በቀደመው ክፍል እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ በሚለው የምስራች ቃል ውስጥ ከሚገኙ ትኩረታችንን ከሚስቡ ነገሮች መሃል መድሃኒት፣ ስምና ጽንስ እንደሚገኙ (የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነው ስለሚል) እነዚህ ሶስት ነገሮችም ሰማያዊ ምንጭ እንዳላቸው አይተናል፤ በተለይ መድሃኒትን በተመለከተ እግዚአብሄር በነቢያት በኩል አስቀድሞ እንደተናገረ እንዲያውም እርሱ ራሱ መድሃኒት ሊሆን እንደወሰነ ከቃሉ አይተናል። በእግዚአብሄር አሰራር የተገለጠ መድሃኒት ስጋና ደም (ሰውነት) ሊኖረው የተገባው ስለነበረ ያ ይፈጸም ዘንድ እግዚአብሄር አንድ አሰራር ገለጠ፣ እርሱም በቃሉ ላይ እንዲህ ይላል፦
ዮሐ.1:9-14 ‘’ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።’’
መድሃኒታችን እግዚአብሄር የቃል ኪዳን አምላክ እንደመሆኑ እንደተናገረው ሁሉን የሚፈጽም አምላክ ነው፤ ሃዋርያው ዮሃንስ ይህ አምላክ ወደ አዲስ ኪዳን ከመግባቱና በወሰነው የመስዋእት ተራራ ላይ የመድሃኒት ምንጭ ከመሆኑ አስቀድሞ ምን እያደረገ እንደነበር በጥቂቱ ሲያነሳ እንመለከታለን፤ ስለዚህ ወደ አለም ከመግባቱ በፊት ወይም ብሉይ ኪዳንን ዘግቶ አዲስ ኪዳን ከመስጠቱ በፊት፣ እንዲሁም በቀራኒዮ ተራራ ላይ መስዋእት ከማዘጋጀቱ አስቀድሞ ምን ሰራ? ለሚለው ሃዋርያው መልስ ይሰጣል፦
በፍጥረት መጀመሪያ (መላእክት ሳይፈጠሩ፣ ምድርና ሰማይም ገና ወደ መሆን ሳይመጡ በፊት ) እግዚአብሄር ከውስጡ እያወጣና እየተናገረ የሚፈጥርበት ቃል በርሱ ነበረው፣ በዚህም ከእግዚአብሄር አፍ ሁንና ይሁን እያለ ሲወጣ የነበረ መለኮታዊ ድምጽ ፍጥረትን ቀዳሚ መሆኑ ይታያል (ስራው በዘፍጥረት መጽሃፍ ውስጥ ይታያል ማለት ነው)፤ እግዚአብሄር ፍጥረታትን ወደ መሆን ያመጣበት ቃልም በራሱ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ ሲሆን ቃሉ የሃይል ድምጽ እንጂ ከእግዚአብሄር የተለየ ማንነት ስላልሆነ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ተባለ።
ከእግዚአብሄር አፍ የወጣ ይህ ቃል በፍጥረት መጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለነበረ በዘፍጥረት መጽሃፍ ውስጥ የምናየው የአፈጣጠር ሂደት በሙሉ በእርሱ ሆነ፣ ተከናወነ፣ ተሰራ።
ዘፍ.1.1-3 ‘’በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።’’
ስለዚህ በዘፍጥረት ውስጥ ከምናየው ስራና ከሆነው ነገር አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም የሚለው እውነት መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ከእግዚአብሄር አፍ እየወጣ ፍጥረትን የፈጠረ መለኮታዊ ቃል ውስጥ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
እግዚአብሄር ሲናገር የሞተ መንፈስም፣ ነፍስም፣ አካልም ጭምር ይነሳል፣ ህያው ይሆናል፣ ህያው ሆኖም ይቀጥላል፣ በዚህ ህያው አምላክ ፊት በማስተዋል ይመላለሳል። ይህ መረዳት ያገዘው ሰው ሲናገር ‘’ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል’’ ብሎአል (ማቴ.8:8)።
1ዮሐ.1:1-2 ‘’ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን’’
በእግዚአብሄር ማንነት ውስጥ መጀመሪያ የለም፤ እግዚአብሄር ከሆነ ስፍራ ወይም በሆነ ጊዜ መኖር አልጀመረም፤ እርሱ እንዳለ አለ። ፍጥረት ግን ህይወቱ መነሻ ስላለው፣ መጀመሪያው ታሳቢ ነው።
ለአለሙ ሁሉ ይህ ህይወት የሆነ ጌታ ብርሃን ሆኖለት ይመራዋል፤ ብርሃን ሆኖለት ማስተዋል ይሰጠዋል፤ በርሱ ግራና ቀኙን ይለያል፤ ፊቱን እንዲያይ ኋላውን እንዲያሰላስል፣ በትክክል እንዲወስን ይረዳዋል፤ ክፋትና መልካምን እንዲለይ በጎ ዝንባሌ እንዲኖረው ከምንም በላይ አምላኩን እንዲሻና እርሱን እንዲከተል የአምላክ ብርሃን ያግዘዋል።
