ምንስ ልስማ?[3…]

ቤተክርስቲያን

ብዙ የሚሰሙ ድምጾች በተለያየ አይነት መንገድ ከተለያየ ምንጭ ፈልቀው ወደ እኛ ይደርሳሉ፡፡ ቢሆንም ከሁሎቹም ድምጾች በተለየ የእግዚአብሄርን ድምጽ ቦታና ትኩረት ልንሰጥ የሚገባው ነው፡፡ ለዚህ ውሳኔ ዋናው ምክኒያት የሚሆነው የድምጹ ባህሪ ከሌሎቹ የተለየ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ድምጽ ከሌሎች ድምጾች የሚለይበት ዋና ባህሪያት አሉ፡-

  • የእግዚአብሄር ድምጽ ማንኛውንም ድምጽ ይልቃል፣ ይሽራል፣ ያነሳል ያጠፋልም፤ ምክኒያቱም ድምጹ የፈጣሪ ድምጽ በመሆኑ፡፡
  • ድምጹ ህይወት ይሰጣል፡፡
  • ድምጹ ፍጥረትን በሙሉ ፈጥሮአል፡፡
  • ድምጹ ህያው ነው፡፡
  • ድምጹ ከእግዚአብሄር አፍ ይወጣል፡፡
  • ማንም የእግዚአብሄርን ድምጽ ሊያቆም አይችልም፡፡
  • ድምጹ አንዴ ከእግዚአብሄር አፍ ከወጣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸገረ ይሰራል፡፡
  • ድምጹ አይቀየርም፣ ምክኒያቱም ሁለት አፍ የለውምና የተናገረው ሁሌም ትክክለኛ ነው፡፡

”የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ። እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል። በስተ ኋላው ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም። እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።” (ኢዮ.37:2-5)

  • ምን ልስማ?

ይህ ጥያቄ መሰማት ያለበትን ድምጽ ምርጫ ውስጥ የከተተ ጥያቄ ነው፡፡ ቃሉ በ​​​​​​​ማቴ.4:22-25 … ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ ስላለ፡፡ ያላስተዋልክበት ዘመን ሲቆጣጠርህ ትባክናለህ፣ ማስተዋልህ ሲመለስ ግን በዙሪያህ ከሚሰሙት ድምጾች ይልቅ አትኩሮትህን ወደ ቃሌ ታደርጋለህ ይላል እግዚአብሄር፡-
ዘዳ.4:29-35 ”ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ። ይህም ሁሉ በደረሰብህ ጊዜ፥ ስትጨንቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ።አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም።እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ።አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን?አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን?እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም።”
ወደ እግዘአብሄር  በተመለስን ጊዜ ሁሉ ማንን ልስማ የሚለው የውስጣችን ጥያቄ መልስ ያገኛል፡፡ ማመንታት ባለበት ስፍራ ውሳኔን የሚገለባብጥ  ድምጽ ከዚህም ከዚያም ብቅ ይላል፡፡ ድምጽ የምሪት አቅጣጫን የሚያመለክት የህይወት ኮምፓስ ነው፡፡ አማኞች ባካኞች የምንሆነው ይሄን ኮምፓስ ስንጥል ወይም ስንዘነጋ ነው፡፡  እግዚአብሔርን መሻት ከሆነና በልብም ሁሉ በነፍስም ሁሉ መፈለግ ከሆነ እንደፈለጉት እርሱ ይገኛል። ”… ስትጨንቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ።” በማለቱ፡፡ በእርግጥም ከዘህ ሌላ የተሸለ አማራጭ የለም፡፡
​​​​​​​​ኢሳ.45:21 ”ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም።”
እግዚአብሄርን ለመስማት ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ አያስፈልግም፡፡ ወደ ቃሉ ድምጽ ዞር ካልን እግዚአብሄር በትክክል ይናገራል፡- የልባችንን ይናገራል፣ የጎደለነን ይናገራል፣ መጣልም ይሁን ማንሳት ያለብንን ይነግረናል፣ ለምሪት ይናገራል፣ ብቻ የቃሉን መጽሀፍ ቸል ሳንል እናንሳ ከርሱ ጋርም እናጣበቅ፣ እንዲህ ይላልና፡-
​​​​​​​​መዝ.87:4-7 ”የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ።ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል።በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።”
​​​​​​​​ኢሳ.34:16 ”በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፥ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም።”

  • ማንን ልስማ?

የሚናገር ካለ ሰሚዎች ይገኛሉ፡፡ እኛ ግን ከተናጋሪዎች መሀል ልንሰማቸው የተፈቀደልን የህይወትን ቃል የሚያቀርቡትን ብቻ ስለሆነ እነርሱን መስማት ይገባናል፡፡
​​​​​​​​ዮሐ.5:25 ”እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።”
​​​​​​​​1ዮሐ.4:5-6 ”እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል።እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።”
ትክክለኛ ሰሚ ለህይወቱ የሚበጀውን እንዲሰማ ቃሉ ያስጠነቅቃል፡፡ አሳቾች በበዙበት የግርግር አለም የተጣራውንና ህይወት የሚሰጠውን ቃል ከአምላክ ባሪያዎችና ወኪሎች መስማት አማራጭ የሌለው ውሳኔ ነው፡፡

  • እንዴት ልስማ ?

