያ ሲኖረው ቤተክርስቲያን የምትባል መኖሪያ አለችው፡፡
‘’… በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም።’’ (ፊል. 1:9)
አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ያለ ሲሆን በአንድ መንፈስ የሚያቆምና ለክርስቶስ እንደሚገባ መኖር የሚያስችል እውቀትን መስጠት የሚችል ነው።
ሃይማኖትን ፍጹም አደረገው
ብቸኛውና ፍጹሙ ሀይማኖት ሲባል ፍጹም ጽድቅ፣ ፍጹም ፍርድ፣ ፍጹም ህይወት ያለበት ማለት ነው፡፡ ሃይማኖቱ በሰማይ የታወቀ እግዚአብሄር የተቀበለውና የሚሰራበት ነው፤ በዚህ መንገድም ካልገቡ በቀር ሰዎች ራሳቸው በፈጠሩት መንገድ ላይ ህይወት አይቀበሉም ማለት ነው። እግዚአብሄር እስራኤልን ከአህዛብ ለይቶ በሙሴ ህግ እየመራ በከነአን ምድር ያኖረው አንድ ፍጹም ሃይማኖት እስኪሰጠው ድረስ ነበር፤ ሆኖም ያን የእግዚአብሄር አሳብ ያላስተዋሉ ነገስታት ብቅ ባሉ ጊዜ ከስራቸው ጋር ቅጣትና መቅሰፍት ወደ ተስፋይቱ ምድር ስበዋል።
‘’በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።’’ (ሮሜ. 9:4-7)
በአለም ውስጥ አንድ መቶ አንድ ሺህ ሀይማኖቶች ቢኖሩ ከነዚያ ውስጥ በእግዚአብሄር የታወቀው የአይሁድ እምነት ብቻ ነበር፡፡ ፍጹሙ ሀይማኖት እንደተገለጠም ወደ አንድ መቶ ሺዎቹ ሀይማኖቶች ሳይመለከት አንዱን የአይሁድ እምነት ብቻ ወስዶ ፍጹም አደረገው፣ በርሱ የነበረውን ተስፋም ፈጸመው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ተባለ፦
‘’ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።’’ (ይሁ. 1:3-5)
ፍጹም ሀይማኖት የተገለጠው ጌታ ኢየሱስ በመገለጡ ነው፡፡ የአይሁድ ሀይማኖት ፍጹም ያልሆነበት ምክኒያት ተስፋ ብቻ ይዞ የቆየ ስለነበረ ነው፡፡ ተስፋው ሲሞላ ፍጹሙ ሀይማኖት ተገልጦአል፡፡ ፍጹም የሆነ ነገር ሁሉ ሙሉ ነውና ያለመናወጥ የሚጸና ነው፤ በዘመናት መሃል ለሚነሱ የተለያዩ እምነቶች መልስ አለው፤ የአለም ሃይማኖቶች ብዛት አያናውጡትም ምክኒያቱም የእግዚአብሄር መንፈስ የሚመራው ቃሉ የሚያበራበት ነውና፤ በዚህ ሃይማኖት በኩል እግዚአብሄር መንግስቱን ያሰፋል፣ የታመኑትንም መንግስቱን ያወርሳል። እግዚአብሄር ከዚህ ሃይማኖት ውጪ ወደ ሌሎች የእምነት ክፍሎች አይመለከትም፣ ምክኒያቱም መንገዱ ከዚህ ሃይማኖት ውጪ ስለማይገለጥ። ይህን ሃይማኖት የጀመረው ጌታ ኢየሱስ ራሱ ነው፤ ስለዚህ የትኛውም ሰዋዊ እምነት አይስተካከለውም፦
– በዚህ ሃይማኖት በኩል ወንጌል ይሰበካል
– በዚህ ሃይማኖት በኩል ብቻ ዳግም ልደት ይታወጃል
– በዚህ ሃይማኖት በኩል የሃጢያት ስርየት ይገኛል
– በዚህ ሃይማኖት በኩል መንፈስ ቅዱስ ይወርዳል
– በዚህ ሃይማኖት በኩል የሰማይ መንግስትን መውረስ ይችላል
ጌታ ኢየሱስ ወደ አለም የመጣው አንድ ሃይማኖት መሃል ሊገኝ እንጂ የአለም እምነቶችን እውቅና ሊሰጥ አልነበረም፤ ያም እምነት የሙሴ ህግን ተመርኩዞ በእስራኤላውያን ይታመን የነበረ የአይሁድ እምነት ነበር። ያን እምነትና ስርአት ጌታ ፍጹም ሊያደርግ ብዙ ትምህርቶች ያስተምር ነበር።
