ስለ መስቀሉ ቃል ‹1..›

ቤተክርስቲያን

የእግዚአብሄር ቃል ስለ መስቀሉ ቃል በ1ቆሮ.1:18 ላይ እንዲህ ይላል፡-
”የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።”
በመስቀሉ ቃል እውቀት ላይ የሚቀርቡ አሳቦች ወይም የሚንጸባረቁ አቁዋሞች የአማኝን የእምነት ይዘት ይወስናሉ፣ ያም ብቻ አይደለም የዘላለም አድራሻውን ጭምር ይወስናሉ፡፡ ለሚያምኑት ቃሉ የእግዚአብሔር ኃይል ሲሆን ለማያምኑት ሞኝነት (ከንቱና የማይረባ አሳብ ብቻ) ይሆንባቸዋል፡፡ ሰዎች ከንቱና የማይረባ ብለው የወሰኑትን አሳብ መታገስ አይችሉም፡፡ ቁም ነገር እንደሌለው በመቁጠር ወዲያው ይቃወሙታል፡፡ ቃሉን በዚህ ደረጃ የሚቆጥር ሰው ከፍተኛ የመንፈሳዊ እውቀት እጥረት ያለበት ስለሆነ እውቀቱ ከንቱ ይመስለዋል፡፡ ቃሉን በአለም/በስጋዊ ጥበብ የሚሰብኩ ቢኖሩ በትምክህትና በራስ መተማመን ስለሚሰብኩት ይወድቃሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ግን የእግዚአብሄር ሀይል መገለጫ መሳሪያው ነው፣ ስለዚህ የሰው እጅ ጣልቃ ሊገባበት አይገባም፡፡
ሀዋርያ ጳውሎስ ያደገው የአይሁድን የእምነት ትምህርት እየቀሰመ ነበር፤ እንዲሁም ባደገበት ስፍራ ይታወቅ በነበረው የአለም ፈላስፎች ትምህርት ላይ ግንዛቤ ነበረው፡፡ ከጌታ መወለድ በሁዋላ እግዚአብሄር በክርስቶስ ያመጣው እውነት ግን እነዚህን አስተምሮዎች የሚሽር ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሀጢያትና ከሞት ሊያድነን በመስቀል ላይ ሞቶአል የሚለው ትምህርት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የአይሁድ ልማድና እምነት እንዲሁም ጥበበኞች ጊዜና ህይወታቸውን የሰጡለትን ፍልስፍና ከስር የሚነቅል ሆኖ ስለተገኘ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ የመስቀሉ ቃል በየትውልዱ ሲነገር የነበረውን የአባቶች ትምህርት ሽሮ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሄር የማዳን እቅድ የሚያመጣ ቢሆንም መስቀል የሚባለው መቀጣጫ እንጨት በዘመናቸው ከሚያውቁት የወንበዴና ከባድ ፍርደኛ ቅጣት ውጪ ሌላ ክንዋኔ ይፈጠርበታል ብለው ማሰብ አልተቻላቸውም፡፡ የክርስቶስ መሰቀል (መከራ የመቀበሉና በመስቀሉ ላይ የመሞቱ ክንዋኔ በሙሉ) ግን የሰው ልጆች የደህንነት ተሰፋ ሙላትና የደስታ ምንጭ ነው፡፡ በእርሱ የመስቀል ሞት ብቻ የእኛ ዘላለማዊ ህይወት ስለሚረጋገጥ ለአማኞች ብቸኛ ምርጫ ነው፡፡
በወንጌል ስብከት ላይ የሚፈጠረው አሰማም የህይወትን አድራሻ እንዴት ሊለውጥ እንደሚችል ቃሉ ያሳያል፡- ሰው ሲሰማ በንጹህ ህሊና ሊሰማና ሊድን እንጂ አለም በምትተነትነው የእምነት መንገድ የክርስቶስን ስራ ማስተዋል አንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወንጌሉ ሲሰበክ ሀጢያተኛው በእምነት ከሰማው የሚነጻበትን መንገድ ይፈጥርለታል፣ አቅልሎ ከተቀበለው እርሱ እራሱን በተመሳሳይ ስፍራ ያኖረዋል፡፡
ስሜታዊነት፣ ተንኮለኝነት፣ ኩራት እንዲሁም በጎ አመለካከት የሌለበት አሰማም የቃሉን መልእክት የሚያጣምም ስለሆነ እንዴት እንድንሰማ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ቃሉን አሜን ለሚሉ ግን ብርሀን ይታያቸዋል፣ ያ ብርሀን ወደ ጽድቅ የሚመራ ነው፣ ወደ ጌታ ማዳን የሚመራ ነው፣ እግዚአብሄር ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ ወዳዘጋጀው የምህረት ደጅ የሚመራም ነው፡፡ አሜን በሚል ልብ ላይ የሚዘራው ወንጌል የክርስቶስ ስቃይና መከራ በእኛ ሀጢያት አንጻር ገልጦ በማሳየት ህይወትን ወደ ንሰሀ የመምራት አቅም አለው፡፡ በወንጌል በኩል የምናገኘው እውቀት ክርስቶስን አጉልቶ የሚያሳይና የእርሱ የፍቅር ጉልበት በመከራው ውስጥ እንዴት ለእኛ እንደተገለጠ የሚያሳይ ነው፡፡
