ባለጸጋ አምላክ በስጋ ሲገለጥ ቃሉ እንዳለው፦
‘’ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። … እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።’’ ይላል (ዮሃ.1:14፣16,17)።
ባለጸጋ አምላክ ከየትኛውም ፍጥረት መጀመሪያ አስቀድሞ፣ ማንም ሳይኖር ቃል የሆነ አምላክ ብቻ ነበረ፣ ቃል የሆነው ይህ አምላክ ድምጹን እያሰማ የሚናገረውና የሚፈጥርበት ቃልም ነበረው፤ በቃሉ ሁሉን የፈጠረ ይህ አምላክም እግዚአብሄር ብቻ ነበረ። በዘመኑ ፍጻሜም እግዚአብሄር በውስጡ የነበረን ፈጣሪ ቃል ከልቡ አውጥቶ፣ በሴት ማህጸን ውስጥ ስጋ አድርጎ፣ በርሷ ማህጸን በመንፈስ ቅዱስ ተጸልሎ እንዲያድር በማድረግም በሰብአዊ የልደት ሂደት ይወለድ ዘንድ የእርሱ ፈቃድ በመሆኑ በርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሶ (ከአዳማዊ ስጋ ተለይቶ) ግን እንደሰው ልማድ የተወለደ ነው። ስለዚህ፦
‘’ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። … እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ። ደቀ መዛሙርቱ፦ እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት።’’ (ዮሃ. 8:42-43፣ 16:27-30)
ክርስቶስ ኢየሱስ ከአብ ተወልዶ እውነትና ጸጋን በተሞላ ማንነት በተለይ ወገኖቹ በነበሩት በአይሁድ መሃል ተመላለሰ። ያኔ ጌታ ኢየሱስ በአይሁድ መሃል ሳለ ጸጋን ተሞልቶ ብቻ በምድራቸው ላይ አልተመላለሰም፡፡ በአካሄዱ ፍጹም የሆነውን የመለኮት ባህሪ በመግለጥ በጸጋ የሚኖር ህይወት ምን እንደሚመስልም ለመላው ህዝብ አሳይቶአል፡፡ የተትረፈረፈ ጸጋ ያለው ጌታ በምሳሌያዊ ህይወቱ መኖር የሚገባንን የክብር ህይወት ሊያሳየን በሰዋዊ ኑሮ ተመላልሶአል፣ ይህም በአነጋገሩና በድርጊቱ ማድረግ ያለብንን በምሳሌ አሳይቶአል፤ ማሳየት ብቻ ሳይሆን እርሱን እንከተል ዘንድ ሁሌ ይጋብዛል። ሲናገርም፦
‘’እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።’’ ብሎአል። (ማቴ. 11:28-30)
ጌታ ኢየሱስ ስራው መለኮታዊ ሲሆን ምልልሱ (ኑሮው) ከአይሁድ ያልተለየ፣ በዚያ ውስጥ ግን መንፈሳዊ ህይወትን የሚገልጥ ነበር፡፡ ይህ ምንን ያሳያል? ሰዎች እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በምድር ላይ ስንኖር መንፈሳዊ ህይወታችን ምን መምሰል እንዳለበትና ያንን የከበረ ህይወት የምንሻ ከሆንን ከእግዚአብሄር እንደምንቀብለው ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ክርስቶስ ኢየሱስ ከእኛ ከሰዎች የተለየ አምላክ እንደሆነ እናስተውል ዘንድ የምህረቱን ነገር ሁሉ ገልጦአል፤ የእግዚአብሄርን ቸር ስጦታ ተመልክተን በትህትና እንድንቀበል በተመላለሰባቸው ዘመናት ታምራት ሰርቶና አስተምሮ አሳይቶአል፡፡ ይህን በተመለከተ ቃሉ ስለርሱ ይናገራል፦
‘’በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤ ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።’’ (1ቆሮ.1:4-9)
