ስለእርሱ ያልኩት ይህ ነበር (ዮሐ.1:15) – 1…
ስለመድሃኒታችንና ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉ ምን ይላል? እርሱ ማን መሆኑን ለምንጠይቅ የእግዚአብሄር ቃል መልስ አለው። ቃሉ በዮሐ.1:30 እንደሚል፦
‘’አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።’’ ይላል፤ ስለዚህ ቃሉ ዛሬም ስለርሱ የሚለው አለውና ከርሱ እንስማ።
– እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ (ሉቃ.1:21)።
የዮሴፍ ታሪክ በመጽሃፍ ቅዱስ መተረክ የሚጀምረው ክርስቶስን ከምትወልደው ከማርያም ጋር ከነበረው እጮኝነት ዘመን አንስቶ ሲሆን እርሱ በወቅቱ ስለጋብቻው በሃሳብ ተጠምዶ ባለበት ወቅት የእግዚአብሄር የዘላለም አሳብ በህይወቱ ተገለጠ፤ ዮሴፍ ግን አልገባውም ነበርና ትኩረቱ ወደፊት ባቀደው ጋብቻ ውስጥ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ላይ ወደቀ፤ በእጮኛው ላይ እየሆነ ስላለው ያልተለመደ፣ ውጤቱ የሚያስፈራ በሌላ በኩል አደራረጉ ሊገባው ያልቻለ እንግዳ ነገር አእምሮውን ሲያናውጠው ሳለ ድንገት የእግዚአብሄር መልስ መጣለት፤ ስለ እጮኛውና በእርስዋ ላይ ስለሆነው ነገር መልስ የሚሆነውን ከአምላኩ ሲያገኝ ለእርሱም እረፍት ሆነ፣ ለአለምም የምስራች ብስራት ሆኖ ተገኘ።
ያኔ አጥብቆ በማርያም ህይወት ውስጥ ስለሆነው ነገር ሲያስብ፦ ‘’እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።’’ አለው። ይህ ድምጽ በማርያም ማህጸን ውስጥ ስላደረው ስለእርሱ ስለ እግዚአብሄር ልጅ የተነገረ የምስራች የሆነ ቃል ነው። ስለዚህ በቃሉ የሆነ ከሰማይ የወረደ መለኮታዊ አዋጅ እንደሚለው ፦
– እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድን ነው
– የሚያድንበት ስምም ኢየሱስ ነው
– ከማርያምም የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነው።
አዋጅ! ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ መድሃኒት ወደ ምድር ወረደ፣ የመድሃኒቱም ስም ኢየሱስ ተባለ። የእስራኤል ህዝብ ያስተውል ዘንድ በነቢያት እንደተናገረው፦
‘’የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፥ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ። እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፥ እናንተም ለዘላለም አታፍሩምና አትዋረዱም። ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር:- በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ።’’ (ኢሳ.45:15-19)
እግዚአብሄር የጠራቸው መንፈሳዊ እስራኤል የሆኑትና መዳን ሲታወጅላቸው ያመኑት እነርሱ ከሃጢያታቸው በደሙ እንደታጠቡና ጸጋውን እንደተቀበሉ ቃሉ ያሳያል። የምስራቹ ሶስት ዋና ነገር አውጆልናል፦ መድሃኒት፣ ስምና ጽንስ። እነዚህን ሶስት ነገሮች ከቃሉ ስንመረምር ሰማያዊ ምንጮች እንዳላቸው ያሳየናል።
