መጨረሻው ዘመን (3…)

ያለነው በመጨረሻው ዘመን ላይ ሲሆን በምንኖርበት በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚያሳስብ፣ የሚያስጨንቅ ደግሞ የሚያጸልይና ነቅተን እንዳይወርሰን ልንጠባበቀው የሚገባ በዚህ ጊዜም አለምን ተቆጣጥሮ ያለ የሚያስፈራ የአመጽ ብዛት አለ፦
በዚህ ዘመን በአይናችን እየሆኑ ከምናያቸው ጌታ ከሰጣቸው የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች መሃል የአመጽ መብዛት አንዱ አስፈሪ ድርጊት ነው። እግዚአብሄር ግን ለሰው ልጆች አስቀድሞ ያስቀመጠውን ትእዛዝ አልረሳም፦
ዘዳ.30:13-16 ’’ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም። ነገር ግን ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው። ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ። በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።’’
ይህ ቃል የሚጠበቅ እንጂ ቸል የሚባል ከቶ አልነበረም፣ የሰው ልጅ ግን በዚህ በመጨረሻ ዘመን የሚሰማው አልሆነም።
ነገሮች እየከፉ ሄደው ክፋት አለምን ሲቆጣጠር ከሰው ሰው ባልተለየ ሁኔታ፣ የተሻለ ማህበረሰብ እስከማይገኝ፣ አንድ ሃገር ከሌላው የተሻለ ነገር በሌለውም ደረጃ የአመጽ መብዛት እንደሰደድ እሳት ሁሉን እየበላ ይገኛል፦ የተወው የለም፤ የግለሰብን፣ የቤተሰብን፣ የማህበረሰብን፣ የሃገርን ብሎም የአለምን ህዝብ በእጅጉ እያስጨነቀ ነው፣ ልምምዱም ጥፋትን፣ ቅጣትን፣ መርገምንና የዘላለም ሞትን ከመሳብ ለሰከንድ ቸል አላለም፣ አላቆመም። በዚህ ምክኒያት በሃጢያትና በአመጽ ተይዞ በዘላለም ሞት ፍርድ ውስጥ እየገባ ያለው የአለም ህዝብ እጅግ ብዙ ነው። የሚከተሉትን ልምምዶች ብናይ እያልን ያለውን የሚያጠናክሩ ናቸው፦
-በአሁን ጊዜ ማህበረሰቡ ባህል አድርጎ የተቀበለውን በጎ ልማድ እንዲሁም የተቀበለውን የብዙ ትውልዶች መልካምና መሰረታዊ የሆነ የግንኙነት መስመር በብርቱ መጣስ እንዲሁም ከመሰረቱ ማዛባት በብዛት ይታያል፣ ለምሳሌ መከባበር እየጠፋ ታናሽ ታላቅን አይፈራም አያከብርም፤ ልጅ ቤተሰቡን አያከብርም ቦታ አይሰጥም፣ ጨዋነት መለኪያ በነበረበት ማህበረሰብ ውስጥ ዛሬ ላይ ጥፋት የድፍረት መለኪያ ነው(ሌብነት የስራ፣ እርኩሰት የዘመናዊነት፣ ነፍስ ማጥፋት የጀግንነት ምልክቶች በሆኑበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ ባለፈ እግዚአብሄር የከለከላቸውን እነዚህ ክፉ ድርጊቶች ሃይማኖተኞች ሳይቀሩ ሲያዘወትሩት ማየት ያስፈራል)፣ ታላላቆች ለታናናሾች የሚያሳዩት በጎ ነገር ስለጠፋ ትውልዱ ከእድሜው በላይ በሆኑ ክፋቶች ተሞልቶአል፣ አልፎም መመለስ በሚያዳግት አመጽና ክፋት ውስጥም ገብቶአል። በቃሉ አንጻር ሲታይ ይህ ክፉ ልማድ የሰው ልጅን ወደ እርግማን የሚስብ የጥፋት አሰራር ነው።
-እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ያስቀመጠውን የህይወት መንገድ መጣስ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ደጋግሞ በየእለቱ የሚዘወተር ድርጊት ነው፤ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በምርጫ ቢሆንም በህይወት ይኖር ዘንድ እንዲመርጥ ያስቀመጠለትን በጎ ምርጫ እንዳይመርጥ ሞራልን በሚያደቅና ድፍረትን ፍጹም በሚሰልብ በተጽእኖ ውስጥ ስላለ ከአመጽ መመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶአል። ህሊናውን እንዳይከተልና በጎ የሆኑ ነገሮችን ፈለግ እንዳያይ ከበላዩ ያሉት ታላላቆች ወደ መልካም መንገድ የሚሄድበትን ሊያሳዩት አልቻሉም፣ መልካም ምሳሌ አልተዉለትምም።
-መንግስታት ዜጎቻቸውን ከክፉ መንገድ ሊጠብቁ አልቻሉም (በተለይ በምእራብ አገራት ክፉ ልማድ አሻቅቦ መጥፎ ደረጃ ላይ በመድረሱ የመርገም መከማቻ ሆኖአል)። አስቀድሞ የእግዚአብሄርን ቃል በህጋቸው ውስጥ ያካተቱ የነበሩ ብዙ የአለም መንግስታት ያን እያወጡ የሰይጣን ምክር ያለበትን አዲስ ህግ በማከልና ያን በማለማመድ ትውልድ እግዚአብሄርን እንዳይፈራ አድርገዋል።
-በእግዚአብሄር ቃል ላይ ግልጽ አመጽ ማወጅ፦
የጋብቻ ፈጣሪ እግዚአብሄር ራሱ ነው፤ እግዚአብሄር አዳምና ሄዋንን ፈጥሮ ባልና ሚስት አደረጋቸው፣ በፍቅር፣ በህብረት፣ በመተሳሰብ እንዲኖሩ የቤተሰብ ህግጋት የሰጠውና የትውልድን ቀጣይነት በጸና መሰረት ላይ ያስቀመጠው በጋብቻ በኩል ነበረ፤ በዚህ በመጨረሻ ዘመን ያለው ጋብቻ ግን በዚህ እውነት ላይ ተነስቶና አንድ ወንድ ለአንድ ሴት የሚለውን የአምላክ ህግ ጥሶ ወንድና ወንድ እንዲጋባ ተፈቅዶአል፣ አንድ ወንድ ብዙ ሚስቶችን፣ አንድ ሴትም ብዙ ባሎችን (በተለይ ኤስያ ውስጥ) ያገባሉ፣ ሴትና ሴት ይጋቡ ዘንድ ግልጽ ፈቃድ አግኝተዋል።
ቃሉን በመተላለፍ እግዚአብሄርን እየበደሉ የሰውን ስነ-ልቦና አረከሱ፤ በጋብቻ (ጋብቻን በማርከስ፣በማቃለልም)፣ በጾታ (የጾታ ቅየራን በማከናወን)፣ በአምልኮ (ልዩ አምልኮ በመፍጠር፣ የአንድ አምላክ አምልኮን ማስቀረት፣ የአምልኮ ስራትን መቀየር)፣ እግዚአብሄርን መቃወም አበዙ፤ የትዳር ህግ ላላ፣ ረከሰ፣ ብዙዎች በቀላሉ ወደ ማፍረስ ውስጥ ገቡ( ይህም የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እየገባ ያለ ችግር ሆነ)፤ ተጋቢዎች ለመለያየት ህጋዊ መሰረት ስላገኙ፣ የተፈጥሮ ጾታን ስለተቃወሙ፣ ወንድ ሴት ሊሆን መብቴ ነው እያለ ስለደፈረ፣ ሴትም እንዲሁ ስለተናገረች፣ ለዚህ ሁሉ አመጽ የህግ ሽፋን በመስጠት መንግስታት አመጽን ስላባባሱ መቅሰፍት በደጅ ላይ ቀርቦ ይገኛል።
