• እግዚአብሄር የሰራውን የሚያስቡና የሚያመሰግኑ የሚያስተውሉት ናቸው፡፡
ቃሉም በኢዮ.36:24-25 ውስጥ ሲናገር ”ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ። ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል።” ይላል፡፡
ሰዎች በራሳቸው ስራ እንዳይመኩ፣ ነገረ ግን መመካት ካለባቸው በእርሱ ስራ ብቻ እንዲሆን እርሱ በምድር ላይ ተገልጦአል፡፡
በማቴ.1:23 ”እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ….” ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ምን ሊሰራ እንደተገለጠም ሲናገር፡-
”…ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፡- እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፡- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።” (ማቴ.1:21)
ከዘላለም ዘመናት በፊት አቅዶ የሰራው ስራ ይቅርና በየእለቱ የሚፈጽመው ጥቃቅን የሚመስለውን ብናስብ እንኩዋን የእቅዱን ታላቅነት፣ የቸርነቱንና የበጎነቱ ብዛት እናስተውላለን፡፡
ኢዮብ በእግዚአብሄር አሰራር ተደንቆ ተናገረ፡-
”ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥ ከስፍራውም ተንቀሳቀሰ። የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ። እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል። በስተ ኋላው ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም። እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ:- በምድር ላይ ውደቁ ይላል። ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ። ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥ ከሰሜንም ብርድ ይወጣል። ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ተሰጥቶአል፤ የውኆችም ስፋት ይጠብባል። የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፤ የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፤ ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረት ቢሆን፥ ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል። ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።” ( ኢዮ.37:1-14)
ኢዮብ ቆም ብሎ የእግዚአብሔርን ተአምራት እንዲያስብ ማሳሰቢያ ተቀብሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁ ከርሱ ወጥቶ ታላላቅ ነገሮችን ይፈጽማል፤ እኛም የማናስተውለውን ብዙ ነገር ያደርጋል። እኛም ከኢዮብ እይታ ተነስተን እንደ እርሱ ወደ ማስተዋል እናድግ ዘንድ ቆም ብለን እግዚአብሄርን ልንጠብቀውና የሚሰራውን ስራ በማስተዋል ልናስብ አይገባምን? ካልሆነ የእግዚአብሄርን ድምጽ አካሄድ የሚያስተውል አንድ ሰው እንኩዋን ላይኖር በትውልድ መሀልም የእግዚአብሄር ራእይ ሊጠፋ ይችላል፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ አስተውሎ ቃልኪዳኑን የሚያሳስብ ሰው ለምን ይጠፋል? የሚማልድ በጉልበቱም የሚሄድ ለምን በአንዳንድ ዘመን ውስጥ ይታጣል? ያው በመራቅ ምክኒያት ነው! በመራቅ ሁኔታ ውስጥ ሲኮን ሊመጣ ያለው አይገለጥም፣ የእግዚአብሄር ስራ የሚመጣው ለመልካም ይሁን ለጥፋት የሚያውቀው አይኖርም፡፡
ለእስራኤል ህዝብ የእግዚአብሄር ሰው ሙሴ ባይመጣ ኖሮ ምን ያህሉ ህዝብ ወደ ቃልኪዳን ምድር ይገባ ነበር? ሙሴ በእግዚአብሄር ፊት ስለህዝቡ ከመቆሙ አስቀድሞ ከ400 አመታት ባላይ ከእስራኤል አልፈዋል፣ ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሄርን ረስተው ነበርና፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አውቆ የተነሳው ሙሴ ግን ስለወገኖቹ በአምላኩ ፊት በሞገስ ሊቆም ችሎአል፣ ጸልዮአልም ፡-
ዘጸ.32:11-14 ”ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም፡- አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? ግብፃውያንስ፡- በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።”
ሙሴ የእግዚአብሄርን መንገድ ጠንቅቆ የተማረ፣ በአምላኩ የታመነና ታዛዥ አገልጋይ ስለነበረ እርሱ ራሱን ቤቱንና እስራኤልን ከብርቱው የእግዚአብሄር የበቀል ስራ ታድጎአል፡፡ እኛስ ለራሳችን ምን እናድርግ? በዘመናችን እግዚአብሄር ተገልጦ ይሰራ ዘንድ መሆን ያለብንና መሆን ያለበት ምንድነው? አስበነው እናውቃለን ይህንን?
