ራስን የመጣል ስልጣኔ[2/2]

የመጨረሻ ዘመን

ራስን መጣል ከስልጣኔ ጋር?
ራስን መጣል ከስልጣኔ ጋር በአፍሪካ ምድር መዋሃድ ይችላሉ ሲባል እዚህ አህጉር ላይ የስልጣኔ ትርጉዋሜና የራስ አተያይ (ለራስ የሚሰጥ ግምት) በተሳሳተ መንገድ ተጣምረው ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ የገዛ ራስን በተሳሳተ መንገድ ማየት ባልሰለጠነ ስልጣኔ ላይ ተጨምሮ ይበልጥ ነገሮችን እንዳወሳሰበ ለማሳየትም ነው፡፡ራስን መጣል ሳያንስ የተሳሳተ ስልጣኔ ሲታከልበት በጣም ይጎዳል፡፡
ለምን ”ሰለጠንን” ብለን እንደሰለጠነ ሰው ልንሆን አልቻልንም? ያልቻልንበት ዋና ምክኒያትማ ያለመሰልጠናችን በእርግጠኝነት ስብእናችንን ስላነቀው ነው፡፡ ያ ሳይበቃም በዚያ ስለተጎዳን የሃሳብ ልእልናን ስለምንፈራ ነው፡፡ እንዲያውም ከስልጣኔያችን አንዳንድ ነባር ባህላችን የሚሻለው ስልጣኔን ባልተገባ መንገድ ስለተረጎምነው ነው፡፡ የሰለጠንኩ ስሜት ሲመጣብን ከትህትና ይልቅ ወደ ትእቢትና ኩራት እናዘነብላለን፡፡ እንኩዋን ሰልጥነን የሰለጠነ ሀገር ከርመን ስንመጣ ምድራችንንና ህዝባችንን አሳንሰን ኢምንት እናደርጋለን – ስልጣኔን ከስሩ ሳይሆን ከአናቱ ስለገባንበት፡፡ የተዛባ ስልጣኔ ሊያሰክነን ስለማይችል ጉሽ ጠጅ ሆኖ አዙሪት ውስጥ ይከተናል፡፡ ብዙዎቻችን ስልጣኔና ቴክኖሎጂ አንድ ሆነውብን የምናመዝነው በብራችን ቴክኖሎጂን ማፈስና ስልጣኔን መቀባባት ላይ ነው፡፡ በብዙ መልኩ ሰለጠንን ብለን የምንጉዋዝበት መንገድ እጅግ ስግብግብነትን ካማከለ ነገር ጋር ስለሚገናኝ ያሸማቅቃል፡፡ ያን ስልጣኔ ብለን ይዘን ራስን ከመጣል ጋር ስናዋህደው ምን ሊመጣ እንደሚችል እስቲ እንገምት?
በአፍሪካ ውስጥ ሰለጠኑ ወይም ስልጣኔ እየመጣላቸው ነው የሚባሉ ሀገሮችን ብናይ ከማድነቅ ይልቅ እንገረምባቸዋለን (ደቡብ አፍሪካን፣ናይጄርያንና ግብጽን ማየት ይቻላል-እኛም ጭምር) ፡፡ ሀገሮቹ በሙሉ በሚባል ደረጃ የዜጎች ክብር የሌላቸውና በምእራባውያን ክፉ አመል የተለከፉ እንጂ የራሴ የሚሉትን በጎ ነገር የማያዳብሩ ናቸው፡፡ አፍሪካዊ ከሌላ አፍሪካዊ ጋር (ከሀገሩ ልጅም ጭምር) በአብሮነት ሊኖር አይወድም፡፡ከአህጉሪቱ ውጪ ቢሆን ግን ይቀበለዋል፡፡ ለምን? ባይሰለጥንም የሰለጠኑ ህዝቦች መሀል ስላለ የነርሱ በጎ ተጽእኖ እንደዚያ ያድገዋል፡፡
እንደው ለመሆኑ ሰዎች ሰለጠንን ካሉ በግብር ግን የሰውን ልጅ ክብር የሚያዋርድ ተግባር ከፈጸሙ የስልጣኔ ትርጉም ለነርሱ የቱ ጋ ነው? አፍሪካውያን በትክክለኛው የስልጣኔ መስመር እንዳንገባ የሚያስቸግን አንድ የተጣባን ሁዋላ ቀር አመል ያለ አይመስላችሁም?
