ሶምሶምና ህይወት [The failed Prince,1..]

ቤተክርስቲያን

እስራኤል በሀዘንና በጨለማ ውስጥ በነበረበት ወቅት በተስፋ የተወለደ የአንዲት መካን ልጅ ሶምሶን የእስራኤላውያን የወደፊት ተስፋ በመሆን የወገኖቹ ነጻነት በእርሱ ላይ የወደቀ ሰው ነበር፡፡ ያኔ እስራኤል በተገዢነት ውስጥ በመውደቁ በብዙ ነገር ከእግዚአብሄር ክብር ውጪ ሆኖአል፡፡ ህዝቡ በባርነት ስር ስለነበረ መውጣቱና መግባቱ ጭንቀት የተሞላበት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን ህዝቡን ነጻ ለማውጣት በተነሳ ዘመን ሶምሶን ተወለደ፡፡ እግዚአብሄር ለእናቱ ሲነግራት፡- ”እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።” ብሎአል (መሳ13፡5)፡፡
እግዚአብሄር ህዝቡን በርሱ በኩል ነጻ ያወጣ ዘንድ ሶምሶምን በሀይልና በእምነት እንዲዘጋጅ ጊዜም ትምህርትም ሰጠው፡፡ ሶምሶምም ለተልእኮ እስከተገለጠበት ዘመን ድረስ የህይወት ዝግጅት ነበረው፡፡ የተነገረው ቃል ለሶምሶን ብቻ ሳይሆን ለእስራኤል ነጻ መውጣት፣ በነጻነትም መኖር ወሳኝ ትእዛዝ ነውና፡፡
ከብዙ ዘመናት በሁዋላ በእብራውያን መጽሀፍ ሶምሶን በእምነት ጀግንነት ተጠቀሰ፡፡ በዕብ.11:32 ሲናገር ”እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።”
ሶምሶን በርሱ ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይገመትን ታሪክ ያከናወነ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው በርሱ ጊዜ የጭፍራ አለቃ ወይ ንጉስ ያልያም ጠቅላይ ሚኒስትር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ለወገኖቹ ከማንም በላይ መመኪያ ሆነ፡፡
በሌላ በኩል ህይወቱ የተወሳሰበና በፈተና የተሞላ ነበረ፡፡ ፈተናው የተከታተለውም በሌላ ምክኒያት ሳይሆን እግዚአብሄር የነገረውን በመርሳቱና የራሱን ስሜት በመከተሉ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ የሶምሶን ባሕርይ ያልተረጋጋና የማይገመት ነበር፡፡ ህይወቱ እንደተጠራበት አጠራር የእግዚአብሄርን ሃሳብ ሊያስፈጸም የተሳነው ነው፡፡ በዚህ ምክኒያት በራሱ ፈቃድ በመጉዋዝ የፈጸማቸው ብዙ ስህተቶችና የሀጢያት መዘዞች ዋጋ አስከፍለውታል፡፡
እግዚአብሄር ይህን ጀግና ሰው ያስነሳው ለእስራኤል ደህንነት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ የተሞላው ሀይል በውስጡ በበረታው ሰዋዊ መሻት ባይጠለፍ ኖሮ ለእስራኤል ታላቅ መዳን ይሆን ነበር፡፡ ጸጋው የእግዚአብሄርን ተልእኮ ሊያስፈጽመው በሚመራው ወቅት ምሪቱን ጥሶ ያልተገባ ስፍራ እየተገኘ ለውድቀት ራሱን አጋልጦአል፡፡

