ሰላም ለናንተ ይሁን[1ኛ…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የሰላማ አላማ
እግዚአብሄር ወደ እኛ ዘንድ የሚመጣው እረፍትን ሊሰጥ ሲሆን ቀርቦ በምህረት ሲጎበኘንም በሚሰጠን እረፍት በኩል ህይወታችንን ማጽናት እንዲሁም የከበበንን ውስጣዊ ሆነ ውጫዊ ጫናና ሁከት ማራቅና በሰላም ማሳረፍ ነው፡፡ የሰላም መሰረት በሰዎች ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ እንዳለው የሚያውቅ አምላክ ወደ አለምና ወደ ሰው ልጆች ሲመለከት ቅድሚያ ትኩረት የሚያደርገው የጠፋብን ሰላም ላይ ነው፡፡ በዘኊ.6:25-27 ያለው ቃል ሲናገር፡-
”እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።” ይላል፡፡
በቅርበት ሊጎበኝና የሰውን ልጅ ሊያድን ያቀደው አምላክ በአዲስ ኪዳን ሲገለጥ ሰላማችንን ዋነኛ አጀንዳ አድርጎት ነበር፡፡ ሰዎች እርስ በርሳቸው በምድር ላይ እንዲሁም ከእግዚአብሄር ጋር በመላው የሰማይ ፈቃድ ጉዳይ ላይ በመጣላታቸው ምክኒያት በመሀል ጥል ጸንቶ ስለነበረ ይህን ጥል ሽሮ ሰላምን ሊያውጅና እርቅን ሊፈጥር ክርስቶስ ወደ አለም መጥቶአል፡፡ ቃሉ በቆላ.1:19-20 እንደሚያስረዳው፡-
”እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።”
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የፈጠረው ሰላምና እርቅ የተገኘው ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ በስቃዩ፣ በመከራውና በሞቱ ጊዜ ባፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ በርሱ መለኮታዊ ሰላም ውስጥ ያለው እርቅ ደህንነትን፣ ፈውስን ፣ጸጋንና በረከትን ወደ ሰው አምጥቶአል፡፡ የሰው ልጆች እግዚአብሄር ያቀረበልንን ይህን መለኮታዊ ሰላም ካላስተዋልን በጠላት አሰራር ተጋርደን በአለም ላይ በተንሰራፋው ጥል እንደምንጠፋ ግልጽ ነው፡፡
እያንዳንዳችን በተለያየ ምክኒያት ይገባንና ያስፈልገን የነበረውን ስንፈጠርም የተሰጠንን ሰላም ከማንነታችን ውስጥ አውጥተን ጥለናል፡፡ የዚህ ችግር መነሻዎች የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሄዋን ናቸው፡፡ እነርሱ ከፍጥረታቸው የተቀበሉትን ሰላም ስለሀጢያት አሳልፈው በመስጠት ፈሪ፣ ድንጉጥና ተርበትባች ሊሆኑ በቅተዋል፡፡ ልጃቸው ቃየንም ከፍ ወዳለ ሁከት በመግባት ይበልጥ ሰላሙን ወዳስጣለው ነፍሰ-ገዳይነት ተሻግሮአል፤ ከሰላሙ አምላክ አብልጦ ሊርቅና ተቅበዝባዥ ሊሆንም በቅቶአል፡፡
ኢዮብ በመጽሀፉ በምእራፍ 5:17-27 ሲናገር፡-
”እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ። በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም። በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ። በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።” ይላል፡፡
ድንኩዋናችን በሰላም እንዴት ይሁን? የእግዚአብሄር ምህረትስ በእኛ ላይ እንዴት ትጽና? ለዚህ መልስ የሚሆነው የራስህ ስራ ስለሆነ መርምረውና አንተው እወቀው አለ፡፡
በእርግጥ ሰላማችንን ካጠፋው የእኛው ክፋት ይልቅ ሰላማችንን የሚፈጥረው የእግዚአብሄር ምህረት እጅግ ታላቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ተስፋው እግዚአብሄር ካለሆነ ድንኩዋኑ የሰላም፣ ኑሮውስ የእረፍት ሊሆን እንዴት ይችላል? ስለዚህ በከንቱ ከምትጠፋ ስራህን አስተውልና ዳን፡- ወደ አምላክህ በንሰሃ ቅረብ፣ ዝም ከሚልህ እግዚአብሔር ሲገስጽህ ተግሳጹን ተቀበል፡፡ በእርግጥ እርሱ ይሰብራል፥ ግን መልሶ ይጠግናል፤ ደግሞ ያቈስላል፥ሆኖም እጆቹ ይፈውሳሉ።
የሰላም ምንጭ?
