በኮሬብ ተራራ ቁም (2/2)

ቤተክርስቲያን

•ኮሬብ ተራራ — የእግዚአብሄር ቅባት መቀበያ ተራራ
ከቀርሜሎስ ተራራ የወረደው ኤልያስ ምን ገጠመው? በዚያ ተራራ እግዚአብሄርን አምልኮ ነበር፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ ታምራት ሲሆንም ተመልክቶአል፤ የህዝቡ ልብ ወደ አምላኩ ሲመለስና የአጋንንት ሰራዊቶች (የበአልና የአጸድ ነቢያቶች) ከህዝቡ መሀል በእጁ ሲደመሰሱ እርሱ ራሱ አይቶአል፤ በጸሎቱም ምድሪቱ ላይ ከሶስት አመታት ድርቅ በሁዋላ ከባድ ዝናብ ያዘነበውን ታምራት ተቀብሎአል፡፡ ወዲያው ግን ከከፍታው አካባቢ ወርዶ ወደ ሰፈር ሲመለስ በዚያ የተንሰራፋው ክፉ መንፈስ በኤልዛቤል በኩል ዛቻ ላከበት፡፡ በእግዚአብሄር ክብር ውስጥ በተራራው ላይ የተገዳደራቸውን አጋንንቶች በሰፈር ውስጥ በዝቅታ አካባቢ ሆኖ ሲፈራና ሲሸሻቸው እናያለን፡፡ከተራራው በፈጠነ ሩጫ ቢወርድም የአጋንንቱን ዛቻ ከሰፈር ማስወገድ አልቻለም፡፡ምክኒያቱም እየራቀ የነበረው ከቀርሜሎስ የአምልኮና የበቀል ተራራ አካባቢ ነበርና ነው፡፡
1ነገ.19:1-3 ”አክዓብም ኤልያስ ይህን ሁሉ እንዳደረገ፥ ነቢያትንም ሁሉ በሰይፍ እንደ ገደለ ለኤልዛቤል ነገራት።ኤልዛቤልም፡- ነገ በዚህ ጊዜ ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብላ ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች። ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፥ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፥ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ።”
ኤልያስ በሰፈር ውስጥ ሊጸልይ አልቻለም፡፡ይልቅ በእግዚአብሄር ተራራ ላይ የጸለየውን ጸሎት ዳግም አምኖ እንዳይጸልይ እምነቱ በፍርሀት ተውጦ ለሽሽት ተዳረገ፡፡
ኤልያስ በሰፈር ውስጥ በተሰማው ዜና ቅስሙ ተሰበረ ደከመም፣ ከዚህ የተነሳም ወደ ሽሽት ገባ፡፡ከያዘው ፍርሀት የተነሳ እግዚአብሄርን መጠየቂያ ፋታ እንኩዋን አላገኘም፡፡በድካም ውስጥ ሆኖ መሞት እስከሚመኝ ድረስ አዘነ፡፡ ኤልያስ ቀርሜሎስ ተራራ ላይ በሆነው ነገር እስራኤል፣ ንጉሱና ኤልዛቤል ልባቸውን ወደ እግዚአብሄር ይመልሳሉ ብሎ ጠብቆ ይሆናል፡፡የሆነውን ባየ ጊዜ ግን ተስፋው ተቆረጠ፣ ሞትን ተመኘ፣ በቃኝ አገልግሎት አለ፡፡
1ነገ.19:4-7 ”እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፡- ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ።በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና፡- ተነሥተህ ብላ አለው።ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ።የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፡- የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው።”
ሰው ምንም እንኩዋን በእግዚአብሄር ብርታት ከመንፈሳውያን ሰራዊት ጋር ተዋግቶ ማሸነፍ ቢችልም ከእግዚአብሄር ሀይል አካባቢ ለአፍታ እንኩዋን ሸርተት ካለ በስጋው አንዳች ነገር ፈቀቅ ማድረግ እንደማይችል የነበዩ ህይወት ያስተምረናል፡፡የሰውን ልክ የሚያውቀው እግዚአብሄር ስለ ድካሙና ተስፋ ስለ መቁረጡ ነቢዩን አልገሰጸውም፡፡ይልቅ ተከትሎት በደከመና በወደቀበት ስፍራ ላይ ሊያበረታው መጣ፡፡የድካም መንፈስ ባጠቃንና ተስፋችንን በነጠቀን ሰአት እግዚአብሄር መጥቶ እንደሚቀሰቅሰን ቃሉ ያረጋግጣል፡-
ኤፌ5:13-14 ”ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።ስለዚህ፡- አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።”
በመልአክ ቅስቀሳ ከእንቅልፉ የነቃው ኤልያስ በእግዚአብሄር ምግብ እንደበረታ እኛም ደክመን በምናንቀላፋ ጊዜ እግዚአብሄር ያለንበት ድረስ መጥቶ እንደሚረዳን ይህን ተስፋ መያዝ ያስፈልጋል፣ሰው መቼም በሀይሉ አይበረታምና፡፡
