ማምለጥ የምትፈልጉ የእግዚአብሄር ህዝብ!
• የሚሰማኝ ትክክል ነው በሚል እርግጠኛ ሆናችሁ ለስሜታችሁ እጅ አትስጡ/ ሙሉ በሙሉ አትቀበሉ፡፡
በውሎአችሁ ውስጥ ስሜታችሁ ወዴት ይመላለስ ኖሮአል? የተነካችሁበት ሁኔታ እንደማይገዛችሁ እርግጠኛ ናችሁ? ወይስ የአሳባችሁ ክልል በማን ሲጎበኝ ነበር (በአለም፣ በስጋ፣ በተለያየ መንፈስም ሊሆን ይችላል)፣ ምንስ ሲይዝና ሲጨብጥ፣ የቱንስ መንፈስ ሲያስተናግድ ዋለ?
• ውስጣችሁ የሚመላለሰውን ድምጽ በጥድፊያ አሜን አትበሉት፣ በተለያየ ምክኒያት ድምጹ ሊሰማ ይችላል፤ በግርድፉ ስላስተዋላችሁ ለድርጊት አትንደርደሩም፣ ከፊል እውቀት አውቃችሁ ሊሆን ስለሚችል ከፊሉን እውነት ብቻ ሊያሳያችሁ ሙሉው እውቀት ሲመጣም ከቦታችሁ ሊያስለቅቃችሁ ስለሚችል፣ ምርመራ ያልተደረገለትንም ድምጽ አትታመኑ፣ ድምጹ ከተለያየ ምንጭ ሊመጣ ይችላልና፣ ይልቅ እያንዳንዱን በቃሉ ማጣሪያ ቅድሚያ ፈትሹት፡፡
• ህልም አይታችሁ በህልሙ አትመኩ፣ በርሱ ታምናችሁ በመነዳት ወደፊት የምትንደረደሩ ህልማችሁን ሙሉ በሙሉ (100%) ሳትታመኑ ከእንቅስቃሴ ራሳችሁን ግቱ (ቆም በሉ)፡፡
… እንደዚህ ያሉ ማስጠንቀቂያዎች ትውልዱን ማንቃት የሚችሉ ደውሎች ቢሆኑም ማስጠንቀቂያዎቹን ልብ የሚልና የሚቀበል ሰው ግን ያስፈልጋል፤ ቃሉ ላይ ትኩረት በሚያደርግ ልቦና በመፈለግ፣ ምርመራ በማድረግና የሚተላለፈው መልእክት ከፍ ያለ መሆኑን ተገንዝቦ የሚሰጠው ምላሽ በህይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ በማመን ያን ቢያደርግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በነቢዩ ኤርሚያስ ዘመን እግዚአብሄር ለህዝቡ ለእስራኤል ሲናገር ማንም ራሱንና የራሴ የሚለውን እንዳይታመን ይልቅ እግዚአብሄር የሚለውን ብቻ እንዲያምን በአጽንኦት አስጠንቅቆአል፡፡ ይህን ለምን አለ? በኤር.29:8-12 ውስጥ ምክኒያቱ በግልጽ እንደሚከተለው ተቀምጦአል፡-
”የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፡- በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ።”
እግዚአብሄር ይህን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ህዝቡ ከመልካም የህይወት ይዘት ወጥቶ በክፉዎች ምክር የተተበተበ መስመር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በዚያ ምክኒያት፡-
• እስራኤላውያን በዙሪያቸው በተኮለኮሉ ነቢያቶቻቸውና ሙዋርተኞቻቸው አሳብ ስለተወሰዱ ሌላ ቃል መቀበል አልቻሉም፡፡
• ህልም ሲያልሙ ከክፉ ስራቸውና ከተያዙበት የሙዋርት መንፈስ የተነሳ ስለሚያልሙ የእግዚአብሄር ራእይ በእነርሱ ዘንድ ሊገኝ አልቻለም ነበር፡፡
• በቅጣት ወደ ተሰደዱበት ምድር ከገቡም በሁዋላ ቅጣታቸውን አሜን ብለው መቀበልና በጸጸት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አልቻሉም (መታዘዝ መስዋእት ከማቅረብ እንዲሻል ከአባቶቻቸው ታሪክ ሊማሩ አልቻሉም)፡፡
• በምርኮ ለተሰደዱባት አገር ሰላምን ፈልገውና ተረጋግተው ሰባውን የቅጣት ዘመን እንዲፈጽሙ ታዘው ሳለ ያን አልተቀበሉም (ለመቀጣት መታገስ ያድናልና)፤ ስለዚህ በእምቢተኝነታቸው በቀጠሉ መጠን ጥፋት ላይ ጥፋት ተከታተላቸው፡፡
• የእግዚአብሄርን ነቢይ ባለመስማት የፈለጉትን የምኞታቸውን ነቢይ ለራሳቸው በመሾማቸውም ጭምር እግዚአብሄር አዘነባቸው፡፡
… ስለዚህ ውስጣቸው የተሰማቸውን ሆነ ነቢያቶቻቸው የሚናገሩትን እግዚአብሄር ጠላው፣ ተጸየፈውም፡፡ ድፍረት ስላበዙም በስደት ካሉበት ምድር ድረስ ዘልቆ መቅሰፍትን አወረደባቸው፡-
