ሶምሶምና ህይወት [The failed Prince,2..]

ቤተክርስቲያን

የሚከተለው ታሪክ አሳዛኙ የሶምሶን የህይወት ክፍል ነው፦
መሳ.16:16-21 “…ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች።እርሱም፦ ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደክማለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት።… እርስዋም በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው፤ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ።እርስዋም፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ፦ እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም።ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር።“
መላጣው ሶምሶን፣ ጸጋውን በጠላት ያስገፈፈው ሶምሶን ነው።ጸጉሩ ላይ የተቀመጠው ሃይል የርስቱ ዋስትና ሆኖ ሳለ ቸል አለውና ተዋረደ።ከቀድሞው በተለየ አሁን ጸጋው በላዩ ላይ ስላልነበረ ጠላቶቹ ሊፈሩት አልቻሉም። እርሱ በእርምጃውና በእይታው ደከመ፣ሞገሱም ተገፈፈ ተዋርደም።ማንም በችግሩ ሊደርስለት ስላልቻለም ብቻውን ተዋግቶ ብቻውን ጠፋ።
ጸጋ ከላዩ የተገፈፈ ከማንም በላይ ለጠላት የተጋለጠ ሰው ነው።የእግዚአብሄር ከለላን የማያስተውል ሞገሱ በራሱ እውቀትና ጥበብ የሆነ ይመስለውና ይዘናጋልም።ይህ ሰው ከእግዚአብሄር ምክር ውጪ በሄደው መንገድ ላይ የሚረዳው አምላክ ስላልነበረ የሚያስጥለው ሳይገኝ ፍጻሜው አሳዛኝ ሆነ።
ሶምሶን ከእንቅልፉ የባነነው ሃይሉ ከላዩ ከተነሳ በሁዋላ ነበር።ማስተዋልና ጉልበት ጸጋው ሳለ ነበርና ከርሱ ውጪ በሆነ ጊዜ የሚያጠፋ ድንዛዜ ላይ ወደቀ።
የእግዚአብሄር ጸጋ መንፈሳዊ አይን ይከፍታል።የጠላት ምሽግን ለማየት፣ያጠመደውን ወጥመድ ለማወቅና እቅዱን ከንቱ ለማድረግ መንፈሳዊ እይታ ግዴታ ነው።በመንፈሱ አለም ያለው የጠላት ሃሳብና ፈቃድ ረቂቅ ነው፦አይጨበጥም አይዳሰስምም።ነገር ግን በእግዚአብሄር ጸጋ ሃይል ይገለጣል። ጸጋ የተለየው ይህን ትጥቅ ስለሚፈታ የሚደገስበትን የጠላት ሴራ አያውቅም።ያለበትን ሁኔታ ስለማያስተውል በማይሆን አጋጣሚ ጠላት ሰፈር ይገባና ይመታል።ሶምሶን የመለየት ችሎታ ስላልነበረው የወደዳት ሴት ለጠላት አሳልፋ ትሰጠው ዘንድ ስትተጋ ሊጠረጥራት አልቻለም።
ከጠላት ጋር ወዳጅነት
ብዙ ጠላት ያለው ብዙ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።መንፈሳዊ ሰው ሲዘናጋ ስፍር ቁጥር የሌለውን የአጋንንት ሰራዊት የተዋጋለት ጌታ መሆኑን ይዘነጋል፣እርሱን ቢተው ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ይረሳል።የሚከተለውን ጥቅስ እንመልከት፦
መዝ.91:3-7 “እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል።ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም።በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም።“
ጠላት ሲያስት ግን ከግምት በታች እንደሆነ እንድንቆጥረው ያደርጋል።አንዳንድ ሰው ሰይጣን ተራ አሳብ ብቻ ይመስለዋል።እንዲህ እንድናስብ የሚያደርገው ደግሞ እርሱ ራሱ ነው።በመዘናጋት ውስጥ ጉድ ሊሰራ እንዲያ እንድንዘናጋ ያደርጋል።ሶምሶንን እንመልከት፦ከጠላቱ ጋር እንዴት እንደተጣበቀና ጥፋቱን እንዳፋጠነ።
“…ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች።እርሱም፦ ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደክማለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት።…“