መንፈሳዊ ሰዎች በአለም ጥበብ ተይዘው ከሆነ አለም ላይ ባተኮረ ህይወት ይጠመዳሉ፡፡ የአለም ጥበብ መሰረተ-እውቀቱ ምድራዊ ስለሆነ መንፈሳዊ ሊያደርግ አይችልም፡፡ የፈጠረን አምላክ ከሚሰጠው እውቀት ውጪ በፍልስፍና እውቀት መደገፋችን እምነትን አያስገኝልንም፡፡ ፍልስፍና የሚያደርሰው ወደ ተፈጠሩ ነገሮች፣ ወደ አእምሮአዊ እውቀት እንዲሁም አለም ላይ እየሆኑ ስላሉ ግልጽና ሚስጥራዊ ነገሮች እንጂ መንፈሳዊው አለም ያለበትን ሁኔታ አይገልጥም፡፡ ፍልስፍና ጣኦትን በህሊና የመፍጠር ችሎታ አለው፡፡ ወንጌል ግን ክርስቶስን በህሊና ውስጥ ይስላል፣ እርሱን ማመን ያስተምራል፡፡ በአለም የሚገኙ አዋቂዎች የክርስቶስን ስብከት እንደ ከንቱ ንግግር ይቆጥሩታል፣ ሰባኪዎችንም ተራ ለፍላፊ አድርገው ያያሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እነርሱን ሞኞች ይላቸዋል፣ ዋጋ ያለውን ነገር አቅልለዋልና፡፡
የእግዚአብሄር ጥበብ የተባለው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር ጥበብ የሆነበት ምክኒያት እግዚአብሄር ያቀደው እቅድ ሁሉ ተጠቅልሎ በእርሱ መኖሩ/መዝገብ በመሆኑ/ እና ክርስቶስ በማስተዋል ሲታወቅ የእግዚአብሄር ዘላለማዊ እቅድ የሚታወቅ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሙሴ እንዲሰራ ያሳየው ድንኩዋን፣ ህዝቡ የሚመራበት ስርአት፣ ፍርድና ህግ ሊመጣ ላለውና በክርስቶስ ውስጥ ተጠቅልሎ ላለው የእግዚአብሄር ምስጢር ምሳሌ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በዘላለም አሳብ የገለጠው (በክርስቶስ መከራና ሞት የገለጠው) የማዳን ስራ በመስቀሉ ላይ ፍጻሜ አግኝቶአል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶአል፡፡
ወንጌሉ ስለክርስቶስ የመሰቀል ስራ የሚናገር ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ የሞተበትን አላማ የሚገልጥ፣ በመስቀል ላይ በመሞቱ ያመጣውን ደህንነት ለአለም የሚያደርስ የምስራች ነው፡፡ ይህ ታላቅ የድል ብስራት ነፍሳቸው ዘላለማዊ ህይወትን ለተጠማች ሰዎች የደስታ ብስራት ቢሆንም በአለም ላይ በሚገኝ ጥበብ የታጠቁ ከእውቀታቸው ጋር የማይገናኝ አሳብ ስለሚሆን ይንቁታል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል በ1ቆሮ.1:18 ውስጥ ያስቀመጣቸው አንኩዋር እውቀቶች በአጽንኦት እንድናያቸው ይጋብዛሉ፣ ከነርሱም አንዳንዱ የሚከተሉት ናቸው፡-
የመስቀሉ ቃል
ስለ ጌታና በመስቀል ላይ ስለሰራው ስራ የሚያወራው ቃል ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል በመስቀል ስለመሰቀልና በመስቀል የመሰቀል ሁኔታ ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳውቃል፡፡ ወንጌል በመስቀል ላይ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው ይላል፣ ከፍተኛ ቅጣትና አሰቃቂ ሞት የሚከናወንበት ነውና፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሀጢያት የሌለበት የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ሳለ ሀጢያተኞች የሚቀጡበትን የመጨረሻ የቅጣት አይነት በምን ምክኒያት ሊቀበል ቻለ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ የክርስቶስ መልእክት እንደ ፋና ሆኖ ጨለማን በመግፈፍ የሰው ልጅን በመንገዱ ይመራዋል፡፡ መልእክቱ ሰውን ወደ ጌታ የማዳን ስራ እርሱም የመስቀሉ ስራ ወደ ሆነው ያደርሰዋል፡፡
