ሰላም ለናንተ ይሁን[2ኛ…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የአለም ህዝቦችና መንግስቶቻቸው ምድርን ለሚንጠው ሁከት ሰላምን በማፈላለግ ብዙውን ዘመናቸውን ፈጅተዋል፡፡ ሰላምን ለማምጣት ብዙ መክረዋል፣ በህብረት ለፍተዋል፣ አጥፊው ላይ ወስነዋል፣ የተጣሉትን ሊያስታርቁ ደክመዋል፤ ነገር ግን እንደልፋታቸው መጠን የተሻለ ነገር በአለም ላይ አልመጣም፡፡ ይህንም ይሁን ያን እርምጃ ይውሰዱ፣ በዚህኛውም ይሁን በዚያኛው ብልሀት ይሂዱ ያልደረሱበት ጥበብ እንዳለ እናያለን፤ የሰላም ጎዳና ወዴት መሆኑን እንዳላስተዋሉትም እንረዳለን፤ የምንጩን ማንነት አልደረሱበትማ፡፡ ተረድተው ቢሆንስ ወደላይ ቀና ሲሉ በታዩ ነበር፤ በአለም ላይ ላለው ሰላም ምንጩ አንዱ እግዚአብሄር መሆኑን ባገናዘቡም ነበር፡-
ኤፌ2:14-17 “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ”
2ቆሮ.13:11 ”በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” ይላልና፡፡
ቃሉ እንደሚያመለክተው የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ሲሆን በሰላም መኖር እንችላለን እንጂ ከርሱ ውጪ ሰላምን የሚፈጥርልን ከየትም አናገኝም፡፡ ዛሬ የሰላም አምላክ ቤታችን ይግባና ሰላም ለእናንተ ይሁን ይበለን! ምድርም ትረፍልን!
ለምድራችን የሰላም አስፈላጊነት ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ እውነት ነው፤ ይህ ውድና አስፈላጊ ሰላም ሁላችንን፣ ዙሪያችንንም ጨምሮ ሊወርስ አስፈላጊ ነው፡፡ እግረ-መንገድ አምላክ ሰላምን ይስጥ ሲባል ለማን ይስጥ የሚለውን ማወቅም ይገባናል፡፡ ሰላም፣ ከእግዚብሄር የሚወጣው እርሱ፡-
ሰላም ለእያንዳንዳችን አስፈላጊ ነው
መዝ.4:6-8 ”በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።”
የአለም ስርአት አስጨንቆ የሚያስጮሀቸው ነፍሳት እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በሚያዩትና በሚሰሙት እየተማረሩ ልባቸው የሚቆስል፣ ቢፈልጉ የማያገኙት የሚመስል መፍትሄ በውስጣቸው እየተመላለሰ የሚኖር መልካም ሰዎች ያልተመለሰ ጥያቄያቸውን ሲጎነጉጉኑ ይኖራሉ፡፡ ለበጎነት መልስ፣ ለሰላም መልሰ፣ ለነፍስ እረፍት መልስ… ለሁሉም መልስ ግን ከእግዚአብሄር ዘንድ አለ፡፡
በጎውን የሚሹት ባለተስፋዎቹ እግዚአብሄር የፊቱን ብርሀን እስኪያበራላቸው ድረስ በትእግስት ጸንተው መጠበቅ ይገባቸዋል፤ ችግሩ ግን እግዚአብሄርን የማያውቁ አመጸኞች የምድርን ፊት መሙላታቸው ነው፡፡ እነርሱ የሰላምን አምላክ አላወቁትም፣ ሰላም ራሱ አያውቃቸውምም፤ እግዚአብሄርን የማያውቁ ሰዎች እርሱ ያየኛል የሚል ህሊና የላቸውም፣ ስለዚህ መንገዱን በድፍረት የተላለፋሉ፣ ሀጢያትም ይሰራሉ፣ እርሱ ደግሞ ዝም ባለማለት ስለክፋታቸው ያስጨንቃቸዋል፣ ሰላምም ይርቃቸዋል፡፡
መዝ.14:2-6 ”የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤ ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም።”