በቅድሚያ ስለራሳችን ስንል የተጣደፍንበት፣ ጉልበታችንን የጨረስንበት ወይም አሁን የማደርገው ቆይቶም ቢሆን ይጠቅመኛል በሚል እሳቤ ለሌላ ያደረግነው ነገር ቢኖር ሞገስ ያለው ተግባር እንዳልፈጸምን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በመንፈሳዊ ህይወት በኩል ስናየው እኛ የሚያረካ ስራ እንደሰራን ከምናስመስልና ከሚመስለንም ይልቅ በርሱ ስራ ብንታመን በብዙ የተሸለ ነገር እንደምንቀበል ማሰብ ይጠቅማል፡፡ በራሳችን እንዴት እንመካለን? የእኛ ስራ እንከን አለው፣ እርሱ ግን ፍጹም ነው፤ የአኛ ስራ ስጋን ያማከለ ነው፣ እርሱ ግን ዘላለመዊና ለትውልድ የሚበጀውን የሚያከናውን ነው፤ እኛ በእኛ ጉዳይ ላይ ተወስነን እንሰራለን፤ እግዚአብሄር ግን ለፍጥረቱ ሁሉ ያስባል፣ ያን ያሰበውን ከዘመን ወደ ዘመን ተሸጋጋሪ እንዲሆን አድርጎ ይሰራዋል፡፡ ሰው ስሜታዊና ራስ ወዳድ ነው፤ እግዚአብሄር ግን ሰውን ሲወድ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም የሰጠውን አንድያ ልጁን ለሞት ሊያውም ለውርደት ሞት አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ ነው፡፡
ይህን የእግዚአብሄር ስራ ሰዎች ዘምረውለታል፡፡ እኛም የዘመሩትን ሥራውን እናከብር ዘንድ ደግመን ደጋግመን እናስብ፡፡ እንደ ንጉስ ዳዊት ያለ ጥብቅ ልማድ እንዲኖረን ያን ማዘውተር ያስፈልጋል፡- በኤዶምያስ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። (መዝ.63:1-6) አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ። ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ። ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ። በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም እናገርልሃለሁ፤ የሚል ነው፡፡
ሰዎች እግዚአብሄርንና ስራውን በተመቸን ጊዜ ብቻ እንድናነሳው መጠበቅ የለባቸውም፣ እኛም ብንሆን እንደዚያው፡፡ በቃሉ ትምህርት መሰረት እርሱን ማሰብ ዘወትር የሚገባና ወደ እርሱ የሚያቀርብ ስራ ነው፡-
መዝ.42:5-9 ”ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስብሃለሁ። በፍዋፍዋቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ። እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፤ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። እግዚአብሔርን፡- አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ።”
መከራንና ፈተናን መርሻ መንገድ እግዚአብሄርን ማሰብና ስራውን ማሰላሰል መቻል ነው፤ ከድካም ወጥቶ ወደ ብርታት ውስጥ ለመግባት መንገዱ የራስን ድካም ማውጣትና ማውረድ ሳይሆን የእርሱን ስራ በማሰብ መበራታት ነው፡፡ ንጉስ ዳዊት ነፍሱ በጭንቀት ተወጥራ፣ አዝናና ታውካ ሳለ ወደ እግዚአብሄር መዘርጋት አቅጦት እንደነበር እናያለን፡፡ እርሱ ግን በዚህም በዚያም ብሎ የነፍሱን ጭንቀት ለመርሳት እየታገለ እግዚአብሄርን ወደ ማሰብ ውስጥ በመግባት ከዚያ ውስጥ የእምነት ፈውስ ተሞልቶ ሊወጣ በቅቶአል፡፡
• ስራውንና መንገዱን ማወቅ፡፡