ህይወት የሚሰጠውን የወንጌል ምስራች የሚከልል ስጋዊ አስተሳሰብ ሀይማኖተኛ ያስመስላል እንጂ እውነተኛውን የወንጌል ሀይማኖት አያኖርም፡፡ ከዚያ የህይወት ስርአት ወጥቶ የወንጌል መልእክትን የተቀበለ በእምነት ተስፋና ፍቅር ይያዛል፣ ትምክህቱ ጌታ ስለሚሆን ክብሩን ከእርሱ ይቀበላል፡፡
ገላ.6:12-15 ”በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።”
ጌታ መስቀል ላይ በዋለ ወቅት በዚያ ሰአት ከፍተኛ መከራና ስቃይ እንዲቀበል ሆኖአል፡፡ ሰው ጻድቅ ሆኖ ይህን የሚያህል የከፋ ስቃይ መሸከም አይችልም፣ የሀጢያትን ዋጋ መቀበል አሜን ሊለው አያበቃውም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ከዚያ ስቃይ በሁዋላ ሊመጣ ያለውን የሰው ልጆች ደህንነት ስለተመለከተ በመስቀል ላይ ያን የሚያህል ስቃይ በትእግስት ተቀበለ፡፡ በመስቀሉ ስራ የኛ የደህንነት መሰረት ተጣለ፡፡
የደህንነት ትምህርት በመስቀል ላይ ስለተከናወነው የክርስቶስ መከራና ሞት የሚመሰክር ትምህርት ነው፡፡ በክርስቶስ እንዲሁም በመስቀል ላይ በሰራው ስራ እኛ ከአለም አለምም ከእኛ እንድንለያይ ሆኖአል፡፡ ምክኒያቱም ወደ ጌታ እየተጠጋንና በጸጋው እያደግን ስንሄድ ለአለም ያለን ፍቅር እየቀነሰና የአለም ፍላጎት ከውስጣችን ይከስማል፡፡ የጌታ ማዳን በውስጣችን እየበራ የአለም ምስል እየደበዘዘ ስለሚሄድም አመጽ ከባህሪያችን ላይ እየወደቀ ይሄዳል፡፡ አማኝ ሲደነቅ በክርስቶስ የማዳን ስራ፣ ሲመካ ጌታ ባዳነው ደህንነት ብቻ ይሆንና ይህች አለም ያጨቀችውን ዝባዝንኪ ወደ መጸየፍ ደረጃ ይደሳል፡፡
1.እግዚአብሄር ስለ እኛ ሀጢያት አደረገው
2ቆሮ.5:21 ”እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”
በእስራኤላውያን ዘንድ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ በፍርድ ውስጥ መታየት ትልቅ እፍረት ነው፡፡ በአለም ሊኖር ያለው ስጋ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ነፍስና ስጋ በከፍተኛ መከራ፣ ሳግ፣ ጭንቅና ጩሀት መሀል ሆኖ ሲታይ እጅግ ይዘገንናል፤ ነገር ግን በሰው ውሳኔ ይህ ፍርድ ሲሆንና የተፈረደበት ሰው በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሲታይ መከራው ይጎላል፤ ሀጢያተኛ ተመልካች ግን በዚያ ሁኔታና ያን በመሰለ የጭንቅ ሰአት ላይ የሰውየውን ስቃይ አይቶ ከመፍራት ይልቅ አመጽን አጉልቶ በመመልከት ይዘብታል እንጂ ባየው አሰቃቂ ፍርድ ንሰሀ አይገባም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ስለእኛ ያን ውርደት ተቀብሎአል፡፡
መስቀሉ የሰው ፍርድና የእግዚአብሄር ምህረት በክርስቶስ ሰውነት ላይ የተገናኙበትን ቅጽበት ያስተናገደ ስፍራ ነበር፤ ሀጢያተኛ ሰው በክርስቶስ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ሀጢያቱ ሁሉ በክርስቶስ ስጋ ላይ አርፎአል፡፡
1ጴጥ.3:18 ”ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ”
እግዚአብሄር የሰውን ልጅ ከከፋውና ለአጋንንት ከተዘጋጀው ዘላለማዊ ፍርድ የሚያድንበት ሌላ መንገድ አላገኘም (የዘላለም ፍርድ አስቀድሞ የተዘጋጀው ለሰይጣንና ተከታዮቹ እንጂ ለሰዎች እንዳልነበረ ልብ ማለት ያስፈልጋል)፤ ስለዚህ የወለደውን አንድያ ልጁን አሳልፎ ለሞት ሊሰጥ ተገደደ፡፡
