• እግዚአብሄር ምን እንድንሰራ ነው የሚፈልገው?
ሮሜ.12:11-12 ”ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ…”
የእግዚአብሄር ልጆች ቀዳሚ ስራ እግዚአብሄርን ማመንና መከተል እንዲሁም ሲሰራ መንገድ እንጂ እንቅፋት ያለመሆን ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በአባትነቱና በአምላክነቱ ካልወደደው ትክክለኛው የህይወት ይዘት ውስጥ ሆኖ ሊመላለስ አይችልም፡፡ አይሁድን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል፡-
ዮሐ.8:39-42 ”መልሰው ፡- አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም፡- የአብረሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት። ኢየሱስም አላቸው፡- እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና።”
እግዚአብሄር እንድንሰራው የሚያዘው ስራ ከመንፈሳዊ ነገር ጋር የተገናኘ ነው፡፡ መንፈሳዊነትን የሚገነባው የእግዚአብሄር መንፈስ ሀይል በመሆኑ እኛም ለመሰራት ሆነ ለእግዚአብሄር መስራት የተመቸን እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡ አይሁድ በአዲስ ኪዳን መባቻ ላይ የፈጠሩት እንቅፋት ይህን ያስተዋለ አልነበረም፤ ጌታ አመጣጡ ለአብረሃም ቃል የገባውን ተስፋ ሊፈጽም በሌላ በኩል በነርሱ በኩል የተነገረው የተስፋ ቃል ከእነርሱ አልፎ አህዛብንም እንዲባርክ ለማድረግ ነበር፡፡እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሄር መንግስት የማይገቡ የማያስገቡም ሆነው ድርብ ጉዳት ተጎዱ፡፡
ገላ.2:16-18 ”ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም።ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።”
በአይሁዳውያን አምልኮ ውስጥ ጠንክሮ የተተከለ የሙሴ ህግ የብሉይ ኪዳን መሰረት ነበር፡፡ ይህ መሰረት የማይናወጥ ሲሆን ሰውን በስራው የሚያጸድቅና የሚኮንን ነበር፡፡ ስለዚህ ከህጉ ጠንካርነት የተነሳና ከአይሁድ እምነት ማነስ የተነሳ ጌታ ኢየሱስ የሰጣቸውን የፍቅር ድነት ሊታመኑበት አቅቶአቸው ነበር፡፡ ህጉን ሊፈጽሙ እንዳይችሉ ነብያት ሳይቀሩ እያመለከቱዋቸው ትግላቸው ከራስ ፈቃድ ጋር እንዲሁም ፍጹም ሆኖ ከመገኘት ጋር ሆነና በዘመናቸው የተገለጠውን የእግዚአብሄር ማዳን ሊያገኙት ተሳናቸው (ሮሜ.3:10-18፣ መዝ.14:1)፡፡
የእግዚአብሄር ስራ ግን ጌታ ኢየሱስ ጀምሮ የፈጸመው ስራ ስለሆነ ሰው በራሱ አንድ ብሎ የሚጀምረው ወይም ጎድሎ የቀረና በችሎታው የሚፈጽመው ከቶ አይደለም፡፡ ነገር ግን ምንም ስራውን እግዚአብሄር በክርስቶስ ሰርቶ ቢፈጽመውም ወደ እያንዳንዳችን ህይወት ስራውን በማምጣት በህይወታችን መግለጥ ይፈልጋል፤ በሚገልጠው ስራ ውስጥ ደግሞ የሰው ድርሻ አለ፡- ሰው እራሱም እንዲሰራ ሌላው ወገኑም ጨምሮ እንዲሰራ ለፈቃዱ መሰጠት ይገባዋል፡፡ ያኔ ስራው መካሄድ ይጀምራል፡፡ እግዚአብሄር በሰው ህይወት ውስጥ እየሰራ እንዳለ የሚታወቀው በዚያ ሰው ህይወት ጸጋው ተገልጦ ሲታይ ነው፡፡ ሀዋርያው ያን አስመልክቶ ሲያብራራ እንግዲህ ጸጋው በናንተ ከተገለጠ መንፈሳዊ ስራው በእናንተ ይገለጥ ሲል ያሳስባል፡፡በሮሜ.12:6-18 የተገለጠው ቃልም ያብራራል፡-
”እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”
ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች እኛ ችለን አደረግናቸው ልንል አያስደፍረንም፤ ምክኒያቱም ጸጋ የሚባል የማስቻል መለኮታዊ ስጦታ ውስጣችንን እያነቃቃ፣ እያስተማረ፣ እየመራ፣ እያስቻለ በሌላ በኩል ራሳችንን እንድንገዛ እግዚአብሄር እንዲሰራ እያደረገ በእግዚአብሄር ፊት ደስ የሚያሰኝ መስዋእት አድርጎ ስለሚያቀርበን ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ከእግዚአብሄር ጸጋ ስንጎድል ከላይ የተገለጡትን የእግዚአብሄር ስራዎች መስራት የሚያዳግተን፡፡
ሰው በእግዚአብሄር መንፈስ ካልተሞላ የእግዚአብሄርን ስራ መስራት አይችልም፡፡ በዮሐ.8:39-42 የተጠቀሱት አይሁድ እንደ አባታቸው ያለ ስራ እንዳይሰሩ ምን አገዳቸው? የእግዚአብሄር መንፈስ ስላልነካቸውና ተቃዋሚው መንፈስ ስለሞላቸው ደረቅ ጩኧትና ዲስኩረኞች ብቻ ነበሩ እንጂ የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበት ስራ አልነበራቸውም፡- ቅዱስ መንፈስ ስለሌላቸው ብቻ!
