ህያው የእግዚአብሄር ቃል ህይወትን ይሰጣል፣ ያም ብቻ አይደለም መንፈስን ያነቃል፣ ሃይልን ያጎናጽፋል።
‘’ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ።’’ (ዘዳ. 8:3)
የእግዚአብሄርን ቃል ድምጽ የሚያከብሩ ቅዱሳን አትኩሮታቸው ዘመናትን የሚሻገረው ግን የማይሻረው ህያው ቃሉ ላይ ነው። ሆኖም ብዙ ትውልድ የህያው ቃሉን ታላቅነት ባለማስተዋል የተናገረበትን መንፈስ በሰዋዊ ቅኝት ለውጠዋል፤ ቃሉ ሰውን እኩል የሚያገለግል፣ ትውልድ የማይመርጥ፣ የማይለዋወጥ፣ መነሻው የሰው ፈቃድ ወይም አሳብ ስላልሆነ የማይቀያየር ነው። የእግዚአብሄር ቃል ማረጋገጫ ሲሰጥ:-
‘’ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።’’(ዮሃ. 12:47-50)
ንጉስ ዳዊት ልቡ በአምላኩ ፊት የቀና ንጉስ ነበር፤ እርሱ ከህጻንነቱ አንስቶ በትህትና ቃሉን የተከተለና በእርሱ የታመነ ነበር። በሚገጥመው ነገር ሁሉ ቃሉን ከፍ ሲያደርግ ይታያል፤ ለቃሉ ክብር ይሰጣል፣ እግዚአብሄርን በቃሉ ያሳስባል።
የእግዚአብሔር ቃል ለሚሹት ማጽናኛንና ተስፋን እንዲሁም በሀዘን ውስጥ ላሉ እና ለሚሰቃዩ ብርታት እና መጽኛ የሚሰጥ ነው። ንጉስ ዳዊት በመዝሙር 23 ውስጥ በእግዚአብሄር ያለውን መጽናናት ይገልጻል። ይህ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ቃል በየትውልዱ የተነሱ ሰዎችን እያጽናና ከትውልድ ትውልድ የቀጠለ ቃል ነው። አንድ ሰው በየትኛውም የእምነት መንገድ ላይ ቢሆን ህያው ቃሉን ብቻ ከሰማ የውስጥ መነካትና መለወጥ ይታይበታል፤ ምክኒያቱም የቃሉ የማጽናናት፣ ልብን የመንካትና የመለወጥ ችሎታ ስላለው ነው።
በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ መንቃት፣ መጠባበቅ፣ መፈለግና እርሱን ለመገናኘት ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ናቸው፤ ይህ ሁሉ የሚቻለውም በእግዚአብሄር ቃል ሃይል ብቻ ነው፤ የመንፈስ ድምጽ ለመንፈሳችን ሲመጣ መንፈስ ነቅቶ እንዲጠብቅ የቃሉ ሃይል ያነቃዋል። በዚህ በኩል የእግዚአብሄርን ቃል ክብር የማያስተውሉ እጅግ የሚጎዱ ናቸው።
‘’ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።’’(ሉቃ.12:39-40)
የእግዚአብሄር ቃል በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እግዚአብሔር እንደሚናገር ያመለክታል፣ በዚህ አቅጣጫ ተዘጋጅቶ መጠበቅ በተለያየ መንገድ ይገናኘን ዘንድ ያስችላል። ሰው ከጌታ ኢየሱስ መገለጥ(ዳግም መመለስ በፊት) ወደ እርሱ ይጠራል ያልያም እርሱ ሲመለስ ይገናኘዋል፤ ውጤቱ ደግሞ በእኛ ዝግጅትና መንፈሳዊ አቋም ላይ የተመሰረተ ነው፤ ቃሉም ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለብን ያስረዳል።
ይህን ታላቅ አጋጣሚ በድል ለመወጣት በህይወታችን ዝግጅት ስናደርግ መሰረቱ ቃሉ ይሆናል ማለት ነው። ለመዘጋጀትም ምሪት የሚሰጥ የሚያንጽም ብቸኛው የእውቀት ምንጭ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ ይህን ለማድረግ ሃይል አለው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በቃሉ ለሕይወታችን ጌታን ለመቀበል እንዴት መዘጋጀት እንዳለብን ያሳየናል።
ቃሉ ጌታ ኢየሱስ እንዳዳነን ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ሞት እና ኩነኔ በኃጢአት ምክንያት እንደመጣና ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞት ያለብንን የሞት እዳ እንደከፈለና እንደዋጀን ይገልጻል። ይህ የወንጌል ዋና መልእክት ነው። ጌታ ኢየሱስን በማመን የመዳን ጸጋን እንድንቀበል የሰው ልጆችን ይጣራል። እርሱ በሞቱ በቆረሰው ስጋውና ባፈሰሰው ደሙ ሊያድነን ከውሃና ከመንፈስ ወልዶም የእግዚአብሄር ልጆች የምንሆንበትን ጸጋ ሰጥቶናልና፤ (ይህም በእምነት፣ ንስሐ በመግባትና ለሃጢያት ስርየት በመጠመቅ ደህንነት የምናገኝበት መንገድ ነው፣ሃሥ. 2፡37-38)።
‘’የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።’’(ማር. 8:31)
