በእግዚአብሄር ዘላለማዊ እቅድ ላይ የሚመጣ ብዥታ ቤተክርስቲያን ማንነትና ተልእኮ ላይ ተጋብቶ ተመሳሳይ ብዥታ እንዲፈጠር ያደርጋል። የእግዚአብሄር እቅድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሻጋሪ ነው፡፡ በእርሱ ዘንድ ያለው እቅድ ለሰው ልጅ ያለውን አሳብ የያዘ ነው፡፡ በሚመጣው እያንዳንዱ ትውልድ ያን ዘላለማዊ እቅድ በመግለጥ የሰው ልጆች በእቅዱ ውስጥ እንዲገቡ ይጋብዛል፣ ኑ ብሎ ወደ እርሱ ይጠራል፡፡
በሰማይ ያለው እቅዱን ሊገልጥ ሲመጣ አስቀድሞ እራሱን በመግለጥ ህዝቡን ይተዋወቃል፡፡በቀድሞ ዘመናት በተገለጠ ጊዜ እርሱን የሚያሳውቁ አገልጋዮችን በመምረጥ ቃሉን ወደ ሰዎች ይልክ ነበር፡፡ በመጨረሻ ዘመን ግን አንድ አካል በማዘጋጀት (ቤተክርስቲያንን በመመስረት) በርሱዋ በኩል አለምን እየደረሰ ይገኛል፡፡ ቃሉ ሲያረጋግጥልን እንዲህ ይላል፡
1ጢሞ.3:14 ”… ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።”
እግዚአብሄር ቤተክርስቲያንን የመሰረተው እቅዱ ውስጥ ስለነበረች ነው፡፡ እርሱ ዛሬም በፈጠራት ቤተክርስቲያን ያድራል (ይገኛል)፣ በዚያ ሰዎችን ያድናል፣ አምልኮን ይቀበላል፣ ሰዎች በዚያ የእውነት ወንጌልን ይሰማሉ፡፡ አምልኮ፣ ስግደትና ውዳሴ በዚያ ይደረጋል፣ ህዝቡን በግል በዚያ ሁሌ ይገናኛል፡፡
ቤተክርስቲያን የእውነት አምድ በመሆንዋ እውነት ይገለጥባታል፣ ይሰበክባታልም፡፡ እግዚአብሄርም ላመኑና ወገን ለሆኑ ልጆቹ እውነትን ባኖረባት ቤተክርስቲያን ተልእኮን ይሰጣል፡፡ ይህንን ተልእኮ መጽህፍ ቅዱስ በማር.16:15-16 እና በማቴ.28:19-20 ባለው ክፍል እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡-
“እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።“
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።“
ጌታ ኢየሱስ ይህንን ትእዛዝ በቤተክርስቲያን ላሉ አማኞች ነው ያስተላለፈው። ስለዚህ ህዝቡ የጌታ ትኩረት የሆነውን የወንጌል ተልእኮ ዋነኛ ስራ አድርጎ ሊቀጥል ይገባል ማለት ነው፡፡ በወንጌሉ በኩል እውነተኛው አምላክ ከመገለጡም በላይ የእግዚአብሄር መንግስት ይታወጃል። የሚድኑም ወደ እግዚአብሄር መንግስት ተጨምረው በምድር ላይ የክርስቶስ አካል በመሆን በአንድነት ይንቀሳቀሳሉ።
የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከሃዋርያት ህልፈት በሁዋላም የሚያቆም ስላልሆነ እነርሱን ያንቀሳቀሰ የጌታ ሃይል ለርሱ በተለዩ አገልጋዮቹ ላይ አድሮ ተመሳሳይ ስራ እየሰራ ይቀጥላል።
ወንጌል የጌታ ኢየሱስ የድነት እውቀት በመሆኑ የርሱን የማዳን እቅድ ወደ ሰው ልጆች ለማስተላለፍ እንደ ድልድይ አድርጎ ይጠቀምበታል። ስራውንም በርሱ በቤተክርስቲያን እያቀጣጠለ በማስፋፋት ወደ አለም ሁሉ ያደርሰዋል።
