መንፈሳዊ ድካም(4…)

የመጨረሻ ዘመን

በመንፈስ ቅዱስ የተበረታታች ነፍስ ስታመሰግን እንዲህ አለች፦
‘’ሃሌ ሉያ።
ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤… የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ’’ (መዝ.107:1-6፣ 11-15)
የእግዚብሄር መንፈስ አይኖቻችንን ከፍቶ ያሳየናል፣ ታዲያ ሲያሳየን የእግዚአብሄርን አሰራር እንድናስተውል፣ የእጆቹ ስራዎች ድንቅነት እንዲያስመሰግኑን፣ በታላቅነቱ ግርምት ደግመን ደጋግመን እንድናወድስ የሚያስገድድ ነው።
ነገር ግን መንፈሱ የራቃቸው በባዶነት ተጠቅተዋልና የጌታቸው ምስጋና በውስጣቸው ይደክማል፤ በባዶነት ውስጥ እያነከሱ ያሉ እነዚህ ወገኖች የልኡል ምክርን ቸል ወደማለት ሲያዘነብሉ ከሃይል ወርደው በመንፈሳዊ ድካም ይያዛሉ፤ ድካሙ ነፍስን ያጠቃል፣ የአስተሳሰብና የእምነት አቅምን ያሳጣል፣ ህይወትንም ተቅበዝባዥ ያደርጋል። እንዲህ ሲሆንናችግሩ ቀጥሎ በህይወት ላይ መገለጡ ሲቀጥልትጋትን በማስተው መንፈሳዊነትን ጨርሶ ያፈዝዛል።
ኢዮ.6:14 ‘’ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛልለቀረበውስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።’’

