የመጨረሻው ዘመን ስልጣኔ ፣ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ፣ ማህበራዊ ህይወት ወዘተ ከፍታ ላይ ሆኖ የሚታይበት ዘመን ነው፡፡ሰው ተራርቆ መኖር ያበቃበት፣አንዱ ጉዋዳ የሆነው ጊዜ ሳይፈጅ ሌላው ጆሮ ድረስ ፈጥኖ ተጉዞ የሚሰማበትና ድርጊቱ በማስረጃ የሚተላለፍበት፣ የኑሮ ውጣውረዶች እጅግ ተቃልለው በብዙ መልኩ ትውልዱ የተመቻቸ ኑሮ የቀረበለት ዘመን ነው፡፡ገንዘብ አይጠር እንጂ ቴክኖሎጂ በእጅ ነው፡፡የስልጣኔስ ነገር?
ስልጣኔ እንደ ቴክኖሎጂ ውጤት ከፋብሪካ ተመርቶ አይወጣም፡፡ስልጣኔ የአእምሮና የስነልቦና ልእልና ፍሬ ስለሆነ በማህረሰብ ላይ የሚሰራው ስራ ተተክሎና አድጎ ፍሬው እስከሚታይ ረጅም ሂደት የሚያልፍ ነው፡፡ ስለ ስልጣኔ ሲነሳ ስልጣኔ በብዙ አቅጣጫ ሊታይ እንደሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ የተወሰነውን ለማየት ይሞከራል፡፡በዚህም አንዳንዶችን ለማየት ያህል፡-
ስልጣኔ ከእውቀት ጋር ተያይዞ የሚታይ የሰው ልጆች በእውቀት የመላቅ ውጤት እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡በዚህ አንጻር ብዙ ሀገሮች ቴክኖሎጂን ከሀገራቸው ህዝብ ጋር ለማስተዋወቅ የሚችሉበት የኢኮኖሚ ጉልበት ቢኖራቸውም ከስልጣኔ አንጻር ብዙ ሲቀራቸው እናያለን፡፡ለምሳሌ አረብ ሀገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ ግን ታናሽ ስልጣኔ ያላቸው ሀገሮች ናቸው፡፡አውሮፓውያን የአረቦችን ያህል ኢኮኖሚ ባይኖራቸው እንኩዋን ቴክኖሎጂውና ስልጣኔው በብዙዎቹ ዘንድ በአብሮነት አለ፡፡ስልጣኔ በአውሮፓና በአሜሪካ ከፍ ብሎ የሚታየው በአእምሮ እውቀት ልቆ በመታየት ብቻ አይደለም፡፡ከህይወታቸው ጋር በመዋሃድና ስለሰው ያላቸው አመለካከት ከፍ ማለትም ጭምር ነው፡፡ቴክኖጂ ያፈራውን ሸመታ አፍሪካውያንም አይተናነሱም ፣ስልጣኔው አስቸጋሪ ሆነ እንጂ፡፡
እውቀት ከመማር ጋር ቢያያዝም በመኖር ካልተተረጎመ ስልጣኔ አይሆንም፡፡ጥቂት የማይባሉ አፍሪካውያንና አረቦች እስከ ፕሮፌሰር የደረሰ የትምህርት ሊቃውንት ቢኖራቸውም በአመለካከት ደረጃ ከፍ ማለት ሳይችሉ ቀርተው ሁዋላቀር አመለካከት ያንጸባረቃሉ፡፡
ስልጣኔ በጎ ስብእናን ከመጎናጸፍ ጋርም ይሄዳል፡፡ስልጡን ሰው ለሰው ልጆች ያለው አመለካከት ከፍ ያለ ነው፡፡እከሌን ከእከሌ በዚህና በዚያ መስፈርት የሚለያይ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ ክብር የሚሰጥ ነው፡፡እኔ ያለኝ ስጋ እሱም አለው፣እኔም ያለኝ ደም እርሱ ውስጥ አለ፣የሱም አእምሮ እንደኔ ያስባል፣እኔ እንደምፈልገው እርሱም ይፈልጋል ወዘተ አይነት የስብእና ልእልናን ያራምዳል-ስልጡን ሰው፡፡
ስልጡን ሰው ለሌላው የሚጨነቅም ነው፡፡በአድሎ ለወገኔ ብቻ እያለ አያዳላም፡፡”ያም ይሄም የኔ ነው፣ወገኔ ነው” ይላል፡፡ስልጣኔ የውስጥ እምቅ ችሎታ ምልክት ስለሆነ በሰው ልጆች መሀል ጎልቶ የሚያሳይ በጎ ባህሪን ይፈጥራል፡፡የሰለጠነ ሰው ”ምን ሆንክ ምን ላደርግልህ እችላለሁ፣ የምረዳህ ነገር ካለ?”ይላል ሰውን በቅን ልብ ለመረዳት፡፡