በጠላት ወጥመድ ውስጥ መውደቅ
ሶምሶን በጠላት ማስተዋሉ ስለተጋረደ መዋል ከነበረበት ወጥቶ ጠላት መንደር ገባ፣ በዚያም አደረ፤ ከጠላቱ ጋር ተወዳጀ።ሆኖም ጠላቶቹ በወረዳቸው አግኝተውታልና ወጥመድ አዘጋጁለት።በዚያ በወደቀበት ወጥመድ ምክኒያት ወህኒ መግባት ብቻ ሳይሆን መታወርም ደረሰበት።እግዚአብሄር በተለየው ጊዜ፦
“…ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ።እርስዋም፦ ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ፦ እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም…“
ጸጋውን አስገፈፈ
ሶምሶን በተነጠቀው ጸጋ ምክኒያት ራሱንም እስራኤልንም አዋርዶአል።ተስፋ ያደረጉት ሁሉ እንዳሰቡት ሊያርፉና ከጠላታቸው ፈጥነው ነጻ ሊወጡ አልቻሉም።ሶምሶን የዘጋው በር የራሱን ብቻ ሳይሆን የእስራኤልንም ጭምር ነበር።የርሱ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም የነጻነት መንፈስ ነበር ከርሱ ጋር የተዳፈነው።የኛ መቆም የሌሎችም መቆም እንደሆነው ሁሉ ውድቀታችን ለብዙዎች ተስፋ መቁረጥ ሊሆን ይችላል።ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን እስራኤልም ለዘመናት በሃዘን ድባብ ውስጥ ወድቀዋል።በእርሱ እጅ የነበረው የእስራኤል ተስፋ፣ምህረትና ደስታ እንደ ጸሃይ ሲጠልቅ በዘመኑ የነበረው ትውልድ በሙሉ አብሮ ተስፋው እንደሚጠልቅ ግልጽ ነው።
በወህኒ አደረ
አጥምዶ የጣለ ጠላት ምርኮ አሙዋጦ ካልወሰደ በቀላል አይለቅም፤ ከዚያ በላይ ወደ ወህኒ ይወረውራል።ሶምሶን የጣለውን መልሶ እስኪቀበል የሃዘንና የጨለማ ጊዜያቶች እንዲያሳልፍ ተገድዶአል።ወህኒ የአካልም የህሊናም እስር ቤት ነው።የነፍስ መሻት ፈጽሞ የሚገደብበት ስለሆነ ከጸጸት በቀር በዚያ ስፍራ ነጻነት ያለው ነገር አይታይም።ከርሱ ዘመን አስቀድሞ እስራኤል በጠላት እጅ ወድቆ በግፍ በተገዛ ጊዜ በንሰሃ ወደ እግዚአብሄር ጮሆአል።የእግዚአብሄርም መልስ ሶምሶን ነበር።የህዝቡ የነጻነት ክንድ በሶምሶን ህይወት ውስጥ ሆኖ ሳለ ያን ለጠላት ሄዶ ማስረከቡ እስራኤልን የመታደጊያ ክንድ እንዲታሰር አድርጎአል።
ንሰሀ መግባት
የሶምሶን ህይወት በወህኒ የተገደበ ሰለነበር እንደቀድሞው ነጻነት አልነበረውም።በታሰረበት ስፍራ ሆኖ ግን የእግዚአብሄርን ሃይል ለመነ።
መሳ.16:28 “ሶምሶንም፦ ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ።“
ሶምሶን በውስጡ የተቀበረውን በቀል የሚገልጥበት ቀን የቀረበ መሰለው። በምቹው ጊዜ ግን እውነተኛ ንሰሃ ቢገባ ከአምላኩ መድሃኒትን መቀበሉ አይቀርም ነበር።ትክክለኛ ልመና ሊለምን ያለመቻሉን ስናይ ለእስራኤል ቀርቶ የነበረውን ተስፋ እንዴት ዳግም ሊያጠፋ እንደበቃ እናስተውላለን።ደግሞ በእግዚአብሄር ጥሪ የወጣ በሚሄድበት መንገዱ ላይ ጥሪውን እንጂ የልብ ፈቃዱን እንዳያስተናግድ የሳምሶን ህይወት ያስተምረናል።ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ የተጠራና ለእግዚአብሄር የተለየ ዛሬ እንዴት መኖር ይገባዋል? ይሄ በጥንቃቄ መመለስ ያለበት የቤትስራ ነው፣ ለሁላችን።
በአግባቡ ከያዝነው በሚመች ጊዜ የተቀበልነው ምህረት በፈተና ጊዜ ራሱ ያስመልጠናል።ተቀብለን ካስነጠቅን ወዲያ በቂም ብናስሰው ግን ያን የሚታደግ ጸጋ ዳግም ልናገኘው አንችልም። ገና ቀን ሳለ እስቲ መብራታችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ።
ከደከምንበት ነገር ተነስተን እንዴት ወደ ሃይል ልንመለስ እንችላለን?የእግዚአብሄር መንፈስ የሚያበረታ መንፈስ በመሆኑ ያን
ከእግዚአብሄር እንድንቀበል በጥብቅ መፈለግ፣በትህትና መጠየቅ፣እውነተኛ ንሰህ መግባትም አስፈላጊ ነው።