የእግዚአብሄር ጸጋ ወደ ሰዎች ሲመጣ ስራው ከአዲስ ልደት ይጀምራል፤ የእግዚአብሄር ልጅነት በስሙ በማመናችን የተገኘ መሆኑ በቃሉ ተመልክቶአል፤ ይህ የእርሱ ቸር ስጦታ እንጂ ልጅ ለመሆን የሚያበቃ ሰዋዊ ምንነት ስላለን አይደለም። እግዚአብሄር ጸጋውን እለት እለት እየጨመረልን ስለሄደ በዚህ ክፉ አለም ሳንጠፋ ጸንተን እንድንቆም ረድቶናል። የጸጋው አሰራር በአስተሳሰባችን ላይ ይሰራል፣ በእምነታችን፣ በውስኔያችንና በድርጊታችን ላይ የቀናና የተስተካከለ ውጤት እንድናመጣ በህይወታችን ተገልጦም ያግዘናል። ቃሉም ዋስትና ሲሰጥ፦ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ የተመሰረተ እምነት የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳመጣልን፣ ሃዋርያትም ለክርስቶስ የመሰከሩት በጸጋው በደቀመዛሙርት ህይወት እንደ ጸና የሚታይ መሆኑን ነው። ደቀመዛሙርት የሆንን በሙሉ በመንፈሳዊ ህይወትና በስጋዊ ኑሮ ውስጥ ጭምር በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በተሰጠን በጌታ በኢየሱስ ጸጋ ባለ ጠጎች እንድንሆን እንዳስቻለን ሃዋርያው አስረድቶአል።
በእግዚአብሄር አሰራር ለሰው ልጅ በአጠቃላይ መዳን ተሰጥቶአል፣ ያን በአለም ሁሉ የታወጀ ደህንነት ያመጣው የእግዚአብሔር ጸጋ የአምላካችን ክብር እስኪገለጥ እየጠበቅን እንዴት መኖር እንዳለብን ያሳያል፣ እንዲሁም በህይወታችን ውስጥ ገብቶ እያስተማረ ምሪት ይሰጣል። የእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ የመቤዠት ሥራ በተግባር በመገለጡ አሰራሩ ለአለም መዳንን ሰጥቶአል። የተገለጠው የእግዚአብሄር ክብር ግን በሥፋቱና በይዘቱ በእስራኤል ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ ጌታ ኢየሱስ እውነትና ጸጋ የተሞላው ለአይሁድ ብቻ በረከት ሊሆን ሳይሆን ለመላው አለም ጭምር የታወጀ ተስፋ ነው። ምንም እንኳን በሰው ደካማ እምነት ምክኒያት አሰራሩ ቢገደብም አሁንም ሰዎች በስራው ላይ ታምነው በእርሱ ላይ ቢደገፉ የበረከቱ ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ።
ጌታ ኢየሱስ ያሳየንና የመራን መንገድ ላይ ከገባን ከዚያ በጸጋ የሚደገፍ የተትረፈረፈ ህይወት መጎናጸፍ እንችላለን፤ ፈለጉ በርሱ ያለውን ጸጋ እለት በእለት እንድንፈልግ በማስቻል በህይወታችን መንፈሳዊነት የሚገለጥበትና በዚያ ምክኒያት ስለ እውነት መኖር የሚያመጣው ትርጉም የሚታይበት ነው፡፡ ያ አይነት ህይወት ምን እንደሚመስል ጌታ ከማሰየቱም በላይ ከእርሱ እንድንማርም ነግሮናል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ጸጋ የምንኖረው ህይወት በጌታ ተጀምሮ በሃዋርያት አስተምህሮ ውስጥ በመገለጥ የቀጠለ ስለሆነ እኛም በዘመናችን ያን የከበረ ህይወት እንድንኖር በቃሉ ላይ መደገፍ ይገባል፣ የቃሉን መንፈስም ለህይወታችን መቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታ ወደ እርሱ ከጠራን በኋላ ፍሬያማ ህይወት እንኖር ዘንድ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምራል፣ ይህም የጸጋው ሃይል እንዲሰራ መንፈሱን እያበዛልን በአእምሮና በመንፈስ የተዘጋጀን እንድንሆን በማስቻል ነው፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወት በእኛ ማንነት ላይ የሚገለጠው በስጋዊ ባህሪያችን ስንመላለስ አይደለም፣ ስጋዊ ህይወት የእግዚአብሄርን ክብር ይገድባልና። ነገር ግን ጸጋው በመንፈስ ቅዱስ ለተያዘ ህይወት ስለሚወርድ ስጋዊ መሻታችን ፈጽሞ እንደሌለ እስከሚሰማን በእግዚአብሄር ቃል ፍቅር ተጠምደንና ጌታን ለማስደሰት ብቻ ወስነን እንድንኖር ያስችላል፡፡
