በመጨረሻ ዘመን ይሆናል የተባለው እየሆነ፣ ቀረ የሚባለው ጥቂት ሆኖ እያለ የአዳም ልጆች ዘመኑን በጥልቅ ብናየው፣ ብናተኩርበት ተጥቃሚ እንደምንሆን መገንዘብ መልካም ነው፤ ጊዜው ካለፉት ጊዜያቶች ጋር እየተነጻጸረ፣ ሰአቱ ካለፉት ሰአቶች ጋር እየተመዘነ፣ ወቅቱ ከሄዱት ጋር ተመዝኖ ሁኔታው የሚፈቅደውን ሳይሆን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መሆን የነበረበትን ብናስተውል መልካም ነው። ዋስትና ያለው ህይወት ያስፈልገናልና፣ አለም ወደ ጥፋት ስትንደረደር አብረን እይተንደረደርን ከሆነ ዛሬ አንድ ማስጥንቀቂያ ከልባችን ቢደርስ ደግሞ ቆም ብንል ወደ ማምለጫ አምላክ ፊታችንን ብንመልስ፣ ልባችንንም ብናቀና ይህ መሻት በእኛ በኩል ሊኖር ይገባል።
‘’ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።’’ (ራእ. 22:10-11)
ይህ ቃል ከተነገረ ሺህ አመቶች አልፈዋል፤ ሆኖም ማሳሰቢያው በየእለቱ አዲስ ነው፣ ማስጠንቀቂያው ትኩስ ነው፣ የእግዚአብሄር ቃል የማይለወጥ ነውና።
ነገር ግን እየሆነ ያለው ሌላ ነው፦ እውነትን እንዳንይዝ የሚያምታታ መንፈስ ስንት አለ፣ እንዳንሰክን እያወከ የሚነካካ፣ ተስፋችንን በእውነት ላይ እንዳናሳርፍ የሚነቀንቅ እውቀትና ውዥንብር ላይ ወድቀን እንድንሳፈፍ አእምሮአችንን የሚያወዛግብ ክፉ ትምህርት አለ።
‘’ፈሪሳውያንም ጻፎችም፦ ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን ይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው፦ ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።’’ (ማር.7:5-9)
በመጨረሻው ዘመን ላይ ስንገኝ የሚሆኑት በሙሉ ከሃዋርያት ዘመን ጀምረው የቀጠሉ ናቸው፤ በዚያን የሃዋርያት ዘመን በህዝብ መሃል ያሉ ጠማማ ትምህርት አስተማሪዎች ህዝብ እያሳቱና በቃሉ ላይ እየዘበቱ የሚጣሉት ከእግዚአብሄር ጋር እንደነበር ሁሉ ዛሬም ያው አዝማሚያ ሳያቆም እየሆነ ነው። በሌላ በኩል እነዚህን ሰዎች በመስማት እንዳንምታታ፣ ድርጊታቸውን እያየንምነፍሳችን እንዳትጨነቅ በቃሉ መታመን ግዴታ ነው። ነገር ግን እስከአሁን ድረስ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ህይወት መንገድ የሚሰርጉና እንቅፋት የሚያኖሩ መሰናክሎች ጥቂት አይደሉም። መጽሃፍ በሃሰት ባህሪያቸውና ትምህርታቸው እንቅፋት ስለሆኑ ሰዎች ማንሳት የሚጀምረው ከቀድሞ ጀምሮከመነሻቸው በመምዘዝ ነው፦ ሐሰተኞች ነቢያት እግዚአብሄር ተገልጦ በሚሰራበት አካባቢ ነበሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሄር በመረጣቸው በሕዝቡ መካከል እንኳን ሊያሳስቱና ወደ ጥፋት ሊመሩ ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ወንጌል እየታወጀ ባለበት በዚህ ዘመን፣ እግዚአብሄር ከሰጠው የመዳን ትምህርት ጋር እየሰራ ባለበት በዚህ ትውልድ መሃልም እንዲሁ ሐሰተኞች አስተማሪዎች በሰፊው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፦ ደረቅ ትምህርት፣ ጥፋትና ማባበል የተደባለቁበት ትምህርት፣ ለአለምና ለስጋ ተመቻችቶ የሚቀርብ ትምህርትም አላቸው። ትምህርቱ በቀጥታ አመጽን ገልጦ የሚያስተምር ሳይሆን በስውር በመንቀሳቀስ የጽድቅ መንገድ እንዲጠረጠር፣ ድፍረትን ለሃሰት አስተማሪዎች በመስጠት፣ ስጋዊ ፍላጎትን መንፈሳዊነት አላብሶ በማቅረብና እውነተኞችን በማሳጣት ላይ አትኩሮ የሚሰራ ነው።