በዚህ በመጨረሻው ቀን ውስጥ የወንድና የሴት የአገልግሎት ስፍራ እንደቃሉ እንዳይሆን አመጸኞች ብርቱ ክንድ እያሳረፉ ይገኛሉ፣ ልብወለድ እምነት መብዛት( መጽሃፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶች ያለፍርሃት መስፋፋት)፣ ከአንድ የጌታ ሃይማኖት ብዙ ሰው ሰራሽ ሃይማኖቶች መፈልፈል፣ ከአንዱ የአብረሃም አምላክ በፈላስፎች ወደ ተፈጠሩ ብዙ አማልክት-ነክ እውቀት መሻገር፣ ቃሉን ማቃለል፣ ምንም አይመጣም ብሎ መሳለቅ፣ አስፈሪ የማህበረሰብ ልምምዶችን እንደዝና መያዝና ማሰራጨት (ግብረሰዶማውያን መብት፣ የሌዝቢያን መብት፣ የትራንስጄንደር (ጾታ ቅየራ) መብት እየተባለ አመጽን ህጋዊ ማድረግ)፣ ሌብነትን ማደፋፈር፣ ግልሙትናን ማበረታታት (በስመ-ፋሽን ዲዛይን ይታፈሩ የነበሩ ልምምዶችን በገሃድ በአደባባይ እየተገበሩ ማህበረሰቡ እንዲደፍራቸው ማድረግ፣ የዝሙት ስእሎች፣ ፎቶዎች፣ መጽሃፍቶችና ፊልሞች በአደባባይ ወጥተው ለህዝብ የሚሰራጩበት ዘመን ነው)
-በተፈጥሮ ላይ ማመጽ፦
‘’አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።’’ (ዘፍ.3:17-19)
አመጽ በሞላው ልብና በተበላሸ አመለካከት እንዲሁም ባፈነገጠ ምግባር ምክኒያት ሰው ራሱን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን በየጊዜው እየጎዳ ይገኛል፤ አየር ሲበከል፣ ባህር ሲቆሽሽ፣ ዝናብ ርቆ ድርቅ ሲበዛ፣ ጫካ ሲመነጠር ለሰው ተስማሚ ውሃ እየጠፋ ከባቢው ከሰው ጋር የተጣላ እስኪሆን ድረስ በጥፋቱ ሁሉ አስተዋጾ እያደረገ ያለው ሰው ራሱ ነው፤ አስቀድሞስ ሰው በሰራው ሃጢያት ራሱን ምድርንም አስረግሞ የለምን? እርግማን የጥፋት ሃይል ነውና፣ ማንም ሊያቆመውም አይችልም፤ በሰው ውሳኔ መልካሚቱ ምድር ተዋጊ ሆነች፣ ለክፋታችን መልስ እንዲሆን እርሱዋም ከፋችብን።
በመጨረሻው ዘመን እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ደግሞ የክፋት አሳተሳሰብና ድርጊት ይበልጥ የሚገለጥበት አካሄድ ያለው በመሆኑ ምድር ላይ እርግማንን እንዲስፋፋና እንዲከፋ አድርጎአል። ሰው እግዚአብሄርን ካልፈራ አንዱ ስለሌላው ስፍራ አይኖረውም፣ ስለተፈጥሮ ስፍራ አይኖረውም፣ እግዚአብሄር በጥንቃቄ እንዲጠቀምበት የሰጠውን በረከት ዋጋ አይሰጠውም፤ መልካምነት ቢባል፣ በጎነት፣ ትውልድ መቅረጽ፣ ነገን ማሰብ፣ በጎ ነገር ማስቀመጥ እነዚህ ፍጹም ሊታሰቡ አልተቻለም። ከእግዚአብሄር አሳብ ጋር ተጣልቶ በምድር ላይ እረፍት ያለው ኑሮ፣ የተረጋጋ ውሳኔ ከበጎ አሳብ የሚነሳ የሰው ለሰው ግንኙነት የለምና፣ ስለዚህ በዚህ የአእምሮ ደረጃ ላይ የሰው ልጅ ደርሶ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሊከተል እንደሚያዳግተው ማስተዋል ይገባል።
-የምድር ብክለት፦
በተፈጥሮ ህይወት ብቻ የሚታወቅ ስፍራ ላይ የሰው እንቅስቃሴ ሲመጣ ጸጥና ረጭ ብሎ ይኖር የነበረ አካባቢ መበላሸትና መበከል ይጀምራል፤ በዚህ ዘመን ራሱን በሚወድ የሰው ዘር ምክኒያት የማይበላሽ ነገር ምን አለ? ነገን አስቦና ተመልክቶ ስለማይሰራ፣ ለራሱ ትርፉን ዛሬ ይሰብስብ እንጂ ምን አገባኝ በሚል ስሜት መጥፋት የሌለበትን የተፈጥሮ ስጦታ ለምሳሌ የውሃ አካልን በመበከል በቀላሉ የማይሽር የጥፋት ጠባሳ እያኖረ ይገኛል (ባህርና ውቅያኖሶች ሰዎች በፈጥሩት ቆሻሻ፣ የኑክሊየር ዝቃጭ በመሳሰለ እጅግ በካይና ገዳይ ቆሻሻ ከሃብታም አገር በድብቅ ወደ ደሃ አገሮች የባህር ጠረፍ እየተጋዘና እየተቀበረ አካባቢን እየበከለ ይገኛል)፤ እነዚህን የመሳሰሉ ክፋቶች በዚህ የመጨረሻው ዘመን እየከፉ በመሄድ ላይ የሚገኙ ናቸው።
