ቃለ መለኮት(3…)

ቤተክርስቲያን

የህያው እግዚአብሄር ቅዱስ ቃል አመጸኛና ታዛዥ ላልሆኑ ሰዎች የትኩረት አቅጣጫ የተነፈገው፣ ቀዝቃዛ ስሜት በሚታይባቸው ቸልተኞች ተሸፍኖ ያለ፣ አሳቢነቱ ዝቅተኛና ትርጉሙ በማይሰማው ኢ-አማኝ አእምሮ ውስጥ ከንቱ የሚመስል ወይም ለፍጥረት ብዙም ፍላጎትና ጉጉት የማይፈጥርና የማይስብ ጉዳይ የሚመስል ነው። አለምም በማየት፣ በመዳሰስና በቀመር ስለምታምን በነዚህ ስጋዊ መታመኛ መሳሪያዎች የምትደገፍ ናት። እግዚአብሄር ግን ስለቃሉ በመናገር ያሳስባል፦
‘’እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት፦ ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። ስለዚህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።’’ (ህዝ.12:25-28)
እግዚአብሄርን በሚያምኑ ዘንድ የተለየ ልምምድና አካሄድ አለ፣ እርሱም በተናገረው ቃል አብዝቶ መታመንና በቃሉ እውቀትም መመራት መቻል ናቸው። ህያው አምላክ ይናገራል፣ እንደተናገረውም ይፈጽማል ብሎ ለመናገር ብርቱ በሆነ የእግዚአብሄር ምህረት ልንደገፍ ይገባል፤ ምክኒያቱም እንዳንታመን ሊያደንቅፉን የሚችሉ የስጋ፣ የአለምና የአጋንንት እውቀቶች ስላሉ ሲሆን እግዚአብሄር ግን በቃሉ ጉልበት እነዚህን አሸንፎልን ያቆመናል። ወደ እርሱ ስንጠጋ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን የሚፈጥረው ኃይል አለ።
ይህ ቃል ‘’ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው! ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት! ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ?’’ ይላል (ኢዮ. 26:2-4)።
ያንተ ሃይል በተለይ መንፈሳዊ ሃይል የሌለውን ትሁት የሚጎበኝ ሲሆን፣ ሃያልና ክፉ በሆኑ መናፍስት በቀላሉ የሚጠቃውን ደካማ ሰው በማየትህ፣ በመራራትህና በቸርነትህ በመጎብኘትህም ምንኛ ረዳኸው! ሰው እኮ ከአንተ ውጪ ባርያ ነው፣ የራሱ ወዳጅ ሰው የሚገዛው፣ የራሱ ስጋ የሚገዛው፣ የአጋንንት ሃይል፣ እውቀትና ማታለል የሚነዳው ሰው! እግዚአብሄር ለዚህ ምስኪን የሰው ልጅ፣ በቃሉ የሆነ መለኮታዊ ጥበብ ሰጥቶ ከመናፍስት በላይ ጠቢብና አዋቂ ሲያደርገው ያንን ሰው፣ ጥበብ ከቶ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት! ይህ በእርግጥ ያስደንቃል።
በአዲስ ኪዳን አጵሎስ የሚባል የመጽሃፍ አዋቂ እናገኛለን፤ ይህ ሰው በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እውቀት የበረታ ስለነበረ ነብያት ስለክርስቶስ የተናገሩትን በአስተውሎት የተከታተለና የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፤ የእግዚአብሄር ቃል በዚህ ሰው መንፈስ ላይ ታላቅ ጥበብ አኑሮ ስለነበር ከህጉና ከነቢያት ድምጽ ውስጥ ክርስቶስ ኢየሱስን እንዲያይ የሚያስችል የእውቀት ሃይል ስላገኘ የሃዋርያትን ትምህርት ይቀበል ዘንድ አልዘገየም።
‘’በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።’’(ሃስ. 18:25-26)
ከእግዚአብሔር በሆነው ብቻ እንጂ በሌላ በምንም መንገድ ልናውቃቸው የማንችላቸውን እውቀቶችን የመግለጥ ኃይል አለው ቃሉ፣ የምንቀበለው እውቀትም ምስጢራትን የሚገለጥ ነው። ለምሳሌ ዓለማት እንዴት እና በማን እንደተፈጠሩ ከቃሉ ተረድተናል፣ በአለም እውቀት ይሄ በእርግጠኝነት ሊነገር አይችልም፣ ከሰዎች ግምት የሚነሳ መላምት ብቻ በአለም ይነገራል፣ አስተምህሮም ይወጣል።
‘’ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።’’ (እብ. 11:3)
የእግዚአብሔር እውነተኛ ማንነት የተገለጠው በቃሉ በኩል ነው፣ እግዚአብሄር ማን ነው፣ ደግሞ አሳቡ፣ ፈቃዱ፣ ፍላጎቱ ምን ይመስላል? እንዲህ ያለ እንቆቅልሽ በቃሉ በኩል ብቻ ይገለጣል። ሰዎች ከሞት በኋላ ምን ይደርስብናል? ወዴት እንሄዳለን? መጨረሻችን ምን ይሆናል? ይህም እውቀት ከአለም አይገኝም፣ ከአምላክ ብቻ ይገኛል እንጂ።
