ባለመቻል ማንከስ/ማነስ

የመጨረሻ ዘመን

ያለመቻል አቅም ማጣት፣ መጉደል፣ ማንከስ፣ ወደ ሁዋላ ማለት፣ ፍጥነት መቀነስ፣ ጥንቃቄ ያለማድረግ፣ በመሳሰለው ነገር ይገለጣል፡፡ አቅም ያጣንባቸው ጊዜያቶች በውስጣችን ያለውን አሳብ ወይም ራእይ እንዳንፈጽም ወደ ሁዋላ ይጎትቱናል፣ ወይም እቅዳችንን እንዳናከናውን ያደርጉናል፡፡ አቅማችን በራእያችን ልክ ወይም ከዚያም በላይ ካልሆነ ልንደርስበት የምንፈልገው ግብ ይርቃል፡፡ አንዳንዴ አቅም ማጣት በጥበብ ቢያዝ ችግሩ ሊታለፍ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም በውስጥ የማይኖር እምቅ አቅም በሌለበት በሚፈጠር ያልታሰበ ውጤት ከመስመር ውጪ ልንሆን ስለምንችል በዚያ ብቻ መመካት ውጤታማና ዘላቂ አያደርገንም፡፡
ያለመቻል የሚፈጥረው ሌላው ችግር ጉድለት/አቅመ-ቢስነት ነው፡፡ አቅም ስናጣ ከምንጠበቅበት ስፍራ አንገኝም፣ የታሰበውን ነገር አናደርግም፣ በጊዜያችን አንጠቀምም፣ ከዚያ ባለፈ በእኛ ላይ ያለውን የእግዚአብሄር ፈቃድ አንቀበልም፡፡ ተማሪ እንኩዋን በተመደበለት ሰአት ክፍል ገብቶ ትምህርቱን ባይከታተል አስተማሪው ለሰአቱ ያዘጋጀውን እውቀት ሳይቀበል እንደሚቀር ይታወቃል፡፡ በዚያ በዘገየባቸው ደቂቃዎች ከአስተማሪው መረዳት የነበረበትን እርዳታ አያገኝም፡፡ ስለዚህ ተማሪው በብዙ ይጎዳል፡፡ እግዚአብሄርስ በየወቅቱ ለእኛ የሚገባውን ሊያደርግ ሲመጣና እኛ በጊዜው ሳንጠብቀው ስንቀር ውጤቱ እንደምን ይጎዳን?
በሌላ በኩል ያለመቻል ያስነክሳል፡፡ ማንከስ ከአካላዊ ጉድለት የተነሳ ብቻ ሳይሆን ከስነልቦናዊና ከመንፈሳዊ ሁኔታ ያለመስተካከልም ይመጣል፡፡ ትክክለኛና ተገቢ አመለካከት ባለመያዝ የሚፈጠሩ የተዛቡ ስሜቶች፣ አመለካከቶችና አቁዋሞች በብዙ የጎዳሉ፡፡ ብቃት ቢኖረን በብዙ የምንጠቀምባቸው ሌላውንም ወገን መጥቀም የምንችልባቸው አካሄዶች በጎደሉ ጊዜ ብዙ የተዘበራረቁ ነገሮች በህይወት ውስጥ ይመጣሉ፡፡
በሌላ መልኩ ነገሮችን ማድረግ ወይም መቀበል ባልቻልንባቸው ጊዜያቶች ሊያንጹን የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮች ያመልጡናል፣ ከመልካም አጋጣሚ ልንዘገይም እንችላለን፡፡ ነገሩ እንደሚጠቅመን አውቅን እንኩዋን ውስጣችን በሚፈጠር የመንፈስ ጥንካሬ ማነስ ጥቅማችንን እንጥላለን፣ ቸል እንላለን፣ እናባክናለንም፡፡
መጉደል፣ ማነስና አቅም ማጣት ከመሳሰሉ ችግሮች እንላቀቅ ዘንድ ያለመቻላችንን ልብ ስንል ግን ወደቻዩ አምላክ መመልከትና መጠጋት እንመርጣለን፡፡
ፍጥነት መቀነስ መረጋጋት እንደሚያመጣ ሁሉ ያለትክክለኛ ስፍራ ያን ማደረግ መልካም አጋጣሚዎችን ያሳጣል፡፡ ስለዚህ ሁሉም በቦታው ስለሚያምር  መዘግየት/ፍጥነት ያዝ ማድረግ የሚገባንን ጊዜና አጋጣሚ ጠንቅቆ ማወቅ ወሳኝ ነው፣ ያለበለዚያ ያለቦታው መንቀርፈፍን ፈጥሮ መልካም ያልሆነ ውጤት እንዳያስከትል ያሰጋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ባለመቻላችን ምክኒያት ጥንቃቄ ያጣ አካሄድ ውስጥ እንገባለን፣ ጉድለቱም ያወለካክፈናል፡፡ ጥንቃቄ እንደሚጠብቅ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ ያለጥንቃቄ ላልተፈለገ ነገር መጋለጥ ይመጣል፤ ማጣት፣ መነጠቅ፣ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የሎጥን ህይወት እንደ ምሳሌ ማየት ይቻላል፡-
ዘፍ.19:15 ”ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፡- ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው፡- ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ። ሎጥም፤ አላቸው፡- ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤ እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?  እርሱም አለው። የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።”
እውቀት ግን ያተርፋል
​​​​​​​​ዳዊት በብዙ ነገር የተቀባና የተባረከ ሀያል ንጉስ ነበር፤ እንዲሁም ከዚህ ያለፈ አንድ ለየት ያለ እውቀት ነበረው (ንጉስ ሁሉን ማድረግ የሚችል ጉልበተኛና ጦረኛ ከሚል አመለካከት በጸዳ እምነት)፡፡ እርሱን በመዝ.40:17 ውስጥ ሲገልጸው፡-
”እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ ጌታ ግን ያስብልኛል፤ አንተ ረዳቴና መድኃኒቴ ነህ፤ አምላኬ ሆይ፥ አትዘግይ።” ይላል፡፡
ዳዊት በወጣበት የጦርነት ውሎ ድል በድል የሚያደርግ ንጉስ ቢሆንም ወደ አምላኩ በትህትና የሚመለከት ቁጡብ መሪ ነበር፤ እንዲሁም የሀገሩ ህዝብ በጣም የሚወደውና የሚያከብረው ጠላቶቹ ደግሞ የሚፈሩት ጀግና፣ ጥበበኛና እግዚአብሄርን የሚያገለግል ምንም ቢሆን እርሱ አቅም የሌለው ምስኪን አምላኩ ግን ብርቱ ረዳቱና መድሀኒቱ እንደሆነ የሚያምን ነበር፤ በድካሙም የሚረዳውና የሚያስብለት አምላኩ ስለሆነ ያን ከልቡ ተቀብሎ እርሱን ብቻ የሚጠባበቀው አስተዋይ ንጉስም ነበር፡፡
እኛም ከዚህ መረዳት ያለብን ባልቻልንባቸው ነገሮች ላይ መፍትሄ ለማግኘት ከመሞከራችን በፊት ያልቻልንባቸውን ነገሮች ለይተን ማወቅ፣ ያለመቻላችንንም መቀበል፣ ሁሉን ለሚችለውም ያን መስጠት/መተው አለብን፡፡ ያን ማወቅ ምናልባት ከብዙ ጥፋት ያተርፈን ይሆናል፡፡ጥቅምም አለው፣ ለምሳሌ፡-