ኤር.29:17-20 ”የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እነሆ፥ ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድድባቸዋለሁ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ። በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፥ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለጥላቻና ለመደነቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።”
አስቀድሞውኑ እሰራኤላውያን ባቢሎን የወረዱት የእግዚአብሄርን ማስጠንቀቂያ ስለናቁና በቅጣት ከምድራቸው ስለነቀላቸው ነው፡፡ ትእቢታቸው ማቆምያ ስላልነበረው በቅጣት ተላልፈው ከገቡበት ምድርም ሆነው ሊጸጸቱ አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ በላያቸው የተነሳች የእግዚአብሄር እጅ ተከታትላ ታጠፋቸው ገባች፡፡
ኤር.3:25 ”ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይክደነን።”
• እርሱ ግን አለ፣ የእግዚአብሄርን ቃል ስሙ፡፡
በድካም ህይወት ውስጥ የምንኖር የእግዚአብሄር ህዝብ ለቃሉ ትሁት ከመሆን የተሸለ መዳኛ አማራጭ ልናገኝ አንችልም፡፡ ለመዳን አንድ ነገር ልብ እንበል እስቲ፡- የልቦናችንን ዝንባሌ ከራሳችን ወጣ ብለን እንመርምር፤ በእውነት ውስጣችን ምን ይፈልጋል? ልባችን የሚሰማው እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሆነውን ነገር ነው ወይስ አይደለም? መንፈሳችን በተጎሳቆለ አኩዋሃን ውስጥ ሲገባና ውስጣችን የመዘጋት አዝማሚያ ሲያሳይ የሚመረምር ትኩረት በዚያ ነገራችን ላይ እስቲ እናድርግ፣ በሚቻል ፍጥነትም ያልተገባ ስሜትን እንጋፈጥ፡፡ ህያው ቃሉን ለመመልከት እንሞክር፣ ቃሉ እንደሚሰራ እያመንን በንሰሀ ለመጸለይ እንሞክር፣ በቀጥታ በስሙ እየገሰጽን ነገሩን በመጋፈጥና ቃሉን ይዘን በመጸለይ እንጽና፤ እምነት በሚፈጥረው በረከት ውስጣችን ይሞላል፣ ፈውስም ይሆንለታል፡፡
ቃሉን መስማትና እግዚአብሄርን መጠየቅ የነበረባቸው እስራኤላውያን ግን ስለተሰማቸው ነገር እግዚአብሄርን አልጠየቁም ወይም አልጠበቁም፡፡ አልፎ ተርፎም ድፍረት ውስጥ ገቡ፤ ማመዛዘን ስላቃታቸው በስህተት መንፈስ ተደገፉ፣ ስተውም ሙልጭ ብለው ራቁ፣ ሀሰተኞች ነቢያት በቀላሉ ከመንገድ አንሸራተዋቸዋልና፡፡ በትህትና የመከራቸውና ያባበላቸው የፍቅር ማባበል ለምን ትሁት እንዲሆኑ አላደረጋቸውም? ሊያስተውሉ ያቃታቸው ቃል የሚናገረውን በኤር.29:11-14 ውስጥ እናያለን፡-
”ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።”
እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበውን ቸል ማለት ብዙ ጉዳት ውስጥ ይከታል፤ የታመኑት ግን እርሱን በመሻት ውስጥ የሚመጣላቸው መልስ ግልጽ ነው፡-”ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፣… እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ” የሚል፡፡
• እግዚአብሄር የሰላም አሳብ ለህዝቡ ስለሚያስብ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል፡፡
ያለንበት ህይወት ጉስቁልና ይመስል ይሆናል፣ ቢሆንም አንዳንዴ የዚህን ምንጭ መመርመር ይበጃል፡፡ እግዚአብሄር ማንንም በክፉ
ስለማይፈትን እግዚአብሄር ነው ወደዚህ ችግር የከተተኝ ብሎ ከማጉረምረም በፊት ራስንም ሁኔታዎችንም መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ለተወሰኑ ሰአቶች የራስን/የውስጥን ድምጽ በመግታትና የቃሉን መንፈስ በመታዘዝ በጽሞና መቆየት ቀላል ያልሆነ ድምጽ ያመጣል፡፡ እግዚአብሄር በእርግጥ ይናገራል፡፡ ስለፈተናችን ምንጭ የሚናገረው ቃል የሚናገረን ምን እያለ ነው?