በሃሰት መንፈስ እየተመሩ እውነተኛውን አምላክ የሚቃወሙ ከወንጌሉ ጋር የሚጣሉ ናቸው፤ በሚነዱበት መንፈስ ልክ ቃሉን የሚገዳደሩና የሚያጣምሙም ናቸው፤ እነርሱ የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው ለውድቀታቸው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው በእግዚአብሄር ህዝብ መሃል ማስገባት የሚችሉ መሆናቸውን ቃሉ ያሳያል። የዋጃቸውን ጌታ ደሙን አፍስሶ የሃጢያት ስርየትን የሰጠውን ክርስቶስ ኢየሱስ መካድ ማለት ከባድ ፍርድ መሸከም ማለት ነው፤ የሚነዱበት ይህ መንፈስ እንደምን ጨካኝ እንደሆነ ማየት ይቻላል፤ ይህ መንፈስ ተላላፊም ነው፣ ስለዚህ ከራሳቸው አልፎ ሌሎችን በማባበል የሚያስቱበት መንገድ ከመንፈሳዊ አሰራር ጋር የሚገናኝ ስለመሆኑ የሚታይ እውነት ነው፤ በ2ጴጥ. 2:2-6 ላይ ያለው ቃል እንዲህ ይላል፦
‘’ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም። እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።’’
የእግዚአብሄር ቃል ከአሳቾች ጋር የሚተባበሩትን የሚዳሩ ሲል አጸያፊ ስራ እንደሚሰሩ ያሳያል፤ እውነትን ከልብ አውጥተው የሚወረውሩ በሰው ልጆች ፊት ተራ ነገር እንዲመስል የሚሰሩ፣ የራስ ጥፋታቸው አስፈሪ የሆነ ሰራተኞች ናቸው። በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ከእግዚአብሄር ጋር የሚላተሙ እንደሚደቅቁ ይህ የፍርድ ቃል ያሳያል።
የመጨረሻው ዘመን ሃሰትኛ አስተማሪዎች አንዱ መለያቸው ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን በልበ-ሙሉነት ማዋረዳቸው፣ ማንጉዋጠጣቸውና መሳደባቸው ነው፤ እያንዳንዱ አካሄድ ግን ዋጋ ያስከፍላል፤ ክፉ መናፍስት እንዳያስተውሉ፣ እግዚአብሄርን ፈርተውም ወደ ንሰሃ እንዳይገቡ ህሊናቸውን በመዝጋት ለፍርድ አዘጋጅተዋቸዋልና፤ ቃሉ በዚህ በመጨረሻ ዘመን ላይ እንዲህ ፍርድ ውስጥ እስከመግባት የሚያስደፍር ድርጊት ውስጥ ከመግባት በፊት የእግዚአብሄርን ፍርድ አስቦ መፍራት ውስጥ እንዲገባ አስቀድሞ የተሰጡ ምሳሌዎች ያሳስባሉ፤ ሃሰተኞች በሙሉ ይህን እንዲመለከቱና እንዲስተካከሉ ሲገባ ያን ባለማድረጋቸው እግዚአብሄር ሲገለጥ የሚሆነው ምን እንደሆነ ቃሉ ያሳያል፦
‘’ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ።’’ ይላል።
ሃሰተኛ አስተማሪዎች ከሚያዩትና ከሚሰሙት የእግዚአብሄር ነገር ፈቀቅ ብለው ከቃሉ እውቅና ውጪ በሆነ አሰራር በራሳቸው ፍልስፍና ይመራሉ፤ ይህ አካሄዳቸው የልባቸውን እንዲያስተምሩያደፋፍራቸዋል፤ ሁሌም በዚህ ከእውነት ጋር ይጋጫሉ። እግዚአብሄር ግን ህዝብን ከእግዚአብሄር በሚለዩት ላይ ፍርዱን ተናግሮአል፦
‘’በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ።አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።’’ (ዘዳ.13:1-4)
መቼም ይሁን መች ሃሰተኛ ነቢይ በእግዚአብሄር ህዝብ መሃል ሊነሳ ይችላል፣ ቃሉን እየሰበከ በሚያባብልና በተለየ አስደናቂ አሰራር ሊገለጥ ይችላል፤ ያኔ በእግዚአብሄር ላይ የተናገረው ሃሰት፣ ያቀደው የክህደት አካሄድ በሚሰራው ታምራት ይሸፈናል፣ በዚህ አመጣጥ የሚገለጥ ሃሰተኛ ነቢይና አስተማሪ እውነተኛ መስሎ ያሳምናልና ማወቂያና መፈተኛው ተአምራቱም ምልክቱም አይሁን እያለን ነው ቃሉ፤ ስለዚህ አምልኮው ብቻ መመዘኛው ይሁን፦ ፍሬው ይመርመር፣ ይህ ነቢይ ለማን ይሰግዳል፣ ለማን ይዘምራል፣ ማንን ይመሰክራል፣ ማንን ይጠራል፣ ከማን ጋር ይወዳጃል፣ ማንን ያስቀድማል? በተረፈ የሚያስደንቀው ተግባሩ የእውነተኛው አምላክ ባሪያ ያሰኘዋል በሚል የተሳሳተ ድምድሜ እንዳንጠመድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻል።