በእምነት የተሞላውን ነቢይ እግዚአብሄር ወደ አምልኮው ተራራ ጠርቶት እንደነበረ በእምነት ደክሞ ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ደግሞ ብርታት ወደሚያገኝበት ተራራ ዳግም ሲጠራው እናያለን፡፡
1ነገ.19:6-11 ”ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ።የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፡- የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው።ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ።እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆም፡- ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም፡- ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።እርሱም፡- ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ።”
ነቢዩ በበላውና በጠጣው ምግብ ምክኒያት ረጅሙን ጉዞ እንደተጉዋዘ ሁሉ እኛም ሀይሉን በተቀበልን ጊዜ ተስፋችንን ማደስና አዲስ ራእይ ወደ ምንቀበልበት ወደ እግዚአብሄር መገኛ መድረስ እንደሚያስችለን ማመን ይገባናል፡፡
ወደ መገኛው ተራራ ልብን ማቅናት (በዚህ ዘመን የመለኮት ማደርያ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ መቅረብ) ከጥፋት የመትረፍ እንዲያውም በርሱ ምክኒያት ነገስታቶች አስኪቀቡ በሚያደርስ ጸጋ መጎብኘት ሊያመጣ ስለሚችል የነቢዩ ኤልያስን እይታ በመንፈስ መቀበል ተገቢ ነው፡፡እግዚአብሄር ነቢዩ በጎነትን ሲለምን ሰማው እንጂ ሞቱን ሲለምን አላዳመጠውም፡፡ ከኤልዛቤል ዛቻ የተነሳ በፍርሀት እንዲሞት ጸለየ፡- የሚሰማውን ጸሎት በፍርሀት ምክኒያት ተቀምቶ የማይሰማ ጸሎትን ጸለየ፣ እግዚአብሄር ግን ያ እንዲሆን ፈቃዱ ስላልነበረ ከሞት ይልቅ ዳግም ራእይ ወደሚቀበልበት ወደ ኮሬብ እንዲጉዋዝ ምሪት ሰጠው፡፡
•በእግዚአብሄር ተራራ ላይ ምን?
ኢሳ.2:3-5 ”ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፡- ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።”
•የጠላት እቅድ በተራራው ላይ
ኢሳ.14:13-15 ”አንተን በልብህ፡- ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።
ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።”
ከተራራ ከወረድን ቁልቁለት ላይ እንገኛለን፡፡ከከፍታ መውረድ፣ ዝቅታ አካባቢ መመላለስ፣ በዚያ ከሚኖሩ ጋር መጋጨት ላይ ይጥላል፡፡ ዝቅታ ለጠላት መጋለጫ ስፍራ ነው፡፡ቁልቁል ሲወርዱ እነ ኤልዛቤል አካባቢ መከሰት ይፈጠራል፡፡የእነ ኤልዛቤል ሰፈር ጠላፊ አለበት፡፡ኤልዛቤል ኤልያስን በቀርሜሎስ ሳለ አላስፈራራችውም፣ስጋት አልሆነችበትም፡፡ከተራራ ወርዶ በርሱዋ ሰፈር እንዳለፈ ግን ማስፈራራትና ዛቻ ደረሰው፡፡እርሱ ግን ወደ እግዚአብሄር ተራራ ዳግም እግሩን አቀና፡፡ነቢዩ ማምለጫው የእግዚአብሄር መገኛ ተራራ እንደሆነ ስላስተዋለ ወደዚያ ተጉዋዘ፡፡
•የክህደት ተራሮች
1ነገ.11:7-10 ”በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ።፤ ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ።”
ተራሮች ሁሉ ግን የእግዚአብሄር መገለጫ አይደሉም፡፡እስራኤላውያን ከእግዚአብሄር በራቁበት ዘምን ሁሉ በራሳቸው ተራሮች ላይ ለአማልክት ሰውተዋል፡፡
ሳኦል የሚረዳው አብሮት ስላልወጣ በሄደበት ቀርቶአል፤ በጊልቦአ ተራራ ሳኦል ሞቶአል (እግዚአብሄር ባልተገለጠበት ስፍራ የጠላት ጥቃት ስላለ)፡፡እግዚአብሄር በሚገኝበት ስፍራ እንጂ በፈቀድነውና በወሰንነው አካባቢ ሁሉ የርሱን መገኘት መጠባበቅ እንደማንችል ሁኔታው ያስረዳል፡፡
1ሳሙ.31:1-3 ”ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ።ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ።”