የመጨረሻ ዘመን፡- የነገሮች ፍጻሚያ የሚመጣበት ዘመን፣ የእግዚአብሄር እቅድ የማጠናቀቂያ ዘመን፣ የእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ መገለጫ ጅማሬ/ ዋዜማ፣ የአለም መጨረሻ፣ እግዚአብሄር በዚህ አለም የከፈተውን ፕሮግራም ማጠናቀቂያ፣ የጻድቃን አገር መገለጫ ዋዜማ፣ የዘላለም ጠላት ዲያቢሎስና አጋንንት በዘላለም ቅጣት የሚቀጡበት ፍርድ መባቻ ነው።
የአለም ፍጻሜ ምልክት የሚገለጠው፦ የፍጥረቶች ማብቂያ ዘመን መድረሱን ለማሳየት፣ የእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ መጀመሪያው ጊዜው እንደደረሰ ለምሳየት፣ እግዚአብሄር ለተለያየ ትውልድ የተናገረውን በሙሉ እንደሚፈጽመው ለማሳየት፣ ተስፋው ፍጻሜ ላይ መድረሱን ለመግለጥ፣ ታምነው ለጠበቁት እንደተናገረው እንደሚያደርግ ለማሳየት… ነው።
በነዚህ ታላላቅ ክስተቶች ምክኒያት የሰው ልጆች በተለይ አማኞች ንቁ፣ ጠንቃቃ እንዲሁም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ፈጠረን አምላክ የሚጠጉበት አጋጣሚ እንዲኖራቸውና ማነሳሻ አቅም እንዲያገኙ የተሰጣቸው እውቀት ነው፤ ያኔ ጊዜያቸውን የዋጁ እንዲሆኑ ማንቂያ ያገኛሉ፤ አማኞች ንቁ ሊሆኑ ይገባል እንጂ የያዙትን ውድ ሃይማኖት በድካም እንዲለቁ ያመለኩት ጌታ ፈቃድ አይደለም፤ የጀመሩትን መልካም ተጋድሎ የሚያቋርጡበት ወይም ተስፋውን የሚያዳፍኑበት ዘመን ከቶ እንዳልሆነ እንዲረዱም ጭምር የተሰጣቸው ነው።
ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ በስጋ ኑሮ ላይ ብቻ እንዳናተኩር እንዲሁም የኛ በምንለው ነገር ተይዘን በአለም እንዳንዋጥ ቃሉ ያነቃቃል፤ ምክኒያቱም ካልተጠነቀቅን የስጋ ባህሪይ ከአላማችን ውጪ በሚያደርግ አካሄድ ውስጥ ሊያሰምጠን ስለሚችል ነው፤ ባህሪያችን የማይጠፋና ተፈጥሯዊ ነው፣ ነገር ግን በእግዚአብሄር ሃይል የሚገዛ ነው፤ በመንፈሳዊነት የበረታ አማኝ ደግሞ የሚያሸንፍ አማኝ ስለሆነ እምነቱ የጠለቀ ነውና የማይጠፋ ርስት ላይ የተስፋ መልህቁን ጥሎ በመንፈስ የታገዘ ህይወት የሚኖር ነው።
በ1ጢሞ.4:1-2 ውስጥ የተቀመጠው ማሳሰቢያ የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት የተከተሉ፣ ሃይማኖትን የሚዋጉና እውነተኞችን የሚያስቱ እንዳይወርሱን ቅድመ-ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው፤ በተበረዘ እውቀት የናወዙ ህሊናቸውን አሳልፈው የሰጡም ስተው ያስታሉ፣ ጠፍተው ያጠፋሉ፣ ታስረው ያስራሉ…። የአጋንንት ትምህርት ከመሰረቱ ሃሰት በመሆኑ የትምህርቱ አድማጮች ከርሱ በሚካፈሉት መንፈስ አማካይነት ለጥፋት አሰራር ይገለጣሉ። በመጨረሻው ዘመን የዚህ ትምህርት እድገት ሰዎችን ሃሳዊ መሲህ ደረጃ ያመጣቸዋል።