ጌታ ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ ገዢ የሰላምም አለቃ ነው፡፡ ለሁሉም የተረጋጋና የተጠበቀ ኑሮና ህይወት አስገኚና ምንጩ አንድ ጌታ ብቻ ነው፡፡ ሁከት ግን ከክፉዎች ይመነጫል፣ ይሰራጫልም፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥል ሰውን ከእርቅ አርቆ፣ ሁከትም እንዲሁ ከሰላም አለያይቶ የሰውን ልጅ በውዥንብር ውስጥ እያመላለሰ ሳለ ጌታ በወሰነው ሰአት ሁሉን ሊያስተካክል ተገለጠ፡፡
የኤፌ2:14-17 ቃል እንደሚያውጀው፡-
”እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ”
የሰውን ልጅ መከራ፣ ሁከት፣ ስቃይና የዘላለም ሞት የሻረው ጌታ ኢየሱስ ሰላማችን ነው፡፡ የማያባራው የጠላት ጥቃት ሰውን እያስጨነቀ ባለበት አለም ውስጥ ጌታ ይገለጥ እንጂ በሰው ህይወት የሚያፈሰው ፍጻሜ የሌለው ሰላሙን ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ እኛ ሲመጣ ያለ ቅድመ-ሁኔታ የልብ ሰላም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁሌ በደጃችን በቆመ ጊዜ ጠርቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ይላል፡፡ ከርሱ መምጣት በፊት የምናገኘው ህይወታችን ፍጹም ባዶ ነበር፤ ቃሉ ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ ማለቱም ከመንፈሳዊ በረከት ባዶ ነበራችሁ ማለቱ ነው፤ ያለክርስቶስ ስለነበርን ያለብርሃን፣ ያለሰላም፣ ያለእረፍት፣ ያለደህንነት፣ ያለጸጋና ያለተስፋ እንደነበርን ሲያስረዳን ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በተገለጠልን ጊዜ ግን አነኚህ ጉድለቶቻችን ሊሞሉልን ችለዋል፡፡
እግዚአብሄር ሰላማችንን ሲመልስ ልጁን በመስቀል ላይ እንዲሰዋ አድርጎ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ሰላም ታላቅ ዋጋ ተከፍሎበታል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሰላም እንዲህ ውድና ጥልቅ ሲሆን አለም የምትሰጠው ሰላም ግን ጊዜያዊና ርካሽ ነው፡፡ የአለም ሰላም ሸቀጥ ነው፣ በልዋጭ የምናገኘው ነው፣ በመስዋእትና በክፍያ የሆነ ነገር (ከፍለን የምንቀበለው) በመሆኑ ንጹህ የሆነ አይደለም፡፡ የአለም ሰላም አፍታዊ በመሆኑ አያስተማምንም (ነፍሰ-ገዳይ የጠላውን አጥፍቶ አረፍኩ ሊል ይችላል) ፡፡ የአለም ሰላም በሌሎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ስለሆነም የሌሎች እንቅስቃሴ ሊያውከው ይችላል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ግን ታላቅና ከፍ ያለ ጌታ በመሆኑ በሰላም ላይ የሚነሱትን ሁሉ ጸጥ በማድረግ ፍጹም ሰላም ያሰፍናል፡-
ኢዮ.25:2 ”ገዢነትና መፈራት በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ በከፍታውም ሰላም አድራጊ ነው። በውኑ ለሠራዊቶቹ ቍጥር አላቸውን? ብርሃኑስ የማይወጣው በማን ላይ ነው?” ሲል በአድናቆት ይጠይቃል፡፡
የእግዚአብሄር ከፍታ የሌሎችን ዝቅታ ሲያመላክት የሀይሉ ብርታትም የጠላቶችን ተቃውሞ ጸጥ ማድረግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ መረዳት ፊታቸውን ወደ ፍለጋው ያዞሩም ፍጹም የሆነውን ጌታ በእምነት ሊቀበሉ የተገባ ነው፡፡
ጌታ ፍጹም፣ ሰላሙም ፍጹም ነው፡፡ ከጌታ በምንቀበለው በዚህ ፍጹም ሰላም ተተክለን ስንኖር በሰላሙ ስር ሰድደንና ተመስርተን ባለመናወጥ እንኖራለን፤ ሆኖም እንዲህ ስንል ጌታ ኢየሱስ በአለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ… ያለውን ባለመርሳት መሆን አለበት፡፡
በጠላት አሰራር የምትታወከውን አለም ያሸነፈ ጌታ በውስጥ ሰውነታችን ስለሚያበረታን ለአለም መከራ እጅ አንሰጥም፡፡ ኢየሱስ በውስጣችን ከሌለ ግን አሸናፊው ሰላም በውስጣችን አይደላደልም፡፡
ዮሐ.14:27 “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” አለ እርሱ፡፡
አለም ሰላሜ ስትል የምትጠራው ሰላም እግዚአብሄር ከሚሰጠው ፍጹም ይለያል፡፡ የእግዚአብሄር ማንነት ልዩ ስለሆነ ከእርሱ የሚፈልቀው የሰላም ስጦታ ከአለም ጋር አይተካከልም፡፡
ጌታ ኢየሱስ የውጪውን አለም ሰላም ሊያደላድል የመጣ ሳይሆን የውስጣችንን አለም ሰላም ሊሞላ ነው ቃል የገባው፡፡ የአለምን መከራ አሸንፌአለሁ ስላለ የምንኖረው በተሸነፈው የአለም መከራ መካከል ነውና በአሸናፊው ጌታ ተመክተን አለምን እኛም እናሸንፍ፡፡