እውነታው በግልጽ እንደሚያሳየው እግዚአብሄርን የማያውቁ ሰዎች እርሱን መፍራት የማይችሉ መሆናቸውን ናቸው። በእርሱ ዘንድ ያለ ብርሀን ስላላበራላቸው መንገዳቸው የጨለማ ነው፡፡ እርሱ አብርቶላቸው በሆነ ኖሮ ግን የሰላምን መንገድ ባወቁ ከእርሱም ጋር በታረቁ ነበር፡፡
የጻድቃን ነፍስ ጩሀት ሰላም ከሌላቸው አስጨናቂዎች ጠብቀኝ የምትል ነች፡፡ ንጉስ ዳዊት እግዚአብሄር እንደልቤ ያለው ሰው ቢሆንም ከሰዎች በኩል እጅግ ፈተና የበዛበት ኮብላይ ሰው ሆኖ ነበር፡፡ ነፍሱ በአስጨናቂዎች ተከብባ ባለበት ወቅት እግዚአብሄርን ከነርሱ አስጥለኝ ትል ነበር፡፡
መዝ.28:2-4 ”ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ። ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ። እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።”
ክፉ አድራጊዎች እግዚአብሄር የሚሰጠውን ሰላም መነገጃ ያደርጉታል እንጂ አይኖሩትም፤ ለሌሎች መጥፊያ ይጠቀሙበታል እንጂ ህብረት ማጠናከርያ መንገድ አያደርጉትም፡፡ ከውስጥ ሳይሆን ምላስ ላይ በተቀመጠ ሰላም እየሸነገሉ የዋሃንን የሚያጠቁ፣ ክፋትን በልባቸው አምቀው የሚያባብሉ እጅግ አደገኛ አካሄድ ስላላቸው ከነርሱ እንዲጠብቀው ንጉስ ዳዊት አምላኩን መለመኑ የጥፋቱን ከፍታ ስለተረዳ ነበር፤ ከነርሱ ጋር አብሮ መኖሩ እንኩዋን ወዮ አሰኝቶት እንደነበረ ከመዝሙሩ እናያለን፡-
መዝ.120:5-7 ”መኖሪያዬ የራቀ እኔ ወዮልኝ፤ በቄዳር ድንኳኖች አደርሁ። ሰላምን ከሚጠሉ ጋር ነፍሴ ብዙ ጊዜ ኖረች። እኔ ሰላማዊ ነኝ፤ በተናገኋቸው ጊዜ ግን በከንቱ ተሰለፉብኝ።”
ከዚህ ባለፈ ግን ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም የሚያስጨምሩትን መንገዶች ንጉስ ሰለሞን እንዲህ ይገልጣቸዋል፡-
”ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና። ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።”(ምሳ.3:1-4)
ሰላም ለህዝቡ ያስፈልጋል
መዝ.29:11”እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።”
እግዚአብሄር በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ሰላም ትኩረት እንደሚሰጥ ሁሉ ማህበረሰብም በአጠቃላይ ሰላም እንዲሆን ይፈልጋል፤ ሰላም እርስ በርስ መሀልም ሊሰፍን እጅግ አስፈላጊ ነውና፡፡
እግዚአብሄር በህዝቡ መሀል ሲነግስ ጸጥታና ሰላም ይነግሳል፡፡ በመገዛት የህዝቡ ሰላም ተባርኮ በየእለቱ ይበዛል፤ እግዚአብሄርን መፍራት ከመታዘዝ ጋር ሲሆን እንዲህ መልካም ነገር ያመጣል፡፡ የጽድቅ ውጤት የሰላም መስፈን በመሆኑ እግዚአብሄርን የሚወዱ ሁሉ ከአምላካቸው ጽድቅና በረከትን ይቀበሉ ዘንድ ከእርሱ ጋር ይጣበቃሉ፡፡ የሰላም በረከትም እግዚአብሄርን በሚፈሩ አካባቢ ዘልቆ የሚዘረጋ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሲጎበኝ በረከቱ ሁሉን ያገኛልና፡፡
