በእምነት መመላለስ

ቤተክርስቲያን

በእስራኤል ነገድ ውስጥ የእግዚአብሄርን ህግ ሊጠብቅ የቻለ ሰው አልነበረምና እግዚአብሄር በዚያ ባለመደሰቱ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
“የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ“ (መዝ.78:10)
ያኔ የእግዚአብሄር የግርዘት ቃል ኪዳን በእስራኤል የምድረበዳ ጉዞ ወቅት ተዘንግቶ ነበር።በሌላ መልኩ እስራኤላውያን ከነአን ከገቡ በሁዋላም በሲና ተራራ ፊት ሆነው የተቀበሉትን ህግ እንዲሁ አልጠበቁም።ዛሬም ቢሆን እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነው፡፡ እኛስ ራሳችን እግዚአብሄርን በማየት ሳይሆን በእምነት ልንከተለው ስለተለየን ትእዛዙን በዚያው ልክ በእምነት እንከተላለንን ወይ? በእርግጥ እርሱን ማመናችን የሚረጋገጠው ለቃሉ በምናሳየው ፍቅር ነው።
ኢሳ.50:5 “ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም።“ ይላልና።
እግዚአብሄር ጆሮን ይከፍታል።ጆሮን የሚከፍተውም ሰሚው ያለ እንቅፋት በነጻነት እርሱን እንዲሰማና በፈቃዱ እንዲጉዋዝ ነው።ትእዛዛቶቹ በእምንት እንድንመላለስ ያስችላሉ።ጆሮው የተከፈተ የእግዚአብሄር ልጅ እንደዚህ እርሱን የመስማት ችሎታ አለው።ስለዚህ ከሰማው ነገር ወደ ኋላ አይልም፣ ድምጹንም ከመታዘዝ ውጪ አይወጣም።እምነት ሲያጣ፣ ውስጥ ባዶ ሲሆንና ቃሉ በውስጡ መስራት ሲያቆም ግን በአመጽ ይገለጣል።በዚያ ሳይቆም ቀርቶ አመጽና አለመታዘዙ እየቀጠለ ከሄደ ለድምጹ የልቡን በር መዝጋት ያመጣል። ሰዎች በገዛ አመጻችን የሚከተለንን ክፉ ነገር እንሸከም ዘንድ ብቁ ትግስትና አቅም ስለሌለን ከሚከተለን ጥፋት ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሄር ጋር መከራከር እናበዛለን፡
መዝ.78:9-11 “የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ። የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥“
የኤፍሬም ልጆች የእግዚአብሄርን ቃል ሰምተውና ተማምነው ወደ ሰልፍ ወጥተው ነበር ።ግን ውስጣቸው በተፈጠረው ማመንታት በሰልፍ ቀን አልጸኑም፡፡ወገኖቻቸው እርዳታቸውን እጅግ እየፈለጉ ሳለም ወደ ሁዋላ ተመለሱ። ቀድሞም የታመኑት ቀስታቸውን ኖሮ ጌታቸውን ባላስቀደሙበት ሁኔታ እንዳሰቡት ሳይረዳቸው ከእግዚአብሄር ጦርነት አፈገፈጉ፤ በማመንታታቸው እግዚአብሄርን አሳዘኑ።
በእምነት የመመላለስ ነገር መንፈሳዊነትን ስለሚቀርጽ ከምንመላለስበት መንፈሳዊ መንገድ መውጣት ለጠላት ውዥንብር ያጋልጣል።ምሪት አጥቶ መደነጋገር፣ውጤት የሌለው ሩጫ መሮጥ ሁሉ ኪሳራ ውስጥ የሚወረውረን የእምነት ዋስትናችንን በመጣል ምክኒያት ነው፡፡
መዝ.56:9 “በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ።“ ይላል፡፡እኔ አልመለስ ጠላቶቼ ግን ይመለሱ ነው ዋናው ፍላጎት።
የእግዚአብሄር ልጆች ጉዞአቸው ወደፊት በመሆኑ (ወደፊት ሊመጣ ያለውን በማመን) ወደ ሁዋላ የሚያሰኛቸውን እያራገፉ ከጥሪው ጋር ሊራመዱ ያስፈልጋል፤ ወደ ሁዋላ የሚያደርግ ነገር አያዋጣምና። ጠላት ከህይወት መንገድ ወደ ኋላ ተንሸራትተው እንዲሰነካከሉ ሰዎችን ይታገላል። የእግዚአብሄር ፈቃድ ደግሞ ጠላታችን ወደኋላ እኛ ደግሞ ከርሱ ጋር ወደፊት እንድንራመድ ያስችላል።በእምነትም በፈቃዱ በኩል መሆን ያስችለናል።
መዝ.70:2 “ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቍሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም።“