በአመቺ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ህያው ቃሉን ልስማ፤ ልቤ በተዘጋጀበትና ማስተዋል ባለበት የአሰማም ሁኔታ ላይ ካለሁ በምሰማው ቃል እንደምባረከ እርግጥ ነው፡፡ ይሄ ውሳኔ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ቃሉ አትኩሮትም ይፈልጋል፤ ለዚያ ጥሞና ወሳኝነት አለው፡፡ ቃሉ በመንፈስ ሆነው ሊሰሙት የሚገባ የህያው አምላክ ቃል ነው፡፡ ቃሉ በፍቅርና በተዘጋጀ ልብ የሚሰማ ነው፤ እንዲሁም ለመለወጥ በፈቀደ ልብ መሰማት ይገባዋል፡፡ ጌታ ምን ይናገረኛል በሚል አቀራረብና ለውጠኝ በሚል የናፈቀ ልብ ልሰማውም የሚገባ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአሰማማችን ሁኔታ እንደዚህ ሲሆን ለውጣችን ይፋጠናል፡፡
​​​​​​​​ሉቃ8:18 ”እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
አሰማም የማስተዋል አቅምን በመወሰን በኩል ሚና አለው፡፡ እግዚአብሄር እስራኤላውያን ባልተስተካከለ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሰሙትን አሰማም ነቅፎታል፡፡ልባም ሰሚዎች ግን ይህንን ቸል አይሉም፡-

  • ጆሮዬ ላይ ማጣሪያ ኖሮ (በመንፈስ መለየት ችሎታ እንዲኖረኝ ያስፈልጋልና በዚያ አቁዋም ሆኜ) ልስማ ይላሉ፡፡
  • ቃሉ እንዲባርከኝ፣ እግዚአብሄር እንዲራራልኝና ቁጣውን እንዲመልስ በተሰበረ ልብ ቃሉን ልሰማ ይገባል ይላሉ፡፡

​​​​​​​​ሐጌ.1:12-13 ”የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን እግዚአብሔርን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል፥ አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ላከው ሁሉ ሰሙ፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ። የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን፡- እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ።”
… ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ ሁሉ ሰሙ፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ… እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር የሚለው የማጽናናት ቃልም መጣ፡፡
ከዚህ በተለየ መንገድ ያሉ አሰማሙን ስለማያውቁበት ቃሉ ሲመጣ ይሸሻሉ፤ አዳምና ሄዋን በሀጢያት ተጨንቀው ሳሉ ቅዱሱን ቃል ሰሙና ፈርተው ሸሹ፡፡
ዘፍ.3:8 ”እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።”
በጽድቅ በእግዚአብሄር ፊት የሚያገለግል ትንሽዬው ሳሙኤል ግን ወደ ሰማው ድምጽ አቅጣጫ አዘነበለ፣ የሚፈለገውን የህያው አምላክ ድምጽ ሰምቶ ነበርና፡-
”ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም፡- እነሆኝ አለ።” (1ሳሙ.3:3-4)

  • ከየት ልስማ ?

የምንሰማው ቃል ከአስተማማኝ ምንጭ ቢሆን አንሰጋም፡፡ ብዙ የድምጽ ምንጮች ቢኖሩም እንደ እግዚአብሄር ቃል ግን አስተማማኝ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የቀሩት ሁሉም የየራሳቸውን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ለእኛ አስተማማኝ ድምጽ የሚሰጠን ቃሉ ነው፡፡ ሀዋርያው ጳውሎስ በ​​​​​​​​2ጢሞ.3:14-17 ሲናገር፡-
”አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” ብሎአል፡፡

  • ማንን አልስማ/ ከመስማት ልጠንቀቅ?

እንደውሻ የበሉትን መልካም ምግብ አበላሽተው የሚተፉ (አስመልሰው /የተመገቡትን ቃል ከልባቸው አውጥተው የሚያረክሱ) ስላሉ እነዚህን ፈጽመን አንስማ! ሰራተኞች ቢሆኑም ክፉዎች የሆኑትን /ቀማኞች የሆኑትን አንስማ፣ አመካኝተውና አባብለው የሚዘርፉትን  አንስማ፤ ልዩ ወንጌልን አንስማ፤ ፍልስፍናን አንስማ፣ አሳቾችን/ሀሰተኛ ክርስቶሶችን አንስማ፡፡ እነዚህ ሁሉ የተመሰረትንበትን ወንጌል የሚነቀንቁ ክፉዎች ናቸውና ከመስማት ልንጠነቀቃቸው ይገባል፡፡
​​​​​​​​ፊል3:2 ”ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።”
​​​​​​​​ቆላ.2:8-12 ”… እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ…”
ማቴ.​​​​​24:4-8 ”ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፡- እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።”

  • እግዚአብሄር በሞገስ ሲቀበል ልመናችን ይሰማል፡፡

አስደሳቹ የምስራች ይሄ  ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚሰማኝ ከማወቅ ሌላ ምን ደስታ አለ? ጩሀቴን ካደመጠ አንደሚረዳኝ አውቃለሁ፣
ያ ለእኔ ትልቅ በረከት ነው፡፡
መዝ.20:1-6 ”በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ። ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ያጥናህ። ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ። እንደ ልብህ ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ። በማዳንህ ደስ ይለናል፤ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፤ ልመናህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ። እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፤ በቀኙ ብርታት ማዳን።”