የህያው አምላክን ቃል የሚያስተውሉ አጥብቀው በቃሉ ይደገፋሉ፤ በቃሉ ላይ መዛነፍ እንደሌለ ማመናቸው ህያውነቱን አምነው እንዲቀበሉም ይረዳቸዋል።
‘’እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።’’ (ኢሳ. 45:22-23)
ቃሉን ለኛ በምናስተውለው መንገድ እንደንሰማው ያስችለን እንጂ ጠልቀን ስንመለከተው የእግዚአብሄር ቃል የራሱ ባህሪ ያለው ነው፤ ባህሪው እግዚአብሄርን ሊገልጥ የሚችል፣ ስለእግዚአብሄር የሚያስረዳ ድምጹ ነው፡፡ ደግሞ በተለምዶ ከምናውቀው የሰው ድምጽ የሚለይበት ልዩ ገጽታ አለው፡፡ የሰው ቃል ይለወጣል፣ በተሻለ እውቀት ይሻራል፣ ዳግም አይመጣም፣ አይሰማም፣ ይረሳልም። የእግዚአብሄር ድምጽ ግን ፈጽሞ ይለያል፣ ቃሉ ደግሞ ደጋግሞ ይሰራል፣ ይፈጥራል፤ አንዴ ከእግዚአብሄር አፍ ከወጣ ሁልጊዜ ይሰራል። ሰዎችም ይህን ስለምናምን እግዚአብሄርን በቃሉ እንጠይቃለን፣ እንለምናለን፣ የእግዚአብሄርን ቃል ደግመን ደጋግመን እናነባለን፣ እንባረክበታለን፣ ስናነበውና በእምነት ስናውጀው እንደገና በተነገረው ልክ ሲሰራ እናያለን ።
‘’ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ።’’(ኢሳ. 55:10-12)
ህይወት ያለው ፍጥረት ቃል ለማዳመጥ የተፈጠረለት መስሚያ አካል አለው፤ የእግዚአብሄር ቃል በዚያ በኩል ገብቶ ህይወቱ ድረስ በመዝለቅ ፈቃዱን ይፈጽማል፡፡ ግኡዝ ፍጥረት ስሪቱ ከቃሉ ስለሆነ፣ ካለመሆን ወደ መሆን ስለመጣና ከሌለበት ወዳለበት ሁኔታ የደረሰው በርሱ በመሆኑ ቃሉን የሚሰማበት ልዩ የመስሚያ አግባብ አለው፡፡
የተሰማ የእግዚአብሄር ቃል በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በተመሩ ሰዎች በመጽሀፍ ተጽፎ ለብዙ ሺህ ትውልድ እየተላለፈ፣ በትውልድ ውስጥ እየሰራ እዚህ ደርሶአል፡፡ ቃሉ ከተሰማ በሁዋላ የሚያልፍ፣ እንደመጣ የሚሄድ፣ ከተነገረ በሁዋላ የሚከስም አይደለም፤ በባህሪው የሰው ዘመናት የሚወስኑት በሁኔታዎች የተገደበም ነገር አይደለም፡፡ ቃሉ ህያው ነው፡፡ ህያው በመሆኑ የትኛውንም ትውልድ ይደርስ ዘንድ እንደ አዲስ በዘመኑ ላይ ሆኖ መናገር ይችላል፣ ትውልድ ያረጃል፣ ዘመን ያልፋል፤ የእግዚአብሄር ቃል ግን መቼም የጸና ነው፡፡ ህያው በመሆኑ ለየትውልዱ አዲስ ነገር ይፈጥራል፡፡ በዚህ ምክኒያት ለትውልድ ሁሉ እንዲናገር ተጽፎአል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ከእግዚአብሄር አፍ እንደመውጣቱ በእግዚአብሄር እቅድ ልክ ያከናውናል፣ ይገለጣል፡፡ ቃሉ መልክ አይደለም፣ አካል አይደለም፣ መጠን የለውም፣ ልኬት የለውም፣ ፍጥረትም አይደለም፡፡ ቃሉ ከአፉ የወጣ ድምጽ ነው፣ ሀይል ነው፣ ፈጣሪ ነው፤ የሚያንቀሳቅስ፣ የሚያናውጥ፣ የሚሰባብር፣ የሚጠግን፣ የሚሰበስብ፣ ህያው የሚያደርግ፣ የሚያጠፋ፣ የሚደግፍ፣ የእግዚአብሄርን ክብር የሚገልጥ፤ የሰውን አእምሮ፣ አስተሳሰብ የሚቀይር ፣ የሚያስተካክል … ነው፡፡
ሰዎች ቃሉን ሊለኩ አይችሉም፡፡ ሊታመኑት ግን ተፈቅዶአል፡፡ ቃሉን ቅርጽ ወይም አካል ሊሰጡት አልተፈቀደም፤ በልባቸው ሊያኖሩት ሊጠባበቁትና ታምነው ሊናገሩት ግን ተፈቅዶአል፡፡
በቃሉ ሳያፍሩ አዋጅ ሊናገሩ፣ እግዚአብሄር የተናገረውን ሳያፍሩ ሊያስተጋቡ ተፈቅዶአል፡፡ በቃሉ ላይ ሰዋዊውን ፈቃድ መግለጥ ግን ክልክል ነው፡፡ አማኝ ቃሉን ያለመቆጠብ ሊታመንበት፣ እንደቃሉ ሊለምንበት፣ እግዚአብሄርም በቃሉ ሊጠይቁት ተፈቅዶአል፡፡