ይህን የሚያደርግ አምላክ በብርሃኑ በጨለማ አለም ላይ ያበራል፣ አለሙም ላይ ያለው የጨለማ ስራ በርሱ ግልጥ ሆኖ ይወጣል፤ ተሰውሮ በሰው ዘንድ ክፋትን የሚዘራና የሚያስተላልፍ መንፈስ በርሱ ይገለጣል፤ አለምን የተቆጣጠረ ያ ጨለማ ሃይል ግን ጌታን ከቶ አያሸንፈውም። ስለዚህ የሰው ልጅ ያለ ህይወት ብርሃን መኖር አይችልምና ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ከፍጥረት አንስቶ ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። አለምንም በብርሃኑ ይጎበኝ ስለነበር በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ተባለ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ዓለሙ ግን የህይወት ብርሃንን ማንነት አላወቀም።
የህይወት ብርሃን የሆነ አምላክ በምድር ላይ ወገኔ የሚለው አብረሃምና የርሱ ዘር የሆነ ህዝብ ነበረው፤ ህዝቡም እስራኤል ተብሎ ተጠርቶአል፤ እግዚአብሄር ለዚህ ህዝብ ቃልኪዳንን ሰጠ፤ ስለ እስራኤል ሃዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦
‘’በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም። እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፥ ነገር ግን፦በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ተባለ። ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው።’’ (ሮሜ.9:3-8)
ወገንን ያዘጋጀ አምላክ ወደነርሱ መጣ፤ ህዝብን ያዘጋጀ አምላክ በህዝቡ መሃከል ተገኘ፤ ቃል ለገባለት ወገን ቃሉን ጠበቀ፤ ልጅነትን ለሰጠው እስራኤል አባትነቱን ሊያስመሰክር ተገለጠ፤ ይህ አምላክ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክነቱ እንዲታወቅ በሥጋ መጣ፤ የእርሱ ወደ ሆነው ወገን እንደቃሉ መጣ፥ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ሆኖም ለተቀበሉት አባትነቱን ሳይነፍግ፣ በስሙ ለሚያምኑትም እርሱነቱን ከማሳወቅ ሳይታቀብ ግልጥ ሆኖ ታየ፤ ለእነርሱ ለታመኑቱ አምላክ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠ፤ ምክኒያቱም እነርሱ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
እግዚአብሄር በስሙ ያመኑትን በሙሉ በርሱ በኩል ዳግም ወልዶ ልጆቹ ያደርግ ዘንድ አስቀድሞ አንድ ልጅ ከራሱ መውለድና ወደ አለም ማስገባት ያስፈልገው ነበር፤ ስለዚህ ቃሉን ከራሱ አወጣ፣ ወደ ማርያምም ልኮ ቃሉ በማርያም ማህጸን ውስጥ ሥጋ ሆነ፤ ዮሐ.1:14 በግልጥ እንዳስቀመጠው የእግዚአብሄር ቃል ከማርያም ማህጸን ስጋ አልተካፈለም ወይም ቃሉ ስጋዋን አልደረበም፣ ነገር ግን ራሱ ቃሉ ስጋ ሆነ፣ ይህ ስጋ የሰው ነገር ሳይሆን ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በአይሁድ መሃከል አደረ፤ እነርሱም አንድያ የእግዚአብሄር ልጅን የክብሩ መንጸባረቅና የባህሪው ምሳሌ መሆኑ እንዲሁም ለአለም ይገለጥ ዘንድ ከአባቱ ከእግዚአብሄር ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አዩ አመኑም።
የብዙዎች ጥያቄ ከማርያም የተወለደው ልጅ እንዴት የእግዚአብሄር ልጅ ይባላል ወይም እግዚአብሄር እንዴትስ ወለደው ይባላል? የሚል ነው፤ ደግሞ ሰው እስከወለደው ድረስ እግዚአብሄር ወለደው እንዴት ይባላል? የሚል ጥያቄም ሁሌ ይነሳል። በርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማፈላለግ ብዙዎች ደክመዋል፤ ያቀረቡት ትንተናና መልስ ግን ሰዋዊ ሆኖ ከተወለደው ልጅ ባህሪ ፍጹም ያፈነገጠና እርሱን የማይወክል ሆኖ ኖረ፤ በዚያ ሁኔታ አሁንም እየኖረ ስላለ በየትውልዱ የበቀለ ጭቅጭቅ አሁንም ድረስ ሊቆም አልቻለም።