የሰው ልጅ እነዚህን ነገሮች ያውቅ ዘንድ ለሺህ አመታት አጥንቶአል ለፍቶአልም፣ በመገመት እና ብዙ ንድፈ ሃሳቦችን በማውጠንጠን መልሶችን ለሰው ልጆች ማምጣት ይችሉ እንደነበር ሳይንቲስቶች፣ ፈላስፋዎች፣ የስነከዋክብት አጥኚዎችና ሌሎችም እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል፣ አሳምነዋልም፤ ነገር ግን ያ ግምታቸውን ብቻ የሰጠ ወደ እውነት ያልቀረበም ነበር፦ ንድፈ ሃሳቦች ብቻ አወጡ፣ አስተማሩ፣ አሳወቁም እንጂ እርግጠኛ ነገር ባለቤቱ ነገረን ሊሉ አልደፈሩም። ምክንያቱም ማንም በትክክል ምስጢራቱን ሊያውቅ አልተቻለውም፣ መለኮታዊ ነበርሩና።
‘’እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን፡- ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።’’ (1ቆሮ. 2:6-13)
በሌላ በኩልም የእግዚአብሔር ቃል ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ሰው ልጅ ሕልውና ምስጢር፣ ተያይዞም በአለም እውቀት ፈጽሞ ልናውቃቸው የማንችላቸውን ነገሮች የሚያሳውቅ ነው፤ የርሱ ምስክሮች ግን የእግዚአብሄርን ህዝብ ታሪክ ያስተውላሉ፣ የዓይን ምስክር ሆነውም እውነተኛ የሆነ ዝርዝር ዘገባ ይሰጣሉ።
‘’ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ።’’ (2ቆሮ. 8:7)

ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ያሉ ፍልስፍናዎችና ሰዋዊ አሳቦች ለሰው ልጅ እንቆቅልሽ የመፍትሄ አሳቦች እንደሆኑ ተደርገው ስለሚቆጠሩ አለማውያን ለማረጋገጫነት የሚያስቀምጡዋቸው መለኪያዎች ናቸው። አማኞች ግን የእግዚአብሔር ቃል ካጸደቀው ነገር ጋር መሄድና በርሱ መደገፍ እንመርጣለን፤ ቃሉ ካልተቀበለው ምንም ማድረግ የማንችል በመሆኑ ነገራችን እንዲሰራ፣ ተቀባይነት እንዲኖረው ወይም እንዲስተካክል የእግዚአብሄር ነገር ላይ ብቻ ትኩረት እናደርጋለን፦ እምነታችን በጌታ ላይ ብቻ በመሆኑ። ቃሉም ያን ያሳስበናል፦
‘’በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።’’ (2ጢሞ. 1:14-15)
የሰዎች የሥነ ምግባር ስርአት ከመንፈሳዊ አሳቦችና አካሄዶች ጋር አይመሳሰሉም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ የእግዚአብሄርን ቃል የሚገልጥ በመሆኑ ግምታዊ መረጃ ካላቸው እውቀቶች ጋር ሊጋጠም/ሊስማማ አይችልም፤ መፍትሄው ሰዋዊውን አካሄድ ትቶና ከህይወት አውጥቶ የእግዚአብሄር የሆነው አሳብና አላማ ላይ መመካት ብቻ ነው።
‘’አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።’’ (2ጢሞ. 3:15-17)
መንፈሳዊ አላማ ያላቸው አሳቦች አካሄዳችንንና መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያጸኑት ቅዱስ መጽሃፍት ሲመሰክርላቸው ብቻ ነው፤ ቃሉ በአጽኖት ሲያመለክት፣ ሲያስተምርና ሲመራ በእርግጥም የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበት መሆኑ ይረጋገጣል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እውነት መመዘኛ፣ መለኪያና ማጽኛ እንጂ የሰው ሃሳብ ማነጻጸሪያ አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ጉድለትን፣ መተላለፍን፣ ስርአት መጣስንና በስጋ አሳብ የሚነዳ የዘፈቀደ ህይወትን አያባብልም፣ አይሸከምም፤ ነገር ግን አንድ ሰው ከወደቀበት የጎደለ ህይወትና ነቀፋ ከሞላው ማንነት ውስጥ ተነቅሎ እንዲወጣ እንዲሁም መንፈሳዊ ስፍራውን ወደ እግዚአብሄር የፈቃዱ አሳብ እንዲቀይር አቅም ሊሰጠው ይችላል፣ መውጫ መንገድን ያመለክተዋል፣ አካሄዱን ያስቀይረዋል።