1.ጸጉራሙ ሶምሶን – የእግዚአብሄር ጸጋ በላዩ ያለው ሶምሶን
መሳ.13:24-25 ”ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ። ”
1.1 ለጠላቱ የማይበገር ነው
ጸጉራሙ ሶምሶን ጸጋ በላዩ የነበረበት ሰው ነው፡፡እንደ እግዚአብሄር ቃል የሚመላለሰው የሶምሶም ህይወት በእግዚአብሄር እቅድ ተመርቶአል፡፡ በዚያም ጸጋ ሀይል ሆኖለት ጠላቶቹን ፊት ለፊት የሚጋፈጥበት ድፍረት ነበረው፡፡ በጸጋው የእግዚአብሄርን አሳብ ሲያገለግል እስራኤልን ይጠብቅና ጠላታቸውን ይዋጋ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችም እንዲሁ የእግዚአብሄር ጸጋ በእኛ ህይወት ሲኖር ብቻ ከጠላት ጋር መዋጋት እንደምንችል ያለበለዚያ ግን አቅም እንደማይኖረን ማስተዋል አለብን፡፡
1.2 ወገኑን ነጻ የሚያወጣ ነው
ለነጻነት ታጋይ ሆኖ የገዛ ወገኖቹን ከጠላት ሊታደግ ብቻውን በእግዚአብሄር ድፍረት የወጣ ሰው ነበር፣ ሶምሶን፡፡ በላዩ ያረፈውን የእግዚአብሄር ሀይል ያስተዋለው ሶምሶን ጠላቶቹን ያዋረደው በስፍራቸው ገብቶ ነው፡፡ሶምሶን በላዩ ያለውን ታላቅ ሀይል ቢያስተውልም ሊጠብቀው የሚገባውን ትእዛዝ ግን ያስተዋለ አይመስልም፡፡ ያን ባለማድረጉም የሚጠበቅበትን ያህል ስራ ለህዝቡ ሊፈጽም አልቻለም፡፡
1.3 ከሌላ ወገን ጋር ላይቀላቀል ቅዱስ ሆኖ ለአምላኩ የተለየ ነው
መሳ.14:3 ”…አባቱና እናቱም፡- ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን፡- ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው።”
ሶምሶን ናዝራዊ ሆኖ ሊኖር ይገባው እንደነበር አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ያልተገረዘ በህዝቡ መሃል የእግዚአብሄር እድል ፈንታ እንደሌለው በዘፍ17፡12 ውስጥ የተነገረ ስለነበረ ካልተገረዙ ጋር የነበረው ግንኙነት በሁዋላ ጥፋት አምጥቶበታል፡፡ ለእግዚአብሄር ተለይቶ የእግዚአብሄር ሀይል በርሱ ይሰራ ዘንድ ከየትኛውም ያልተገባ አካሄድ ሊርቅ ቢገባውም ያን ሲደርግ ግን አይታይም፡፡”ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና” የሚለው ቃል እንዲጠነቀቅ የሚያዝ ነበር፡፡
1.4 የተወለደበትን አላማ የማይስት ነው
ሶምሶን የእግዚአብሄርን ምሪት ተከትሎ መውጣት ቢሳነውም የተወለደበትን አላማ የሳተ አልነበረም፡፡ፊት ለፊት አትኩሮ ይመለከት የነበረው ጠላቶቹ የሆኑ አስተዳዳሪዎችን እንዴት እንዲያሸንፍ በማሰብ ነበር፡፡ ሀይልን ከተቀበለ በሁዋላ፡-
• ወደ ጠላት ሰፈር መቼ መግባት እንዳለበት ግን ምሪትን አልጠየቀም፡፡
• የቤተሰቡን ባርኮትና ምክርም አልሰማም፡፡
• የሙሴን ህግ አላስተዋለም፡፡
በዚህና በተመሳሳይ ምክኒያቶች ታላቁና ሃያሉ ሶምሶን ለእስራኤል መፍትሄና እረፍት ሳይሆን በአጭር ተቀጨ፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ለሰው ልጅ የሚመጣው ከራሱ አሳብ እንዲወጣና ወደ ቅዱሱ አምላክ አሳብ እንዲገባ ነው፡፡ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሲሆን በየትኛውም ዘመን የነበረና ያለ ነው፣ ዛሬም ቢሆን ሰው ይህን አሳብ ቸል ባለማለት መመልከት ያስፈልገዋል፡፡