ወደ እግዚአብሄር ቃል መለስ ስንል ክርስቶስ ገና ሳይወለድ ስለርሱ የተነገረ ነገር እንዳለ እናያለን፤ ከዚያም እልፍ ሲል ክርስቶስ ተወልዶ በምድር ላይ ስራውን እንደፈጸመና ወደ ሰማይ እንዳረገ ያን አከናውኖም በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ ያሳያል፤ በተለያየ አጋጣሚ ታሪኩን ከሚናገሩ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዳንዶቹ የሚከተሉት የሚሉ ናቸው፦
የእግዚአብሄርን ልጅ ሲገልጠው
– በማቴ.1:20 ላይ የእግዚአብሄር ልጅ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያሳያል።
– በዮሐ.1:13 የአዳም ልጆች ክርስቶስን ሲለብሱ ምን እንደሚሆኑ ሲናገር፦ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም ይላል።
– ዮሐ.3:6 ስለ አዳም ልጆች አወላለድ ሲናገር፦ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ሲል ከእግዚአብሄር መወለድን ሲገልጽ ደግሞ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው ይላል።
– በዮሐ.6:51 ላይ የእግዚአብሄር ልጅ ሲናገር፦ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው ብሎአል።
– በዮሐ.6:53 ላይ የእግዚአብሄር ልጅ ሲናገር፦ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ይላል።
– ሮሜ.1:3-4 ሲናገር ይህም ወንጌል በሥጋ (ሰማያዊው ስጋ) ከዳዊት ዘር (በማሪያም ማህጸን ውስጥ አድሮ) ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ (በስጋ ሞቶ በመንፈስ ግን ህያው ስለሆነ) ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
– ዮሃ.1:14፣ ስለእግዚአብሄር ልጅ ሲናገር፦ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።
– ዮሃ.6:56፣ ስለእግዚአብሄር ልጅ ሲናገር፦ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ አለ።
– ሐዋ.2:29-31፦ ‘’ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።’’ ይላል።
– ሮሜ.6:6 ፦ ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና ይላል።
የአዳምን ልጆች ምንነት ሲገልጣቸው
– ሮሜ.6:12 ፦ እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ ይላል።
– ሮሜ.6:19ም ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ ይላል።
– ሮሜ.6:12፦ እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ ይላል።
– ሮሜ.6:19ም ሲናገር፦ ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ ይላል።
– ሮሜ.7:4-5 ፦ በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበር፤
– ሮሜ.8:3-4 ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ።
– ሮሜ.8:5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።
– ሮሜ.8:13 እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።
– 1ቆሮ.1:29 የአዳም ልጆችን ክብር ያጋልጣል፦ ስለዚህ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ይላል።
– ይህን ድካማችንን ስናውቅ፣ ማንነታችን ስንገነዘብና ለራሳችን የሚበጀን እርሱ አምላክ ብቻ መሆኑን ስንወስን ሁሉም በትክክለኛ መስመር ውስጥ ይገባል፤ የእግዚአብሄርም ፈቃድ በዚያ ይፈጸማል።