ለህጉ መልስ ያለው ከጸጋው ዘንድ ነው
‘’…እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።’’ (ሮሜ. 3:9-12)
ሰው ከእግዚአብሄር ፊት ወድቆአልና ቅድስና በራሱ አካሄድ አይገለጥም፣ በችሎታው መለኪያውን አያሟላም፤ የቅድስና እውነት በእግዚአብሄር የቅድስና ልክ የሚለካ ከሆነ የቱ ሰው በዚያ ልክ ሊገለጥ ይችላል? ይሄን ይሆናል ብሎ መቀበል ፈጽሞ አይቻልም። ህግ ቅድስናን ከሰው ፈልጎ ሊያገኘው እንዳልቻለ (እስራኤል ከልኬቱ በታች ወድቆ የህጉን ጥያቄ ሊፈጽም ያለመቻሉን) አሳይቶአል። እግዚአብሄር ግን አንድ ታላቅ መልስ አዘጋጀ!
አስቀድሞ እግዚአብሄር ከግብጽ የወጣው ህዝብ ተቀድሶ በፊቱ የሚቆምበትን የቅድስና ቃል ሰጠው፤ ይህም በዘሌ.19:1-4 ላይ እንዲህ ይላል፦
‘’እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’’ አለው።
አጠቃላይ እውነታው እንደሚያሳየን እግዚአብሄር ቅዱስ በመሆኑ ቅድስናን በሰው ዘንድ ማየት ይሻል፤ ያለ ቅድስና እግዚአብሄርን ማየት አይቻልም የሚለው የቅድስና አዋጅ ሌሎች አማራጮች ላይ በሩን ይዘጋል ማለት ነው፤ ታዲያ ሰው በምን መንፈሳዊ አቅሙ ይቀደስ? ከእግዚአሄር ተቀብሎ የነበረው አቅም በሃጢያት ጉልበት አንዴ እስከ ለዘላለም ተሰብሮአልና። ሃይል ከሌላ ስፍራ ካልመጣ የሰው ነገር በዚህ በኩል አብቅቶለታል፤ ሃዋርያው ጳውሎስ ይህን ሊመሰክር የሚከተለውን ተናግሮአል፦
‘’… ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።’’ (ሮሜ.3:20-24)
የህጉ ቃል የተሻረ አይደለም፣ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ እያለ ዛሬም ይጣራል፤ ይህን ሲል ግን አንድ አስችሎ የሚያኖርበትን አሰራር በአዲስ ኪዳን ልኮአል ነው ዋናው ነገር።
የእግዚአብሔር ቅድስና እንዴት ይገለጣል? የእርሱ ቅድስና ከራሱ ባህሪ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እግዚአብሄርን በማወቅና ባህሪውን በመረዳት የርሱን ቅድስና እንረዳለን። ቅድስና ለሰዎች ሲገለጥ የእግዚአብሔር ማንነት ለሰዎች ይገለጣል፤ እንዲሁም ሰው ያን በማስተዋሉ ምክኒያት መቀደስን አጥብቆ ከአምላኩ ይሻል፤ እግዚአብሄርም ያን መሻቱን አክብሮ በጸጋ ሰውን የቅድሰናው በረከት ተካፋይ ያደርገዋል። እኛም እግዚአብሄርን እያወቅን ስንሄድ በእርሱ ዘንድ ያለውን ጽድቅ ወደ ማወቅ እንደርሳለን።
በጻድቅ አምላክ ዘንድ ፍጹም ጽድቅ አለ። ያም በመሆኑ በእርሱ ዘንድ ምንም ዓይነት ዓመፅ የለም። በአምላካችን ውስጥ ፍጹም የሞራል ንጽህና ይገኛል። በእርሱ ዘንድ ያለውን ጸጋ አጥብቀን ስንሻ እነዚህንና ሌሎች የሚያስፈልጉን ነገሮች ከእርሱ እንደምንቀበል ጥርጥር የለውም።
