የአምላክ ምስጋና ሊያውም በሰንበት ቀን (በእግዚአብሄር እረፍት ውስጥ) የሚቀርብ እጅግ የላቀ ደስታና ምህረት የሚያመጣ በመሆኑ ዘማሪው ንጉስ ያን አስተውሎ በመዝሙሩ ጅማሬ በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር ይላል፡፡ ሲቀጥልም፡-
”እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ። አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው።” ይላል (መዝ.93:1-4)፡፡
እግዚአብሄር የሰንበትን እረፍት ለእስራኤል ሰጥቶ ነበር፤ ህዝቡም በዚያ እለት ከሁሉ ድርጊት እንዲታቀቡና አሳባቸውን በእርሱ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ካመለከተ በሁዋላ በእለቱ ወደ እርሱ የሚቀርቡበትንና አምልኮአቸውን የሚሰዉበትን ስርአት ሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ይህ በአዲስ ኪዳን ወደ ተገለጠው የዘላለምም እረፍት ወደ ሆነው ወደ ጌታ ኢየሱስ የሚያመለክት ጥላ እረፍት ነበር፡፡ ዛሬም እግዚአብሄር በእረፍቱ ውስጥ ሆነን እንድናመልከው ይሻል፡፡ እግዚአብሄር በትርምስ ውስጥ አይመለክም፣ ፍጹም ልብን ይሻል፤ በታወከ መንፈስ፣ ባልቀና ልብ፣ አመጽ በተበተበው መንፈስ፣ እግዚአብሄርን በማያውቅ ልብ ተሁኖ አምልኮ ወደ ፊቱ አይደርስም፡፡ ሰዎች የእርሱን ማንነት ባላወቁበት ሁኔታ በእርጋታና በመስዋእት መንፈስ ለእርሱ ሙሉ ምስጋና ማቅረብ አይችሉም፡፡
ኢሳ.66:1-4 ”እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤ እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና።”
በመዝ99፡5 ውስጥ እግዚአብሄርን የሚያውቁና የሚያመልኩ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አንዲያደርጉ ቅዱስ በመሆኑም ወደ እግሩ መረገጫ እንዲሰግዱ ያሳስባል። ነገር ግን ትሑት ልብ ሳይኖራቸው ወደ ትሁት አምላክ ሊጠጉ ቢሹ፣ ልበ ደንዳናና መንፈሳቸው ያልተሰበረ ጨቃኞች ሆነው ፊቱ ቢቀርቡ፣ በቃሉ ፍርሀት ሳይያዙና ቃሉን ከማድረግ ይልቅ እየናቁ አምልኮና ስግደት ሊሰዉ ቢመጡ እግዚአብሄር ይጸየፋቸዋል እንጂ አንዳች ሞገስ ከእርሱ አይቀበሉም፡፡
የኃጥእ መስዋዕት በእግዚአብሄር ፊት ተቀባይነት ያጣ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ በደልና ጸያፍ ነው። ሰው በክርስቶስ ደም ታጥቦ በፊቱ ሳይቀርብ የሰመረ መሥዋዕት ሊኖረው አይችልም፣ እግዚአብሄርም ወደ ጎን ይለዋል። ሰዎች ራሳቸውን በሚያታልሉበት ከንቱ እምነት ውስጥ ሲሆኑ በራሳቸው ትምክህት ይነዳሉ። የማያምኑ ልቦች እና ያልነጹ ኅሊናዎች ወደ ራሳቸው በንሰሃ ከመመለስና የእግዚአብሄርን ፍርሀት ከማምጣት ይልቅ ወደ ሚሰብራቸው ከንቱ አምልኮ ያዘነብላሉ፤ አግዚአብሄርም ለከንቱ አምልኮአቸው መልስ ስለማይሰጥ አዛኞች ይሆናሉ።
የከበረ አምላክ በትህትናና በቅንነት ይገለገላል። በቅን አምልኮ ውስጥ የሚገለጥ ምስጋናም ከከበረው አምላክ ፊት ይደርሳል፣ እርሱም በበኩሉ የሰው ልጆችን ጠላቶች ያዋርዳል፣ ትሑታንንም ያጽናናል፡፡ ለህዝቡ በሰጠው የእረፍት መንፈስ ውስጥ የሚመላለስ የህዝቡ አምልኮ በአዲስ ኪዳን ዋነኛ የፈውስ መንገድ ሆኖአል፡፡ የጽድቅ ልብስ ክርስቶስን በጥምቀት የለበሱ መንፈሱንም የጠጡ ያዳነቸውን ጌታ ከፍ የሚያደርጉበት መሰረቱ ሰንበት የሆነ (ዘላለማዊው እረፍት ጌታ ኢየሱስ የሆነ) የዝማሬ ቅኔና የአምልኮ መንፈስ ቢፈስ እጅግ ተገቢ ነው፡፡
የፍጥረታትን እንቅስቃሴ እና ድርጊቶቻቸውን እንደ ፈቃዱ ምክር የሚመራ እንዲሁም የሚቆጣጠር ሃያል አምላክ እግዚአብሄር በሰማይ ሆኖ ምስጋናን ይቀበላል፡፡ የዚህን አምላክ ማዳን የሚያውቁ ሀይሉንም ጭምር ስለሚረዱ እርሱን በመዝሙር ያከብሩታል ከፍ ያደርጉታልም።