ከዳንንበት ቀን አንስቶ ሁልጊዜ ያለነቀፋ በፊቱ እንድንኖር እግዚአብሔር ንስሐ እንድንገባ ያሳስባል። በትህትና በመታዘዛቸው እና ንስሃ በመግባታቸው ምክንያት ታላቅ በረከትን ለተቀበሉ ሁሉ ቃሉ በምሳሌዎች የተሞላ ነው። የደስታ ህይወት እንድንኖር አምላካችንን በትክክል ስላሳወቀንም እርሱን እያመለክን እንድንቀጥል ድጋፍ ያደርጋል።
እግዚአብሄርን ያገለገሉ ባሪያዎቹ ሃዋርያት ለቃሉ ክብር እየሰጡ የተገዙ ነበሩ፤ ከነርሱ የተማርነው የቃሉ ህያውነት የመስቀሉን ቃል እንድናነሳ፣ እንድንመሰክር፣ ጌታን በነገር ሁሉ እንድናመሰግንም የሚያስችል ስለመሆኑ ነው። በፍርድ ቀንም በፊቱ በሞገስ ለመቆም እንድንዘጋጅ እለት እለት ቃሉ መመሪያ ይሰጣል። በቃሉ ስልጣን በማመን እንደገና መወለድን እንደተቀበልን ሁሉ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያስችለናል፤ በመንፈስ ቅዱስ ሃይልም የክርስትናን ህይወት በታማኝነት እና በውጤታማነት ለመኖር የሚያግዘን ነው።
‘’ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው።ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ’’ (ሃስ. 2:39-42)
ቃሉ በእኛ ውስጥ ሕያው ሆኖ በቀጣይነት እንዲሰራ የእግዚአሄር መንፈስ በውስጣችን ማደር አለበት፣ በመንፈስ የሆነ የቃሉ ስራም የጌታን ትንሣኤ ያሳስባል፣ ለእርሱ ልንዘጋጅ እንዲገባም ያሳስበናል፤ ትንሳኤውን በውስጣችን እያወጀም ቃሉ ወደ ክርስቶስ ይስበናል። ቃሉ ካላስተማረንና ካልተናገረን ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ልናውቅ ስለማንችል ግምት ብቻ ተናጋሪ ያደርጋል፣ ይህም እምነት እንዳይኖረን እንቅፋት የሚሆን ነው።
‘’ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተ እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ። እንደ ብልጥግና ሁሉ በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ። ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ። በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። ለባሪያህ መልካም አድርግ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ።’’(መዝ.119፡10-16)
ትእዛዝ ሃላፊነት ስለሚያስከትል ለብዙዎች ሸክም ነው፣ የእግዚአብሄር ሰው የሆነው ዳዊት ግን ከአምላኩ አፍ የሰማው ቃል ያስደስተው ትእዛዙንም በደስታ ይመለከት እንደነበር ቃሉ ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል ከውስጥ የሚወጣ ምስጋና በመስጠት የደስታ ዝማሬዎችን እንድናፈልቅ ያነሳሳል፤ የቃሉ ፍቅር በምንኖርበት ህይወት ደስታ እንዲኖረንና ጌታ ሲመጣ የምናገኘውን የዘላለም ህይወት እንድንለማመድ የሚያደርግ ነው።
‘’አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።’’ (መዝ.119:97-103)
የእግዚአብሄር ልጆች ከእግዚአብሄር ስጦታ የተነሳ አስተዋይ ልቦና የታደሉ ናቸው፤ መናፍስት የሰውን ልጆች ተቆጣጥረው እንደሚሰጡት እውቀት፣ እንደሚናገሩትም የአለም ጥበብ ያለ ሳይሆን ከሰማያዊ እውቀት የተካፈለ ማስተዋል ያለበት ነገር ነው፤ የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ማግኘትና ማወቅ ላይ ያተኮረ ሰው በረጅም እድሜ ዘመን ማስተዋል ካከማቸ ሰው እንደሚልቅ ከላይ ባለው ቃል ውስጥ ተመልክቶአል።
‘’ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው። መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ። አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፤ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፤ እንደ ቃልህ አድነኝ። ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ።’’ (መዝ.119፡167-172)
