ሰላም ለናንተ ይሁን[3ኛ…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ምክረ ሰላም
”እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።”(1ቆሮ.14:33)
ግን አንዳንዴ ሁከት ሲያስጨንቀን፣ ሰላም አጥተን ስንባዝንና እፎይ ያልንበት ጊዜ እስካይታወሰን በፈተና ስንቅበዘበዝ ወደ እኛ ተመልሶ የመምጣቱ ነገር ያጠራጥረናል፤ በእውነተኛ ትርጉሙም ላይ ጥያቄ በማንሳት ሰላምን እንነቅፋለን፤ እርሱ ማን ነው? እስከማለት እንደርሳለን፡፡
በእርግጥስ ሰላም ለእኛ ምንድነው? አንጻራዊውን ሰላም ለማለት አይደለም፤ ልቦናን ተቆጠጥሮ ውስጥን ስለሚያረጋጋው ሰላም ለማለት እንጂ፡፡ ይህ ሰላም መለኮታዊ ነው፤ ስራውና ተጽእኖው በቀጥታ መንፈሳዊው ማንነታችን ላይ የሚያርፍ ስጋዊ ህይወታችን ላይ በመሻገርም የሚገለጥ ነው፡፡
መዝ.55:22 ”ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።”
ሰላም እኮ በውጤት የሚገለጥ ልብንም ህይወትንም የሚገዛ ተጽእኖው ብርቱ የሆነ ነገር ነው፤ ከንግግር ያለፈ ግብረገባዊ ልምምድ በመሆኑም ሰዎች ተጽእኖው አርፎባቸው እስኪለወጡ ድረስ የሚገዛ በተግባር መታየት የሚችልም ሀይል አለው፡፡
ዕብ.12:14 ”ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።”
ሰላም ምኞት አይደለም፣ ልምምድ ነው፡፡ ሰላም በጎ ፈቃድ አይደለም፣ ውስጣዊ የህይወት ይዘት ነው፡፡ አመጸኞች በለስላሳ አንደበት እየሰበኩት በክፋት የሚጠመጥሙት የነገር ክር አይደለም፣ ወይም እያደቡ የሚያወጡት የሽንገላ ቃል አይነት አይደለም፡፡
ያዕ.3:16 ”ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።”
ሰላም ግን የእርካታ መነሻ ነው፤ ሰላም የጽናት መሰረት ነው፤ ሰላም እርቅ ነው፤ ሰላም እረፍት ነው፤ ሰላም እርጋታ ነው፤ ሰላም የልብ ማህተም ነው፤ ሰላም የእግዚአብሄር መለያ ምልክት ነው፤ ሰላም የሰውና የእግዚአብሄር ውል ነው፤ ሰላም በሰዎች መሀል ስምምነትን፣ ጽናትን፣ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ መፈላለግንም ሆነ ጽናትን የሚፈጥር አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡
ሰላም በአለም ባይኖር የሰው ልጅ ይሄኔ ምን ይሆን ነበር? በህዝብ መሀል ይቅርና በቅርብ ሰዎች መሀል ለጥቂት ወቅት እንኩዋን ሰላም ቢጠፋ ብዙ የከበረ ነገር አብሮ ሊጠፋ ይችላል፡፡
ዘፍ.37:3-4 ”እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፤ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት። ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።”
በአለም ላይ በተፈጠረ ጥል የአለም ህዝቦች ጎራ ለይተው ተፋልመዋል፤ እጅግ ብዙ ህዝቦች ህይወታቸውን ገብረውበታል፤ ሰላም ለብዙ ዘመናት ከአለም ርቆ እጅግ የከፉ ሰቆቃዎች በሰው ልጅ ላይ ተከስተዋል፡፡
ስለዚህ ሰላምን ስናስብ ሰዎች በምድር ላይ እየናፈቁ ከሚፈልጉዋቸው ነገሮች መሃል ዋና ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰላም ምድርን ማስዋቢያ ጌጥ ነውና በእርግጥ ልንፈልገው ይገባል፣ በሰዎች ልብ ውስጥ አድሮ የሰዎችን አለም ያስውባልና ለሰው ልጆች ደስታ መሰረት ነው፣ በዚያ ሳቢያ ሁሉም በርሱ ውስጥ አርፎ ለማደር ይመኛል፡፡ የእግዚአብሄርም የሰላም በረከት ከፍ ያለ ነው፡፡
ዘኊ.6:22-27 ”እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው፡- እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።”
የእግዚአብሄር ሰላም እጅግ ተፈላጊ ነው፣ ምክኒያቱም የርሱ ሰላም በጥለኞች መሀል ከሚፈጠር እርቀ-ሰላም ያለፈና ሙሉ ማንነትን የሚወርስ በህይወት ውስጥ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡
¬ሰላም እውነተኛውን አምላክ በመከተል የሚፈጠር ሁኔታ ነው
¬¬¬የሰላምን አስፈላጊነት የቱን ያህል ብንረዳም ሰላምን ራሱን አግኝተን በውስጡ ካልኖርን የህይወት ማስተማመኛ የለንም፡፡ ሰላምን እንወቅ፣ አውቀን እንፈልግ፣ ፈልገን ለራሳችን ገንዘብ እናድርገው፡፡ ይህ አፈላለግ የሚሰምረውም በሰላም ባለቤትና ምንጭ በጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በእያንዳንዱ የሁከት ግዛት ላይ ሀይሉን ገልጦ ተጽእኖውን መስበር የሚችል ጌታ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሲያገኘን ቅድሚያ መንፈሳዊ ግዛታችንን ነጻ ያወጣና ወደ እኛ መጥቶ ሰላም ለናንተ ይሁን ይለናል፡፡ ይህን አዋጅ በህይወታችን ውስጥ የሚልከው ካነጻንና ከተቀበለን በሁዋላ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ወደዚህ ጌታ ሲቀርብና አካሄዱን ከእርሱ ጋር ሲያደርግ የርሱ ሰላም ወደ ህይወቱ መግባት ይጀምራል፡፡ ሰላም የጸና ሂደት እንደመሆኑ እንደ ደከመ መብራት ብልጭ ድርግም የሚል ባህሪይ የለውም፡፡
የሰላም ሰው ለመሆን በእግዚአብሄር መጎብኘት ይገባል፡- እግዚአብሄር በሰው አካሄድ ሲደሰት የልቡን ጨለማ ያስወግድና ነፍሱን በሰላም ይሞላል፡፡ በህይወቱ የጀመረው ሰላም ስር በሰደደ ጊዜ በመላው እርሱነቱ ውስጥ በመሰራጨት አእምሮና ስሜቱን ይገዛል፡፡ የግለሰብ ህይወትን የለወጠ ሰላምም ተዛምቶ ቤተሰብን ሲልም ማህበረሰብን ያዳርሳል፡፡ ይሄ ሁሉ ሂደት በተሳካ ሁኔታ በስፍራው የሚጸናው ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ የሰው ህይወት በእግዚአብሄር ቃልና መንፈስ ሊሰራ ሲፈቅድ ነው፡፡ በርሱ አሰራር ነጻ የወጣ ሰው ሰላም ያለው ይሆናልና፤ በሰልፍ ጊዜም እግዚአብሄር ይሙዋገትና ጠላቱን ምርኮ ያደርግለታልና፡፡
ሰው ግን በብዙ መንፈሳዊ ጠላቶች የተከበበ ፍጥረት ነው፡፡ አምላኩ ባይራራለት ኖሮ ክፉዎቹ ጠላቶች ሰላሙን ነስተው ትርጉም አልባ ህይወት ባኖሩት እንዲያውም ከምድር ገጽ ባጠፉት ነበር፡፡ መልካሙ ነገር ግን የሰውን ልብ በእጁ የያዘው ጌታ የእያንዳንዳችንን መንገድ ስለሚያነብ አመለካከታችንን ወደፈለገው አቅጣጫ ያዘነብለዋል፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ጋር በመታረቅ ከእርሱ ጋር መጉዋዝ ከእርሱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጠላታችንም ጋር (ከተጣላነው ሰውም ጋር) ሰላም ማውረድ እንደሆነ ማወቅ ትልቅ ማስተዋል ነው፡-
ምሳ.16:7 ”የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።”
እንዲሁም ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም መፍጠርና መስማማት በዙርያችን ያሉ የተበለሻሹ ነገሮች ሲኖሩ ወደ ደህና ይዞታቸው እንዲመለሱ ያደርጋል፣ ይህንንም በቃሉ ስለተናገረ እግዚአብሄር ያደርገዋል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም የምንፈጥረው በንሰሃ በመመለስ፣ ራስን በፊቱ በማዋረድና ኃጢአትን ከድንኳን በማራቅ እንደሆነ ቃሉ ግልጽ አድርጎአል፡፡
ኢዮ.22:21-28 ”አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል።
የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ። ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።”
የእያንዳንዱ ሰው ተጠባቂ ነገር ከእግዚአብሄር ጋር የሚፈጥረው ስምምነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማወቅ፣ እርሱን መውደድ፣ በወዳጅነት ከእርሱ ጋር መጣበቅ፣ እርሱ እንደሚፈልገው ከእርሱ ጋር መራመድና መኖር የሰላም መሰረት ነው፡፡ በሀጢያት ምክኒያት ከእኛ የጠፋው እውነተኛ ሰላም ክርስቶስ ኢየሱስን ስናገኝ ወደ እኛ ተመልሶአል፡፡ ሰላምን ከእርሱ ተቀብለን በእኛ እንዲጸና ደግሞ ከእግዚአብሄር አፍ ሕጉን ልንቀበል፣ በልባችንም ቃሉን ልናኖር ይገባል፡፡ በዘሌ.26:3-9 ሲናገር፡-
”በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም።ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ።”
የሰው ልጅ ከእግዚአብሄር ጋር እንደመታረቅ ያለ ከፍ ያለ ጉዳይ ምን አለው? ያን የሚያስተውል ካለስ እስከመቼ ወደ ሁዋላ ይላል? በሰላም ከተደረገ ስምም በሁዋላ የደስታ ከፍታ በሆነው ሁሉን በሚችል አምላክ ደስታ ደስ መሰኘት ይሆናል፣ ፊትንም ወደ እግዚአብሔር ያለሃፍረት ማንሳት ይቻላል። ወደ እርሱም መጸለይ፣ በእርሱ መሰማትና ከእጁ መቀበልን የመሳሰለ ታላላቅ በረከት በሰላም ምክኒያት መቀበል ያስችላል።
ሀዋሪያቶች አስተውለው የመጨረሻ የተባለን የእርቀ-ሰላም ጥሪ ለሰው ልጅ ሲያስተላልፉ እንዲህ ብለዋል፡-
2ቆሮ.5:19-21”እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”
ታረቁ የሚሉን ከሰላም አምላክ ጋር ነው፣ አስተውለናልን? እግዚአብሄር በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አድርጎ ሊታረቀን ከፈቀደ እኛስ አሺ ብለን የማንታረቀው ለምንድነው? ተበዳዩ በደሉን ልርሳና ሰላም በመሃከላችን ላድርግ ብሎ የሰላም በር ሲከፍት በዳይ የሆንን እኛ እርቅን በእንቢተኝነት መግፋታችን ያለማስተዋላችን ውጤት አይደለምን? አግዚአብሄር ይቅር ብሎ ሊቀበለን፣ሊታረቀንና ሰላም ሊሰጠን የወሰነበትን ምክኒያት ሃዋርያት ሳያብራሩት አላለፉም፤ በ2ቆሮ.5:21 ላይ እንዲህ ብለዋል፡- ”እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”
ሰላም መፍጠር – እርስ በርስ፣ በሰላም ቀንበር
ሰላም ለሰው ልጆች እንደቀንበር ነው፡- አንድም እርስ በርስ በህብረት ስለሚያጣምድ፣ አንድም ሰው ስለሌላው ሲል አፈንጋጭ እንዳይሆን ስለሚገድብ፡፡
ስለዚህ በዚህ አለም ከሚኖሩ የከበሩ ሰዎች የሚጠበቅ ማንነት ነው፡- ሰላምተኛነት፡፡ የሰላም ሰዎች በሌሉበት ዘመን የሚሆነውን ሁሉ ግን እኛም እያየን ነው፡፡እግዚአብሄርን ካልፈሩ የሰላም ሰው መሆን በእርግጥ አይቻልም፡፡ሰላም እንዴት ይመጣል?
መልሱ ለጠቢባን እውቀት የሚተው ነው ልንል እንችላለን፡፡ አባባሉ ምክኒያታዊ የሚሆነውም ፍጹም ሰላም ከእግዚአብሄር በመሆኑ፣ እግዚአብሄርም የሚገኘው በመለኮት መገለጥና ጥበብ ምክኒያት በመሆኑ ነው፡-
ምሳ.3:13-17 ”ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ ዕንቍም ትከብራለች፥ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።”
የእግዚአብሄር ጥበብ በማስተዋል የምታከብር በሰላም ጎዳና የምታራምድም ነች፡፡ ጥበቡን የሚገልጥ ጌታ እርሱን በማወቅ የሚገኘውን ትርፍ የምናስተውልበትን እውቀትና ጥበብ እንዲሰጥ ልንለምነው ይገባል፡፡ ሰላምን ለማግኘት አርቆ መመልከት ይጠይቃልና፡፡
መዝ.34:11-16 ”ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።”
ሰላም መቀበል-አምላካዊ ሰላም (ሰላም ለእናንተ ይሁን)
1ጴጥ.10-12 ”ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።”
እግዚአብሄር በቃሉ ላይ ያመጹበትን አጥፍቶ የለም ወይ? ለታመኑት ለተጠጉትና እርሱን ተስፋ ላደረጉት ግን የሚያርፉበትን በረከት እርሱም መለኮታዊ የሆነ ሰላሙን ይሰጣቸዋል፡-
መዝ.29:10-11 ”እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።”
ብዙ የአለም በረከቶች ስጋዊ ኑሮን በማመቻቸት ሊያግዙን ቢችሉም በእግዚአብሄር የሆነ የሰላም በረከት ግን እስከነፍስ በሚደርስ እርካታ ከፍ ያለ እረፍትና ሙላት የሚሰጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄር የጽድቅ ዋጋ በምድር ለቅዱሳኑ ሰላም ማድረግና ዘላለማዊ ሰላምም በዘላለማዊ መንግስቱ ውስጥ መስጠት ነው፡፡
ራእ.1:4-5 ”ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።”