ቃለ መለኮት(1…)

ቤተክርስቲያን

ቃለ-መለኮት ወይም የመለኮት ቃል የእግዚአብሄር ድምጽ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ድምጹን ከራሱ አውጥቶ የሚናገር አምላክ ሲሆን ማስተላለፊያ መንገዱ ግን የተለያየ ነው፦ እግዚአብሄር በቀጥታ ድምጹን ለሰዎች ያሰማል፣ አሰምቶአልም፤ ድምጹን በመላእክት አንደበት ያስተላልፋል፣ አስተላልፎአልም፤ እንዲሁም የነቢያትን አንደበት ተጠቅሞ ወደ ህዝቡ ድምጹን ሲያሰማ ኖሮአል፣ አሁንም ያን ያደርጋል። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆን ቃል ቀጥሎ እንመለከታለን፦
‘’ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን’’(እብ. 1:1-2)
እግዚአብሄር ድምጹን ሲያሰማ፣ ለሰው ልጅ ሲናገር ንግግሩ በተለያየ መንገድ ውስጥ ወደ ሰው ልጆች ይመጣ ነበር፦ በህልም መጥቶ ድምጹን አሰምቶ ያውቃል፣ በራእይ መጥቶ፣ እንዲሁም ፊትለፊት ተገልጦ ተናግሮአልም፣ ለምሳሌ ለአዳምና ለሄዋን እንዳደረገው፣ ለሙሴም እንደተናረገው ማለት ነው።
– እግዚአብሄር በመልአክ ሲናገር ነበር (ዘጸ.23:20-21)፦
‘’በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።’’
እግዚአብሄር የመላእክትን አንደበት ተጠቅሞ በቀጥታ ድምጹን ሲያሰማ ማለት መልአኩ በገጽ እየታየና በአንደበቱ እየተናገረ ድምጹ ሲሰማ የሚወጣው ያ ድመጽ የራሱ የመልአኩ ሳይሆን በቀጥታ የእግዚአብሄር ሲሆን ማለት ነው፤ በእንዲህ ያለ ወቅት በቀጥታ እግዚአብሄር አንደበቱ ላይ ስለሆነ እኔ እግዚአብሄር እያለ መናገር ይችላል ማለት ነው።
‘’የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፦ እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም፦ ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም፦ ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ።’’(መሳ. 2:1-4)
– እግዚአብሄር በነቢይ ሲናገር ነበር (ዘሁ. 12:5-6)፦
‘’እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።እርሱም፦ ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።’’