ሰው በእግዚአብሄር ሲጠራ የጽድቅ ከፍታው እየተገመተና የሚመጥን ብቃት ይኖረው ዘንድ ተመርምሮ ከቶ አይደለም፤ የእግዚአብሄርን የጽድቅ ልክ የሰው ልጆች ልናሟላ ከቶ ስለማንችል ይህንን ልናስብ አይገባም። ስለዚህ እግዚአብሄር ሲጠራን በሃጢያት ህግ አገዛዝ ስር ሳለን እንዲሁም በኃጢአት ሃይል ታስረንና በሃጢያት ጉልበት ተጨንቀን ሳለን ነበር። በዚህ ምክኒያት በሕግ በኩል ሲታይ ምንም አይነት ማምለጫና ተስፋ አልነበረንም። እንዲያውም ሕግ ሃጢያታችንን አጉልቶ የሚያሳይ መሳርያ ሆኖ ፍርዳችንን የሚያፋጥን አዋጅ ሆነ፤ ቃሉ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ እንደማይጸድቅ ስለደመደመ ህግን በመጠበቅ ጽድቅን ማግኘት ከቶ የማይቻል መሆኑ ታየ። በሌላ በኩል የእግዚአብሔር ጸጋ የእኛን ድካም አግዞአል፤ የሚያስችል የእግዚአብሄር እርዳታ ሆኖ በህይወታችን ተገልጦአል፤ በመገለጡም ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንድንችል አድርጎአል። ስለዚህ የእግዚአብሄር ጸጋ ባይኖር የኃጢአት ይቅርታ ባልኖረ ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ ጉልበትና በተቀበልነው እምነት አማካኝነት መጽደቅ ችለናል። በጸጋ በምናገኘው መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ እንዲሁ እድገት አለ።
’’እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።’’ (1ጴጥ. 1:14 -18)
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች መሆን ያልቻልነው ቅድስና በአዲስ ኪዳን በተቀበልነው የቅድስና መንፈስ መሆንን አግኝተናል። የሰው ልጅ ወደ ቅድስና ጥሪ የሚደረግለት ከአምላኩ ጋር የሚሄድበትን የህይወት ጥራት እንዲያገኝ ሲሆን የቅድስናውም ምንጭ እግዚአብሄር ራሱ ነው፤ ያንንም ፀጋውን በመስጠት ብቁ እንዲሆን ያስችለዋል።
ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሰረት የሰውን የቅድስና ልክ በጸጋው ጉልበት ከፍ በማድረግ እኛን ወደ ራሱ ያቀርባል። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ቅድስናን ጠብቀው ከሚያረክሳቸው ባእድ አምልኮ እንዲርቁና የአምላካቸውን ትእዛዝ ብቻ እንዲጠብቁ ለማድረግ በህግ በኩል አስጠንቅቆአቸው ነበር። ይህ የእግዚአብሄር ትእዛዝ በአዲስ ኪዳን በትክክል ሊፈጸም የቻለው ጸጋን የተሞላው ጌታ በመካከላችን በማደሩና ለያንዳንዳችን ከጸጋው ከፍሎ ስለሰጠን ነው።
‘’እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።’’ (ዮሃ.1:16-17)
