ስልጣንና ባለስልጣን በምድር ስርአት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ የአስተዳደር፣ የስነ-ስርአትና የሰላም አብይ መሰረቶች ናቸው።ቃሉም በሮሜ.13:1-4 ላይ ሲናገር፦
“ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።“
ስልጣን የማድረግ መብት፣የትእዛዝ ጉልበትና የፈቃድ ሃይል ነው።ስልጣን የጉልበት ወይም የህግ ድጋፍ ውጤት ነው።ባለስልጣን ምንጊዜም በሃይሉ ወይም ህግ በሚሰጠው ይሁንታ በሌሎች ላይ የሚሰለጥንበትን እድል ያገኛል። ባለስልጣን የፈቀደውን ይፈጽማል፣ ማንኛውንም አጋጣሚ ለራሱ ጥቅም ሊያውለው ይችላል። የትኛውንም አይነት ስራ ከርሱ ስር ባሉ ሰዎችና ስፍራ ላይ መፈጸም ይችላል፣ ያለመከልከል ያን ያደርጋል።ስልጣን ያለው አካል በስልጣኑ ጉልበት ምንም ነገር በማንም ላይ ማድረግ መብት አለው። ስልጣን የሌላውን ይዞታ፣ መብት፣ ንብረት ካስፈለገም ህይወት የመንጠቅ ጉልበት አለው። ለምሳሌ ጨካኝ ስርአት ባለበት አገር የሚኖሩ መሪዎች ስልጣናቸውን ተመክተው ይገድላሉ፣ ያስራሉ፣ ይነጥቃሉ፣ ብዙ ጭከና ይፈጽማሉ። ለነርሱ ስልጣናቸው ከግለሰብ መብት በላይ ነው። ሰዎች መብታችን ነው ይገባናል ከሚሉት የራስ ነገር በላይ በነርሱ ላይ የሰለጠኑት እነዚያ ባለስልጣኖች ያሻቸውን ይጠይቁዋቸዋል፣ ይነጥቁዋቸዋልም።ሁልጊዜ የሰው ፈቃድና ስልጣን ሲገናኙ ብዙ በጎና ክፉ ነገሮች በሃገርና በወገን ላይ ይከሰታሉ።እንዲያም ሆኖ ሰብአዊ ስልጣን ሰው በሌላው ሰው ላይ የሚኖረው ስልጣን በመሆኑ ጊዜያዊና የሚሻር ይሆናል።
እግዚአብሄር ደግሞ ባለስልጣን አምላክ ነው።ስልጣኑም መለኮታዊ ነው። ስልጣን የአምላክነቱ ባህሪ ስለሆነ ማንም ስልጣን አይሰጠውም፣ አይሾመውም፣ ስልጣኑን ሊነጥቀውም አይችልም። የበላይ ባለስልጣን እራሱ በመሆኑ ባለስልጣን የተባሉ ምንም ቢኖሩ ከርሱ መለኮታዊ ስልጣን በታች ይሆናሉ።
ኤፌ1:20-23 “ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።“
በሰማይና በምደር ያሉ ስመ-ገናና የሆኑ አለቅነትና ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት ቢኖሩም ከፈጠራቸው አምላክ ሊበልጡ ስለማይችሉ ስማቸው ከርሱ ስም በታች፣ ሃይልና ስልጣናቸውም ለርሱ የተገዛ ሊሆን ግድ እንደሆነ ቃሉ ያሳያል።
ማር.1:23 “በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ።ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።“
ቆላ.2:9-10 “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።“
በሌላ በኩል የሰውና የእግዚአብሄር ስልጣን የተለያየ መሆኑ ግልጽና በሁሉም የተገለጠ ነው።ሰው ስልጣን ተቀባይ እግዚአብሄር ደግሞ ስልጣን ሰጪ ነው።እግዚአብሄር ሰው በስጋ ለባሽና በመናፍስት ላይ እስኪሰለጥን ድረስ ከፍ ያለ ስልጣንን ይሰጠዋል። የአለም መንግስታት በራሳቸው ብልሃትና ጉልበት ስልጣን የያዙ ይምሰላቸው እንጂ ስልጣን እንዲይዙ የሚያደርገው እግዚአብሄር ብቻ ነው። እግዚአብሔር የሚስጠው መንፈሳዊ ስልጣን ደግሞ ሰው በመንፈሳዊ አለም ላይ እንዲሰለጥን የሚያደርግ ነው።
እግዚአብሄር ሲፈጥር በስልጣን ነው፣ መለኮታዊ ስልጣኑን በመግለጥ ሁሉን ያደርጋል።ሲጠራ፣ ሲልክም፣ ሲያስነሳ ሲጥልም ስልጣኑን ተጠቅሞ ነው።እግዚአብሄር ሲናገር ድምጹ በስልጣን ይወጣል።ስለዚህ በቃሉ ስልጣን ፍጥረታት ከሌሉበት ወጡ። ካልነበሩበት ወደ መሆንና ወደ መገኘት መጡ። እግዚአብሄር ይሁን እያለ ሲናገር ቃሉ ተራ ንግግር ሆኖ የሚቀር አይደለም።በተናገረበት አላማ ልክ የማደረግ ጉልበት አለው፣ባለስልጣን ቃል ነውና።እንዲህ አለ፦
ኢሳ.55:10-11 “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።“
ህያው አምላክ እጅግ ከፍ ያለ ባለስልጣን ቢሆንም ከሰው በተለየ መንገድ ስልጣኑን ለፍጥረቱ ጥቅም ያውለዋል።በተለይ በተለይ ሰውን በጥፋቱ ከወረደበት የሞት አዘቅት ያወጣ ዘንድ ስልጣኑን ገልጦ ፍርዱን ሽሮአል። የሞት ህግ ብርቱ ቢሆንም እግዚአብሄር ውስጥ ያለው የስልጣን ሃይል የሞትን ጣር ይውጥ ዘንድ መንገድ አዘጋጀ።