መለኮታዊ ድምጽና ቃሉ አንድ ናቸው፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ቃሉ ድምጹ በጽሁፍ ተዘግቦ ስለተቀመጠልን የምናገኘው ነው፤ መጽሀፍ ላይ ያሰፈረውን ቅዱስ ቃሉን ወቅታዊ ሊያደርገውና የህዝቡን መንፈስ ሊያነቃው ሲፈልግ በመንፈሱ መልሶ ድምጽ ያደርገዋል፡፡ ህዝቡ ሁሉ እንዲሰማው መንፈሱም ነቅቶ ወደ ተግባር እንዲለውጠው ቃሉ በመንፈስ ተነግሮ/ተሰብኮ ህያው ድምጽ ይሆናል፡፡ በግል ህይወታችንም በአእምሮአችን የተቀመጠው የእግዚአብሄር ቃል/በመጽሀፍ ያነበብነው ቃል/ መንፈሱ መጥቶ በውስጣችን ድምጽ አድርጎት ያሰማናል፡፡ ነፍሳችንም በዚያ ድምጽ ትነቃለች፡፡
በማር. 12:18-27 ውስጥ ሰዱቃውያን ከኢየሱስ ጋር የሚነጋገሩበት ክፍል አለ፤ ሰዱቃውያን ስለተለያየ ነገር ሲናገሩ የስነ ምግባር ጉዳይንም አንስተዋል፤ ስለ ትንሣኤ አንስተውም ንግግር አደረጉ፣ እንቆቅልሽ የሚመስል ታሪክም ለጌታ አቀረቡለት። ባቀረቡት ታሪክ ሰባት ወንድማማቾችንና ሚስታቸውን አንስተው በዚያ ጌታ ኢየሱስን ሊፈትኑ ሲሞክሩ ይታያሉ።
… እያንዳንዱ በሞተ ጊዜ ተከታይ ወንድም የቀድሞ ወንድሙን ሚስት አገባ አሉ። ይህ በዘዳግም 25፡5-10 ባለው የሌዋውያን ጋብቻ ህግ መሰረት የሆነ እንደነበር እናስታውሳለን። ዋናው ፈተናቸው በመንግስተ ሰማያት ሴቲቱ የማን ትሆናለች የሚል ነበር፡፡ ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን በተሳሳተ መንገድ የመተርጎም አካሄድ እንዳላቸው እና ለእግዚአብሔር ኃይል ሙሉ በሙሉ እንግዳዎች እንደሆኑ በመናገር መልሶላቸው ነበር።
የእግዚአብሄር ኃይል የት ሊገኝ እንደሚችል መገንዘብ እንደሚገባን ቃሉ ያስተምረናል፤ ይህ ቃል በእውነት ሲገለጥልን መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ እውነተኛ አማኞች ያደርገናል እንጂ የሰው ጥበብ መንፈሳዊ ሊያደርግ እንደማይችል ማስተዋል አለብን፦
‘’… እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።’’ (1ቆሮ. 2:3-5)
ወንጌል በተሰበከበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሄር ቃል ተሰብኮአል፣ ቃሉን ያመኑትም መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። በሌላ በኩል መንፈስ ቅዱሳት መጽሃፍትን በየጊዜው ካልገለጠልንና ምሪት ካልሰጠን ህይወት የሚሆን እውቀት እንደማንቀበል የሰዱቃውያን ልማድ ያስተምራል።
ስለዚህ የእግዚአብሔርን ኃይል ማግኘት የሚፈልግ የእግዚአብሔርን ቃል በልቡ መቀበልና ማመን ይገባዋል፡
– ቃሉን የሚፈልግ ሃይሉን ይፈልጋልና
– ቃሉን መቀበል ማለት ኃይሉን መቀበልም ነው
– ቃሉን ማመን በኃይሉን መሞላት ነው
– ቃሉን መታዘዝም በኃይሉ መንቀሳቀስ ነው
– ቃሉን መናገር ሰዎች ኃይሉን እንዲያገኙ ማድረግ ነው
ኢየሱስ ምድራዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዱቃውያን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩትን የእግዚአብሄር ቃሎች በራሳቸው ትርጉዋሜ ወስደው እንደተሳሳቱ አሳይቶአቸዋል፤ ባለማወቃቸውና በቃሉ የሚገለጠውን የአምላክ ኃይል ባለማስተዋላቸውም ገስጾአቸዋል። ሕያው የሆነውና ኃይል ያለውን የእግዚአብሔር ቃል አቅልሎ መመልከት ከቶ እንዳይገባ ከነርሱ ህይወት እንማር።
ኤርምያስ የይሁዳ ሕዝብ በጣዖት አምልኮውና በኃጢአት ስራው እንዳይጠፋ ለብዙ ዓመታት ያስጠነቀቀ ነቢይ ነበር። ቃሉ ግን በሕዝቡ ዘንድ ቸል ተባለ፤ ይልቁን የነብዩን ስብከት ለማጣጣል ሌሎች ብዙ ራሳቸውን የሾሙ ሀሰተኛ ነቢያት ተነሱ፣ ከነርሱ ሁሉም ህዝቡን የሚያዘናጉ ሰላምና ብልጽግና እንደሆነ የሚሰብኩ ነበሩ እንጂ የሚያስጠነቅቅና የሚያዘጋጅ ቃል የሚያመጡ አልነበሩም። ኤርምያስ ለእነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት የሰጠው ምላሽ በመጽሐፉ ምዕራፍ 23 ላይ እንዲህ ይላል፦
“በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን ይላል እግዚአብሔር።’’(ኤርምያስ 23:29-30)
ስለዚህ ማንም ቃሉን አንስቶ ቻይነቱን ቢያውጅ ቢነግር፣ ኃይል በሰው ዘንድ አለ ቢል ሊያሳምንም ቢጥር፣ እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ በኃያልነቱ ይገለጥና ይሰራል እንጂ ለየትኛውም ፍጥረት አይሳካለትም። እግዚአብሔር የሚቃወማቸው ሰዎች በዚያ መንገድ በቃሉ ላይ የሚታበዩ ናቸው። ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ ኤርምያስ የተናገራቸው የትንቢት ቃሎች ሆነው የታዩና እውነቶች የነበሩ መሆናቸውን ነው። እንደተባለውም ቃሉ እንደ እሳትና መዶሻ በመሆን ዓለት የሆነን ትእቢተኛ ልባቸውን የፈጨና የማረከ ሆኖባቸው ነበር።
በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ እውቀት መለኮታዊ የሆነ የኃይል ልምምድ ያመጣል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጠው ቃሉ ተገልጦ በእኛ ላይ ሲሰራ ነው፣ ቃሉን ማወቅ ኃይሉን ማወቅ እና መለማመድ የሚያስከትል መሆኑን ከተረዳን አትኩሮታችን የፍለጋችን አቅጣጫም ጭምር ወደዚያ እንዲያመራ ማድረግ አያዳግትም። እንደ ቃሉ ይኖር የነበረ ነቢይ በህይወቱ የገጠሙትን ታላላቅ ተግዳሮቶች በእስራኤል ህዝብ ላይም የተንሰራፋውን የመናፍስት ማነቆ በቃሉ ላይ በነበረው እምነት በኩል እንዴት እንዳስወገደ በ1ነገ.18 ውስጥ ያለው ታሪክ ያሳያል፣ እንዲህም ይላል፦
‘’መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ፦ አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ።’’ (1ነገ. 18:36-39)
እግዚአብሄርን የሚገልጥና በህዝቡ መሃል ማንነቱን የሚያሳውቀው ከእርሱ የወጣው ቃሉ ነው፤ ከሰዎች አሳብ ይልቅ የቃሉ ሃይል የሰዎችን ልብ መቀየር ሁኔታዎችንም መለወጥ ይችላልና። ነቢዩ እምነቱ ከፍ ያለ ስለነበረ የማደርገው ነገር ሁሉ በቃል መሰረት እንዳደረግኩት አምላክ ሆይ መስክር ሲል ጠየቀው፤ እግዚአብሄርም በቃሉ የታመነ አምላክ ነውና መልሱን በእሳት ሲመልስ እናያለን። በቃሉ ምክኒያት ለህዝቡ መመለስ ሆነ፣ ከዚህም በላይ የቃሉ ፍርድ ጠላቶችን እስከማሳረድ በሚደርስ ፍርድ ውስጥ ሲከትታቸው እናያለን።
ንጉስ ዳዊት በቃሉ ላይ ከፍተኛ መታመን የነበረው ሰው ነበር፣ ንጉሱ የእግዚአብሄርን ቃል አረጋግጦ ይወጣል፣ ይገባል፣ ይዋጋል፣ እርቅ ያደርጋል፣ ህዝቡን ይመራል፤ ስራውን ሁሉ በቃሉ ይፈጽማል፤ እግዚአብሄርን ይሰማ የነበረ ይህ ንጉስ አምላኩን ይወድ ስለነበር እንዲናገረው ዘወትር ይናፍቅና ይጠይቅ ነበር፤ እግዚአብሄርም መሻቱን አይቶ ብዙ ቃልኪዳን ሰጠው፣ እንደነገረውም አከናወነለት፦
‘’እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ንጉሡ ነቢዩን ናታንን። እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው።ናታንም ንጉሡን። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው።በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው።ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ። ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፤ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል።’’ የሚል ቃል ነቢዩ ወደ ዳዊት አመጣለት (2ሳሙ.7:1-11)። ይህም ታላቅ ቃል የዳዊት ቤትን መሰረት በስራኤል ላይ የሚያጸና ታላቅ የተስፋ ቃል ነበር።