ስለመድሃኒት ሲነሳ ለእስራኤል ከዚያ አስቀድሞ መድሃኒት ሆኖለት አልነበረም ወይ? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በተለያዩ ጊዜያት እስራኤል ከጠላት ድኖአል፣ ከበሽታ ድኖአል፣ ከመቅሰፍት ድኖአል፤ ለህዝቡ እጅግ የበዛ መልካምነት ከአምላኩ ተከናውኖአል፣ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በላይ አንድም ወገን ከሃጢያት ሊድን ስላልቻለ እግዚአብሄር ያን መፍትሄ በራሱ ሊያዘጋጅ ወሰነ። አስቀድሞ ህዝቡን ሲታደግ እንደታየው (የደህንነት ስራዎቹ ሲከናወኑ) እግዚአብሄር ማዳኑን በሰው በኩል፣ በመላእክት በኩልና እግዚአብሄር ራሱ በላከው በትር ህዝቡን ሲታደግ ኖሮአል። ከሃጢያት ለመዳን ግን የትኛውም ፍጡር አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደማይችል እግዚአብሄር ስለሚያውቅ የማዳኑን ስራ እርሱ ራሱ እንደሚፈጽመው በብሉይ ኪዳን ደጋግሞ አስታወቀ። ነቢዩ ኢሳያስ እግዚአብሄር የመድሃኒት ምንጭ መሆኑ ስለበራለት ስለእርሱ ተናገረ፦
‘’እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ። ውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ።’’ (ኢሳ.12:2-5)
የመድሃኒቱ ምንጭ ከህያው እግዚአብሄር ዘንድ ስለሚፈልቅ አያልቅም፣ ሰዎችም መድሃኒትን ተቀብለው፣ ድነው፣ ረክተውና አርፈው እንዲኖሩ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖአልና። እግዚአብሄር በነቢያት በኩል ለህዝቡ እንደተናገረው ሁሉ ለአህዛብም ተስፋ ሰጥቶአል፤ የሚያድነው ቀርቦም የሚታደገው እርሱ ራሱ ስለሆነ ቃሉ የታመነ ነው፦
‘’ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።’’ (ኢሳ.45:21-3)
እግዚአብሄ ለአብረሃም፣ ለይስሃቅና ለያእቆብ የተናገረውን ከነርሱ በሁዋላም ለዘራቸው አድርጎአል፤ ምክኒያቱም እስራኤል በሚገባበትና በሚወጣበት ዘመን ሁሉ የእግዚአብሄር እጅ ከእርሱ ጋር ነበረች፣ ማዳኑም በወደረኞቹ ላይ ተገልጣ ስትታደግ ህዝቡ በሰላም እንዲኖር አስችሎታል፤ ህዝቡ ይህን መለስ ብሎ እንዲያስተውልና በእርሱ እንዲታመን እግዚብሄር በቃሉ ይጠይቃል፦ ከጥንቱ አድኖ ያሳየ የተናገረስ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን ሲልም ራሱ መልስ ይሰጣል፤ ያን ያደረገ እርሱ መሆኑን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላከ እንደሌለ ህዝቡ በመረዳት በሚመጡ ዘመናት በሚገለጥ ጊዜ ሌላ አምላክ እንዳይፈልጉ ገና ከመሆኑ አስቀድሞ አስጠንቅቆአል። በሌላ በኩል ቃል ኪዳኑ በምድር ላይ ከሆነው የስጋ ደህንነት የላቀ የነፍስ ደህንነትን የሚመምለከት የእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ እንደነበር ያሳያል፤ መላ የሰው ዘር እስከ ምድር ዳርቻ ተበትኖ ያለ ቢሆንም እግዚአብሄር እርሱ አምላክ ስለሆነ ከእርሱም በቀር ሌላ ስለሌለ ሁሉ ወደ እርሱ ልባቸውን ቢመለሱ በመመለሳቸው እንደሚድኑ አስቀድሞ ተናግሮአል። ነቢያትም አጥብቀው ለህዝቡ የንሰሃ ምክኒያትን ሲናገሩ የነበረው እግዚአብሄር ማዳኑን ሊገልጥ እንዳለው በመንፈስ ስለተረዱ ነበረ። ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳያስ ህዝቡ ከሃጢያትና ከሃጢያተኞች ብዛት ግራ እንደተጋባ፣ ወደ ጽድቅ የሚወስድ ምሪት አጥቶም ያለ ራእይ እየተርመሰመሰ እንደሆነ ተመልክቶ ይናገር ነበር፤ ሃጢያት መፍትሄ አጥቶ ከእግዚአብሄር ጋር ስለለየ ሰላም ጠፍቶአልና የነፍስ ሰላም ከህዝቡ ርቆአል ሲል አመለከተ፤ ሆኖም ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚያወጣ የእግዚአብሄር የማዳን ተስፋ እንዳለ ነብዩ በመንፈስ ስለተመለከተ መልካም ነገርን ተናገረ፦