‘’ አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል’’ (2ጢሞ.3፡14-17)
ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ቃል በዘር ይመስለዋል። ምሳሌው ቃሉ ለማደግና ፍሬ ለማፍራት ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ነው። በቅን እና በታዛዥ ልብ ውስጥ የተተከለ ቃል የሚለይና የሚታወቅ መንፈሳዊ ለውጦችን ይፈጥራል። በሰው ልብ ውስጥ የተተከለው የእግዚአብሔር ቃል እያፈራ፣ እየተባዛና ፍሬው በአለም ዙርያ እየተዳረሰ ከትውልድ እስከ ትውልድ ክርስቲያኖችን አጽንቶአል፣ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንንም ለብዙ ዘመናት አጽንቶ ጠብቆአል። ክርስትና ለ2000 ዓመታት የኖረበት ብቸኛው መንገድ በቃሉ ውስጥ ባለው የሚያፈራ፣ የሚያሳድግና የሚያስፋፋ ኃይል ስላለ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚወርደው ብቸኛና የጸና መለኮታዊ አሳብ ማስተላለፍያ መሳርያ ቢኖር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ሰዎች ይሞታሉ፣ አሳቦቻቸውና ስራዎቻቸው ይሻራሉ፣ የገነቡዋቸው ሕንጻዎችም ይፈርሳሉ፤ ነገር ግን የሰበኩት ንጹህ፣ ህያውና መጽሃፍ ቅዱሳዊ ቃል ካለ ያ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ፣ እየሰራና ለእግዚአብሄር መንግስት እያዘጋጀ ወደ ቀጣይ ትውልድ ይሄዳል፤ እኛም ጋ ደርሶ በትውልዳችን ከሰራ በሁዋላ ወደ ነገ ትውልድ ዘልቆ ተመሳሳይ ስራውን እያከናወነ እስከ ጌታ ዳግም መገለጥ ሰአት ድረስ ይዘልቃል።
‘’እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። ምሳሌው ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።’’ (ሉቃ. 8:10-11)
የእግዚአብሔር ቃል እያንዳንዱ ሰው በግሉ ሙሉ የሕይወት ለውጥ እስኪያመጣ ድረስ፣ የሚያነበው ወይም የሚሰማው እያንዳንዱ ነገር ወደ ለውጥ ያመጣው ዘንድም ራሱን ማዘጋጀትና የቃሉን ድምጽ መታዘዝ እንዲችል አቅም የሚሰጥ ነው። የቃሉ ጉልበት የሚከተሉትን ያደርጋል፣ እንድናደርግም ያስችላል፦
– አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል (የራሴን ጉዳይ ብሎ) እንዲያነብና እንዲያምን መቻል ይሰጠዋል
ቃሉ መንፈስ ነው፣ ህይወትም ነው፤ የጌታን ቃል መመገብ ህይወትንና መንፈስን ለመቀበል አስቻይ ነው። ከቃሉ ውጪ ለሰው ልጅ ብዙም አስተማማኝ ድጋፍ አይኖረውም፤ ምንም ይሁን ምን አለኝ ብሎ የሚታመንበት ነገር ቢኖር እንኩዋ ዘልቂነት የሌለው ነው። በአለም በሙላት ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቃሉን የተደገፉት መጨረሻቸው ታላቅ ደስታን የሚያስገኝላቸው ነው።
– አንድ ሰው ከሌላው ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መካፈል ይሰጠዋል
ህይወት የሚበዛውና ወደ ተለያዩ ወገኖች የሚደርሰው ቃሉ ሲመሰከር ነው፤ ቃሉን የሚያካፍሉ ህይወትን ያካፍላሉ፤ ለነፍሳት የሚጸልዩና የሚማልዱ ምህረትን ወደ ሰዎች ያቀርባሉ፤ የዚህን ነገር ታላቅነት ሃዋርያው ጳውሎስ በአጽኖት ይናገራል፦
‘’ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።’’(2ጢሞ.4:2-4)
– አንድ ሰው በሰማውና ባነበበው የቃሉ ትምህርት በኩል በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ የህይወት ለውጥ ይቀበላል።
ከሰው ልጅ ታሪክ እንደምናየው የሰውን ህይወት ሙሉ በሙሉ የመለወጥ እና ወደ አዲስ አቅጣጫ የመምራት ሃይል ያለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ለምሳሌ ሃዋርያው ጳውሎስን መመልከትና ከጌታ አፍ የሰማው ድምጽ የህይወት መንገዱን እንዴት ሊያስለውጠው እንደቻለ መረዳት እንችላለን(ሃስ.9)።