ሁልጊዜ ለክፉ መናፍስት የእግዚአብሄር ሞገስ አስፈሪ፣ አስደንጋጭና ጭንቅ ቢሆንም ለሰዎች የደስታና የመዳን መመኪያ ነውና ምስጋናን ይፈጥራል፡፡ በሰማይ ያለው ሁሉን የሚችል አምላክ በክብር ነግሷል፣ ግርማንም ለብሷል። እግዚአብሄርን የማያውቁ የምድር መኳንንት ክብራቸው ግርማና መመኪያቸው ሆኖ ቢሞገሱ ቢፈሩም ምስጋና ከሚፈጥረው ከእግዚአብሔር አስፈሪ ግርማ ጋር ሲነፃፀሩ ኢምንት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ነህ.9:5-7 ”ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ። ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ፡- በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ።አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ”
የአለም አይን በሰይጣን አሰራር የተያዘ ነው፣ ስለዚህ ጌታ እስኪገለጥና ብርሃኑን እስኪሰጥ የአምልኮና የስግደት እውቀት በዚያ አይኖርም ማለት ነው። ነገር ግን በግል ማንነትን ለቅዱሱ አምላክ በመለየት አምልኮን ማጽናት ቢቻል፤ እንዲሁም በአገር ላይ የእግዚአብሄር ምህረት እንዲገንን ህዝቡ ለእርሱ መገዛት ውስጥ ቢገባ እግዚአብሄር በዚያ ይከብራል፡፡
(መዝ.48:1-14) ”በሁለተኛ ሰንበት የቆሬ ልጆች፤ የምስጋና መዝሙር። እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው።በሰሜን ወገን በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው፤ እርሱም የትልቁ ንጉሥ ከተማ ነው። እግዚአብሔር በአዳራሾችዋ መጠጊያ ሆኖ ይታወቃል።…እንደ ሰማን እንዲሁ አየን በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል። አምላክ ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ምሕረትህን ተቀበልን። አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው፤ ቀኝህ ጽድቅን የተሞላች ናት።አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራራ ደስ ይበለው፥ የአይሁድም ሴት ልጆች ሐሤት ያድርጉ።ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፤ አዳራሽዋን አስቡ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ። ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘላለም ይመራናል።”
ኢየሩሳሌም እግዚአብሄር ፈቃዱን ለሰው ልጆች የገለጠባት እስከመጨረሻም የሚገልጥባት የአምላክ ከተማ ናት፤ ምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም የመንፈሳዊቷ ኢየሩሳሌም ምሳሌም ናት፡፡ ምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም የእግዚአብሄርን የዘላለም አሳብ ለምትገልጠው ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ገጽ ማሳያ በመሆንዋ በእርስዋ ውስጥ ከእግዚአብሄር ህዝብ የሚቀርበው አምልኮ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ስለዚህ በኢየሩሳሌም የሚቀርብ ይህ አምልኮና ስግደት የዘላለሙን አምልኮ ማሳያ ነው፤ የንጉሱ ዳዊት ግዛትም ለዘላለማዊው የእግዚአብሄር መንግስት ስልጣን ምሳሌ ነው፡፡ በዚያች ከተማ ሆኖ ንጉስ ዳዊት ወደ ዘላለሙ ንጉስ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠቁሙ የምስጋና መዝሙሮችን ያስተጋባ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰአት ላይ ሆነን እንኩዋን ምድር በኃጢአትና በክፋት ተሸፍናለች፣ ቢሆንም በቅድስና ባጌጠችውና የፍጥረት ሁሉ ውበት በሆነችው ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ህዝቡ የአምላክን ምስጋና የሚያቀርብበት ጊዜ ቅርብ ነው፡፡
1ዜና.16:7-14 ”በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ትእዛዝን ሰጠ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። ባሪያዎቹ የእስራኤል ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱንም የአፉንም ፍርድ። እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው።”