‘’ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን፤ ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱም የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል። ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና። እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ። ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል።’’ (ኢሳ.59:11-18)
አመጽ ሲበረታ ምን መፍትሄ አለ? ግፍና አመጽ ሲሰፍን ለእግዚአብሄር ህዝብ ትልቅ የጉስቁልና ዘመን ይሆናልና፣ ህዝቡን የሚታደግ አምላክ ግን መድሃኒት ይሆን ዘንድ ተስፋ ሰጠ። እግዚአብሄር ወደ ህዝቡ በተመለከተ ጊዜ ደስተኛ አልሆነም፣ በዘላለም ተስፋ የተጠራ ህዝብ ወደ ንሰሃና ጽድቅ የሚመራው አንድ ሰው እንኳን እንደሌለ ባየ ጊዜ ማዳኑን ያቻኩል ዘንድ ወሰነ፤ እርሱ ህዝቡን በነቢያት መራ፣ በመሳፍንት አዳነ፣ በነገስታት ምድራቸው ላይ ጸንተው እንዲኖሩ ብዙ ጊዜ ታደገ። ነገር ግን በነፍስ የሆነ እረፍት ህዝቡ አልነበረውምና ተቅበዝባዥ ነበረ፤ በአምላኩ ጸንቶ የሚኖርበት ልብ ስላልነበረው በአምላኩ ዘንድ ሞገስ አጣ።
የነፍስን ጥፋት ያስተዋለ አንድም ስላልነበር በፊቱ እንዲቆም የሚፈቅድለት የሰው ልጅ ሊገኝ አልቻለም፤ ስለዚህ እግዚአብሄር የዘላለም አሳቡን ወደ ምድር ሊያወርድ ወሰነ፣ ቃሉን ከራሱ አውጥቶ ስጋ አድርጎ በማዘጋጀት የደህንነትን ስራ በዚያ ስጋ እርሱ ራሱ የሚገባውን በመፈጸም የሰው ልጅን ከሞት ይታደግ ዘንድ ወሰነ። ‘’የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።’’ በማለት እግዚአብሄር ስለተገለጠበት ሰውነት ብስራት ተናገረ፣ በዚያ ሰውነት በኩል ስለተሰጠው የማዳን አሰራርም በምሳሌ አሳየ። ይህ እውነት በርቶላቸው ለተጠባበቁት የማዳኑን ሂደት ጠቁሞአቸዋል፤ ስፍራው ላይ የመድሃኒት ምንጭ በተከፈተ በዚያን እለት ምን ሊባል እንደሚገባ ቀድሞ ሊያስተዋውቅም ሲፈቅድ እንዲህ አለ፦
ኢሳ.25:6-9 ‘’የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።’’
እግዚአብሄር ሰማያዊ ስጋ አዘጋጅቶ እርሱን የሃይሉ መገለጫ ክንዱ እንዲያደርገውና እንዲገለገልበት ከዘላለም የነበረ አሳቡ ነው፤ ይህም የርሱ የደህንነት መንገድ ነው። ከላይ ባለው ቃል ውስጥ የተነገሩ ነገሮች ለሰው ልጅ መዳንና የከፍታ/የመንፈሳዊ ህይወት መኖርያ መሰረቶች ናቸው፤ በነርሱ ውስጥ ያሉ አሰራሮችም የሚሰጡት ታላላቅ ውጤት እንዳለም ከነርሱ ማየት እንችላለን፦
– የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር – የደህንነታችን አድራሻ ወደ አንዱና ብቸኛው አምላክ የሚያመለክት ሲሆን እርሱም የጥንቱ አምላክ፣ ለአብረሃም፣ ለይስሃቅና ለያእቆብ የተገለጠው እርሱ መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ይህ አምላክ በአዲስ ኪዳን መድሃኒት ይሆን ዘንድ አሳቡን የምስራች ማለቱን ያሳያል
– በዚህ ተራራ ላይ – እግዚአብሄር አንድ ትልቅ ስራ የሚከናወንበትን ስፍራ እንደመረጠ ቃሉ ያሳያል፤ ይህ ተራራ በስፍራም በጊዜም የተለየ ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ እግዚአብሄር የደህንነት ስራ ሊፈጸምበት የወሰነው እንደሆነ እናያለን
– ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል – ይህ ቅኔያዊ ንግግር ስጋችን በነዚህ ልዩና የተመረጡ ምግቦች እንደሚረካና እንደሚደሰት ሁሉ በአምላክ ታላቅ ስራ ነፍስ ታላቅ እርካታና ደስታ ከእርሱ ዘንድ እንደምትቀበል የሚያመለክት ነው
– በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለ መጋረጃ – መጋረጃ መለያና መሸፈኛ በመሆኑ ህዝቡ ሊያይ ይገባ የነበረውን ክብር ከማየት የተነፈገበት አንድ አሰራር እንደያዘው እግዚአብሄር ደግሞ ያንን ከአይንና ከልቦናቸው እንደሚጥልልላቸው እነርሱም አየተው እርሱ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር የአባቶቻቸው አምላክ መሆኑን የሚያውቁበት አሰራር መሆኑን የሚያሳይ ነው
– በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋ መሸፈኛ – አህዛብ በሙሉ ከእግዚአብሄር ህዝብ ተለይተው እግዚአብሄርን ከማወቅ ውጪ የሆኑበት አሰራር ነበር፤ በዚህ አሰራር መንፈሳዊ እውቀታቸው ተሸፍኖ ስላለ እግዚአብሄር ማን መሆኑን አላወቁም፣ በፈንታው አምላክ ወዳልሆኑ ፊታቸውን አዞሩ፣ በነዚያ ዘመናት ፍጥረታትንና የእጅ ስራቸውን አምልከዋል፣ አጋንንትን ተከትለዋል፤ እግዚአብሄር ግን ማዳኑን በዚያ ተራራ ላይ በገለጠ ጊዜ ያ ድንዛዜ ከላያቸው እንደሚገፈፍ ከህዝቡም ጋር በአንድነት ወገን እንደሚሆኑ ያመለክታል
– ሞትን ለዘላለም ይውጣል – ይህ የትንቢት ቃል እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ለዘላለም ከሚያስወግደው ፍርድ እንደታደገ፣ በሰው ላይ የታወጀው የፍርድ/ የእርግማን አዋጅ በእርሱ በራሱ እንደሚሻር የሚያመለክት ነው
– ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል – እግዚአብሄር በዚህ ተራራ ላይ በሚገልጠው የማዳን ስራ የሰው ልጅ ያጣውን የመንፈስ ደስታ ይመልሳል፣ በሃጢያት ፍርሃት ከሚያለቅስበት፣ ከሚተክዝበትና መጨረሻውን እየገመተ ከሚኖረው የፍርሃት ህይወት ያወጣዋል፣ በነጻነት እንዲኖር ከሃጢያት ባርነት ያላቅቀዋል፣ የደስታ ዘይትን ይቀባዋል
– የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል – በሃጢያትና በአመጽ ምክኒያት የተተወበትን ዘመን፣ ከእግዚአብሄር ከአምላኩ የተለየበትን ዘመን ይሽራል፣ አዲስ የአባትና የልጅ ግንኙነት ይፈጠራል፣ የንጉስ ክህነት ይሰጠዋል፣ እግዚአብሄርን በክብሩ ፊት ያመልካል፣ ያገለግላል
– በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል ይባላል – የነቢያት ቃል ተፈጽሞ የሚታይበት ዘመን ይመጣል፣ ያኔ ቃሉ መፈጸሙ የሚታወቅበት፣ እግዚአብሄር እንደተናገረው መስራቱ የሚረጋገጥበት፣ በርሱም የደስታ ምስጋና፣ አምልኮና ዜማ የሚወጣበት ጊዜ ይሆናል
– እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል – ጌታን እንደተስፋ ቃሉ ያገኙ አምላክነቱን የሚያውጁበት ያ ዘመን ነው፣ እኛም አምነን ለርሱ የምንገዛበት ጊዜ የመጣልን የቃል ኪዳኑ ፍጻሜ በቀራኒዮ ላይ ስለተከናወነ ነው፤ እግዚአብሄር በስጋ ተገልጦአል፣ ስለዚህ በማዳኑ ደስ ይለናል፣ አማኑእል እግዚአብሄር በሰዎች መሃል ተገኝቶአል፣ ስሙም ኢየሱስ ተብሎአል።
ኢሳ.62:11-12 ‘’እነሆ፥ እግዚአብሔር ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል። ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት። እግዚአብሔር፦ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም። የተፈለገች ያልተተወችም ከተማ ትባያለሽ።’’