በሚሠራበት ቀን (2…)

እግዚአብሄር በምህረት በሚጎበኝበት ቀን (ዘመን) ትውልድ ተዘጋጅቶ ይጠብቅ ዘንድ ይፈለጋል፤ እግዚአብሄር መቼ ይሰራል? ለማን ይሰራል? እንዴት ይሰራል? የሚል ማስተዋል ያለበት ምርመራ ይገባልም። በእስራኤላውያን ዘንድ ዘመንን ማወቅ ትልቅ ስፍራ ስላለው ጠቢባን ያማክሩ ነበር፤ በንጉስ ዳዊት ዘመን ጊዜን የሚመረምሩና የሚያስተውሉ ከህዝቡ መሃል የተመረጡ ሰዎች ስለነበሩት የእግዚአብሄር ህዝብ ዘመኑንና በዘመኑ ላይ የሚገለጠውን የእግዚአብሄር ፈቃድ በመረዳት የህይወት ይዘታቸውን ያስተካክሉ/ይቃኙ ዘንድ አስችሎአቸዋል። በ 1ዜና.12:32 ላይ ሲናገር፦
‘’እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር።’’ ይላል።
በዘመናችን ሁሉ መዘጋጀት ለምን?
እግዚአብሄር የሚጎበኝበት የራሱ ሰአት ስላለ ያ በደረሰ ጊዜ እርሱ ይገለጣልና ነው። በዚያን ወቅት ትውልድ የተዘጋጀ፣ የተቀደሰና እምነት የተሞላ ልብ ቢኖረው በሚሰራበት ወቅት ምህረቱ ያገኘዋል፤ ጌታ ሁሉን የሚችል አምላክ ሰለሆነ አንድም ልብ ቢሆን አሳቡን ማሰናገድ ቢችል ምህረቱ ለትውልድ በሙሉ ሊገለጥ ይችላል፤ ይህም በሙሴና በዳንኤል ዘመን ታይቶአል። የሙሴን ትውልድ ስንመለከት በርሱ ትውልድ መሃል እግዚአብሄር ለስራ ወርዶ ነበር፤ በዚያ ዘመን ለአምላኩ የተለየው ሙሴ ተገኝቶአል። ሙሴ የተዘጋጀ ልብ ቅዱስም ህይወት ነበረውና ከእግዚአብሄር ጋር ይስማማ ዘንድ አላቅማማም። እግዚአብሄርም በተገለጠበት ስፍራ ሊሰራ ያለውን ስራ ወዲያው አስታወቀው፤ ደግሞ እግዚአብሄርና ሙሴ ስለተስማሙ የእግዚአብሄር ታላቅ ስራ ተሰራ።
ማስተዋል ባለበት ዝግጅት ሳይኖር በረከትም ያልፋል፣ ቁጣም ይመጣል
‘’በዚያ ቀን ብዙዎች፡- ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ ​በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።’’ (ማቴ.7:22-28 )
ጌታ ሲናገር የእግዚአብሄር ህዝብ የሚጎዳው የእግዚአብሄርን ድምጽ መከተል ሲሳነው እንዲሁም ቃሉን ሰምቶ ማድረግ ሳይችል ሲቀር ነው፤ ቢሳካለት ግን ቃሉ በዘምኑ መሃል አሳልፎ መጨረሻው ላይ እስኪደርስ ይመራው ነበር። በጎው ዘመን ሲመጣ ዝም ከተባለ፣ እንደ ተራ ነገር ከተቆጠረ፣ በሚታየውና በሚሰማው ነገር መሃል እየሾለከ የሚመጣው ስራው እንደገጠመኝ ከታሰበ ሄዶ ሄዶ አይቀሬው ክፉ ድንገት እንደጎርፍ ከደጅ ይደርሳል። ያኔ የተላከው ቃል እንዴት ሊረዳ ይደርሳል? አጋጣሚ መስሎን የተላለፍነው፣ አይመለከተኝም ብለን ቸል ያልነው፣ በኛ ባለማስተዋል ያላገኘን ታላላቅ የእግዚአብሄር ስራ አንዴ ላይመለስ ተላልፎናልና ባወቅነው ጊዜ ላናገኘው ውስጣችንን የሚበላው የሚፈስብን ጸጸት ብቻ ይሆናል፤ ይህ ችግር በትውልዱ ላይ ከቀጠለ እግዚአብሄር እያስጠነቀቀ ያለው አስፈሪ ጊዜ ሊመጣ ግድ ነው።
ሲገለጥ በሰአቱ ታላቅ ነገር ይታያል