-በቴክኖሎጂ ጥፋት መፈጸም፦
ቴክኖሎጂ የሰውን ውጣ ውረድና ልፋት በማቃለል ታላቅ ስራ እየሰራ ይገኛል፤ እግዚአብሄር በሰጠው እውቀት ሰው በስልጣኔ ከፍ እያለ ከመቼውም ይልቅ ደግሞ በዚህ ዘመን ብዙ የግኝት ትንግርቶች እያሳየን ይገኛል፤ ቴክኖሎጂ ለየትኛውም አይነት አገልግሎት መዋል ስለሚችል ከታለመለት አላማ ወጥቶ ወደ ጥፋት ሲዞር እያየን ነው፤ ከታለመላቸው ተግባር ውጪ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ያሉ የፈጠራ ውጤቶች መልሶ የሰውን ልጅ እያስጨነቁ አሉ፤ በተለይ ትልቅ እፎይታ ፈጠሩ ተብለው የሚወደሱ ግኝቶች በአጥፊዎች በኩል ለሰው ልጅ የጥፋት ስጋት ሲሆኑና ፍጥረትን ሲያሳዝኑ ውለው ያድራሉ።
ለምሳሌ ሞባይል ስልክ ያልተወደሰውን ያህል በርሱ በኩል የሚቀባበሉ የኢንተርኔት መልእክቶች (ስእል፣ ፊልም፣ ጽሁፍ የመሳሰሉት) እርኩሰትን እንደበሽታ ከአንዱ የአለም ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በጥቂት ደቂቃዎች እያስተላለፉ ትውልዱን እያረከሱ ነው፤ ልጆች በስልክ ሱስ እጅግ ተጠምደው ስናይ ልንሰጋ ይገባል።
-ጦርነት መፍጠር፦
ጦርነትን ስራዬ ብሎ መፍጠር፣ ከጦርነት ማትረፍ (የደም ገንዘብ መሰብሰብ)፣ ህዝብ እየፈጁ ሃብት ማጋበስ፣ ሽብር መፍጠር፣ ድሃ ሃገሮችን እርስ በርስ ማጣላት ሰለጠንን የሚሉ ሃገሮች የሚሰሩት የእለት ተእለት ተግባር ነው፤ አፍሪካውያን ተቧድነው ሲዋጉ ለሁለቱም እኩል መሳርያ በማቅረብ የሚታወቁ ሃገራት (በተለይ አውሮፓና አሜሪካ) ያለምንም ሃፍረት ስለስራቸው ትክክልነት በየእለቱ የሚናገሩት ጉዳይ ነው፤ በግለሰብ ደረጃ እንደ ብስኩትና መድሃኒት ጦር መሳርያ የሚፈበርኩ በተለይ የአሜሪካ ባለሃብቶች በየቀኑ በገፍ የሚያመርቱትን ገዳይ መሳርያ ለማን ይሽጡት? በማንስ ይሞክሩት? በአለም ዙርያ በነርሱ አመጽ ምክኒያት የሚፈሠው የሰው ልጅ ደም ምንም አይመስላቸውም፤ የሚሰሩት አመጽ አይሰማቸውም፣ አይቆረቁራቸውም፣ ንሰሃ አያውቁምና፤ ይህን የሚያደርጉ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን በተለይ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ነን የሚሉ ናቸው። የልባቸው መደንደን፣ የህሊናቸው መቃጠልም በየእለቱ ነፍስ እንዲጠፋ የሰው ልጅ ከጦርነት እንዳይወጣ አድርጎአል፤ ጦርነት ከነርሱ ቀጠና ውጪ ሆኖ እንዲቀጣጠል ዘወትር ያራግባሉ፤ በነርሱ ፊት ፈራጅ አምላክ ስለሌለ (ስለማያውቁትም) በግለኝነት ምኞት ብዛትና በራስ ወዳድነት ተቃጥለው የሰውን ልጅ በጥይት አረር ይፈጁታል፤ በዚህ ዘመን አገሮች እርስ በርስ ሰላም የላቸውም፣ አገሮች ህዝባቸውን በሰላም ለማኖር ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው (በተለይ ከመሳርያ ሻጭቹ አገራት ውጪ ያሉቱ)፤ በተለይ በደሃ አገራት ላይ ጫናው ቁጥር ስፍር የለውም::