ቤተክርስቲያን የደህንነትን ወንጌል ለአለም ታደርስ ዘንድ የተሾመች ብቸኛ መንፈሳዊ አካል ነች። የክርስቶስ አካልና የእውነት አምድ በመሆንዋ ከሰማይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላት እርሱዋ ብቻ ናት፡፡ በተሰጣት ስልጣንም ከእርሱ የሚመጣውን ዘላለማዊ ስራ የመግለጥ ብቃት አላት፡፡ስለዚህ የአለም ብርሃን ሆና ከፍ ብላ ትታይ ዘንድ በርሱ ላይ መጽናት ይገባታል (ማቴ.5:14)፡፡
ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንደመሆንዋ የእግዚአብሄር ቤተሰብ ናት (ኤፌ.2:19፣1ጴጥ.4:17)፡፡ ሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ከመንፈስ የተወለዱ የእግዚአብሄር ልጆችን ዘወትር በመንፈሳዊ ምግብ የምትመግብና የምትንከባከብ ናት (ገላ.4:26)፡፡ እርሷ በተሰጣት ስልጣን እየመገበች፣ እያሳደገች፣ እየኮተኮተች፣ እያረመችና እየገሰጸች በውስጥዋ የተወለዱትን ልጆች ለግዚአብሄር መንግስት ታበቃለች።
2ቆሮ.5:20 ”እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ
እኛ ኃጢአት አደረገው፡፡”
ቤተክርስቲያን በዚህ በተመሰቃቀለና ጸንቶ መቆም በተሳነው አለም ውስጥ ጽኑ የእውነት መሰረትና አምድ ሆና ያለመነቃነቅ ስትቆም ተልእኮዋን ታሳካለች። ጳውሎስ ቤተክርስቲያን “የመታረቅ አገልግሎት“ን ለአለም የምታቀርብ ስለመሆንዋ ተናግሮአል። ምክኒያቱም እግዚአብሄር በክርስቶስ ሆኖ አለሙን ከራሱ ጋር ያስታረቀበትን አሰራር ለአለም የምትገልጠው እሱዋ ብቻ ናትና፡፡
የእግዚአብሄር የመጨረሻ ግብ የሰው ልጅን ከራሱ ጋር ማስታረቅና በፍጻሜው በድል ወደ ቤቱ መሰብሰብ ስለሆነ ቤተክርስቲያን ብርቱ መጠቀሚያ መሳሪያው ሆና አላማውን ታስፈጽም ዘነድ መትጋት ይጠበቅባታል፣ እግዚአብሄር ለነፍሳት መሰብሰብ አገልግሎት አምባሳደር አድርጎ ስለሾማት።
እግዚአብሄር በልጁ ሆኖ የሰራውን የማዳን ስራ ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ እንደ አላማ ከፍ አድርጋ በማንሳት ለአለም ማሳየትና መንገር አለባት። ጌታ ኢየሱስ መከራ የተቀበለው፣ የተሰቀለውና ደሙን ያፈሰሰው ሰውን ሁሉ ለማዳንና የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣንን ለማጎናጸፍ ስለመሆኑ አጉልታ ማሳየት አለባት፡፡
ቤተክርስቲያን የተሰጣት ሀላፊነት ነፍሳትን ማዳን ሳይሆን አዳኙን መስበክና ማሳየት በመሆኑ ትኩረትዋን ነፍሳት መድረስ ላይ ማድረግ ይገባታል፣ ያኔ እርሱ የራሱን ድርሻ (የደህንነትን ስራ) ይፈጽማል። በተቀበለችው የጸጋ ሀይልም በርትታ ከጸናች በአዋጅዋ ምክኒያት ነፍሳት ወደ ንሰሃ ይደርሳሉ፣ ወንጌሉም ሰፍቶ ለፍጥረት ሁሉ ይዳረሳል፡፡