ስራውን አስብ[1…]

የመጨረሻ ዘመን

ስራውን አስብ!
• እግዚአብሄር በግልህ ህይወት የሰራውን፣
• እግዚአብሄር ለመላው የሰው ልጅ/ለአለሙ ሁሉ የሰራውን፣
• እግዚአብሄር በየዘመናቱ የሰራውንና የገለጠውን፣
• እግዚአብሄር ከዘላለም አቅዶ በአዲስ ኪዳን የፈጸመውን፣
• እግዚአብሄር በአለም ፍጻሜ በዘላለማዊ መንግስቱ ሊገልጠው ያለውን፡፡
ስራው በትክክል ገብቶን ከሆነ ለልባችን የዝማሬና የቅኔ ምንጭ ይሆናል፡- በእያንዳንዳችን ህይወት የሰራው ስራ አስገርሞን፣ አለምን የተመለከተበት ርህራሄ ደንቆን፣ ከብዙ ዘመናት አስቀድሞ የገባቸውና እንደተናገረው ያደረጋቸው ስራዎቹ እያስገረሙን አምልኮና ምስጋና በውስጣችን ይፈጥራል፡፡ እግዚአብሄር ስራውን እያሰብን እንድንመካና እንድንደሰት ይፈልጋል፡፡
”እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።” (1ዜና.16:8-10)
”ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ። ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።” (መዝ.64:9-10)
የእግዚአብሄር ስራ በእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት የሚታቀድና የሚከናወን ሲሆን የሚከተለንና የሚያኖረን የማዳኑ ስራ፣ ህይወታችንን ሊደግፍና ከተለያየ ፈተና አውጥቶ ሊያበረታን፣ ሊያቆመን፣ ሊያጸናንና ለዘላለም ህይወትም ሊጠብቀን የሚችል የእግዚአብሄር ችሎታ መገለጫ ክንዋኔ ነው፡፡
መዝ.145:11-21 ”የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል። የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ። እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል። አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።”
እግዚአብር ሲሰራ አሻራውን በዘመናት ላይ ስለሚያስቀመጥ ትውልድ ሁሉ እንዲያስበው ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሄር አሰራር በኛ ላይ ሲገለጥም የሚፈጥረው ለውጥ የጸና በመሆኑ የሚዘነጋ ሳይሆን በእኛ እየኖረ የሚታሰብ ነው፡፡ ያም ስለሆነ እግዚአብሄርን እናነግሰው ዘንድ ስራውን እያሰብን እንጠራዋለን፣ እናመልከዋለን፡፡ በዘዳ.32:3-8 ውስጥ ሲያስረዳ፡-
”የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ። እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው። እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው። ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው። የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ።”
የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄር ያደረገላቸውን አስደናቂ ተግባርና ውለታ ሊረሱ ይገባ ነበር ወይ? ስራውን ዘምረውለት ነበር፣ አመስግነውትም ጭምር፡፡
መዝ.106:9-13 ”የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው። ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው። ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም። በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ። ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።”
እግዚአብሄር ሊሰራ ሲወርድ እስራኤልን በግብጽ ምድረ-በዳ ሲባዝን አገኘው፤ በባርነት እየተረገጠ ሲለፋ፣ በጥማት ምድር ሲሰቃይ በዚያ አየው፣ ራራለትም፤ የአባቶቹን ቃል-ኪዳን አስቦም ነጻ ሊያወጣው ወሰነ፡፡ ሁዋላም ስራውን በታምራት ገለጠ፡፡ እግዚአብሄር ሊጎበኘው በወረደ ጊዜ እስራኤል በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ ላይ ደክሞ ነበር፤ ስለራራለት በበረሀው አሩርና ንዳድ እንዳይቃጠል ሲል ከበበው በፍቅሩም ይዞ ተጠነቀቀለት፤ ከወደረኞቹ ግብጻውያን ያስመልጠው ዘንድ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው። እስራኤላውያን በግብጽ ምድር በባርነት እንዲኖሩ እግዚአብሄር ስላልፈቀደ ዘመኑ ሲሞላ እጁን አንቀሳቀሰ፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድም ህዝቡ ወደ ምድረ-በዳ ወጣ፤ ቀይ ባህርን በታምራቱ አሻገረው፡፡ ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው። እግዚአብሔር ብቻውን ህዝቡን መገበ፣ ተንከባከበ፣ መራውም፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም። ክብሩን አሳየው፣ በአህዛብ መሀል በአስፈሪ ክንዱ ከልሎ በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ ከነአን ምድር ባገባው ጊዜ የእርሻውን ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥ ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤ የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣ። ይሹሩን በእግዚአብሄር ስራ ተደላደለ፣ ወደ እረፍት በገባ ጊዜ ሰነፈ፣ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ ባሳረፈው ዘመን ስራውን አላሰበም፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ። ለስራው የሚገባውን ምስጋና ዘነጋ፣ ፊቱንም ቀድሞ ወደ ማያውቃቸው ወደ ከነአን አማልክት መለሰ፡፡ በጭንቁ የደረሰለትን አምላኩን ትቶአልና እግዚአብሄር ተቆጣ፤ የሚገባውን የስራውን ምስጋና ለማይገባቸው አማልክት ሰጥቶአልና እግዚአብሄር አዘነበት፡፡ እግዚአብሄር ተቆጣም፡፡