የእግዚአብሄር ቁጣ ሃሰተኞችን ሰምቶ በሚከተል ላይ የሆናል
‘’ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም’’ (2ጴጥ. 2:9-10)
ትውልድ ከእግዚአብሄር እውነት እጦት የተነሳ የሚስተው ልቡ የሚጠፋበት አሳችን የሚቃወምበት የእውነት ቃል ስለሌለው ነው፤ ያም እጥረት ወደጥፋት እየመራው ነው። አሳቾች ግን በመሃከላችን ሲገቡና በፍቅር በምንኖርበት ህብረታችን ውስጥ ሲቀላቀሉ ከፍሬያቸው በመለየት ልንጠነቀቃቸው ይገባል።
‘’ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ።’’
ስለዚህ በመሃከላችን ሰርገው የገቡ ቢኖሩ ፍሬያቸው ምን እንደሚመስል እንድናውቅ እግዚአብሄር ተግባራቸውን ግልጥ አድርጎ ያሳያል፣ ሃሰተኞች እነዚህን በማድረግ ይገለጣሉ፦
– በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል
– ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከቅዱሳን ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ
– ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው
– የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ
– መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው
– የተረገሙ ናቸው
– ቅንን መንገድ ትተው የተሳሳቱ፣ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ የተከተሉ ናቸው
– ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው ናቸው
– እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች ናቸው
– በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው
– ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉ
– በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ
– በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ያታልላሉ
– ጌትነትንም የሚንቁትን ይወዳጃሉ
– ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም
– በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ
በመጨረሻ ዘመን ያለው የሃሰት ትምህርት እጅግ ብርቱ ነው፣ የሰማነው እየሰማነው ያለውም ትንቢት እጅግ አሳሳች ነው፣ ድንቅና ታምራቱ ብዙዎችን እያስካደ ነው፤ ሰዎች በቃሉ ላይ የተጣበቁ ካልሆነ በነርሱ ሽንገላ ከመጠለፍ አያመልጡም፣ በእግዚአብሄር ጸጋ ካልታገዙ በቀር አሳሳች ወጥመዳቸውን ብዙዎች አይለዩም፣ ስለዚህ የሃዋርያትና የነብያትን ድምጽ ሰምተው የመለየት ሃይልን እግዚአብሄር እንዲሰጥ መለመን ይገባል፣ ሌላ አሸናፊ መንገድ የለምና።
‘’በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል።አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።’’ (2ጴጥ. 2:22-24)