‘’እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፡- ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፡- እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።’’ (ማቴ.24:3-12)
እንጠንቀቅ ዘመኑንም እንዋጅ
ዘመኑን የሚዋጅ እምነት ካለንና ያን በህይወታችን የምንለማመድ ከሆነ በእግዚአብሄር መንፈስ አሰራር የዘመኑን ምልክት የሚያስተውል ልብ ይኖረናል፤ በጌታ ጥበብና ማስተዋል ይበልጥ ወደ እርሱ በመጠጋት ተስፋ እናደርገዋለን እንጂ የእንቅፋት ምክኒያት በህይወታችን አናኖርም ወይም ወደ ኋላ የሚገፋ ሸክምን አናስተናግድም፤ ዘመኑን የሚዋጅ ለአለም ትርፍ አይሮጥም፣ በአለምም ሩጫ አይጠለፍም፣ ምክኒያቱም እምነቱን በአምላኩ ስላደረገና በቃሉ ታምኖ ስለሚጠባበቅ።
‘’ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።’’ (ማቴ.24:42-44)
የመምጣቱ ነገር ምንም እርግጠኛ ቢሆን እንኳን የመምጫው ሰአት አይታወቅምና ምልክቶቹን እየተመለከትን በጥንቃቄ መውጣትና መግባት፣ ለርሱ እየተገዙ በመንፈስ መመላለስም ይጠበቃል። በጸጋው የሚያቆም አምላክ ልጆቹን እስከፍጻሜ እንዴት ማኖር እንዳለበት ያውቃል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ አማኝ ተዘግጅቶ እየኖረ፣ ከርሱ ጋር በህብረት በሚያኖር የህይወት ውስጥ ሊኖር ይገባል። የአለም መንፈስ በመጨረሻው ዘመን ከክህደት ባለፈ በመዘበት የሚመላለስ ማንነትን እስኪፈጥር ብርቱ የሆነ ነው፦
2ጴጥ.3:9-12 ‘’ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል’’
የመምጣቱ ነገር ምልክቶቹን ተከትሎ እንደመሆኑ እነዚህን እየተጠባበቅን ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ በመሆን በጌታ ሰላም እንድንገኝ በሃይሉ ችሎት መትጋትና እስከመጨረሻው መጽናት እንደሚገባ ቃሉ አበክሮ ይናገራል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣልና በአለም ደስታ እየሰከሩ መኖርን ፈጽሞ ማራቅና በመንፈስ በመመላለስ መትጋት እንደሚገባ ጌታ በቃሉ ሲያመለክት እንዲህ ይላል፦
‘’ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።’’ (ሉቃ21:33-36)
ከእያንዳንዱ የሚያስቀርና የሚያሰናክል ፈተና ለማምለጥ ትጋት ያልተለየው የህይወት ዘይቤ እንዲኖረን ይገባል፤ ከእያንዳንዱ የሃጢያት ወጥመድም መጠንቀቅና ወደ ፈተና የሚመራን አካሄድ በመቁረጥ በየእለቱ አካሄድን ከጌታ ጋር ማድረግ የግድ ነው። መንፈሳዊ ህይወትን በሚጋፋ አካሄድ ከመጠመድ የመራቅ መሻቱ በእርግጠኝነት ካለን ወደ ጌታ በሚያቀርብ መንፈሳዊ ልምምድ መታጠር ይገባናል፤ መንፈሳዊ አይኖቻችን ሊበሩ የጠላትን