እኔ በአምላኬ ታምኛለሁና አላፍርም፣ ጠላቶች ግን በታመንኩት አምላክ ስም ይፈሩ፣ ይጎስቅሉ፣ ወደ ፊት ከማሳደድ ተገትተው ወደ ሁዋላ ይመለሱ። አጋንንት ሁሌም ቀድመው እንቅፋት በማኖር ያሰናክላሉና፣ የምናመልከው አምላክ ግን ወደ ሁዋላ ስቦ ያሳፍራቸዋል።
በእምነት የሚመላለስና የኢየሱስን ድምጽ የሚሰማ በቃሉ ብርሃን ልቆ እየቀደመ ከጠላት አሰራር ማምለጥና መጋረድ ይችላል።ሃዋርያት ከኢየሱስ ጋር ስላሉ ጠላትን እንዲያ አድርጎላቸዋል።
እስራኤላውያን ከማመን አፈግፍገው የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ቸል ሲሉ ቁጣው ቀድሞአቸው ይወጣ ነበር።በእምነት ማጣት የሚያደርጉትን በደል አይቶም እግዚአብሄር ለቁጣው ይተዋቸው ነበር።የሚያስፈራው ደግሞ የጠላት ክንድ ሳይሆን የእግዚአብሄር መለየት ነው።እምነት ማጣትና የውጊያ ትጥቅ ለጠላት ማስረከብ አንድ ናቸው፡፡ባለማመን መሰናክልም ህያው እግዚአብሄርን አናየውምም።
ሰው በእግዚአብሄር ላይ ያለውን እምነት ሲያጣ ወይ ራሱን ለጠላት ያስማርካል ያለበለዚያ በአምላኩ ላይ ያጉረመርማል።ልባችንም አልፎ በእግዚአብሄር ላይ ጠላት ሆኖ የመነሳት አዝማሚያ ያሳያል፣።ትልቁ ውድቀትም ይሄ ነው፡፡
ኤር.7:24 “ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።“ ብሎ የወቀሳቸው በእምነት ወደ ፊት ከሚጓዙበት የእግዚአብሄር አሳብ ፈቀቅ ስላሉ፣ የገዛ ክፉ ልባቸውንም ስላመኑ ነበር።
በእምነት መመላለስ ግን ከሚታመነው አምላክ ጋር ያገናኛል፣ ወደ ክብሩ ያስገባል፣ ሃይሉንም እንድንቀበል ይረዳል።
ዮሐ.6:28-29 “እንግዲህ፦ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት።ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።“
ያለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት እንዴት እንችላለን? እግዚአብሄር የትኛው ስራችንን በደስታ ሊቀበለውስ ይችላል? የጽድቃችን መጠን በጎ ነገር ሊሰራ አቅም ስላጠረው እግዚአብሄር እምነትን ስራ አደረገልንና የናንተ ስራ በላከው ማመን ብቻ ነው ተባልን።እምነታችን ግን እንደ አይሁድ አይሁን፣ጥርጥር ያለበት ስለነበረ ተቀባይነት አልነበረውምና።
ዮሐ.6:30 “እንግዲህ፦ እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ?“ ሲሉ ያለማመናቸውን ይፋ አድርገዋል።
በማየት ለመመላለስ ሙከራ ማድረግ ብዙ ቀውሶች ያስከትካል፦
• በማየት መመላለስ የሚሹ መዳንን አያዩም
ዕብ.10:38 “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።“
ያለማመን ማፈግፈግን ስለሚፈጥር ከመንገድ ያወጣል።እንደ ጴጥሮስ አንተ ካልክ ግን ይሁን ብሎ ማድረግ መልካም ነው።
• በማየት መመላለስ ወደ ሁዋላ ያስቀራል
ዘፍ.19:17 “ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው፡- ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።“
የቃሉ ትእዛዝ አስቸኳይ እርምጃ እየጠየቀ ቃሉን ባለማመናችን ሆነ ከማመን መዘግየታችን እኩል ጥፋት ላይ ይጥሉናል፣የሎጥን ሚስት ማሰብ በቂ ነው።ነቢዩ ግን ታዛዥነቱን ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፦
“ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም።“(ኢሳ.50:5)
ኤር.7:24 “ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።“