ዕብ.1:1-3 “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤“
ሰውን በስልጣኑ ነጻ ያወጣ አምላክ በዚያ ሳያበቃ በመናፍስት ላይ መለኮታዊ ስልጣን ሰጠው።ስሙን አስታጥቆ በስሙ ውስጥ ያለው ስልጣን ወደ እርሱ እንዲተላለፍ ፈቀደለት። በዚህም አምኖ በስሙ የሚያወጣውን ቃል እንዳለው እንዲሆንለት አድርጎአል።
ዕብ.2:14-15 “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።“
የሰውን ልጅ አንገት አስደፍተው ያስፈራሩ የነበሩትን ሁለት ሃይላት ማለትም ሞትንና ሞት ላይ ስልጣን ያለውን ሰይጣን እግዚአብሄር በልጁ ሞት ከስልጣን ውጪ አደረጋቸው።ከእንግዲህ ወደ እግዚአብሄር የተጠጉ በሚገዛቸው ሰይጣን ላይ ባለስልጣን ይሆኑ ዘንድ በእምነት ወደ ፈጠራቸው የመጠጋት እድል ፈንታ አላቸው።ማን ነው በዘመኑ የዚህ እድል ተጠቃሚ?
የስልጣናችን ምስጢር
ቃሉ በሉቃ10:17-20 ሲያረጋግጥ “ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት።እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም።ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።“ ይላል።
በመናፍስቱ አለም ያሉ ጠላቶቻችንን የጣለና እነርሱን በእኛ ያስገዛ ጌታ ያን ያደረገው በሰጠን ስልጣን አማካይነት ነው።ያገኘነው ስልጣን ቢያንስ በሁለት መንገድ ይገለጣል፦
- በልጅነት ስልጣን
ዮሐ.1:9-13 “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።“
የልጅነት ስልጣን የወራሽነት መብት የሚያሰጥ በአባት ቤት ያለ የመጨረሻው ከፍተኛ ስልጣን ነው።የልጅነት ስልጣን ተዘግቶ የነበረውን የእግዚአብሄር መንግስት አስከፍቶአል። በመላእክት ሰይፍ ታጥሮ የነበረን የእግዚአብሄር መገኛ መንፈሳዊ ስፍራ በዚያ ስልጣን ክፍት ሊሆን ችሎአል።ሰው ዳግም ከእግዚአብሄር ይወለድ ዘንድ እግዚአብሄር ሲፈቅድ በመንግስቱ በልጅነት ስልጣን እንዲኖርና ልጅ ከአባቱ ሊያገኝ የሚገባውን መብት በመስጠት ነው።
ዮሐ.3:3-7 “ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።“
- በስሙ ስልጣን
ማር.16:15-18 “እንዲህም አላቸው፦ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ።“
የልጅነት ስልጣንና የስሙ ስልጣን በአንድነት የሰው ልጅ ከአጋንንት ጋር ላለው ጦርነት ድርብ የውጊያ ጉልበቶች ናቸው።የተለያዩ እምነቶች ግን እነዚህን ስልጣኖች እያጎደሉ፣ አንዱን በአንዱ እያጣፉ ወይም ስልጣኑን በሚያዳክም የእምነት መንገድ ሰውን እያሳቱ የእግዚአብሄር ስጦታን ያጠፋሉ።በምንም መልኩ ግን ልጅነት ሳይቀድም በስሙ ስልጣን ለማትረፍ መሞከር በጠላት እጅ የሚያስጥል አደጋ ይፈጥራል።(ሐስ.19:13-18)
ስልጣንን በአግባቡ መጠቀም፦
- ስልጣን ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ስልጣንን ከለጋሱ አምላክ እንደተቀበልነው በአገባብ መጠቀም ትኩረት የሚፈልግ ነገር ነው።
ሐዋ.26:15-17 “እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና።የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።“
ስልጣናችንን ስንጥል የሚፈጠር አደጋ አለ፦
- የተዋረደ ህይወት (አለማዊ ህይወት) ውስጥ እንዘፈቃለን።
- እግዚአብሄርን መውደድ እናቆማለን(ያለመታዘዝ ውስጥ እንገባለን)
- ባለስልጣን መሆን ብቻ ሳይሆን ከስልጣን ውጪ ሆኖ በአጋንንት እስራት ውስጥ ዳግም መውድቅም አለ።
ዋናው ነገር የተቀበልነውን አክብረን መኖር ምርጫችን ማድረግ ነው።ቀድሞ በገዛን መንፈሳዊ ጠላት ላይ ባለስልጣን ከሆንን፣ ለቅዱሳን መላእክት ብቻ ክፍት ሆኖ የቆየውን ሰማይ በልጅነት ስልጣን እንድንገባበት ከተፈቀደልንና እንደ ባለ ሃገር ከተቆጠርን ወደ ሁዋላ መመልከት መንሸራተትም ጭራሽ አያስፈልግም።ያም ቢሆን የጌታ እርዳታ ሲበዛልን የሚሳካ ነው።