ህግ በሙሴ ተሰጠ፣ ነገር ግን በህጉ ሊጸድቅ የቻለ አንድም ሰው አልነበረም። ጸጋ ስለተገለጠ ግን ኢየሱስን ያመነ ሁሉ አንዳችም ከጽድቅና ቅድስና የሚጎድል አልሆነም። ህጉ እኛን ተመለከተ፣ ከእኛ ግን ምንም ጽድቅ ሊያወጣ አልቻለም። ጽድቅ ከኢየሱስ ወጥቶ በጸጋው በኩል ወደ እኛ በመግባቱ ግን ሙሉ ጽድቅ በእኛ ህይወት ተገኘ፣ ይህም እግዚአብሄር በክርስቶስ በኩል የፈጸመው ፈቃዱ ነበር።
ፍቅር የህጉም ጥያቄ ነው
እግዚአብሄር አምላክህን ውደድ ሲባል የውዴታው ልክ ሙሉ ልብን፣ ሙሉ የነፍስ ፈቃድን፣ ሙሉ አሳብን፣ ሙሉ ሃይልን የሚጠይቅ ነው። ይህም በተገዛ ማንነትና በልበ-ሙሉነት ሲፈጸም የሚሳካ ብቻ ነው። አምልካችንን መውደዳችን የሚታወቀው ለርሱ አሳብና ፈቃድ ቅድሚያ በመስጠት፣ በውዴታ እርሱን በማምለክ፣ ቃሉን በፍቅር በመቀበልና የርሱን ነገር ብቻ አድምቀን በማሳየት በኩል ነው። ለእግዚአብሄር የተቆጠበ ሃይል ለምን ይተርፋል? ታናሽዋን ጉልበታችንን ብንሰጥ፣ በፍቅር ለእግዚአብሄር ብንሰዋውም ከርሱ ዘንድ የምንቀበለው ሃይል በመንፈሳዊው አለም ላይ ታላቅ ተጽእኖ የሚፈጥር ነው። ልባችን ደግሞ ብዙ ነገር ይመላለስበታል፣ ብዙ ነገር ይታጨቅበታል፣ ክፋትና በጎነት፣ ከፍታና ዝቅታ፣ ሩቅና ቅርብ የሆነ ነገር ሁሉ ያለመከልከል ይገዛዋል፤ ልብ አመጽን መታዘዝንም ይዞአል፤ ክብሩን ውርደቱንም ይዞአል፤ የስጋው የመንፈሱም ነገር ሳይቀር ታትሞበታል። ከዚህ ነገር ሁሉ መሃል የእግዚአብሄር ነገር ጎልቶ ከወጣ ድንቅ መለወጥ ይሆናል፤ እግዚአብሄር በዚያ እንዲከብርም በልብ የታጨቀው ሁሉ ወድቆ እግዚአብሄር ብቻ እንዲጎላ ሰው በራሱ ላይ ቢወስን ፍጹም የህይወት ለውጥ ይከተላል።
‘’ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፡- መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።’’ (ማቴ. 22:35-40)
እግዚአብሄርን መውደድ ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖር ዋነኛ መለኪያ ነው፤ እርሱን በመውደድ ህጉን መፈጸም ይቻላል፤ እግዚአብሄር አቅምን ይሰጣልና፤ እግዚአብሄርን ስንወድ ወደ እግዚአብሄር የተጠጋን ሰው በፍቅር እንድንቀበል ያስችላል፤ ፍቅር በአምላካችን ማህበር ውስጥም ገዢ ሆኖ እንዲሰፍንና በሁሉም ዘንድ አንዱ አምላክ እንዲነግስ ከፍ ያለው እግዚአብሄርን የመውደድ እውቀት ሊኖር ይገባል። እግዚአብሄር ህግን ከሰጠ በኋላ በህጉ መጽሃፍ የተዘረዘረውን ሁሉ በሁለት ትእዛዛት ቋጥሮአል። ስለዚህ ምክኒያት በህጉ ውስጥ ያለ ማንኛውም ነገር ከነዚህ ሁለት ትእዛዞች በአንደኛው ላይ ይወድቃል ወይም በዚያ ውስጥ ይጠቃልላል ማለት ነው።
እግዚአብሄርን በመውደድ ውስጥ የእግዚአብሄር ሁሉን ቻይነት እውቀት ይገኛል፦ ስለዚህ እርሱ በቀረበን ጊዜ በልባችን ያለውን አሳብ ይገልጣል፣ ፍላጎታችን፣ ምኞታችን፣ ፈቃዳችንም ጭምር በርሱ ፊት ይታወቃል፣ ስለዚህ እርሱን በመውደዳችን ተማምነን ለኔ ያስብልኛል እንላለን፣ አይጥለኝም እንላለን፣ የምወደው አምላክ ይመክትልኛል፣ በፈተናዬ ቀርቦ ይረዳኛል፣ ጠላቴን ያሸንፍልኛል እንላለን፣ በነዚህ ውስጥ ሁሌም እንወደዋለን።
