በዘመን መሀከል እግዚአብሄር

የመጨረሻ ዘመን

የባቢሎን ምድር በገነነችበት ዘመን ምድሪቱን ያሳወቁትና ዝናዋን ከፍ ያደርጉት ነገስታቶችዋ ብቻ አልነበሩም፡፡ምድሪቱዋ የመናፍስት መናሀሪያ እንደመሆንዋ በአማልክቶቹዋ ብዛትም የታወቀች ነበረች፡፡የመንግስታቶችዋ ዝና፣ ስመጥር ስራዎችና ወረራዎች እንዲሁም ጠቢባኖችዋ በዘመኑ ከፍ ያሉ ነበሩ፡፡በነዚያ ዘመናት መካከል ግን የእስራኤል አምላክና የባቢሎን አማልክት የሚወዳደሩበት አውድና አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡በአጋጣሚው መሀል ህያው አምላክ የመረጣቸው ህዝቦች ከአህዛብ መሃል ተገኙ፤ የአይሁድ በባቢሎን መገኘት ግን የእንግድነት ሳይሆን ይምርኮና የዝቅታ እንዲያውም የባርነት ነበር፡፡
ኤር.44:2 ”የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም። ይህም የሆነው ያስቈጡኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት፥ ለማያውቁአቸውም ለሌሎች አማልክት ያጥኑ ዘንድ ያመልኩአቸውም ዘንድ ስለሄዱ ነው።”
እስራኤላውያን አምላካቸውን በመተዋቸው ለአህዛብ ነገስታትና አማልክት ተላልፈውና በነርሱም ተዋርደው ነበር፡፡ስራውን የማይረሳ አምላክ ግን መታሰቢያውን በባቢሎን ምድር ማንሳት ፈለገ፡፡ስለዚህ በዚያ በረከሰ የባእድ ምድር የራሱን ማንነት ሲገልጥ በህልም በኩል ነበር የመጣው፡፡በናቡከናጾር ዘመን እግዚአብሄር ሲገለጥ በባቢሎን ምድር በንጉሱ ዙርያ የተኮለኮሉ የህልም ተርጉዋሚዎች፣ አስማተኞች፣ መተተኞችና ከለዳውያን ነበሩ፡፡እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ክፉ መናፍስት አሰራር የተጠመዱና የሚመሩ ከክፋት አጋንንት ጋር ቁርኝት ያላቸው ነበሩ፡፡ክፉ መናፍስት በሚገልጡት የተለያየ አሰራር ንጉሱንና መንግስቱን በማስገረም ስለተቆጣጠሩ ንጉሱ የሾመውን የሰማይ አምላክ እስካያስተውል ድረስ ተወርሶ ነበር፡፡መናፍስት ሰዎች ልባቸውን ከህያው አምላክ አንስተው ወደማይናገሩ ጣኦታት እንዲመለከቱ የተለየየ ማደናገርያን፣ማዘናጊያን፣ማስፈራርያንና ታምራትን የጠቀማሉ፡፡መናፍስት ጠሪዎች በህዝቡ መሀል ጠቢባን ተብለው እስኪቆጠሩ ድረስ አጋንንት ይረዱአቸዋል፡፡
ዳን.2:2-13 ”ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።ንጉሡም፡- ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኮአል አላቸው።፤ ከለዳውያኑም ንጉሡን በሶርያ ቋንቋ፡- ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ ለባሪያዎችህ ሕልምህን ንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን ብለው ተናገሩት።ንጉሡም መለሰ ከለዳውያኑንም፡- ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፤ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትቈረጣላችሁ ቤቶቻችሁም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ።ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብታሳዩ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፤ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን አሳዩኝ አላቸው።”
በወቅቱ በመላው አለም ላይ ናቡከደናጾርን አስነስቶ የአለምን ህዝብ በእጁ እየተቆጣጠረ በነበረበት ጊዜ ባርያው ናቡከደናጾር ያስነሳውንና ያነገሰውን ፈጣሪ ፈጽሞ አላወቀምና እግዚአብሄር አንድ ስራ ሊሰራ በባቢሎን መካከል ሲንቀሳቀስ እናያለን፡፡ስራው በህልም ይጀምራል፡፡ህልሙም ለንጉሱ ታይቶ መጥፋቱ ቀጥሎ ሊሰራ ላለው ስራ መንገዱ ነበር፡፡ ንጉሱ ግን ከህልሙ የተነሳ ተጨነቀ፡፡ይህ የእግዚአብር አሰራር ነበር፡፡በዚህ አሰራር ውስጥ እግዚአብሄር ሁለት መልእክት ላከ፡-የመጀመሪያው የህልሙ ምንጭ እርሱ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛው ህልሙን አጋንንትና ጠቢባኑ ሊያውቁት እንደማይችሉ የሚያሳይ ነበር፡፡ ስለዚህ፡-