ያዕ.1:11-15 ”ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።ማንም ሲፈተን፡- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”
ሌላው ቢቀር እስራኤል ራሱን ወደ ፈተና መራ ወይስ እግዚአብሄር ወደዚያ አስገባው እንበል? እስራኤል የወደቀበትንና የተሰደደበትን ምክነያት በትክክል ብናገኘውና ለልባችን ማስተዋል ቢሆን (ህዝቡ በራሱ ህልምና በሚያሳስቱት ሀሰተኞች እንጂ በእግዚአብሄር ለጥፋቱ እንዳልተፈተነ ካስተዋልን) ፈቅደን ራሳችንን ወደ መፈተሽ እንገባለን (ማንም ሲፈተን፡- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል ስለሚል)፣ በፍተሻው ራሳችንን ያጠራን ሲሆንም ጸሎታችን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ወደ ተቀባዩ አምላክ እንዲሄድ እናውቃለን፡፡
በአንድ ወቅት ዳዊት በሰራው መተላለፍ ምክኒያት በቤቱ ላይ መቅሰፍት መጣበት፣ ስለዚህ የተወለደው ልጁ ሞተ፡፡ የሆነውን ነገር ሁሉ ያየው ንጉስ እጁን ወደማንም አላመለከተም፡፡ ይልቅ የሰራው ሀጢያት ጸጸተውና በእግዚአብሄር ፊት በንሰሀ ተቀምጦ አለቀሰ፣ እግዚአብሄርም ማረው፣ የመጽናናት መንፈስንም ሰጠው፡፡ ንጉስ ስለሆነ አያልፈውም ወይም እንደልቤ ስላለው ያን እንደ ልዩ ጥቅም አይቆጥርለትም ነበር፡፡ መፍትሄው በንሰሀና በተሰበረ ልብ መቅረብ ነበረና ያ መንገድ ወደ እግዚአብሄር አዘንብሎ ምህረት እንዲቀበል አስችሎታል፡፡ ያኔ ስለዳዊት የተጻፈው የቃሉ ማስታወሻ እንዲህ ይላል፡-
”ለመዘምራን አለቃ፤ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ። እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።” (መዝ.51:1-12)፡፡
• ልባችንን ፍጹም አድርገን ብንሰጠው በጠራነው ጊዜ ሊገኝ እግዚአብሄር ቃል ገብቶአል፡፡
ያለጥርጥር ልቡን ሳያደነድን፣ በእምቢታ ሳይጣላ አምላኩን በፈቃዱ እሺ ያለ ካለ እርሱን እንዲሰማው ማመን ይገባል፣ መጽሀፉም ይደግፈዋል፡-
ኢሳ.6:8-10 ”የጌታንም ድምፅ፡- ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፡- እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። እርሱም፡- ሂድ፥ ይህን ሕዝብ፡- መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።”
አሁን ማሰብ ካለብን በዓይናችን ማየት ያለብንን ማየት ብንችል፥ በጆሮአችንም መስማት የሚገባንን ብንሰማ፥ በልባችንም ማስተዋል የሚገባንን ብናስተውል፥ ብንመለስና ምህረቱ አግኝታን ብንፈወስ፥ ልባችን ከድንዳኔ፥ ጆሮአችን ከድንቁርና፥ ዓይናችንም ከእውርነት ተፈውሶ ሊያገኘን የሚችለውን ምህረትና በጎነት ለአፍታ እንኩዋን ማሰብ መቻል ነው።
• በእግዚአብሄር ስም ሀሰተኛ ትንቢት በሚናገሩ ላይ የእግዚአብሄር እጅ ትከብድባቸዋለች፡፡