የጌታ ኢየሱስ ህይወት ልዩና መለኮታዊ መገለጥ ያለው እንደነበር በቃሉ ተምረናል፡፡ ምስሉ አዳምን መስሎ ተገለጠ እንጂ ባህሪው መለኮታዊ ነው፤ ይህ በመሆኑ ዛሬ በእኛ ህይወት እርሱ ሲገለጥ ራሱ በጸጋው በህይወታችን ውስጥ እየሰራ እርሱ የኖረውንና በምድር ላይ የገለጠውን ህይወት እንድንኖር ያበቃናል፡፡
‘’እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።’’ (2ቆሮ.3:3-6)
ብቃታችን ከእግዚአብሄር በተሰጠን ጸጋ ምክኒያት እንጂ የጽድቅን ህይወት ለመኖር የሚያበቃ በጎ ነገርስ በውስጣችን ስላለ አይደለም፤ ነገር ግን ጌታ በመንፈሱ በእኛ በማደር በሚሰጠን ጸጋ በኩል እርሱ ኖሮት የሄደውን ህይወት ሊያኖረን በእኛ ውስጥ ይሰራል፡፡ ያኔ በስጋ እንደተገለጠ ዛሬ በህይወታችን ውስጥ በመንፈሱ ይገለጣል፤ ያኔ ወደ እኔ ኑ እንዳለ ዛሬ ወደ እኛ መጥቶ በእኛ ይኖራል፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወትም እንዲህ በእኛ መታየት ይጀምራል፡፡
‘’… እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።’’ (2ቆሮ. 9:7-15)
አለም በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶ ያየችው ጌታ ላይ ተገልጦ ይሰራ በነበረው መለኮታዊ ሀይል ምክኒያት ነበር፡፡ ዛሬም በጸጋ ላይ ጸጋ ለመቀዳጀት ያ የኢየሱስ መንፈስ (የጸጋ መንፈስ) በእኛ ህይወት መገለጥ አለበት፡፡ እውነተኛ ለመሆን የእውነት መንፈስ እንዲወርድና የሚረዳን ያው የጸጋ መንፈስ የግድ እንዲደግፈን ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ መንፈሳዊነት በአሸናፊነት ካልቆመና ዘልቆ በህይወታችን ካልቀጠለ ህይወት ስጋዊ፣ ድግግሞሽና አሰልቺ ይሆናል፡፡ ክርስትናን የጀመሩ ብዙዎች ታክተው መንገድ ላይ የቀሩት አንዳንዶችም ለመንፈሳዊነት አዲስ ብልሃት ያወጡት የጸጋውን መንፈስ ተቀብለው በርሱ መኖር ስላልቻሉ ነው፡፡ ነገር ግን እውነተኛ አማኞች እለት እለት ጸጋውን ብንጠማና ብንራብ፣ እግዚአብሄር እስኪመልስ በትእግስትና በእምነት ብንጠብቅ በጸጋ የተጠበቀ ህይወት ልንኖር እንችላለን፡፡ በጸሎት የታገሰ ህይወት ፍሬውን ይቀበላል፤ ከዚህ መለስ የምንሄደው መንገድ ዘላቂ ያልሆነና ሰውኛ ብቻ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ እድገት በሳምንት እድሜ ውስጥ እንዳልመጣ ሁሉ የጸጋ ስራ በህይወታችን የሚገለጠው ሊቀበል በታገሰ አጠባበቅ ውስጥ እምነታችንን ስናኖር ነው፡፡ የማያምን ከጌታ ዘንድ አንዳች ነገር ሊቀበል እንዳይችል መጽሀፍ አስቀድሞ አስጠንቅቆናል፡፡
ለመቀበል እንትጋ፤ ተግተን በመጠበቃችን የእግዚአብሄር መንፈስ በህይወታችን ከገባ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጸጋ በህይወታችን ውስጥ መሰረቱን ጥሎ በፍሬያማ አሰራሩ እየተስፋፋ ይሄዳል፤ እንደሌላ ሰው ያደርገናል፣ ለመልካም ይለውጠናል፣ በእግዚአብሄር ፊት ያለነቀፋ እስክንመላለስ ያሳድገናል፡፡ ለእኛ ይህ የጸጋ መምጣት፣ ማደግና መብዛት ያመጣው ነው፡፡ ነገሩ የጸጋ አምላክ እርዳታና በርሱ ላይ ያለን የእምነታችን፣ የመሰጠታችንና የመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግ ውጤት ነው፣ በቃሉ ላይ ያለን እምነትም ውጤት ነው፣ እንዲሁም የጌታ ፍቅር ሲገዛን ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በጸጋ ላይ ጸጋ ሲመጣ የእግዚአብሄር ስራ ከአንድ ወደ ሁለት ሲል ወደ ሶስት መቀጠሉን ያሳያል፡፡
‘’እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል’’ ይላልና።