በሚሰራበት ቀን! እግዚአብሄር በምህረቱ በሚጎበኝበት ቀን፣ ጸሎትን ሰምቶ በሚመልስበት ቀን፣ ታላቅ ቀን፣ ታላቅ ነገር ይሆናል። ብዙ ጊዜ እግዚአብሄር በሚሰራበት ቀን በመጠባበቅና በማስተዋል ሆኖ በዚያ ቀን መገኘት ከተቻለ ግን በህይወታችን ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ህይወታችን ወደ ከፍታ የሚያወጣ ሃይል ልንቀበል እንችላለን። በተዘጋጀ ህይወት ሆነን በመከራ ቀን መሃል እንኳን ብንሆን እግዚአብሄር ሰምቶ ሊታደግ ይመጣል፣ ያ ቀን የሚሰራበት ቀን ነውና።
መዝ.118:24-25 ‘’እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን። አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።’’
እግዚአብሄር ወደ እኛ ሊመጣ የወሰናት ሰአት እንዴት ታስደስት! ስትደርስ በውስጧ የሚገለጠው መድሃኒት እየታየው ንጉስ ዳዊት ከላይ በምናየው ሁኔታ ያመሰግናል፤ የተዘጋጀ ልብ ያለው ሰው አስቀድሞ እግዚአብሄርን እንደርሱ ይጠባበቃል። ሃዘን ቢሆን ፈተና፣ ችግር ቢሆን ጭንቅ፣ ህመም ቢሆን ደዌ፣ ከበባ ቢሆን ውጊያ፣ ክህደት ቢሆን አመጽ… ሁሉም እግዚአብሄር ለእኛ በወሰናት ቀን የሚገልጠው መድሃኒት ይፈውሰዋልና በርሷ ደስ ይበለን። ዮሴፍን እናስታውስ፦ በገዛ ወንድሞቹ የተካደውን፣ በባእድ ሃገር ተሽጦ የተጋዘውን፣ በባእዳን መከራ፣ ክህደት፣ እስራት ሁሉ የቀመሰውን ነገር ግን በእውነተኛ አምልኮና እግዚአብሄርን በመጠባበቁ፣ ስጋውን ነክሶ የደስታ ጊዜውን እግዚአብሄር የሚገለጥበትን ዘመንም ሳይታክት በመጠበቁ እግዚአብሄር በጊዜው መጣና አነሳው፣ አደረገለት፣ ባረከው፣ ለጠሉትና ለከዱት ቤተሰቦቹም ሳይቀር መድህን አደረገው።
ዘፍ.45:3-11 ‘’ዮሴፍም ለወንድሞቹ:- እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና። ዮሴፍም ወንድሞቹን:- ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው፦ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና። ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፥ ወደ እኔም ትቀርባለህ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ። በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና።’’
ይመጣል እንዳለ ይመጣል
የማይዋሽ ጌታ እንደተናገረው ያደርጋል፤ ዋናው ነገር እግዚአብሄር በእርግጥ ተናግሮሃል ወይ? ከተናገረህ እንደተናገረህ እንዲሁ ትሻዋለህ፣ እንደተናገረህ እንዲሁ ትጸልያለህ፣ እንደተናገረህ እንዲሁ ተቀድሰህ ትጠብቀዋለህ፣ ያኔ እርሱ ቀኑን ይገለጥልሃል፣ በቀንዋም ሐሤት ታደርጋለህ፥ በእርስዋም ደስ ይልሃል።
በጥበቃችን መሃል ልንዘነጋው የማይገባ እግዚአብሄር የወሰነው ቀን ደግሞ አለ፤ በዚያ ቀን የሚገለጥ ከግልም ከፍ ያለ ለማህበረሰብ፣ ከዚያም ከፍ ያለ ለሃገር፣ ሲልም ለአለም በሙሉ የሚሆን የእግዚአብሄር ስራ እንደ አገላለጡ ሁኔታ ይኖራል። በቃሉ ላይ እንደተመለከተው በአለም ላይና በሰውም ልጆች ህይወት ላይ የሚሆነውን ታላቅ ለውጥ የሚፈጠርበት ቀን ላይ ስናተኩር ይህን ጊዜ እግዚአብሄር ያለጥርጥር እንደሚያመጣው ቃሉ ያረጋግጥልናል። በዚያ ቀን መንፈስ የሆነ አምላክ በሚልከው መልእክትና ራእይ ምስጢርን ይገልጣል፤ አልፎም በመንፈሳዊው አለም ሊሰራ ያለውን ስራ ለባሪያዎቹ ካመለከተ በኋላ ስራውን ይፈጽማል።