መዝ.85:8 ”እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና።”
እግዚአብሄር በግለሰቦች ላይ የሚፈጥረውን ሰላም በህዝቡም ላይ ሊያሳርፍ ሲነሳ ህዝቡ በህብረትና በስምም ሊቀበሉት የተገባ ነው፡፡ አንድነትና ስምምነት በሌለበት ማህበር ውስጥ እግዚአብሄር አይከብርም፣ ሰላሙም አይሰፍንም፡፡ የእግዚአብሄር ሰላም በሰዎች መሃል መቀባበልና መከባበር ያመጣል፡፡
1ቆሮ.1:10-11 ”ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።”
በዚህ የመጽሀፍ ዱስ ክፍል እንደምናየው ሀዋርያውን ያሳሰበው የደቀመዛሙርት ልብ መከፋፈል ነበረ፤ በተከፋፈለ ልብ ውስጥ አንዱ የእግዚአብሄር መንፈስ ሊሰራ እንደማይችል ስለሚያውቅ፣ ክፉ መንፈስም ክፍተቱን ተጠቅሞ የማህበሩን አንድነትና ሰላም ስለሚያደፈርስ ያንን አስቀድሞ ተመልክቶ ስለሰጋ አትለያዩ እያለ በእግዚአብሄር ስም ለምኖአቸዋል፡፡
ሰላም ለአገር
1ዜና.22:9-11”እነሆ፥ የዕረፍት ሰው የሚሆን ልጅ ይወለድልሃል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ።”
እግዚአብሄር ሰላምን ለእስራኤል ይሰጥ ዘንድ ስለፈለገ በምድሪቱ ላይ ለስሙ ቤት ይሰራ ዘንድ አዘዘ፡፡ በንጉሱ ዘመን ሰላምና ጸጥታ እንዲመጣ የሰላም አምላክ በመካከላቸው ሊያድር ያስፈልግ ነበር፡፡ ሰላም ለአገር እንዲሆን ካስፈለገ ጉልበት ሁሉ ለሰላሙ አምላክ ሊንበረከክ፣ እጅም ወደ ሰማዩ አምላክ ሊዘረጋ ይገባል፡፡
ዳን.3:28-30”ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።”
ናቡከደነጾር ለእግዚአብሄር ህግ የተገዛ ንጉስ አልነበረም፡፡ በሀገሩ በነበሩ አይሁዳውያን ምክኒያት ግን እግዚአብሄር ተገልጦለት ነበር፡፡ በአይሁድ ላይ የሚገዛውን አምላክ ካወቀ በሁዋላም ይህ አምላክ በአገሩ ላይ እንዲሰራ ፈልጎ አዋጅ አስነገረ፣ አይሁዶችንም በባቢሎን አውራጃዎች አሰማራቸው፡፡ በዚያ ምድር ግን እግዚአብሄር ሊከብር ስላልቻለ ምድሪቱን አልባረከም፡፡
ሰላም ለምድር
1ዜና.4:40 ”የለመለመችም እጅግም ያማረች መሰምርያ አገኙ፤ ምድሪቱም ሰፊና ጸጥተኛ ሰላም ያላትም ነበረች፤ በቀድሞም ጊዜ በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ከካም ወገን ነበሩ።”
እግዚአብሄር ለህዝቦቹ ምድርን አስቀድሞ ሊያዘጋጅ ስለወሰነ ያችን ምድር በጸጥተኛ ሰላም አጥሮ ጠበቃቸው፤ እነርሱም ወደዚያ በደረሱ ጊዜ በአድናቆት ተሞሉ፡፡
ዳን.4:1-3 ”ከንጉሡ ከናቡከደነፆር በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ ሰላም ይብዛላችሁ። ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ። ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።”
ናቡከደነጾር በእግዚአብሄር ላይ የጸና ልብ ያልነበረው የባቢሎን ንጉስ ቢሆንም እግዚአብሄር ግን ለምድር ሁሉ ሰላም ምክኒያት እንደሆነ ተረድቶ ነበር፡፡ ሰላምና ሰላምተኛነት ግን ከእግዚአብሄር እውቀትና መገዛት በሁዋላ ይሁን፤ ያለበለዚያ ንግግርና ፊደል ብቻ ይሆናል፡፡ ይሄም ዋጋ የሌለው ነውና ይልቅ የተግባር ሰው እንሁን፡፡