መሳ.2:10-15 ”ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ። ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፥ በዙሪያቸውም ካሉት ከአሕዛብ አማልክት ሌሎችን አማልክት ተከተሉ፥ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡ። እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ወደ ማረኩአቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጠላቶቻቸውንም ከዚያ ወዲያ ሊቋቋሙ አልቻሉም። እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ።”
ቢያስተውሉ ኖሮ ግን እግዚአብሄርን በሚጠባበቁ ሰዎች አካባቢ የሚኖረው የእግዚአብሄር በጎነት ይቀበላቸው ነበር፤ ከመካከላቸው ስራውን ልብ ያሉት ቅዱሳን የሚሰራውን ይህን አምላክ እስኪሰራ ድረስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አሻግረው በመመልከት በዘመኑ፣ በትውልዱ፣ በምድሩና በህዝቡ ላይ እንዲሰራ ጥብቅ ምልጃና ጸሎት ያደርጉ ነበር፡-
ዕን.3:1-7 ”የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር። አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ። እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል። ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል። ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው። የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።”
እግዚአብሄር ለጠበቁት ተገልጦ ሲሰራ ሶስት ነገሮች በዚያ ይኖራሉ፡-
• ስፍራ፣ የእግዚአብሄር ስራ የሚገለጥበት ቦታ
• ጊዜ፣ እግዚአብር ስራውን የሚገልጥበት ዘመንና ወቅት
• ክስተት፣ እግዚአብሄር በወሰነው ስፍራና ጊዜ ተገልጦ የሚያከናውነው ስራ/ድንቅና ታምራት
እግዚአብሄር የተናገራቸውን ትንቢቶች የሚፈጽምበት ጊዜ፣ ስፍራና ሊፈጸማቸው ያሰበውን ስራዎች ባለማስተዋል ወደ ተሳሳተ ትርጉዋሜና የህይወት ልምምድ ውስጥ የገቡ/የሚገቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ስለዚህ የእግዚአብሄርን ስራ በትክክለኛው ሰአትና ስፍራ ፈጽሞ ለማየት ሲባል ከላይ የተባሉትን አብይ አሳቦች ማወቅ ጠቀሜታ አለው፡- እግዚአብሄርን ለመጠባበቅ፣ የሚሰራበትን ዘመን ለማስተዋል፣ አደርገዋለሁ ያለውን እያሰቡ ወደ እርሱ ለመጸይና ለማሳሰብ፣ ስራው በተፈጸመ ጊዜም ለማመስገንና ለማምለክ ጭምር፡፡ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማረጋገጫዎች የሚሆኑት እነዚህ ሶስቱ ማእከሎች ናቸው፡፡
ኢያ.11:4-9 ”እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞችና ሠረገሎች ጋር ወጡ፤ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ። እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፡- ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው። ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም። እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።”
እግዚአብሄር በሚገለጥበት ስፍራና ጊዜ እንደሚሰራ ከላይ በተጠቀሰው ቃል ውስጥ መመልከት እንችላለን፡፡ የጠላት ተዋጊዎች እስራኤልን ለመውጋት ወደ ማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው እንደ ሰፈሩ እግዚአብሄር አየ። ኢያሱንም፡- ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው አለው፡፡ እንዳለውም በማግስቱ ጠላቶቻቸውን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም መቱአቸውም፡፡ ኢያሱ ጠላቶቹን የሚመታበትን ስፍራና ጊዜ በትክክል ስለተረዳ እግዚአብሄር በቀጠረው ሰአት፣ ባለው ስፍራም ስለተገኘ እቅዱ ተሳካ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ነቢያት በተናገሩበት ስፍራና ጊዜ ተገልጦ ስለእርሱ ስራ የተናገሩትን እየጠቀሰ ይፈጽመው ነበር (ሉቃ4:17-21)፡፡
ማቴ.4:12-17 ”ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። በነቢዩም በኢሳይያስ፡- የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፡- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።”
በነቢዩ ኢሳያስ አስቀድሞ የተነገረ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጊዜው ነበረ (ዮሀንስ አልፎ ሲሰጥ ስራው ሊጀምር ሆነ)፣ በዚያን ጊዜም ስራው የሚገለጥበት ስፍራ ታወቀ (ስፍራው የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ ነበር) ስራውም በዘመኑ ፍጻሜን አገኘ (በጨለማ ለተቀመጠው ህዝብ ብርሀን፣ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሀን ወጣላቸው እንደተባለ)፡፡
ኢዮ.36:22-25 ”እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው? መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው? ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ። ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል።”