እግዚአብሄርን በሙሉ ልብ ስንወደው በፍጹም እንወደዋለን፣ ያለማንም ጉትጎታና ያለምንም ምክኒያት። ፍቅራችንን ለርሱ ስንገልጥ በልባችን ያለውን ወደርሱ እናፈሳለን፤ በነፍሳችን ውስጥ አይቀርም፣ ሃሳባችን አይሰውረውም። እርሱም ለእኛ የሚገባንን ያፈሰዋል። እኛ የምንሰጠው እጅግ ጥቂቱን ነው፣ እርሱ ግን የሚሰጠን እንደ ባለጠግነቱ መጠን ነው፤ እንዲህ እንዲሆን ግን በፍጹም ፍቅር ልንወደው ተገቢ ነው። ፍቅራችን ያለግብዝነት የሆነ፣ እንካ በእንካ ያልሆነ፣ ስጋዊና አለማዊ ሽታ የሌለበት መሆን ይገባዋል። የማይለወጥ አምላክ እንዲሰራና በኛ ያለው ፈቃዱ እንዲፈጸም በያንዳንዱ የህይወት ክፍላችን ለርሱ ያለንን ፍቅር ማንጸባረቅ ይገባል።
ሰው ለእግዚአብሄር ሲለይ ቅዱስ ይሆናል፣ ለርሱ የተለየ ምንምና ማንም ለሌላ ነገር እንዳይሆን እርኩስ ሆኖአል (ለእግዚአብሄር የተቀደሰ ለአለም እንደ እርኩስ ነገር ጥቅም ላይ መዋል የማይችል ሲሆን እንዲሁ ለአጋንንት የተቀደሰ ለእግዚአብሄር የማይቀርብ እርኩስ ነው)። እግዚአብሄርም ለርሱ የተለዩ ወገኖች እንድንሆን በልጁ ደም በማጠብ የርሱ ያደርገናል፤ ደሙንም የሚሰጠን በተገለጠው የጸጋ አሰራር በኩል ነው።
‘’ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።’’ (ኤፌ.1:4-7)
እግዚአብሄር ከአለማት መፈጠር በፊት ትኩረቱን በሰው ልጅ ላይ ያደረገ ታላቅ እቅድ ነበረው፤ እቅዱም እያንዳንዳችን በርሱ አሰራር ልጆቹ ተደርገን በፍቅር የተሞላንና ከእርስ በርስ ፍቅር ባለፈ አምላክን የሚወድ ማንነት የተላበስን እንድንሆን ለዚህም የክርስቶስን የማብቃት ስራ እርሱ ራሱ እንዳዘጋጀ የሚያሳይ ነው፤ የክርስቶስ በስጋ መገለጥ፣ መከራ መቀበል፣ መሞትና ከሞት መነሳት እኛን ለመንግስቱ ብቁ የሚያደርግበት አሰራር እንዲሆን እግዚአብሄር ፍጥረታትን ከመፍጠሩ በፊት ያቀደው እንደነበር ሃዋርያው ያስተምረናል። ይህን የሰራ ጌታ ስራው በህይወታችን ይገለጥ ዘንድ የጸጋ አሰራርን አስቀድሞ ገልጦአል።
ራስን ማእከል ባደረገ አለም ውስጥ ከራስ ውጪ ለሌላ የሚተርፍ የፍቅር መስዋእት ማቅረብና ሰዎችን በዚህ መንፈስ ማስተናገድ አዳጋች ነው፤ በእግዚአብሄር መንግስት ለመኖር ምርጫው ያደረገ ሰው ግን በአዲስ መንፈሳዊ አሰራር ውስጥ ማለፍና የተገለጠው የፍቅር መንገድ ላይ መመላለስ አይከብደውም፤ የጌታን አሳብ ለማስተናገድ የወሰነ በመሆኑ እንደ እግዚአብሄር አሳብ ለመኖር ፈቃደኛ ነው፤ አዲስ ልብና መንፈስ ያለው በመሆኑ፣ በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሰረተ ህይወት ስላለውም ያን ያደርግ ዘንድ አያዳግተውም። ይህን የሚመለከት አምላክ እንደ ባለጠግነቱ መጠን ለልጆቹ አስቻይ ጸጋን ይሰጣል፣ የሰጠውን ጸጋ በእምነት ያበዛል፣ ያሳድጋልም።