ሰላም ለናንተ ይሁን
የእግዚአብሄር ልጆች በየትም ስፍራ ይሁን ወቅት እንደፈቃዱ ሆነን ስንገኝ ጌታ በሰላሙ ይቀበለናል፡-
ሉቃ24:33-36 ”በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም። ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው። ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።”
ሰላም የሆነ ጌታ እነሆ በመሃላቸው፣ ማመንታታቸውን አልፎ፣ ጥርጥርና ሙግታቸውንም ገፍፎ በነርሱ ዘንድ ተገኘና በሰላሙ አሳረፋቸው፡፡ ሁላችን ብንሆንስ የጌታ ሰላም ባይበዛልን ኖሮ አለም ላይ ያለው ሁከት ምን አይነት ሰላም ያስተርፍልን ነበር? አለም ግን ሰላም የተባለ ሰላም ካላት ሰላሙዋ ብቁ የሚሆነው ለአለማውያን ብቻ እንጂ ለእግዚአብሄር ልጆች አይደለም፡፡
”በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ.16፡33)፡፡
የሰላም ሰው
ሐዋ.10:36-39 ”የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ።እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።”
የሰላም አለቃ ክርስቶስ ኢየሱስ የእኛን መከራ አስወግዶ ሰላምን ያሰፍን ዘንድ ቅድሚያ ችግርንና ጉስቁልናችንን ተቀብሎአል፡፡ እስከመስቀል ሞት በሚደርስ ሰቆቃና መከራ ውስጥ ያለፈው ሀጢያተኛ ስለነበረ ሳይሆን ስለሀጠያተኛ ሊቆም ስለወሰነ ነበረ፡፡ ሀጢያተኞች ግን በዮሐ.19:1-3 ላይ ሲቀልዱና ሲያንጉዋጥጡት ይታያል ፡-
”በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ እየቀረቡም፡- የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር”
ጌታም ከትንሳኤው በሁዋላ ሲገለጥ እርሱን ተስፋ ባደረጉ ላይ የሰላሙን ጅረት በመንፈስና በነፍሳቸው ውስጥ አፈሰሰው፡፡ ደቀመዛሙርትም የሰላም ትርጉምና በሰላም በኩል የሚታወጀው የምስራች እስኪበራላቸው ድረስ ደጋግሞ ጎብኝቶአቸዋል፡-
ዮሐ.20:19-21 ”ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።ኢየሱስም ዳግመኛ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው።”
ዮሐ.20:26 ”ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።”
የእግዚአብሄር የሰላም ስጦታ ውስጣዊ የሆነ የመንፈስ መረጋጋትና ጸጥታ የሚፈጥር ሲሆን፤ በውስጣችን የሚመላለስ የአሳብ፣ የስሜትም ሆነ የፍላጎት ግፊት ተጽእኖ የማይበግረው ጽናት ነው፡፡ ከውጪ ያሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ቢያቻኩሉም በውስጥ ረጋ ማለት፣ በውስጥ ስክን ማለት፣ ከውጪ ጩሀቶች ቢኖሩም ከውስጥ ጭጭ የሚያሰኝ ሀይል የሚሞላም ነው፡፡ሰላም በልብ እምነትን ሞልቶ መደላደል የሚፈጥር ነው፤ ሸክም ቢኖርም ያለመስጋት፣ በላይ በላይ ፈተና ቢደራረብም የእግዚአብሄር እጅን ሰክኖ መጠበቅ ነው፡፡ ሰላም እንደሚያዩት ሆኖ ግብታዊ ያለመሆን ነው፤ እንደሚሰሙት ያለመንቀሳቀስ ነው፡፡ በመንፈስ መረጋጋት፣ እግዚአብሄር ይችላል ብሎ ባሉበት ስፍራ መደላደል ነው፡፡
በእንዲህ ያለ መለኮታዊ ሰላም የተሞሉት ሃዋርያት የሰላምን ወንጌል ተሸክመው እስከ አለም ዳርቻ ሄደዋል፡፡ ወደ ጌታ ዘወር ያሉ አማኞችም ቢሆኑ የሰላም ሰዎችና የወንጌል አርበኞች ሆነዋል፡፡ ስለዚህ፡-
”በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።”(ሐዋ.9:31)
ሰላም ለእግዚአብሄር ስራና ለእግዚአብሄር ልጆች መሰረት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በሀዋርያትም ዘንድ ይህ ትልቅ ስፍራ ስለነበረው ደቀመዛሙርትን በዚያ በረከት ሁሌ ባርከዋል፡-
ሮሜ.1:7 ”በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።”
ሮሜ.2:10-11 ”ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።”
ሮሜ.15:13-14 ”የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።እኔም ራሴ ደግሞ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትገሠጹ እንዲቻላችሁ ስለ እናንተ ተረድቼአለሁ።”
1ቆሮ.1:2-3 ”በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።”
አእምሮን የሚልፍ ሰላም ባለቤት የሆነ ጌታ ለአእምሮአችን፣ ለነፍሳችንና ለመንፈሳችን የሆነ ሰላሙን ያብዛልን፣አሜን፡፡