እግዚአብሄር ይህን የሚያደርገው ስራውን ለአለም ለመግለጥ፣ ህዝቡ በባሪያዎቹ በኩል በተለያየ የመገለጫ መንገድ የሚቀበለውን ለማሳወቅ ቢሆንም ከእግዚአብሄር ጋር የቅርበት ህይወት ያለው የእግዚአብሄርን አሳብ በርሱ መንፈስ እንዲያስተውልና በአብሮነት እንዲሰራም ጭምር ነው። እግዚአብሄር ያን ያህል ቅርብ የሆነ አምላክ ነው፤ ለተከተሉትና ላመኑት የልቡን አሳብ የሚያሳውቅ ድንቅ አምላክ። ሰዎች የተቸገርነው እኛ ትናንሽ የሆንን ፍጥረቶች ስንሆን ታላቁ ፈጣሪ ይህንን ያህል ትኩረትና ስፍራ ሰጥቶ እንደሚያቀርበን ያለመቀበላችንና ያለማመናችን ነው። የዳዊትን ደስታ መሰረት እስቲ እንመልከት፦
‘’እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥
እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ። ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።’’ (መዝ.33:13-22)
ቃሉና ምስጋናው ከአንድ ስደተኛ እረኛ (በኋላ ንጉስ ከሆነ) ሰው የወጣ አይመስልም፤ እርሱ በብዙ ችግርና ስደት፣ መከራና ጉስቁልና ያለፈ ሰው ነበር፤ ግን ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ቅርበት የፈጠረበት አመስጋኝ ህይወት ልዩ ነው፣ ደስታውና ምስጋናው ልዩ ነው፤ ለምን? አስቀድሞም በኋላም ያይ የነበረው አምላኩንና ስራውን እንጂ ራሱን ስላልነበረ። ብዙ ጊዜ ራስ ራሳችንን ብቻ ስለምናይ የሆነልን ነገር ይጠብብናል፤ እይታችንን ይጋርዳል፤ በትልቁ እየሆነ ያለውን ትንሹ ጊዜያዊ የህይወት እንቅፋት ያጨልመዋል፤ ምክኒያቱም የምናየው ራሳችንን ብቻ ስለሆነ። ከዚህ ብንወጣስ? በእርግጠኝነት ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ስለምንገባ የእግዚአብሄር የበጎ እቅዱ መጨረሻ ላይ እንደርሳለን። ያኔ ሰርቶ የምናየው ለውጦን እናገኛለን፤ በዚያን በሚሰራበት ቀን እኛም ሳንሸማቀቅ አደረገልን ብለን እንዘምራለን፣ እናመሰግናለንም።
ዳን.9:7-14 ‘’ጌታ ሆይ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት አገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው። ጌታ ሆይ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። በእርሱ ላይ ምንም እንኳ ያመፅን ብንሆን፥ በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን ባኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንኳ ባንሰማ፥ ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው። እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፥ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን። እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም።’’