ኢሳ.59:14-17 ”ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና። እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ። ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።”
እግዚአብሄር የተስፋ ቃል በሰጣቸው ወገኖች መሀል ሲመለከት ቅን ፍርድ አላገኘም ነበር፣ ከዚህ ይልቅ አመጽ ገዛቸው፡፡ ሲመለከት በመሀላቸው እውነት የለም፣ እግዚአብሄር ጽድቅ ከህዝቡ ልብ ወጥቶ በሩቅ ቆሞ አየ፤ እውነት ያለሀፍረት ከፈራጆች፣ ከአባቶችና ከካህናት እጅ ወጥቶም በአደባባይ ላይ ወድቆ ነበር፣ በአመጽ ስለታበዩ ቅንነት ዳግም ወደ ህዝቡ ህይወት ሊገባ አልቻለም፤ እግዚአብሄር ሊሰራ ወርዶ እውነትን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር በዚህ ሁሉ መሀል እየጠፋ ስለነበረው ትውልድ እጅግ ተከፍቶአል፡፡
የሚማልድ ሰው እንደሌለ ካየ በሁዋላ በሰው በኩል ሊመጣ ያለ ብቁ ምልጃ ፈጽሞ እንደማይኖር ወስኖ ራሱ የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ፤ ያም የእርቅ መንገድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ የወሰነውን የደህንነት አሳብ ወደ ገሃዱ አለም ሲያመጣ የገዛ ክንዱን መድኃኒት አድርጎ ገልጦአል፡፡ ይህ መድሀኒት ክርስቶስ ነው፣ ክንዱ እርሱ ነው፣ ማዳኑ በስጋውና ደሙ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
ዮሐ.6:51-56 ”ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። እንግዲህ አይሁድ፡- ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።” ብሎአል::
እርሱ ሰው ከሆነ እንዴት? እንዴት ስጋውን እንዴትስ ደሙን? በመለኮታዊ እቅድ በኩል ካየነው ብቻ የዚህን አሰራር እናምነዋለን እንጂ በአለም ጥበብ አንጻር ይህ እውቀት ፍጹም እብደት የሚመስል ነገር ነው፡፡ ግን ይህ ነው ለአለም ሞኝነትና ከንቱነት ያስመሰለው እንጂ በእግዚአብሄር አሰራር እርሱ ብርቱ ነው፤ የእግዚአብሄር ሀይል ነው! በእርግጠኝነት ትውልዶች ሁሉ ነገሩ አምላካዊ ዝግጅት ያለበት መሆኑን ተቀብለን ልንድንበት የተገባ ነው፡፡ የክርስቶስ ደም ወይም ስጋ የእኛ ስጋና ደም አይደለምና አያሳፍርም፣ እግዚአብሄር ያዘጋጀው ከሀጢያት መዳኛ መድሀኒት ነው እንጂ፡፡ ስጋዬ ከሰማይ የወረደ እንጀራ ነው ብሎአል፡፡ ከምድር ባለመሆኑ ወይንም እንደ አዳም ያለ ስጋና ደም ይዘት ወይም ንጥረ-ነገር ያለው ባለመሆኑ ለመዳናችን ዋስትና ነው፣ ያንን የተቀበልን ሞት ሳይሆን ሕይወትን አግኝተናል፡፡ ይህ የመስቀሉ ስራ ውጤት ነው፤ ነገር ግን እውቀቱ በምድር ጠቢባን ዘንድ የተጠላ ነው (ክርስቶስ እንደኛ ሰው ነው ስላሉና በጥበባቸው ስህተት ስለሰሩ)፡፡ በዘመኑ ብዙዎች ያን ባለመቀበል ወደሁዋላ ብለዋል፡-
”ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። …ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም” (ዮሐ.6:55-57፣66)
ለነሙሴ ስለወረደው የሰማይ መና ጌታ አይሁድን ሲያስረዳ ነበር፡- እነሙሴ የበሉት መና እውነተኛና ዘላለማዊ እንጀራ ሳይሆን እግዚአብሄር የዘላለም እንጀራ የሆነውን ክርስቶስን ከሰማይ እንደሚሰጣቸው አመልካች ምሳሌ ነበር፡፡ አይሁዶች ምስጢሩ ስላልገባቸው በብርቱ ተከራከሩ፤ ይከራከሩ እንጂ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም የሚለው የጸና ቃል የሚሻር አይደለም፤ ከታመኑበት የዘላለምን ህይወት ሊሰጣቸው ሞኝነት አድርገው ቸል ካሉት ደግሞ ሊጥላቸው የሚችል ቃል ነበር፣ ዛሬም ለሌሎች ሰዎች እንደዚያው ነው።