በነቢያትም አንደበት ሲናገር በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚናገረው፤ ነቢያት በእግዚአብሄር መንፈስ ተይዘው እግዚአብሄር እንዲህ ይላል እያሉ ቃሉን ያሰሙ ነበር፣ በቀጥታ ድምጽ ደግሞ በአንደበታቸው እኔ እግዚአብሄር… የሚል ንግግር ይናገራሉ።
‘’እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤ እናንተንም፦ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም።’’ (መሳ. 6:8-10)
እግዚአብሄር ድምጹን በመጨረሻ ሊያሰማ የወደደው ግን በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን ቃሉ ያረጋግጣል። በዘመን ፍጻሜ ላለ የሰው ልጅ እግዚአብሄር በልጁ አፍ ተናገረ። እርሱ ራሱ ይህን ሲመሰክር በቃሉ እናያለን፦
‘’እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።’’(ዮሃ.14:10)
የሚናገር እግዚአብሄር ድምጹን ሲያሰማ ብዙ ነገር ይሆናል፣ በዋናነት በቃሉ የሚገለጠው ደግሞ ፈቃዱ ነው። ፈቃዱ ከቃሉ አይነጠልም፤ ለምሳሌ በዘፍ.1 መጀመርያ የእግዚአብሄር ድምጽ ተሰምቶ ፍጥረትም እግዚአብሄር እንደፈቀደላቸው ወደመታየት ሲመጡ ይታያል፦
‘’በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።’’
ፈቃዱ፣ ፍላጎቱ፣ አሳቡ፣ የሚፈልገው ነገር፣ በልቡ ያለው አሳብ፣ እቅዱ፣ የዘላለም አሳቡ፣ ብቻ የትኛውም ነገር ይሁን ቃል ሲናገር ይሆናል፦
‘’እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።’’(ኢሳ. 45:22-23)
‘’ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።’’(ኢሳ. 55:10-11)
ከእግዚአብሄር አፍ የሚወጣው ቃል የእግዚአብሄርን መሻት ያከናውናል የተባለው እግዚአብሄር እንዲሆን የተናገረው ከመሆን አንዳች የሚከለክለው ስለሌለና መፈጸሙ እርግጠኛ ነገር ስለሆነ ነው፤ እግዚአብሄር ይህን ሁሉ በመስራቱ ማንነቱ በቃሉ ይገለጣል ይታወቃልም፤ ይህን የሚያስተውሉ ደግሞ የቃሉ ድምጽ ሲሰማ እግዚአብሄር መምጣቱን ይገነዘባሉ።
ቃል ከእግዚአብሄር አፍ የሚወጣ የአምላክነቱ ድምጽ በመሆኑ የእግዚአብሄር ባህሪ የሚገለጥበት ነው፤ ቃሉ በተለያየ መንገድ እግዚአብሄርን የመግለጥ ጉልበት አለው፤ ስለዚህ እግዚአብሄርን ከቃሉ መለየት አይቻልም፣ የእግዚአብሄር ባህሪ በቃሉ ይገለጣል ስንልም የተለያየ የእርሱነቱ መገለጫዎች ቃሉ እንዳለው ሆነው ስለሚገኙ ነው። እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ነው ስንል ከአፉ የሚወጣው ቃል ሁሉን ይችላል ማለት ነው፤ እግዚአብሄር አይለወጥም ስንል ቃሉ አይለወጥም ማለት ነው።
‘’ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።’’(ኢሳ.40:26)
እግዚአብሄር ሲናገር የሌሉ ነገሮች ይፈጠራሉ፣ ምክኒያቱም ቃሉ የመፍጠር ጉልበት አለው፤ ነገሮች የሚሆኑት የእግዚአብሄር ፈቃድ ከቃሉ ጋር ስላለ ነው፤ በፍጥረት አለም ውስጥ ማንም በቃሉ መፍጠር አይችልም፣ ምክኒያቱም ሁሉም የተፈጠረ፣ ከመለኮት ቃል የተገኘ ስለሆነ ነው፣ እርሱ ራሱ የእግዚአብሄር ድምጽ ውጤት በመሆኑ የሚፈጥር ድምጽ ማውጣት አይችልም፣ ማንም ፍጥረት የእግዚአብሄር ፈቃድ ከወሰነለት ዘመን ማለፍም አይችልም፣ ምክኒያቱም የእግዚአብሄር ቃል ለመፍጠር ከእግዚአብሄር ሲወጣ ከውሳኔ ጋር ስለሆነ ነው፤ እግዚአብሄር ሲናገር ፈቃዱ እንደገለጠው ፍጥረት ይሆናል፣ ይታያል፣ ይከሰታል። በዮሃ. 1:1-3 ውስጥ ያለው ቃል ስለ እግዚአብሄር ቃል ይናገራል፦
‘’በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።’’
ቃል የእግዚአብሄር የልቡ አሳብ መገለጫ ነው። ቃል ከእግዚአብሄር አፍ የተሰማው አሳብ በሙሉ የሚገለጥበት መጠሪያ ነው፤ ቃል መለኮታዊ ድምጽ ሰዋዊ ያልሆነ ወይም ከሰው አፍ ሳይሆን ከአምላክ የወጣ ድምጽ ነው፡፡ ከሰው አፍ የወጣ ድምጽ ከሰው አንደበት ውስጥ ጉሮሮ ላይ በሚፈጠር በነፋስ ግፊት የተፈጠረ መርገብገብ ከአእምሮ ቅንብር ጋር የሚሄድና የሚሰማ ትርጉም የሚሰጥ ንግግር ሲሆን የመለኮት ድምጽ ከመለኮት ቃል የሚወጣ ባህሪውን የሚገልጽ ሀይል የተሞላ ንግግር ነው፡፡ ምንም ነገር ሲፈጠር ከዚያ በፊት ህያው የሆነው የአምላክ ቃል ከእግዚአብሄር አንደበት ወጥቶ እንደነበር ማስተዋል አለብን፤ ሰማይና ምድርን ሆነው ስናይ አንድ የምናስተውለው መንፈሳዊ እውቀት የእግዚአብሄር ቃል ከመለኮት እንደወጣ ነው፤ ስለዚህ በመጀመሪያው ቃል ነበረ ተባለ፣ በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ስለተባለ። ህያው ቃሉ ያለገደብ ፍጥረትን በሙሉ ያዳርሳል፣ ይነካል፣ ይመለከታል፣ ይመረምራል፣ ይፈጥራል፣ ይለውጣል፣ በተለይ በሰው ዘንድ ትልቅ ነገር ያደርጋል፦
‘’የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።’’ (እብ. 4:12-13)
እንዲሁም በጠራው ህዝብ መሃል እየተመላለሰ ሲናገር የነበረውን በማስተዋል፣ ድምጹን በመስማትም የእግዚአብሄርን ህያውነት አውቀው የተከተሉ ሁሉ ሲባረኩ እንመለከታለን። የእግዚአብሄር ቃል እግዚአብሄር ህዝቡን በተለያየ መንገድ እንደሚያናግር ቀጥሎ ያሉት ጥቅሶች ያሳያሉ፦
‘’… እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም፦ እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው፦ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?’’ (ዘሁ.23:17-19)
‘’በለዓምም ባላቅን አለው፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን?አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።’’ (ዘሁ.24:13-16)
‘’በልብህም፦ እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።’’(ዘዳ. 18:21-22)
‘’እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን:- ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም አለው።እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ።’’(1ነገ.8:18-20)
‘’እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል አላቸው።’’(2ነገ. 10:10)
‘’በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ።የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል’’(እዝ. 1:1-2)
‘’በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ።ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።’’(ዳን. 9:1-3)
እግዚአብሄር ይገለጥልን ዘንድ አብልጠን ቃሉን ማንበብና ማመን አለብን፤ የቃሉን ብርሃን ለመቀበል፣ ህይወታችንን እንዲለውጠውም ለቃሉ ትሁት መሆን አለብን፤ እግዚአብሄር ታማኝ፣ ቃሉን የሚያበራም አምላክ ነውና።