በሌላ በኩል የሰለጠነ ሰው ነገሮችን ባላንስ አድርጎ (ማመዛዘን ባለው አመለካከት) የማየት ብቃት አለው፡፡ከሰለጠነው አለም የሆኑ ብዙ ሰዎች አፍሪካውያንን የሚረዱት ብዙም ስለተረፋቸው ላይሆን ይችላል፡፡የኛን ነገር በተለያየ ሚዲያ በመመልከት እንዲህ የሆኑት ያ ስለሌለ ነውስላጠራቸው ነው ብለው ነገሮችን በበጎ ጎኑ ብቻ ተመልክተው የእርዳታ እጃቸውን ይዘረጋሉ፡፡እኛ ግን እንኩዋን ልንደጋገፍ ቀርቶ በገዛ ምድራችን ላይ እርስ በርስ እንጣላለን፣እንጠላላለን፡፡
ያለመሰልጠናችን ለብዙ በሽታዎች፣መከራዎችና ሞቶች አጋልጠውናል፡፡ከእኛ በእውቀት ከፍ ያሉ ናቸው የምንላቸው ምሁራኖች አፍሪካውያንን ከችግራችን የሚያወጡን ሆነው አላገኘናቸውም፡፡ውስጣችን ባለመዋሃድ የሚንከባለለው እውቀት ፊደል ብቻ እንጂ የለውጥ ሀይል አልሆነንም ማለት ነው፡፡
ስልጣኔ መብትና ግዴታን ከመረዳትም ጋር ይሄዳል፡፡ያልሰለጠንን ህዝቦች ሁልጊዜ መብታችን ላይ ነው ትኩረታችን፡፡3 ኪሎሜትር ድረስ ሊሰማ የሚችል ስፒከር በሰፈር ውስጥ የምንከፍተው ”ሙዚቃ መስማት መብቴ ነው ማን ምን አገባው” ብለን ነው፡፡ያላስተዋልነው ነገር ስፒከሩ ነው የእኛ እንጂ በጩሀቱ የተጎዳው ጆሮ የኛ ያለመሆኑን ነው፡፡ስለዚህ ምንድር ነበር የኛ ግዴታ? ስፒከሩን ከፍተን ለመስማት ስንሞክር ያን ጥያቄ በበቂ ሁኔታና ግዴታን መሰረት ባደረገ መንፈስ የምንመልሰው ጉዳይ መሆን ነበረበት፣ሰልጥነን ቢሆን ኖሮ፡፡
በሌላ በኩል ስልጣኔ በማህበረሰብ ውስጥ ስር ሰድዶ እንደሆነ የመከባበር ባህልን በሰፊው እናያለን ፡፡ያለመሰልጠን ወደ እንስሳዊ ባህሪ እንድናዘነብል ያደርጋል፡፡ጉዳዩ ውስጣዊ (ስነልቦናዊ) ህመም ነው፡፡አንዳንዴ ትህትናችን እንኩዋን ሰውን ያሳዝናል- በአጉል እውቀት የቀረበ በመሆኑ(ይሄ አንዱ ራስን የመጣል ስልጣኔ እንደሆነ ልብ እንበል)፡፡
የስልጣኔ ማማ የሚያሳየን አንድ ሌላ ዋና ነገር አለ-ዘመንን ማስተዋል መቻል፡፡ያን ብቃት የተጎናጸፈ ሰው በዘመኑ ላይ ያለውን ተጽእኖ መቁዋቁዋም ይችላል፡፡በዚህ ዘመን እየሆነ ያለው ነገር ምንን ያመለክታል?በቀድሞ ዘመንስ የነበረው ምንን አመጣ? የዛሬውስ ለነገ ምንን ያቀብላል?ትውልዱስ ይህንን አውቆ ምን ያድርግ? ይህ አባባል በጣም ብዙ ነገር ያጠቃልላል፡፡የስልጣኔ ማማ ላይ የወጡት አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ከራሳቸው ሀገር አልፈው የሌላውን አለም ብሩህ ተስፋ የተላበሱ ትውልዶች ለተለየ ተልእኮ ሲያዘጋጁዋቸው ይታያሉ፡፡አስተዋዮችን በተለየ አመለካከት ማየት ፣ በችሎታቸው በኩል በመቆም ማገዝ፣ የወደፊቶቹን ባለራእዮች በዝንባሌያቸው መቅረጽ የተካኑበት ችሎታቸው ነው፡-ምክኒያት ስልጣኔያቸው ስለሚያዛቸው፡፡ የእኛን ሀገር እንመልከት እስቲ?- ስንት ጥበብ የተሞሉ ለግላጋ ልጆች ባክነው ቀሩ? ስንቱ አዋቂዎችስ በየዳርቻው ተገፍተው ቀሩ? መቼም የሚያውቅ ያስተውለዋል፡፡
ራስን የመጣል ስልጣኔ?