  • ያለመቻላችንን ስናውቅ ንሰሃ እንገባለን፡፡

ያለመቻላችንን ያለማወቅ አመጽ ላይሆን ይችላል፣ ባለመቻላችን ውስጥ ሆነን በእችላለሁ ባይነት የምንሰራው ጥፋት እንጂ፡፡ ስለዚህ ሰዎች መወቀስ ካለባቸው አቅም በማጣታቸውና ባለማስተዋላቸው ሳይሆን ሳይችሉ እንደሚችሉ አድርገው በሚሄዱበት አካሄዳቸው መሆን አለበት፡፡
ያለመቻል በተለያየ ምክኒያት ይመጣል፡-
ስንፍና፡- ማድረግ ስንችል ስንሰላችና ሳንፈልግ ስንቀር ወይም ጉዳዩን ስናቃልል የሚፈጠርብን ያለመቻል/አቅም ማጣት ጥፋት ያመጣል፡፡
​​​​​​​ምሳ.15:19-21 ”የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፤ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት።ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል።ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል።”
ጉድለት፡- ሊኖረን የሚገባን ክህሎት ሳይኖረን ቀርቶ የሚፈጠር ጉደለት የብቃት ማነስ ይፈጥራል፡፡ ይሄን ስናስተውል ለእውቀትና ክህሎትን ለማዳበር መማር፣ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሄር የጎደለንን የሚያውቅ ከልብ በትጋት የሚያስፈልገንን ብንለምነው ያን የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው፡፡ ብቻ እንመነው፡-
”በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ።”(ዘጸ.31:3-5)
ሁሉም በሚሰማራበት መስክ ውጤታማ እንዲሆን ብቃትን ቢለምን ያለስስት ከአምላኩ ዘንድ ማግኘት እንደሚችል ቃሉ ያስረዳል (ማቴ.7፡7)፡፡
አቅም ማነስ፡- ጉልበት ማነስ፣ በገንዘብም ማነስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ችግሩን ማስተዋል የሚችልና ጉልበት የሚሆነውን አምላክ የሚሻ ከገባበት ማጥ ይወጣል፡፡
ማቴ.26:40 ”ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፡- እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ​ልትተጉ አልቻላችሁምን?”
መዝ.121:1-8 ”ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።”
1ዜና.29:12 ”ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።”
ቸልተኝነት፡- የአንድን ነገር ውጤት ቸል በማለት ያልታሰበና ከቁጥጥር የወጣ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ ምን ይሆናል ብለን ከእግዚአብሄር ትእዛዝ ፈቀቅ ስንል ብዙ መዘዞች ተራ በተራ ይከታተሉብናል፡፡
2ዜና.29:6-11 ”አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፥ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም።ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው።እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ።አሁንም የቍጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ።ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።”