ኢዮ.36:2733 ”የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፤ ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ። የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው? እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፤ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል። በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ብዙም ምግብ ይሰጣል። እጆቹን በብርሃን ይሰውራል፥ በጠላቱም ላይ ይወጣ ዘንድ ያዝዘዋል፤ የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፤ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።”
1. አለም ስራውን ታያለች፣ ሆኖም ስራውን በስፍራ ወስና አቅፋ ትቀራለች፡፡
በአለም የሚኖሩ አህዛብ እግዚአብሄር የሰራውን ስራ ያያሉ፣ የሰራውን ብቸኛ አምላክ ባያውቁም ያደንቃሉ፣ ይፈራሉ፣ ከሆነው ነገር በሁዋላ ግን ያዩትንና የሰራውን እግዘአብሄርን ይረሳሉ፡፡ ረሀብን ያያሉ፣ ቸነፈርን፣ ድርቅን፣ ጦርነትን… እነዚህን ሁሉ ያያሉ፣ ያወራሉ፣ ፈጥነውም ይረሳሉ፤ ለምን ሆነ አይሉም፣ ለምንና ማን አደረገው ሲሉም አይጠይቁም፡፡ የሆነው ሁሉ እንደሆነና በዘፈቀደ እንደመጣ ይገምታሉ፡፡ ሱናሚ በኢሲያ፣ ረሀብና ጦርነት በአፍሪካ… ሲሉ እያንዳንዱን በስፍራና በሰአት ለይተው ያወራሉ፣ ያወራሉ እንጂ ለምን አይሉም፤ ምክኒያቱም ምንጩን መረዳት ስለማይችሉና አምላክን ስለማያውቁ ነው፡፡
ሉቃ21:25-28 ”በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።”
የአህዛብ ጠቢባን ምድር ላይ ያለን ክስተት በመተንተን ከፍተኛ ስራ ይሰራሉ፡፡ የሚያዩትና የሚሰሙት ህዝብም በሚሆነው ይጨነቃሉ፤ ከመጨነቅ ያለፈ ግን ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያለማወቅ በብዙ ያስታልና፣ እግዚአብሄርን ያለማወቅም ጥፋትን ያፈጥናልና፡፡
እግዚአብሄር ሰማይና ምድርን የሞላ አምላክ ነው፤ ስለዚህ የትኛውም ስፍራ የርሱ መገኛ ነው፡፡ እርሱ በጊዜም ላይ አምላክ በመሆኑ በየትኛውም ሰአትና ወቅት ሊገኝና ሊሰራ ይችላል፡፡ የጊዜ ክስተትና ውስንነት የሰው ልጅ ጥያቄና እንቆቅልሽ ይሆናል እንጂ ለፈጣሪው አምላክ ያ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብና በአለም የሚኖር የተቀረው ወገን ዋናው መለያቸው በአምላክ አሰራር ላይ ያላቸው እውቀት ልዩነት ነው፡፡
2. የእግዚአብር ህዝብ ግን በእግዚአብሄር ጊዜ የተፈጠረውን ክስተት (ስራውን) ያስባል፡፡
ቃሉ እንደሚያረጋግጠው አህዛብ የሚሆነውን በመስማትና በማየት ውስጥ ሆነው ሲጨነቁ ይታያሉ እንጂ እግዚአብሄርን በማሳሰብ ሁኔታ ውስጥ አይገኙም፡፡ህዝቡ ግን እንደዚያ አይሆንም፣ ይልቅ ነገሮች ሊሆኑ ሲጀምሩ ወደ መድሃኒቱ ይመለከታል፣ ፍጻሜው ላይም ተግቶ እየጠበቀ የቤዛውን መቅረብም እያስተዋለ ራሱን ያነሳል።
ሉቃ21:29-33 ”ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል፡- በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።”