ራስን መጣል ከስልጣኔ ጋር ይዋሃዳል? በግድ ተይዞ ይዋሃዳል በአፍሪካ ምድር! ግን ሰው ራሱን ለምን ይጥላል?ራስን መጣልስ ምንድነው?ለምን ይጥላልን እናቆይና ራስን መጣል ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
ራስን መጣል ራስን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጋር የተቃረነ አመለካከት ነው፡፡ራስን መጣል በጎ ነገር የሌለውና መልካም ስብእናን የሚጥል አመል ነው፡፡ራሱን የሚጥል ሰው ባለማወቅ ጠንቅ ይመታል፡፡እንዲህ አይነት ሰው ያላወቀ ነገር ግን ያወቀ የሚመስለው ሰው ነው፣አደጋው ደግሞ እዚህ ጋ ነው፡፡እንዲህ የሚያስብ ሰው በራሱ ላይ ትልቅ ችግር ፈጥራል፡፡ምክኒያቱም በመጀመሪያ ራሱን ባስቀመጠበት ስፍራ ስለማያገኘው ይቸገራል(የሚያስበውና የሚሰራው ለየቅል ሆኖ)፣በሁለተኛ ደረጃ ማህበረሰቡ እኔ ማለት እንዲህ ነኝ እያለ ከሚሰብከው ቃሉ ውጪ በገሀድ ሌላ ቦታ ስለሚያገኘው በርሱ ላይ የተለየ አመለካከት ይይዝበታል፡፡በዚህ ምክኒያት ይህ ሰው አንገቱን እንዲደፋ ይገደዳል (ቢሆንም እርሱ ግን ላለመሸነፍ ተቃራኒ መንገድ ይመርጣል)፡፡
ራሱን የሚጥል ሰው በሱስ ይጠቃል፡፡ አንድ ሰው ራሱን በራሱ አእምሮ ቁጥጥር ስር ሲያውል ብቻ ነው ያሰበውን ያለመቸገር ሊያከናውን የሚችለው፡፡አእምሮውና ስሜቱ በሱስ የተገዛ ሰው ሲሆን ግን ለሱስ ፈቃድ የተሰጠ ይሆናል፡፡ስለዚህ ሱሱ ውጣ ባለው መንገድ ይወጣል፣ግባ ባለው መንገድ ይገባል፡፡ሱሱን ለማሙዋላት መዋሸት ካለበት ይዋሻል፣መስረቅ ካለበት ይሰርቃል፣መግደል ካለበት ይገድላል (ከፍተኛ የአደንዛዥ እጽ ከዚህም በላይ ያዝዘዋል)፡፡ይህ ሰው ከሱሱ ውጪ አይናፋርና ቁጡብ ሊሆን ይችላል፡፡በሱስ ሲወጋ ግን አይን ያወጣል፣ይበጠብጣል፡፡ሱሱን እስካላረካ ድረስ መስከን አይችልም፡፡
ራስን መጣል የመሸነፍ ምልክትም ነው፡፡ሰው ተስፋ በመቁረጥ ሲሸነፍ ራሱን ይጥላል፡፡ያ ሰው አልሆን ሲለው ወይም ፈጽሞ አይሳካም ብሎ ሲወስን ተስፋ መቁረጥ ላይ ይወድቃል፡፡ተስፋ የቆረጠ ሰው ራሱን ማክበር ያዳግተዋል፡፡ይሉኝታ ከውስጡ ይጠፋና ብዙ ነገሮችንማደፍረስ ይጀምራል፡፡
በሌላ በኩል ሰው በሰው አሳብ ሲሸነፍ ራሱን ይጥላል፡-ሰዎች በተለያየ መንገድ የሰውን ህሊና የሚጎዳ ስራ ይሰራሉ፡፡በተለይ ለክፉ አሳባቸው መጠቀሚያ የሚያደርጉዋቸውን ሰዎች በስተመጨረሻ ተስፋ ቢስ እንዲሆኑ በማድረግ የእብደትና ራስን የመጣል ህይወት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጉዋቸዋል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያወዳድራሉ፡፡እነርሱ ራሳቸውና የራሳቸው መሆናቸውን ይዘነጉና ጎረቤቶቻቸውን ለመምሰል ይደክማሉ፡፡ባልተሳካላቸው ጊዜ መሰላቸትና ህይወትን መጥላት ውስጥ ይገባሉ፡፡ያም ራሳቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ሊያደርግ ይችላል፡፡…..