አሰራር ልናስተውል ጠላታችን የሚያኖረውን ወጥመድም ልንመለክት መንፈሳዊ እቃ ጦርን እንታጠቅ፤ ዘወትር በቃሉ ላይ እንታመን፤ በመንፈስ የምንመላለስበት ጸጋ ጌታ ይስጠን፤ ዘወትር በጽሎት እንትጋ። የሚጸልይ ለእግዚአብሄር የሚናገር ብቻ ሳይሆን ከአምላኩ ዘንድ ምሪት የሚመጣለት ነው። በጸሎት ህይወት ውስጥ የጌታ አጥር አለ፣ በአጥር ውስጥ ታምነን ስንኖር በዘመኑ ላይ እየተከናወነ የሚገኘውን አሰራር በመንፈሱ አለምም የሚገኘውን እንቅስቃሴ በቃሉ ብርሃን ማየት ይችላል። ከአምላኩ ጋር ያለ ወደ ጸጋው ዙፋን ዘወትር የቀረበ በአምላኩ ቸርነት እነዚህን ክፉ ዘመናት ተሻግሮ ወደ ጌታው መንግስት መግባትን የሚያገኝ ነው፤ ይህ ከጌታ የተቀበልነው ተስፋ ነው።
‘’ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።’’ (2ተሰ.1:5-10)
አማኝ እስከመጨረሻ የሚታገሰው በመታገሱ የሚቀበለው የሰማይ መንግስት ስላለ ነው፤ በአውሎ ነፋስ እንደምትንገላታ መርከብ፣ በብዙ ድካምም ከመስመጥ ተርፋ ወደ ወደብዋ እንደምትደርስ በዚያም ከፈተናዋ፣ ከስጋትዋ፣ ከጭንቀትዋም እንደምታርፍ በአለም ፈተና፣ በአጋንንት ቀስት በስጋ ሰልፍም ብዙ ቆስሎ ሳይወድቅ እየታገለ የጌታውን ቀን የሚጠብቅ አዲሱ ሰው (ዳግም ከእግዚአብሄር የተወለደ ሰው) በፍጻሜው ከጌታው የእረፍት መንግስትን ይቀበላል። ጌታ ኢየሱስ የሚረዳ ጸጋውን ለርሱ ይልካልና፤ እንዲሁም የእርሱ የጸጋ ጉልበት በአለም ላይ ከሚገለጠው መከራና ፈተና የላቀ በመሆኑ በዚያ ፈተና ውስጥ አሳልፎ ለመንግስቱ ማብቃት የሚችል ሃይል ስላለው ነው። በዚህ ታምነን ዛሬ እየሆነና ነገም ሊሆን ካለው ቁጣን ከሚቀሰቅስ የአመጽ አሰራር ለማምለጥ በሰው ልጅ ፊትም በድል ለመቆም ብርታት እንዲኖረን ጸጋውን እየለመንን ሁል ጊዜ ነቅተን መኖር ይገባናል።
በመጨረሻ ዘመን ከሚሆነው መከራ ሌላ በሰው ማንነት ላይ የሚፈጠር ኪሳራ የሚያይለው ሰውን ሰው የሚያሰኘው ፍቅር የሚባል የመንፈስ ጉልበት ስለሚቀዘቅዝና አንዱ በሌላው ላይ ጨቋኝ ስለሚሆን ነው፤ እንዲህ አይነቱ አምላኩን የማይፈራና የፈጠረውን የሚጠላ ነው (አምላኩ በውስጡ ያስቀመጠውን የህሊና ጉልበት ስለሚጥስ)፤ እንደዚህ አይነት አስፈሪ ጊዜ ውስጥ ራስ ወዳድነት እጅግ ይንሰራፋል፣ የሞራል ልእልናም ይቆረጥና የሰው ልጅ ውዱ ነገሩ የሆነውን የማስተዋል ልቦና ይነጠቃል። ሰው እግዚአብሄርን ሳይወድ እውነተኛ ፍቅር ለባልንጀራው መስጠት ከቶ አይችልም፤ በመጨረሻ ዘመን ደግሞ የእግዚአብሄር ፍቅር ከሰው መንፈስ ተሟጦ እየጠፋ ስላለ እርስ በርስ መዋደድ፣ ማለትም ባል ከሚስቱ፣ ልጆች ከወላጆች፣ ሰው ከዘመዱና ከጓደኛው፣ አንዱ ከሌላው ጎረቤቱ፣ በሩቅም በቅርብም ያለ የሰው ዘር እርስ በርሱ መዋደድ እያቃተው መጥቶአል። መዋደድ ከሌለ መከባበር የት አለ? መዋደድ ከሌለ ባልንጀራህን ውደድ የሚለው የአምላክ ትእዛዝ በማን ልብ አለ?