ጌታ ሆይ በጥንት ጊዜ ስትጎበኝ አባቶቻችን አልሰሙህም፤ ከተናገከው አንዱንም አልጠበቁም፤ ስለዚህ መአትህን አፈሰስክባቸው፤ ከምድራቸው ነቅለህ በባእድ ምድር በተንካቸው፤ ነገር ግን የጉብኝትህ ዘመን መጣ፣ ስለዚህ ያን የተናገርከውን ስለምትጎበኝበት ዘመን የተናገርከውን ቃልህን አስብ ይል ነበር፤ የእግዚአብሄርን ስራ የሚያውቅ፣ የሚገለጥበትን ዘመንም ያስተዋለ ነብይ። እግዚአብሄር በምህረት በሚጎበኝበት ቀን (ዘመን) ያስተዋለ ትውልድ ተዘጋጅቶ የጠበቀ እንደህን እንዲህ ከእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ጋር ይገናኛል። ነቢዩ እግዚአብሄር መቼ ይሰራል? ለማን ይሰራል? እንዴት ይሰራል? የሚለውን መመለስ ያለበትን የእግዚአብሄር ቃል እንዲሁ አስተውሎአል።
ምስጋናና የማዳን ቀን
እግዚአብሄር በሰራልን ቀን ስራውን ለመቀበል ማመስገን አስፈላጊ ነው፤ ይህን የምናደርገው ፍቅሩ ስለሚያስገድደን ነው፣ወዶን እንድንወደው ስላደረገ፣ አውቀነው አብሮነቱን ስለተለማመድን፣ አምነን በልባችን ስለሞላ ነው። የምስጋናውን መንገድ የምንከተለውም በህይወታችን እገዛውን እንዲገልጥ ብቻ ሳይሆን እስከድላችን ቀን ድረስ የርሱ መንፈስ በእምነት እያነጸ፣ ደሙ ከበደልና ከሃጢያት እያነጻ (ያለበለዚያ በነርሱ ምክኒያት ከፊቱ መቆረጥ ሊኖር ይችላልና) እንዲሁም ቃሉ እየመራ ወደ ፈቃዱ አቅጣጫ እንዲወስደን ነው።
ሰው ግን የእግዚአብሄር ቀን እንደሚመጣለት የመከራ ቀንም ይመጣበታል። በብርሃን ብቻ አይደለም በጨለመ ወቅትም ማለፍ የግድ ይላልና በአለም ስንኖር አለም የሚያገኛት ጉስቁልና ሊነካን ይችላል። ጌታ ከአለም ተነጥለን፣ ተሸሽገን ወይንም ልዩ የመከራ መከታ ስፍራ ተዘጋጅቶልን መኖር እንደምንችል የሚያበስር ሳይሆን የሚመጣውን ሁሉ አሸንፎልን እንደሚያሳልፈን ብቻ ነው። ሰው እንደሆን በስጋ ሲኖር ኑሮው በዚህች ምድር ላይ በመሆኑ በአለም ላይ የሚሆነው ሁሉ ያገኘዋል። ከሌላው አለማዊ ሰው የሚለየው እግዚአብሄር ለርሱ የጉብኝት ጊዜ የሚያዘጋጅለት መሆኑ ነው። የእግዚአብሄር ልጆች ቀናቸው ከአምላካቸው እስኪመጣ ድረስ በዚህ የመከራ ቀን የሚያልፉ ቢሆንም በአምላካቸው እርዳታ ያለመጥፋትን ይቀበላሉ።
‘’ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።’’ (መዝ.18:17-19)
ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ​የተናገረው የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። እንዲህም አለ፦
መዝ.18:1-2 ‘’አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።’’
እግዚአብሄር በሁሉ ጊዜያችን መሃል አለ፤ ስለዚህ አብሮነቱ ከኛ ጋር ካለ በሚያስፈልገን ጊዜ በሁሉን ቻይነቱ ይገለጣል፦ በዓለትነቱ ረደኤት ይመጣል፤ አምባ ሆኖ ይቆማል፣ መድኃኒት ሆኖ ሊውጠን እንዲሁም እንዲያበቃልን ካነቀን ይታደገናል። ይህን ታላቅ አምላክ ብንተማመንበት በእውነት እንደ ዳዊት ‘’ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው’’ ብንል አናፍርም።