እኛ ግን አላፈርንም፣ እንዲህ ሆነን እያለ ራሳችንን የሚያስጥል ስራ በላዩ እንደርታለን፡፡ ያ ደግሞ እጅግ የሚያሸማቅቅ የኑሮ ትእይንት ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ አንድ ራሱን በራሱ ያሰለጠነ ስልጡን መሳይ በነገሮች ሁሉ የሰውን መብት እየጨፈለቀ የኔ ያለውን ግን በተለያዩ የማወናበጃ መንገዶች እያስጠበቀ ይሄዳል፡፡ ያ በእርሱ አእምሮ ከፍ ያለና የላቀ ድርጊት ቢመስለውም እርሱ ግን በውርደት ውስጥ መኖሩን ያሳያል፡፡ ከዚህ በማስከተል ራስን የመጣል ስልጣኔ የሚያስከትለውን ችግር ደግሞ እንይ፡-
1.ራስን የመጣል ስልጣኔ ትክክለኛ ሥልጣኔን በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማል
ይህ ሰው የስልጣኔን ትርጉም በተዛባ መንገድ ነው ያየው ማለት ነው፡፡ ስልጣኔ ማስተዋል ያለበትና እርጋታ የገዛው ሲሆን ለሰው መሆንንና የሰውን መብት ማክበርም የሚጨምር ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በዚህ ትርጉም መዛባት ምክኒያት ተቃራኒውን መንገድ ይከተላል ማለት ነው ያ ሰው፡፡
2.ራስን የመጣል ስልጣኔ ራስን ያለማክበር ነገር ይታይበታል
አንድ ሰው ስልጣኔ ሲያንሰው ራሱን ይጥላል፡- በሱስ በመገዛት፣ ከማህበረሰቡ ያፈነገጠ ህይወት በመኖር፣ ትርጉም የለሽ ስራ በመስራት በመሳሰለው ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ሲለብስ ምን እንደለበሰና ለምን እንደለበሰ አያስተውልም፡፡ አንዳንዶች ፋሽን ትርኢት ላይ ተለብሶ ያዩትን በየቀኑ ያደርጉታል፣ የጸጉር ፍሸናውንና አቆራረጡንም እንደዚያው፡፡ የኛ ነገር ሆኖ እንጂ በትርኢቱ ስፍራ የነበረ ማንም ሰው ያንን ዘይቤ በህይወቱ ውስጥ አስገብቶ እለታዊ መገለጫው አያደርገውም- ትርኢቱ ላይ ይታይ የነበረውን ሁሉ ለምን አላማ እንደቀረበ ያውቃልና፡፡
3.ራስን የመጣል ስልጣኔ የተሳከረ አመለካከት አለው
ሰውን ማክበር መዋረድ ሊመስለው ይችላል፡፡ የስልጣኔ ማማ የሚለው ዝቅታና የተዋረደ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ዝግታና ዝምታ ስልጡን አመለካከቶች ከሆኑ ለርሱ ረብሻና ሁከት መሰልጠን ይመስሉታል፡- ሰክሮ ማወክ ሊሆንም ይችላል፣ እጽ መጠቀምም ከፍ ያለ ነገር ሊመስለው ይችላል፡፡ በአለባበስ መዛባት፣ በአበላልና በአጠጣጥ መዛባት፣ ብዙ ሌሎችም የተወለካከፉ ድርጊቶች ያበዛል- ራስን መጣል የተጠናወተው ሰው፡፡
4.በዚያ አመለካከት የተያዘ ሰው ተገዢ ይሆናል
ሰው ሁሌ ገዢ ወይም ተገዢ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ በአስተሳሰብ ልእልና አንጻር፡፡ በዚህ በሰለጠነው ዘመን አንድ ሰው አእምሮውን በሌላ ሰው አስተሳሰብ ቢያስማርክ (በተለይ በክፋት) እጅግ ሁዋላ ቀር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
ማንም ራሱን ሲጥል ለሰው ፍቃድ ምርኮኛ ይሆናል፣ የራሱን ስለተወ፡፡ አንዳንዴ የውስጥ ስሜት ሳይቀር በሰው ድምጽ ብቻ የሚነቃ ይሆናል፡፡ ገዢው በዝቶአልና ስለዚህ፡- ለፊልም ትርክት ተገዢ፣ ለልብ-ወለድ ነገር ተገዢ፣ ለፋሽን ነገር ተገዢ፣ ለሱስ ተገዢ፣ ለዝሙት ተገዢ፣ ለመጠጥ ተገዢ፣…ይሆናል፡፡ መቼም ለመጣው ሁሉ እንዲህ ተገዢ መሆን በጣም ከባድ ነው፡፡ ተጽእኖው ስነልቦናን በጥልቀት ጎድቶ አእምሮውንና ስሜቱን ይይዛል፣ ለመኖር፣ ለመብላትና ለመጠጣት እንኩዋን ሳይቀር ተገዢ ያደርጋል፡፡ ይህ ከዘመናዊ ባርነት በምን ይተናነሳል? በሰዎች ቅድመ-ሁኔታ የማንፈልገውን ማድረግ ህሊናን የሚጎዳ ተግባርም ነው፡፡
አንድ ሰው በበጎ ነገር ካልተሞላ ውስጡ ነጻነት የለውም፡፡ በጎ ነገር የሙሉ ሰው መገለጫ እስከሆነ ድረስ በተወላገደ መንገድ ስልጣኔን የሚኖር ሰው በልቡ ያለው በሙሉ የተፈታ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ የሰው አመለካከት፣ የሰው ገንዘብ… ሁሉ ስለሚመራው የራሱ የሆነውን ነገር ማግኘት ያዳግተዋል፡፡
መፍትሄው ምንድነው?