በማቴ. 24:12 ላይ ‘’ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።’’ ይላል። አዎ ቀኖቹ እየከፉ ሲሄዱ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ እየተጠጋ ይመጣል፤ ያን የሚያደርገው የሰው እምቢተኝነት፣ አልሰማም ባይነት፣ ልበ-ደንዳናነት፣ ደፋርነት፣ አውቃለሁ ባይነት፣ በአምላክ ላይ መታበይ፣ በድፍረት ቃሉን መካድ፣ ሃሰተኛ ነቢይነት፣ መንፈሳዊ አመንዝራነት፣ የመሳሰሉት ስፍራን ስለሚቆጣጠሩ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን እርግማን እየሳቡ ምድርን የቁም ቅዠት በማድረጋቸውም ነው፤ ወደ እግዚአብሄር ቅረቡ እርሱም ወደናንተ ይቀርባል የሚለውን የአምላክ ቃል ሳያስተውሉ ከርሱ እየራቁ በሄዱ መጠን የአምላክ ምህረት እየራቀ ቁጣ እየተጠጋ በመሄድ ላይ ነው። መራቅ ከማጥፋቱ አስቀድሞ በራስ ላይ ብዙ የችግር ሰንሰለት ይመዛል፦ ፈተና ይጋብዛል፣ በህሊና መመራትን ያስጥላል፣ ህይወትን ያከሳል፣ ደፋር ይደርጋል፣ ጭካኔ ያስተምራል፣ አለምን ያለማምዳል፣ ለሰይጣን አሳልፎ ይሰጣል፣ የእግዚአብሄርን መንገድ ይሰውራል፣ ለህጉ መቅሰፍት አሳልፎ ይሰጣል፣ ፍርድ ላይ ይጥላል፣ ለንሰሃ ጊዜ ያሳጣል አልፎም ለሞት ያስረክባል። ከመጨረሻው ዘመን የእምነት መንሸራተት ማምለጫው መንገድ ግን በዋጀን አምላክ ላይ መጣበቅ ብቻ ነው፤ አምላካችን ከፈተናችን በላይ ነው፣ ከዘመኑ ክፋት በላይ ነው፣ ከሚገጥመን ከሚሰማንም በላይ ነው፣ ስለዚህ በርሱ ላይ መታመን ብቻ እርሱ ወዳሰበልን ያደርሰናል።
ንጉስ ህዝቂያስን እናስብ፦በ2ነገ.18:5-8 ውስጥ ያለው ታሪክ እንደሚያሳየው ይህ ንጉስ በነገሰ ጊዜ ወደ እርምጃ ከመግባቱ አስቀድሞ አባቶቹ የሄዱበትን መንገድ ቆም ብሎ ተመለከተ፣ ገመገመውናም የዳዊትን መንገድ መረጠ፣ ዳዊት ከአምላኩ ጋር እንደሄደው ያለ አካሄድን መረጠ፣ በአባቱ አምላክ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል እስከማይኖር ወደ አምላኩ ተጠጋ፤ እንዲያውም አብልጦ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ። ለዚህ አካሄዱ ከአምላኩ ዘንድ አንድ ነገር ሆነለት፦እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆነ፥ እንዲሁም እግዚአብሄር ስራውን ስላከናወነለት የሚሄድበት መንገድ ተከናወነለት። ለእኛም ይህ የማይሆንበት ምክኒያት ከአምላካችን ዘንድ ፈጽሞ አይኖርም፤ የመጨረሻውን ዘመን ውጥንቅጥ በዚህ መንገድ ብቻ እንቋቁዋመዋለንና፦
‘’የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።’’(ዕብ.10:36-39)