የሀዋሪያቱ ምስክርም በቤተክርስቲያኖች ውስጥ እግዚአብሄር በነርሱ እጅ የሰራውን የሚገልጥ ነበር፡-
”ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ”(ሐዋ.14:26-28)፡፡
ስለዚህ እግዚአብሄር ምን እንድንሰራ እንደሚፈልግ ለማወቅ ስንጠይቅ እግዚአብሄር መንፈሱን በሰው ህይወት አፍስሶ በርሱ ህይወት የሚሰራውን ስራ በማሰብ ነው፡፡ይህን ስናውቅ እንደ አይሁድ አንመጻደቅም፣ የበጎነቱ ምንጭ ስለታየን፣ የሚሰራው በእኛም ህይወት የተገለጠው መልካም ስራ ከየት እንደሆነ ስለገባንም ማለት ነው፣ ይህም ሁልጊዜ ምስጋናና አምልኮ በህይወታችን ሊያመጣ የሚችል ወደሚቀጥለው የእግዚአብሄር ስራ (ሮሜ.12:1 ውስጥ የተገለጠ አገልግሎት) ውስጥ የሚያዘልቅ የጥበብ እውቀት ነው፡፡
1ቆሮ.15:58 ”ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” ይላል፡፡
መሰረቱ የጸና ክርስቲያን በጌታ ላይ እምነቱ የበረታ ነው፤ የርሱ የግሉ ማንነት ሳይሆን የጌታ ፈቃድን ስለሚያስተውል ማለት ነው፡፡
2ጢሞ.2:20-23 ”በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል።ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ”
• እግዚአብሄር የሰራውን በማሰብ ሁሌ እርሱን ማምለክ ተገቢ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ማምለክና መከተል በዚህ አለም ላይ የመኖራችን ዋስትና ነው፤ መንፈሳዊ ስራም ነው፡፡ የእለት ተእለት ስራውን የዘነጋ፣ ያሳለፈ ወይም የቆመ ሰራተኛ ቢኖር የሚሸምተውን ምግብ እስኪያጣ እንደሚቸገር እግዚአብሄርን ማምለክ የሚያቆም ማንም መንፈሳዊ ሰው ቢኖር በቃሉና በመንፈሱ እጥረት ሞት ለሚያስከትል ጉዳት እንደሚዳረግ እሙን ነው፣ ወይም ከመንፈሳዊነት አካባቢ ቢርቅ በድርቀት የሚከሳ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስ የተሰጠውን ስራ ችላ ብሎ ከእግዚአብሄር ፊት ኮብልሎ ነበር፡፡ በተደበቀበት መርከብ ውስጥ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሄር ጭንቅ ውስጥ ከተተው፡፡ ከርሱ ጋር የነበሩ ተጣድፈው ያዙትና ማንነቱን ስራውንም ጠየቁት፣ እርሱም ሲመልስ አኔ እብራዊ ነኝ፣ ስራዬም እግዚአብሄርን ማምለክ ነው ሲል መሰከረ፡፡ ይህን ሲመሰክር በነበረ ጊዜ ግን እግዚአብሄርን በሚያመልክበት ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሳይሆን ከፊቱ እየኮበለለ ያለበት ወቅት ነበረ፡፡ እግዚአብሄርን በእምነትና በትህትና ማምለክ መንፈሳዊ ስራ ነው፡፡
ዮሐ.6:27-29 ”ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።እንግዲህ፡- የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት።ኢየሱስ መልሶ፡- ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።”
• የተከለከለ ስራ
የማይገባ አምልኮ አለ፣ እርሱን ማከናወን ትናንትናም ሆነ ዛሬ በእግዚአብሄር ፊት ጸያፍ ነው፡፡ በአማኞች መሀል ያልተገባ ግንኙነትም እንዲሁ እግዚአብሄርን የሚያስቆጣ ድርጊት ነው፡-
ሐዋ.7:41-43 በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው። እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን?ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል።
1ቆሮ.5:1-6 በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን?
ጽድቅን የሰው ልብ ሊፈጥር ከቶ አይችልም፡፡ በልብ አንዴ ሞልቶ የተቆጣጠረ ክፋትና አመጽ መልካምን ሊያፈልቅ ከቶ እንዴት ይችላል? እንዲህ ማሰብ ትእቢት እንጂ መልካም አሳብ አይደለም፡-
ሮሜ.3:27-30 ”ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው።”
ኤፌ2:8-9 ”ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።”