ከራሳቸው ልብ የገዛ አሳባቸውን እያወጡ ህዝቡን በእግዚአብሄር ስም የሚሸነግሉ እስከ መቼ ይህ ድፍረት አብሮአቸው ይቀጥል ይሆን? አናውቅም፣ ግን እርግጠኛ የምንሆነው እግዚአብሄር የሚያያቸው መሆኑን ነው፡፡ ትላንት በእስራኤል ምድር ያ ሀጢያት ተሰርቶ እግዚአብሄርን እጅግ አስቆጥቶ ነበር፤ አሁን ግን በከፋ መልኩ በተጠናና በተደራጀ ደረጃ በአደባባይ ያን የሚያደርግ የማይፈራ ወገን ትውልዳችን አፍርቶአል፡፡
”የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፡- እነሆ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ በዓይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፡- የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል እርግማንን ያነሣሉ፤ እኔም አውቃለሁ ምስክርም ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። በእስራኤል ዘንድ ስንፍና አድርገዋልና፥ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፥ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና።”
(ኤር.29:21-23) ይላል፡፡
የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ የጠሩ ከፍተኛ ውድቀት ነበር የገጠማቸው፣ በጥንት ጊዜ፡፡ ያኔ በስሙ ያጭበረበሩ፣ የዋሆችን የሸነገሉና ለስሜታቸው መጠበቂያ የቅዱሱን አምላክ ስም የተጠቀሙ በከፍተኛ ሁኔታ ከስረዋል፡፡ በመቅሰፍት ላይ መቅሰፍት እየተደራረበ እስከሚያሳድዳቸውና እስከሚጨርሳቸው ድረስ ሊያቆመው የሚችል ሀይል አልነበረም፤ ግን ዛሬም ያ አምላክ አለ፡፡
በስሙ የተጠራው ህዝብ ያከበረውን አምላክ ባያከብር የሚያሳድደው ጠላት ዞሮ ያጠምደዋል፣ ይይዘዋል፣ ይወጋዋል፣ በመጨረሻም ያጠፋዋል፡፡ በእርግጥ በራስ ምኞት ምክኒያት ከእግዚአብሄር አሳብ እንደ መውጣትና ራስን ለጠላት አሳብ አሳልፎ እንደ መስጠት ምን ከባድ ውድቀት ይኖራል?
የኢትዮጰያን ምድር በሀሰት ትንቢት ስላጥለቀለቁ ነብያቶች እግዚአብሄር ምን ይሆን የሚለው? – በእርግጥ ከላይ የተነበበው የነቢዩ ቃል በነርሱም ይሰራል! ስለዚህ እግዚአብሄርን የሚፈራ ካለ ሳይረፍድበት ከስራው ሊታቀብ ያስፈልጋል፤ ብሎም ለሚጠፋ እንጀራ ሲል መንገዱን ባያበላሽ ይሻላል፡፡ እግዚአብሄር ለእስራኤል ካልራራ ለአህዛብ ይራራል ማለት ከፍተኛ መታለል ነው፡፡
2ጴጥ.2:1-3 ”ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።”
ብዙ አክዓቦችና ብዙ ሴዴቅያሶች በዝተው ዘመናችንን በመቅሰፍታቸው ያስጨንቃሉ፣ ይሁን እንጂ እግዚአብሄር ዛሬም ከጨለማቸው ይልቅ የበረታ የብርሀን ጉልበት ስላለው እነርሱን የሚከተላቸውንም በምህረት ጎብኝቶ ሊያድን ይችላልና (ከነርሱ የመቅሰፍት ድርሻ ከማፈስ መትረፊያም መንገድ ነውና ) ይቅር ብሎ ልባቸውን እንዲመልስ ስለነርሱ ብርቱ ልመና ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ እነርሱን የሚከተለውም ቢሆን ራሱንና ምቾቱን በከንቱ ማጽናናታቸው ከሚጠብቅበት ሁኔታ ወጥቶ ፈቃዱን ቢገታ፣ ህልሙን ጭምር ባይከተልና የበላተኛ ነብያቶችን ድምጽ ቢጸየፍ ይተርፋል፡፡