ንጉስ ዳዊት እርሱና ህዝቡ ከጠላት እጅ የተሰወሩትና እረፍት የተቀበሉት ከአምላካቸው በመሆኑ፣ ምህረታቸውም በእርሱ እጅ ብቻ እንደበዛች ስለሚያውቅም የምስጋና ትእዛዝን ሰጠ፤ አንድም የረዳው አምላክ እያደረገለትና መንገዱን እያቃናለት እያየ ምስጋናውን ላለማስቀረት፣ ደግሞም በምስጋና ውስጥ የእግዚአብሄርን ክብር በቀጣይ ለማየት፡፡ የዳዊት የምስጋና ቅኔ እስከ አህዛብ እንዲደርስ በዝማሬው ውስጥ ተገልጦአል፡፡ ምክኒያቱም አህዛብን ጸጥ አድርጎ ከእግሩ በታች ያስገዛለት አምላኩ መሆኑን ማወቅ ስለሚገባቸው፤ በእስራኤል ያለ አምላክ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑ እንዲታወቅ ስለሚያስፈልግ፤ እንዲሁም አህዛብ የእስራኤልን አምላክ አምነው እንዲቀበሉ ጭምርም ነው፡፡ አህዛብ ምስጋናውን ሲሰሙ እግዚአብሔርን ይፈልጉት፣ የእስራኤል አምላክም በዚያ ይመልስላቸዋል፣ በማዳኑም ይጸናሉ።
ዘጸ.15:11 ”አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?”
ይህ ቀድሞ የእስራኤል ህዝብ ከግብጽ ባርነት ነጻ በወጣበት ዘመን የተዘመረ የድል ምስጋና መዝሙር ሲሆን በዚህ መዝሙር አማካይነት የእግዚአብሄር ማንነት ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ በዚያን ወቅት ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፡- በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡
እውነተኛው አምላክ በመዝሙር ውስጥ ከፍ ከፍ ሲል ሰው ሳይሆን አምላካዊ ሀይል ታምራትን በመስራቱና የእስራኤል አምላክ በመመስገኑ የእግዚአብሄር ምህረት ለህዝቡ ገንኖአል፡፡ በዚያ በምስጋና የእግዚአብሄር ቅድስና ገንኖ ታውጆአል፡፡ በምስጋናው መዝሙር ውስጥ የእግዚአብሄር በቀል በአጋንንትና በአመጸኞች ላይ ጭምር እንደሚሆን ሲያመለክትም፡- አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው አለ፡፡
በመንፈስ የሆነ የእግዚአብሄር አምልኮ ከእግዚአብሄር የደስታ ዘይት የሚያፈስ መልእክት ይዞ የሚመጣ ነው፤ ጠላት ምርኮን በነጠቀበት እንደ ጨለማው ዘመን እንደሆነው ያለ ዘመን ሳይሆን የእግዚአብሄር ክብር የሚገለጥበት ድርጊትን የሚፈጥር ነው፤ ጠላት የሀዘን ሸማ እንዳለበሰው የደቀቀ ሰው ሳይሆን በእግዚአብሄር ነጻ እንደሆነ ህዝብ የደስታ ዝማሬ ከህዝቡ የሚወጣበት ጊዜ ነው፡፡ ህዝቡ አቅም አጥቶ በጠላት ቢበዘበዝም፣ በእምነት ማነስ ምክኒያት ወደሁዋላ ቢንሸራተትም እውነተኛው አምላክ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅ ስለሆነ በመሀል ይገለጣል፤ ተገልጦም የጠላትን አሰራር ይሽራል፡፡ ያን ያስተዋለ ህዝብም ድምጹን በአምልኮ ያነሳል፤ በዝማሬ ያሸበሽባል፤ በአምላኩ ፊት ይሰግዳል፣ ደስታም ይሆናል፡፡ ሙሴ መዝሙሩን ሲቀጥል እንዲህ ይላል፡-
”ጠላትም፡- አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ።አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው።የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ።አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ።” (ዘጸ.15:9-17)
የዘላለም እረፍትን ያገኛችሁ ነገር ግን ጠላት አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች እያለ የሚያስፈራራችሁ የአምላክን ምስጋና አንሱ፤ እግዚአብሄርም ጠላታችሁን በሚያስፈራው የሀይሉ እስትንፋስ ይገስጸዋል፣ የስሙ ሀይል እንደ ባሕር እስኪከደንበት፣ እንደ ኃያል ውኆች በጥፋት ተከድኖ እስኪሰጥም ድረስ ያሳድደዋል፡፡ እንዲህ ስለሚል፡-
”ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤ የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።” (2ሳሙ.22:4-7)