ከላይ ባየናቸውና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ምክኒያት የአለም ሰላም ፈጽሞ ሊመጣ አይችልም የሚል የብዙዎች እምነት መነሻ አብዛኛው የአለም ክፍል የተያዘበትን ይህ ሁኔታ በማጤን ይመስላል፤ በእርግጥ ሰዎች በራሳቸው ምኞትና ግለኝነት (ራስ ወዳድነት) ተጠምደው ስለሚኖሩ፣ የራሳቸውን ፍላጎትም በሌላው ውድቀት ላይ ለማሳካት ስለሚጣደፉ የሰላም እጦት እየከፋ ነው፤ ማናችንም ብንሆን ካለፈው ስህተት ለመማር መሞከር አይታየንም፤ ሁላችንም በንሰሃ አናይም፣ ራሳችንን አናይም፤ ይልቅ ሌላውን ብቻ፤ ስለዚህ ስህተት በስህተት ላይ እየተጨመረ ጉድፋችንም እየበዛ ወደ ጥፋት እየተነዳን ነው፤ ሰላም በሰዎች መሃከል የሚመጣው የሚከፈል መስዋእትነት ለእያንዳንዱ ግለሰብ ያለመድሎና ያለመሰሰት በሃላፊነት ሲከፋፈል ሆኖ ሳለ ይህ በየትኛውም የአለም ክፍል ሲተገበር አይታይም።
-የእርቅ መታጣት፦
ሰላም ፍቅር ትሻለች፣ ርህራሄ የሚሸነፍ ልብ እንዲኖር ጭምር፤ ይህ በሌለበት አጋጣሚ ውስጥ ስርአት፣ መተማመን፣ መግባባት፣ ርህራሄ፣ ትህትናና የመሳሰለው ከየትም አይመጣም፤ በግለሰቦች የታጣ መልካምነት ከማህበረሰብ ብሎም ከሃገር ፈጽሞ ሊገኝ አይችልም፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ አገራት በአንድነት ተያይዘው አለምን ወደ ቁልቁለት እየነዷት ይገኛሉ።
ያለመመለስ ወደ ክፉ ጥፋት እያንደረደረን ነው፤ ወደኋላ አለማየት የፊቱን ገምተን እንዳንጓዝ እያደረገን ነው። እግዚአብሄርን ያለመፍራት እርሱን ያለመጠባበቅ እየፈጠረ ነው፤ እንዲህ ያሉ ሰዎች መብዛት የመፍትሄ እጦትን አባባሰው፣ ክፋትን ከፍ ከፍ አደረገው። እውነቱ ግን ሰዎች በሰላም ለመኖር ካሻቸው ከበላያቸው የሚልቅና የሚገዛ አካል ሊኖር ተቀብለውትም በስምም ሊኖሩ ይገባል፤ በመሃከላቸው የሚገባ የበላይ፣ አባት ሆኖ የሚቆጣጠር ልኡል እጅግ አስፈላጊ ነው። በሰዎች አለመግባባት መሃል ጣልቃ እየገባ የሰላምና የተግባቦት ህግ የሚሆን ፈራጅ፣ ዳኛና ንጉስ ለተጠቂዎች ዋስትና የሚሰጣቸው አስተማማኝ መጠጊያ በዚህ ዘመን በተለይ እጅግ ይፈለጋል፤ ነገር ግን ያ የበላይ አካል (ዋና) ኢየሱስ ካልሆነ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል? የሰላም አለቃ እርሱ አይደል? (ወደርሱ ከተጠጉት ውጪ አንዳቸውም ሰላም አላገኙም)፤ እረፍት ለሚፈልግ እውነተኛ እረፍት እርሱ ነው፤ ለአለም አስፈላጊ የሆነው እውነተኛ ፍቅር የሚፈልገው ካለ ይሀው እርሱ። በእያንዳንዱ የሰው ዘር መሃል ብቻ ሳይሆን በግል በያንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ ገብቶ አእምሮን የሚያስተካክል አሳብን መለወጥ የሚችል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የጋለውን የሚያበርድ፣ የሞተውን ህይወት የሚሰጥ የደቀቀውን የሚያበጃጅ፣ መፍትሄ ያጣውን ነገር ሁሉ ከነሙሉ መፍትሄው ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ሊያተካክል የሚችለው ጌታ ኢየሱስ ነው።