  • እንዴት አቅም መፍጠር እንደሚገባን እናስተውላለን፡፡

ኢዮብ ወደ እግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ ሊኖረን የሚገባውን ነገር ይመክራል፡፡ እግዚአብሄር አባት ቢሆንም አምላክም ነውና በፍርሀት በርሱ ዘንድ መሆን ሞገሱን ያስገኛል፡-
በእግዚአብሄር ሞገስ ለመጎብኘት ከእርሱ ጋር መስማማት፣ ህጉን መቀበል፣ ቃሉን በልብ ማኖር፣ ወደ እርሱ መመለስ፣ በፊቱ መዋረድ፣ ኃጢአትን ከህይወት ማራቅ፣ የምንመካበትን ጥለን እርሱን ትምክህት ማድረግ መልካም ነው፣ ይህን በመከተልም አቅም ይገኛል፡፡
ኢዮ.22:21-27 ”አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ።  ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ።”

  • ወደ ሚችለው እንሄዳለን፡፡

ኢዮ.8:5-6 ”እግዚአብሔርን ብትገሠግሥ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትለምን፥ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት አሁን ስለ አንተ ይነቃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያከናውንልሃል።”
ኢዮ.42:1-2 ”ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፡- ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።”
ኢዮብ የእግዚአብሄርን ሁሉን ቻይነት ሲያስተውል የነበረው በህይወቱ የገጠመውን ከፍተኛ ችግርና ፈተና ተሸክሞ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሃያል አምላክ ስለሆነ እርሱ ያቃተውን አሸንፎ ከተያዘበት ችግርና ፈተና መውጫ ሊያዘጋጅለት የሚችለው ይህ አምላክ ብቻ እንደሆነ አስተውሎ ነበር፡፡ እግዚአብሄርም እንዳመነው አደረገለት፡፡ እንዲሁም እግዚአብሄር በሁኔታዎችም ሆነ በማናቸውም ፍጥረታዊ ሀይሎች ላይ ኤልሻዳይ መሆኑን በማስተዋል የኢዮብ መፍትሄው ፈጥኖ መጥቶለታል፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ሆኖ ከሰው የራቀ ሳይሆን ለታመኑበት መጠጊያና ለልመናቸው ምላሽ የሚሰጥ አምላክ መሆኑን አሳይቶታል፡፡
መቻልን ለተገቢው ነገር በማድረግ መባረክ
አቅምን ወይም መቻልን ተመክቶ በሌላው ላይ መነሳሳት ከትእቢት ሌላ ምንም ሊባል አይቻልም፡፡ የመቻል አቅምን ለበጎ ማድረግ ግን በሁሉም ዘንድ ክብር ነው፡፡ ሳኦል ንጉስ ስለሆነ ብቻ አንድ ታናሽ ብላቴናን በክፋት በማሳደድ ስራ ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግን እችላለሁ እያለ ይመካበት የነበረው ንግስናና ጉልበቱ ክደውት እዚያ ብላቴና እጅ ላይ ወድቆአል፡፡ ብላቴናው ግን በችሎታው ሳይሆን በእግዚአብሄር የሚመካ ሆነና በእርሱ መንገድ ሳይበቀለው በምህረት ለቀቀው፡፡ ለንጉሱ ግን አካሄዱ የሚያሳፍር ስራ ሆነበት  (1ሳሙ.26:6-25)፡፡