ለነፍሳችን ልምላሜ እንዲሆን ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል የታመንነውን ያህል የእግዚአብሄር ሃይል ይሆንልናል፤ እግዚአብሄር በእርግጥ ይናገራል፣ ያኔ በንግግሩ ውስጥ ስራው ይታያል፣ እግዚአብሄር ይተነፍሳልም፣ በእስትንፋሱ ህያው ያደርጋል፤ እግዚአብሄር ስሙን ይገልጣል፣ በርሱም የጠላትን ሃይል ያደቅቃል፣ እርሱ አምላክ ነውና በሁሉም ላይ ሃይሉ ማንኛውንም ነገር ያደርጋል፤ አንድ አምላክ የእርሱ በሆነው ነገር ቸርነቱን፣ ምህረቱን፣ ማዳኑንና ሰላሙን ይሰጣል። ስለዚህ የእግዚአብሄር የሆነውን ለመቀበል ከቃሉ ጋር መጣበቅ፤ ከእግዚአብሄርም ጸጋ መቀበልን ይጠይቃል፦
ቃሉን ማንበብ
ቆላ.3፡16 ‘’የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ።’’
እግዚአብሄር በሚናገረው ቃሉ ውስጥ ያለው በረከት በተናገረውና በተጻፈው ቅዱስ መጽሃፍ ውስጥ ስለሰፈረ ያለመታከት በፍቅር እናንብበው፤ በረከት የያዘው ቃል ሲነበብ በአይን በኩል ገብቶ አእምሮና ልባችንን ይቆጣጠራል፣ ይፈውሳልም። ቃሉን በማንበብ መንፈሱን ወደ ህይወታችን እንጋብዛለን፣ ምክኒያቱም ቃሉ በባህሪው መንፈስ ስለሆነ።
‘’ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።’’(ዮሃ. 6:63)
የእግዚአብሄርን ቃል መሻትና ማንበብ እንደ እለት ምግብ ያለማቁዋረጥ ሊሆን ይገባል፤ ነፍስም የማያቁዋርጥ ምግብ ስለሚያስፈልጋት ባለመታከት ህይወትን ልንመግባት ይገባል።
አንዴ የቃሉ ሃይል በህይወታችን ውስጥ ከበረታና ልባችንን ከገዛው የቃሉ ፍቅር ቃሉን በየጊዜው እየተከታተልን እንድናነብ ያደርጋል።
ቃሉን መታዘዝ
መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብን በቂ ነው፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽመናል ብለን ብናስብ ስህተት ውስጥ እንወድቃለን። በእርግጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ተገቢ ነው፤ በማንበብ መንፈሳዊ እውቀት ስለምናገኝ፣ ህይወታችን ስለሚቃኝ፣ ከህጉ ታምራትን ስለምንቀበል፣ መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ በዚያ መንገድ ብቻ ስለምናገኝም ጭምር ነው። ሆኖም ባነበብነው መጠን ልንቀበለው፣ ልንሰማውና ወደተግባር ልንገባ ያስፈልጋል፤ በመሰረቱ ታዛዥነት እውቀትን ወደ ሃይል የሚቀይር መንገድ ስለሆነ በቃሉ የተገለጠውን ሃይል በህይወታችን ለውጥን እንዲፈጥር አሜን ብለን መታዘዝ ይፈልጋል። ኃይል የተሞላ መንፈሳዊ ኑሮ የሚመነጨው በትጋት ታዛዥነት ሲኖር ነው።
‘’ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።’’(1ሳሙ. 15:22)
ቃሉን ማወጅ
አዳኝ አምላክ የሚነገርለት፣ የሚመሰከርለት፣ የሚታወጅለትም አምላክ ነው፣ ሃዋርያቱ ያስታወቁን ይህንን ነው፦
‘’ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።’’(ቆላ.1:16-29)
ቃሉን በማንበብ እውቀት ተቀብለናል፣ ያነበብነውን በመታዘዛችን የህይወት ለውጥ ውስጥም ገብተናል፤ ይህ የህይወት ለውጥ ደግሞ ሌሎች ያልተለወጡ ጭምር አግኝተውት፣ አምነው ሊቀበሉና የህይወት ለውጥ ውስጥ ይገቡ ዘንድ ይገባል፤ የዚህ ሂደት አስጀማሪና ውጤታማ ባለቤት የቃሉ መስካሪ ነው።
ቃሉን ማካፈል ያን ሃይል በሌሎች ሰዎች ህይወት ውስጥ ማብዛት ነው። ቃሉን በእምነት ብናካፍል፣ ሌሎችንም ብናስተምር፣ ወንጌሉን ያልሰሙ አምነው እንዲቀየሩ መንገድ መራናቸው ማለት ነው። ከማያምኑ ጋር ህይወትን መካፈል የሚቻለው የህይወት እንጀራን በመቁረስና በመመገብ ነው፤ በማካፈልና የመራንን ቃል ሌሎችን እንዲመራ በማድረግ ነው።
ቃሉን ስናካፍል፣ እርስበርስም ስንከፋፈል የቃሉ ባለቤት በመሃከላችን ሲገኝ፣ ሲያስተምረን፣ ሲባርከንና መንገዱን ሲመራን እናያለን፤ ሌሎች እግዚአብሔርን እንዲያውቁ መለኮታዊ ኃይል ተካፍለውም የመንግስቱ ወራሽ እንዲሆኑ ስንነሳ የመንግስቱ ባለቤት ከእኛ ጋር የወጣል፤ የእግዚአብሄር አብሮነት በትግሉ ሜዳ ላይ እንደሚገለጥ በማመን እርሱን በእምነት አስቀድመን እንወጣ ዘንድ ይህ ጌታ በምህረት ያግዘን ይርዳንም።