”… ከለዳውያኑም በንጉሡ ፊት መልሰው፡- የንጉሡን ነገር ያሳይ ዘንድ የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም፤ ከነገሥታትም ታላቅና ኃይለኛ የሆነ እንደዚህ ያለ ነገር የሕልም ተርጓሚንና አስማተኛን ከለዳዊንም አልጠየቀም።” ሲሉ መሰከሩ፡፡በመቀጠል፡-
”.. ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፤ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ።”
የአብረሃም አምላክ በብሉይ ኪዳን ራሱን ለህዝቡ ለእስራኤል አስታውቆ ዙፋኑን በህዝቡ መሃል ቢዘረጋም እሱ የአህዛብም አምላክ ነውና በየዘመናቱ ምስክሩን ሊገልጥ ይሻል፡፡በባቢሎን እግዚአብሄር ከናቡከደነጾር ህልም ጋር የሚያስጨንቅ መንፈስ ልኮ ነበር፡፡በዚያ ሳቢያ ፍቺውንና የህልሙን ባለቤት እንዲፈልግ ለንጉሱ መልእክት ሆነው፡፡ በሌላ በኩል ለህልም ፈቺዎች ህልሙን ሰውሮ አምልኮና አገልግሎታቸውን ተፈታተነው፡፡ያም ብቻ አልነበረም፣ አጋንንቶች የህያው አምላክ ህልምን ሊደርሱበት እንደተሳናቸው ተገለጠ፡፡እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው፣ ከእርሱ በቀር ማንም የለም፡፡በሰማይ ድምጽ ቢያሰማ ያለ እርሱ ማን ነው? በምድር ቢናገርስ ከርሱ ሌላ እኔ ነኝ የሚል የቱ ነው?
ዘዳ.32:37 ”እርሱም ይላል፡- አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ። አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እሰመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።”
እዩ! የሚለው የጥሪ ድምጽ ለነናቡከደናጾር ብቻ ሳይሆን በዚህ በመጨረሻው ዘመን በተለይ በሀሰት መንፈስ ለሚያገለግሉ መምህራንም ጭምር ነው፡፡አንድ ቀን ህልማቸውንም መንፈሳቸውንም የሚያስር ጌታ መገለጡ አይቀርምና፡፡ያኔ የሆነው ግን እንዲህ ነበር፡-
”የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ።ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፡- ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፥ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፥ አንተ የአባቶቼ አምላክ ሆይ፥ የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ።….. ንጉሡም መለሰ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን፡- ያየሁትን ሕልምና ፍቺውን ታስታውቀኝ ዘንድ ትችላለህን? አለው።ዳንኤልም በንጉሡ ፊት መልሶ እንዲህ አለ፡- ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፤ ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፥ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል። በአልጋህ ላይ የሆነው ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው። አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል… ።” (ዳን.2:19-29)
በዘመን መሀከል የሚገለጠው እግዚአብሄር የሰጠውን እርሱን የማወቂያ መንገድ ንጉሱ ከውስጥ ከፈቃዱ ቢቀበለው ኖሮ በመጣለት የእግዚአብሄር መገለጥ ታላቅ መዳን በሆነለት ነበር፡፡ናቡከደነጾር በእግዚአብሄር ፊት በወቅቱ ምስጋና የነበረው ቢሆንም ከተደረገለት ቸርነት ተነስቶ ያመሰገነ እንጂ መገለጡ የፈጠረለት ደስታ ያወጣው አልነበረም፡፡
እውነተኛ አምላክ የሰዎችን እውነተኛ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ናቡከደናጾር ያስጨነቀው ህልም በተፈታለት ወቅት ምን አለ?፡-
”የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ።ንጉሡም ዳንኤልን፡- ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው።ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደርገው፥ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፥ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ ላይ ሾመው፥ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው።” (ዳን.2:46-48)
ሰዎች ለተሸነፉለት ነገር እጅ መስጠታቸው ወይም መንበርከካቸው አይቀርም፡፡የእስራኤል አምላክ ግን ከዚያ ባለፈ በእርሱ የሚያምኑ በእውነትና በመንፈስ እንዲያምኑት እንጂ በማየት እንዳይሆን አጥብቆ የሻል፡፡ናቡከደነጾርም ”በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው” ብሎ ነበር፣ማለቱ ብቻ ግን በቂ አልነበረም፡፡የእስራኤል አምላክ በእውነት አምላክ እሱ ብቻ ነው የሚል ከሆነ ለምን ለኔም አምላክ ይሆናል አላለም? የነገስታት ንጉስ እሱ ነው ካለ የኔ የንጉስ ናቡከደነጾርም የበላይ ንጉስ እሱ ነው ብሎ በራሱ ላይ ሊያነግሰው ለምን አልፈቀደም? የመልሱ ምስጢር ግን ያለው እውነተኛነትና መንፈሳዊነት ላይ በመሆኑ ነው፡፡በዳንኤል ፊት ያን ታላላቅ ቃል የተናገረ ንጉስ ብዙም ሳይዘገይ ያቆመው ታላቅ ጣኦት ፊት ተገኝቶአል፣እንዲያውም የእግዚአብሄር ልጆች እንዲሰግዱ ተፈታትኖአቸዋል፡-
ዳን.3:1-7 ”ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ።በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል። ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ለህዝቡ ሁሉ ሲናገር እናያለን፡፡
”… ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ።”
ናቡከደናጾር ዛሬ ላይ ለሰራው ጣኦት አምልኮን ከሰው ሲፈልግ ትላንትና ያስጨነቀውን እንቆቅልሽ የፈታለትን እዲያውም ከእጅ መንሻ ጋር ፊቱ የሰገደለትን አምላክ ለምን አላፈረም ነበር?
በዚህ መጨረሻ ዘመን ውስጥ እንደናቡከደናጾር ዘመን የራሳቸው ፈቃድ የበለጠባቸው ሰዎች የበዙ ናቸው፡፡በአንደበታቸው ብቻ እግዚአብሄርን የሚጠሩ በልባቸው ግን የራሳቸውን አምላክ የፈጠሩ እነዚህ ሰዎች በሀሰት ትንቢት ህልማቸውን የሚያስተጋቡ ናቸው፣በሰሩት መሰዊያ አለምን እያሰገዱም ነው፡፡ በመሀከል ጥቂት የሆኑ ግን እውነትን የሚናገሩ አስተማሪዎች ደግሞ በእስራኤል አምላክ ተማምነው በወንጌል ይጣራሉ፡፡የሀሰት መንፈስ ብዙ ህልም ፣ብዙ ራእይ ለአለም፣ለአህዛብና ለመንግስታት እያወጣ ይገኛል፡፡እያንዳንዱም በሰማውና ባየው ትንግርት ተገርሞ ተማረኮአል፡፡
አስጨናቂ ክንዋኔዎች፣ ድንቅና ታምራት በመናፍስት ጠሪዎች ቤት በየእለቱ ይገለጣል፡፡ይህ ወደፊትም ከመገለጥ አያቁዋርጥም፤ የእስራኤል አምላክ ወስኖ እስኪያቆመው ድረስ፡፡በዚያው ልክ መንፈሳቸውን በርሱ መንፈስ ካስገዙና ቃሉን ካከበሩት በቀር ለሀሰት መንፈስ የተገዙት ወደ ዘላለሙ ሀያል መንበር ለፍርድ የሚጠሩባት አስፈሪ እለት ከቀን ወደ ቀን እየቀረበ ይገኛል፡፡ያ እውን እስኪሆን ሁሉም በተያዘበት መንፈስ መገስገሱ አልቀረም፡፡እርሱም በራእ.22፣10-11 እንዳለው ነው፡-
”ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።”
የናቡከደነጾርን ልብ ከሰው ልብ ወደ አውሬ ልብ የለወጠ አምላክ ናቡከደነጾር ወደማስተዋሉ ሲመለስ ዳግም እግዚአብሄርን እንዲያመሰግን ያስቻለው ነው፤ በእኛም ዘመን በእግዚአብሄር ማንነት ላይ እየተደራደሩ ያሉትን ሀሰተኞች ሊያርቅና ወደ ትክክለኛው አምልኮ በንሰሀ ሊመልሳቸው እርሱ ስለሚስችል በምህረት ወደ እነርሱ አሁን ይመልከት፡፡ አስቀድሞ በቃሉ ያለው፡-
”እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”(ኢሳ.1:19-10)