ጌታ ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ ህዝቡ በምድር ላይ የሚሆነውን ነገር አይቶ መንፈሳዊ መልእክቱን እንዲያስተውል አሳስቦአል፡፡
3. የእግዚአብሄር ስራ ስፍራና ወቅትን ጠብቆ ይገለጣል፡፡
የእግዚአብር ፈቃድ ሲገለጥ በሆነ ጊዜ በሰዎች መሀል በአንድ ስፍራ ይገለጣል፡፡ ፈቃዱ ተገልጦ አሳቡን ሲፈጽም የሚከሰት ነገር አለ፡፡ ይህ ክስተት የሚታይ ውጤት ያመጣል፡፡ ነቢያቶች እግዚአብሄር የሚለውን ለህዝቡ ሲናገሩ ዘመንንና ስፍራን አማክለው ነው፡፡ እግዚአብሄር ፈቃዱን የሚገልጥበት ዘመን አለው፣ ስለዚህ ባሪያው ያን በማስተዋል በአመታት መሀል ስራህን ፈጽም ይለዋል፡፡
ዕን.3:1-7 ”የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር፡- አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ። እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል። ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል። ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው። የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።”
እግዚአብሄር ስራውን ሲፈጽም እንድናስብ፣ እንድናስተውልና በህይወታችን ታትሞ እንዲቀር የሚፈልገው ምኑን ነው፡- ዘመኑንና ስራውን (ክስተቱን) ነው፣ በአመታት መሀል የሚገለጠውን ስራውን፡፡
የትውልድ አምላክ ስራውን በትውልድ ሁሉ ፊት እንደተናገረው ይገልጣል፡፡ የሚያስተውል ትውልድም አምላክነቱን ያውቅ ዘንድ ስራውን ያስባል፤ የሰራውን ስራና ዘመኑን ያስባል፡፡
ያላስተዋለው ግን ስራውን ሳይሆን ስፍራውን ይዘክራል፡፡ በዚህ ሁኔታዎችን ከምድራዊ ጉዳዮች ጋር ሲያመሳስለው ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር የሰራባቸውን ስፍራዎችና ነገሮች እንደ እስራኤላውያን የመዝናኛ፣ የቱሪስት መፈንጫና የገንዘብ መሰብሰቢያ ምንጭ ያደረገ ህዝብ የለም፡፡ መንፈሳዊ ክስተት ያስተናገደና ሊያስተናግድ ባለው ስፍራ አካባቢ ያልተገባ አለማዊ ጉዳይ የሚፈጸመው ሌላ ሳይሆን እግዚብሄርን ባለማወቅ ምክኒያት ነው፡፡
በእስራኤል ምድር ብዙ አካባቢዎች በታሪካዊነት ተመዝግበውና ተጠብቀው ለቱሪስቶች መዝናኛ ውለዋል፣ እግዚአብሄር የሰራቸውን ስራዎችና የታምራቱን ዘመናት ዘንግተው ማለት ነው(ጌታም ሲወለድ በሄሮደስ አካባቢ የነበሩ የአይሁድ አስተማሪዎች የጌታን ዘመን አስተውለው ለንጉሱ ሊገልጡ አልቻሉም ነበር)፡፡ አህዛብም የአሁድን ፈለግ ይከተላሉ፣ ስለዚህ ስራውን ማስተዋል ዘንግተው ስፍራው ላይ ትኩረት ያደርጋሉ (በአለም ውስጥ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች ለማግኘት የሚደረግ አሰሳና የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ከፍተኛ ነው) የእግዚአብሄር ቃል ግን ስፍራውን ሳይሆን ስራውን አስብ ይላል፡፡ መስቀል ላይ ጌታ መቼና ምን ሰራ? የሚለው ይታሰብ ወይስ የማስታረቅ ስራ የተሰራበት መስቀል ምንነት ይታሰብ (መጠኑ አይነቱ እየተባለ ጊዜ መፍጀት ይሻላል?) የተቆረሰው ስጋውና የፈሰሰው ደሙ መታሰቢያ ሆኖ ስለ ህይወት ሲባል ይነሳ ወይስ አመት-በአል ይሁን? በደብረ-ዘይት ተራራ አመታዊ በአል ይከበር ወይስ በዚያ ተራራ ላይ እግሮቹ ሊቆሙ ያለው ጌታ ይታሰብ? ጥያቄዎቹ ጥብቅ መልስ የሚሹ ናቸው፡፡