.እንደባለ አእምሮ በሰለጠነ አመለካከት መራመድ
ግዴታና መብትን ማወቅ የተፈጥሮ ህግን ማሙዋላት ስለሆነ ቀላል እውቀት አይደለም፡፡ ለሰው ነገር ስፍራ መስጠት፣ ስለራስ ስፍራ መስጠት፣ ሰውን ማክበር፣ ለሰው አስተያየት ስፍራ መስጠት፣ ከሰው ጋር በሰላም መኖር፡፡ ሁልጊዜ ለሰው አስፈላጊ ነኝ ብሎ ራስን ማዘጋጀት፡፡ እኔ ጋ ያለው ፍላጎት የሌለውም ነው ብሎ ማሰብ፡፡ በዚህ አንጻር ራስን ከሰው ማስበለጥም ሆነ ማሳነስ ጤነኛ አመለካከት ስላይደለ ያንን ስሜት መቆጣጠር፡፡ ሰዎችን በአመለካከታቸውና በስብናቸው እንጂ እጃቸው ላይ ባለውና በሌለው ያለመመዘን ከፍ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡
.ራስን ማወቅ
የቱ ነው ብርቱ ጎኔ፣ የቱስ ነው ድካሜ? በብርቱ ጎኔ ለሌላው ልትረፍ፣ ደካማው ጎኔን እንድደግፍ ግን ከሌላው ልማር፡፡ ይሄ አመለካከት አያሳፍርም፡፡ ብርቱ ጎኔን አጉልቼ ለማሳየት እንደምደክመው ሁሉ ደካማ ጎኔን ለመሸፈን ሳሆን ለማረቅ መጣር አለብኝ በእውነት፡፡ ሰው ራሱን ሲያውቅ ጣቱን በሌላ ላይ መጠቆም ያቆማል፣ ሰው ሁሉ በተመሳሳይ ድካም ውስጥ ስላለ፡፡ ስለዚህ ራስን በማወቅ ራስን ከተጽእኖ ነጻ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡
.እግዚአብሄርን ማመን
በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ይሄ፡፡ ሰውን እንደሰው ለመቀበል አቅም የሚሰጥ ብቸኛው መንገድም ነው፡፡ ያለማንም ተጽእኖ በነጻነት ለመኖር የሚሻ ሰው ያለጥርጥር ወደ ፈጣሪው መጠጋት አለበት፡፡ ሁሉ ሰው ራሱ ነጻ ካልሆነ ነጻትን ሊሰጥ እንዴት ይቻለዋል? እግዚእብሄር ከአፈጣጠራችን ውጪ የተደረተውን ነገር እንድንጥለው ይፈልጋል፡፡ በላያችን በተለያየ መንገድ የተቀመጠን በጎ ያልሆነ ነገር እግዚአብሄር አይወደውም፡፡ ወደ እርሱ በመምጣት ድሪቶአችንን ማርገፍ ይገባል፡፡ ማንም በራሱ እውቀትና ፍላጎት እዚህ ምድር ላይ አልተገኘም፡፡ እውቀት ሲመጣለት ብቻ ራሱን ህያው እንደሆነ አውቆአል፡፡ ፈጣሪው በከፈተለት አእምሮ ሲያስተውል ምድር ላይ ራሱን አገኘው እንጂ ከመኖሩ በፊት የትና በማን እጅ እንደነበረ አያውቅም፡፡ ሰው የሚታለለው ራሱን ሙሉ ሲያደርግ ነው፡፡ አጉል ስልጣኔም በዚህ አመለካከት ይፈጠራል፡፡ ጥብብ ብሎ መገኘትም በዚያ ምክኒያት ነው፡፡ ሰው ሆይ ካንተ በላይ የበላይ አለ፡፡ ሳታየው የሚያይህ፣ ሳታውቀው የሚያውቅህ፣ የትና ወዴት እንድትሄድ ሳታስተውል መነሻህንና መጨረሻህን ያየልህ ፈጣሪ አለ፡፡ ”እግዚአብሄር አምላክ ነው ለእኛም በራልን” ሲል እኮ እግዚአብሄር ፈጣሪና ህያው ሆኖ እኛን ሊያኖረን አለ ማለትም ነው፡፡ እኛም እርሱን እናውቅ ዘንድ ተገለጠልን፡፡ እንዲያውም በብርሀኑ እንድናየውና መኖሩን እንድናውቅ ፍጥረታት ሁሉ ምሰክሩ ሆነዋል፡፡ የእኛ አፈጣጠር ራሱ እሱ መኖሩን ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር እንዳለ ማመን ስንጀምር ሙጥኝ ያልንበትን የራሳችንን ነገር ለቀቅ ማድረግ እንጀምራለን፡፡ ስልጣኑን ባወቅን ጊዜ ራሳችንን የበታች እርሱን የበላይ ማድረግና መፍራት እንጀምራለን፡፡