• በማየት ማረጋገጫ ፍለጋ የማይታየውን መንፈሳዊ በረከት ያስመልጣል
ዮሐ.6:31-36 “ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት።ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።ስለዚህ፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።“
ያለማመን መንፈስ የሚታመነውን ይሰውርብናል።አይሁድ የሚያድናቸው ጌታ አጠገባቸው ሳለ ሊቀበሉት ያለመቻላቸው ብዙ ዋጋ አስከፍሎአቸዋል።የማይታየው ባህሪ – አምላክነቱና የዘላለም ሃይሉ በእምነት አይን ብቻ ይታያሉ።
በእምነት መመላለስ ግን ብዙ መንፈሳዊ ነገር ያስጨብጣል።አማኞችም የእምነትን ነገር እየተለማመዱ መኖር የሚችሉት በእርሱ ሆነው ከኖሩ ነው።ስለዚህ፡-
• በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ ከሚታመነው አምላክ ጋር በአብሮነት መጓዝ የሚያስችል ነው
2ቆሮ.5:6-7 “እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና…“ ማለቱ ይህን ሲያረጋግጥልን ነው።
መንፈስ የሆነውን አምላክ ድምጽ እየተከተሉ መጓዝ የደህንነት ዋስትና ነው፡፡ድምጹን መከተል የሚቻለውም በእምነት መንገድ ውስጥ ስለሆነ የሰው ልጅ ልቡን ከፍቶና አምኖ ለእግዚአብሄር ራሱን ሊሰጥ ይገባል፡፡ሁለጊዜ እንዴት ልታምን፣ እንዴትስ ወደ አምላኬ ልቅረብ? ለሚለው ጥያቄ በእምነት መመላለስ መልስና መፍትሄ ይሆናል፡፡
• በእምነት መመላለስ የተጨበጠ ነገር ቅድመ ሁኔታ ማድረግ ሳይሆን ቃሉን ተማምኖ መውጣት ነው
2ዜና.20:20-21”ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፡- ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ።ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፡-ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፥ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ።
የንጉሱ እምነት ምን አስገኘለት? ድል ነው ያስገኘለት፡፡ እግዚአብሄርን ማስቀደምና በአምልኮ ውስጥ መጠባበቅን በመቻሉ እቅዱ በድል ተጠናቀቀ፡፡ይህ ከምንም በላይ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍንና መፍትሄ ማግኘትን የሚያሳይ አሰራር ነው፡፡
በሌላ በኩል ስናይ በእምነት መመላለስን ለማሳካት በቃሉ ላይ መደገፍ መተኪያ የሌለው መንገድ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡የጸናው የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን ሲነግስ በጎ ተጽእኖ ይፈጥራልና፡፡ቃሉ ህይወት ሆኖም መንፈሳዊ ጉዞን ያጸናል፡፡
በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ያለው ዘላለማዊው እቅድ የሚገለጠው በቃሉ ነው፡፡ቃሉ ትውልድን ሁሉ መምራት የሚችል እውቀትና ጥበብ የተገለጠበት በመሆኑ ማንም ከቃሉ ማለፍ አይችልም፡፡ ስለ እምነት ጉዞ ከታሰበ፣ስለምሪት ከታሰበ፣ስለእውቀት ከታሰበ፣ስለመዳን ከታሰበ፣ስለቅድስናና በአጠቃላይ ስለእግዚአብሄር ስራና እቅድ ከታሰበ ቀድሞ የሚመጣው ህያው ቃሉ ነው፡፡
ዮሐ.12:48 ”የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።” ይላልና ህያው ቃሉ ላይ ተጣብቀን በፊቱ በእምነት መመላለስን እንዲሁም እስከ መጨረሻው ከርሱ ጋር የመጉዋዝ አቅምን ይስጠን እላለሁ፡፡