የበዙት አይሁድ ግን ትምህርቱን ተከትለው ወደሚመራቸው ሊደርሱ ያለመቻላቸው ለነርሱ የተነገረውን ታላቅ ተስፋ እንዳይቀበሉት አድርጎአል። ሳምራውያን በራሳቸው መንገድ ተስፋውን የጠበቁ ቢሆንም ጌታ ያን ሳያጸድቅላቸው ወደ ፍጹሙ እምነት እንዲመለሱ አሳስቦአል፤ ጌታ ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ጋር ያደረገው ንግግር ይህን ግልጥ አድርጎ ያሳያል፦
ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ፦ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ፦ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።(ዮሃ. 4:20-27)
በተለይ አይሁድ ሞላውን የእግዚአብሄር አደራና ስጦታ ከተቀበሉ በሁዋላ መሲህን እንዲጠባበቁ፣ እርሱ በመጣ ጊዜም ጸጋን ሰጥቶ እንዲያድናቸው፣ ልጅነታቸው እንዲረጋገጥም የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ሳለ ባለማመናቸው ጠንቅ ግን ከሃይማኖት ውጪ ሆኑ።
በአጠቃላይ ሲታይ ሀይማኖት የተገለጠ የእምነት መንገድ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እምነትን እውነተኛ ሃይማኖት ከሚያደርገው ገጽታ አንደኛው በእግዚአብሄር ላይ ፍጹም መደገፍ፣ መመካትና ስራውን በሙሉ ልብ የምንቀበልበትን ችሎታ ስለሚገልጥልን ነው። በልባችን ያመንነው ሁሉ እውነተኛ እምነት አይደለም፤ ምክኒያቱም አንድ እውነተኛ አምላክ ስላለ እርሱ በሚያሳየው መንገድ ብቻ እምነታችን ካልተገለጠ ዋስትናችን የተረጋገጠ ባለመሆኑ ነው። በእግዚአብሄር ላይ ያለን እምነት ያለማወላወል እርሱን ለመቀበል ልባችንን በእሺታ የሚሞላ ነው፤ ስናምን በእግዚአብሄር ፍጹም ተደግፈንና ስጋት ሳይገባን፣ በሙሉ ልብ ያደርግልኛል፣ ይሰራልኛል፣ ያስብልኛል ብለን እንድንጠብቅ ይረዳል፤ በሙሉ ትምክህትም እንድንጠራው ያደርጋል፣ እውነተኛ እምነት እግዚአብሄርን እንድንጠጋ በማድረግ እርሱን በመንፈስ እንድናገኘውም ያደርጋል። በእኛ በኩል ማድረግ የሚገባን ዋነኛ ተግባር እውነተኛውን እምነት አጥብቀን እንይዝ ዘንድ ነው፣ በእምነታችን ሊንጸባረቁ ከሚገባቸው ጥቂቶቹ ፦
– አምላካችን እግዚአብሄርን ከሁሉ እንደሚበልጥ ማመን
– እርሱ ከሁሉ እንደሚታደግ ማመን
– ከሁሉም የተለየ መሆኑን ማመን
– ሁሉ ከእርሱ በታች ሆነው እንደሚገዙለት ማመን
– እርሱ ብቻ አምላክ እንጂ ሌሎች አለን ቢሉ እንኳን ሃሰተኞች እንደሆኑ ማመንና
– በዙርያችን ያሉ የምናውቃቸው፣ የማናውቃቸውም ጭምር የእርሱ እጅ ስራ እንደሆኑ (ምንጫቸው እርሱ ብቻ) እንጂ ከእርሱ ውጪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ማመን ናቸው።
እውነተኛ እምነት እውነተኛ መንፈስ የሚመራው ነው፤ በአለማችን ውስጥ የማይታዩ ግን ችሎታ ያላቸው መናፍስት አእምሮን የማሳትና የማሳሳት ችሎታቸውን ተጠቅመው እግዚአብሄርን በአምላክነቱ ልክ እንዳናምነው ያስክዱናል፣ ያጭበረብሩናል ያልያም ያጨልሙብናል። ብናምን ግን የታመነው ጌታ ከሁሉ የጠብቀናል። አሜን።