.በእግዚአብሄር ቃል ማስተዋል
የእግዚአብሄር ቃል የስጋዊውም ሆነ የመንፈሳዊው ህይወት ሚዛን ነው፡፡ የትኛውም ነገራችን ከቃሉ አያልፍም፡፡ እንዲያውም ሰው የተባለ እንደቃሉ መቆም አይችልም፡፡ የቃሉን ሚዛን ሊያሙዋላና ሊደርስበት ስላልቻለም እግዚአብሄር በስጋ ተገለጠ፡፡ ራሳችንን የጣልን በእግዚአብሄርና በቃሉ ፊት ምንኛ ምስኪኖች ስለመሆናችን ቃሉ ግልጥ አድርጎ ሊያሳየን ይችላል፡፡
1ቆሮ.6:9-11 ”ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።”
ከላይ የተዘረዘሩትን ክፉ ድርጊቶች ማድረግ በጀመርንበት ቅጽበት አልተዘፈቅንባቸውም፡፡ በአንድ ጀምበርም መሀከላቸው አልተገኘንም፡፡ዳር ዳር ስንልና እያደር በሱሳቸው ስንጠመድ ግን መላቀቂያ ጠፈቶን ግድ መሀላቸው ተገኘን፡፡ አግዚአብሄር ደግሞ ከነዚህ ከንቱ ልምምዶች ጋር ተጣብቀን ሊያየን ስለማይፈቅድ ቁርጥ አድርጎ መላቀቂያውን ነገረን፡፡ እንግዲህ ራሱን የጣለ ዘመነኛ በእግዚአብሄር ፊት መታየት እንደማይችል ቁርጥ ነው፡፡ መፍትሄው ያው እንደቃሉ፡- ምርጫህን በፍጥነት አስተካክል ወንድሜ!
በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ለምን እንደተፈጠርን፣ ከፍጥረታችን በሁዋላ ምን እንዳጣንና እንደጎደለን፣ ያጣነውን ያን ነገር ደግሞ እንዴትና ከማን እንደምናገኝ በዝርዝር ተገልጾአል፡፡ እግዚአብሄር ለውርደት ሳይሆን ለክብር ጠርቶናል፡፡ ይህንን ስናውቅ ለምን እንደተፈጠርን ይገባናል፡፡ የሰው ልጆች እግዚአብሄር አባት ሆኖን ከእኛ ጋር እንዲኖር እንጂ ጥሎን በተመሰቃቀለና ክብር ባጣ ህይወት ውስጥ እንድንዳክር አልፈጠረንም፡፡ ሆኖም ወሰን ያጣው ፍላጎታችን፣ ስሜታችንና ተግባራችን የእግዚአብሄርን ቃል ስለሚጋፉ ሀጢያት ሆነውብናል፡፡ መቼም ራሳችንን ስንጥል ጽድቅ ላይ አናርፍም፡፡ የምንወድቀው በሀጢያት ወጥመድ ላይ በመሆኑ መፈታታችንና ነጻነታችን ፈጥነው ይያዛሉ፡፡ ያኔ መነቃነቅ እስኪያቅት በሀጢያት ስለምንተበተብ ቀድሞ ካለንበት ጎሰቁዋላ ህይወት ወደሚቀጥለው እጅግ ጎስቁዋላ መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ እንገባለን፡፡
ወደሚሻለው ለመመለስ ግን ቃሉን አስረግጠን ማመን እንዲሁም በርሱ ውስጥ እያየንና እያስተዋልን ራሳችንን ማስተካከል፡፡ የተስተካከለው አዲሱ እኛነት ራሱን በማይገባ ስልጣኔ ላይ ከጣልነው ያኛው እኛነት ይልቅ እጅግ የከበረ ነው፡፡