የሚያደክም መንፈስ ብዙ መንፈሳዊ ነገሮችን ያስተዋል፦በጥቅሉ የተቀበልናቸውን ብዙ ስጦታዎች ያስጥላል፤ ተጽእኖው እየጨመረ ከሄደ እግዚአብሄር ገና ወደፊት እንድንቀበለው ያየልንን ሳይቀር ያሳውርብናል፣ ማስተዋላችን ይታወራል።
ያዕ.1:23-25‘’ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙንሕግተመልክቶየሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል።’’
ስንደክም ብዙ መልካም ነገሮችን ከማድረግ እንቆጠባለን፣ ምክኒያቱም የእግዚአብሄርን ነገር እንረሳለንና። ያም ብቻ አይደለም፣ በጎ ልማዶች ከውስጣችን ወጥተው ሊያልቁ ይችላሉ፤ ቀጥሎ ቀጥሎ ድርቀት እየጸና ሲሄድ የጸጋው ስጦታ ከእኛ እየለቀቀ ባዶ ልንደረግ እንችላለን፤ ያኔ የውድቀት አደጋ ውስጥ ነን ማለት ነው፣ ይህን ሂደት በእርግጥ ልንፈራው ተገቢ ነው።
በድካማችን ምክኒያት እየተገለጡ ከሚታዩ ችግሮች መሃል አንዳንዶቹን እንደሚከተለው ማየት እንችላለን፦
4.ከመጸለይ መድከም
በጸሎት የሚተጋ የአምላኩን በረከት ያውቀዋል፤ ልኡል አምላክ እግር ስር ወድቆ በዚህ መሃሪ አምላክ መጎብኘት ጸጋን ያጎናጽፋልና፤ ሃይል መቀበያው ስፍራ በዚያ ነውና መንፈሳዊ የሆነ ሁሉ ጸሎትን የለት ተእለት ተግባሩ በማድረግ በርሱ ይተጋል፤ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍን ምህረትና በረከት ይቀበልበታል።
መንፈሳዊ ድካም ሲያጠቃ ግን መጸለይ ሩቅና ከባድ ሸክም ይሆናል፣ መንበርከክ ዳገት፣ ቃል አውጥቶ በአምላክ ፊት መናገርም አስቸጋሪ ይሆናል። አቤት ደረቅ ጸሎት (ምንም የጸሎት መንፈስ ሳይኖር መጸለይ) እንዴት ያለ ክብደት መሰላችሁ? ፈውስ አይሆንም፣ በስጋ መዛልና የጉልበት ድቀት አትርፎ መነሳት እንጂ ደስታ አይሸመትበትም፤ ሰአት መቁጠርና አምላክ ፊት ተንበርክኮ ማነብነብ ይሆናል እንጂ ወደ መንፈሱ አለም ጠልቆ መግባት አይገኝም።
ጸጋውን ሲጎናጸፉ የጸሎት መንገድ አስተማማኝ በሆነ አሰራር ወደ አምላክ መገኛ የሚመራና የሚያደርስ ነው፤ የማይጸልይ ግን እንደዚያ በመንፈስ አይጓዝም፣ ወደ አምላክ ማደርያ አይገሰግስም፣ የክፋት መንፈሳውያን ሃይልና ከበባን ጥሶ ወደ አምላኩ መጠጊያ አይቀርብም። የማይጸልይ መንገድ ላይ የቀረ ነውና መዳረሻ የለውም።
ውጤት ያለው ጸሎት ስንጸልይ ግን መሆን ያለበት እንደሚከተለው ነው፦
1ጢሞ.2:1-2 ‘’እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።’’
ይህ ልምምድ ከእኛ ታጋሽነት ጋር፣ ከእኛ ጠባቂነት ጋር፣ ከእኛ እምነት ጋር የሚሄድ ነው፤ ተግባሮቹን በህይወታችን ካልተለማመድን ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ያስቸግራል፦ ልንለምን ወደአምላካችን ስንቀርብ ፊቱን መፈለግ ያስፈልጋልና፤ በጸሎት ለመቆየት በመንፈሱ መገኛ ውስጥ ሆነን በሃይሉ ችሎት በመረዳት እንደመንፈስ ፈቃድ ልንጸልይ ስለሚገባ የእግዚአብሄር እርዳት እጅግ ያስፈልጋል፤ ምልጃም ምስጋናም እንዲሁ።
በድካም ውስጥ ግን የተፈታ መንፈስ ይዘን እንዳንቀርብ የህሊና ነገር ትንቅንቅና ግብግብ ይሆናል። እጅን ማንሳት አይቻልም፣ ቃል ማውጣት አይሞከርም፣ ወደ አምላክ በንሰሃ መቅረብም ዳገት ይሆናል። ይህ ከፍተኛ ስቃይ ነው። የሰው ልጅ ከጌታ ኢየሱስ አለኝታነት ውጪ አንዳችም ነጻነት አይኖረውም፤ የደሙ የማንጻት ሃይል ቀና ያላደረጋት ነፍስ ሁሌ በወቀሳ ትሰቃያለች። ሁኔታው የሚወሳሰበውም መጸለይ ዝግ ሲሆን ነው። የሚሰማኝን ለሚወደኝ አባቴ ከመግለጽ በላይ ክፉ ነገር ምን አለ? ለርሱ መናገር ካልቻልኩ ለማን?
5. ከማመስገን መድከም
ወደ ጸባኦት ይዘረጉ የነበሩ እጆች አሁን ዝለዋል፤ የአምላክ መገኘት ያስፈራን ያስደስተንም የነበረውን ያህል አሁን ምንም ስሜት አይሰጠንም፣ ያን የምህረት በረከት ከመናፍቅ ቸል እያልነው ነው፤ ምን እናድርግ ደክሞናል!
በመንፈሳዊነት ልክ ሲምዘን ያለማመስገን ሃጢያት ነው፤ልኡል አምላክ ያደረገልን ባዶ ሆኖብን እንዳልተደረገልን መቁጠር ምን ማለት ነው? ምህረቱን መዘንጋት፣ ቸርነቱን ቸል ማለት፣ ማዳኑን ወደ ጎን ማለት እኮ አይቻልም፤ ይልቅ ማመስገን ትህትናን መግለጥ፣ የሚወደንን ጌታ ውዴታችንን ማሳየት ይገባ ነበር እንጂ፤ ያ የመንፈስ ደስታን የሚሰጥ መልካምልማዳችን ነው። የተደረገልንን ካላስተዋልን ግን በቀጣይ ህይወታችን ቀጣይ ስጦታ እንዳንቀበል ያደርጋል። የምስጋና ንፉግነት በብዙ መልክ ይጎዳል፤ ሃላፊነትም ያሳጣል።
‘’አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?’’ (ዘጸ.15:6-11)
ሁል ጊዜ ሰው ከእግዚአብሄር እየራቀ ሲሄድ ክብሩ ስለሚርቀው በውስጡ አምላኩ እየራቀበት፣ እግዚአብሄር ያደረገለትና እያደረገለት ያለው ነገርብዥ እያለበት ይሄዳል፣ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሄር ውለታ ይዘነጋዋል፤ በዚያ አያቆምም፣ በሚፈጠረው ክፍተት ክፉ መንፈስ ይገባና አመለካከቱን ማመሰቃቀል ይይዛል። ያልተረጋጋ ማንነት ውስጥ እንዲህ ከገባ በኋላ እግዚአብሄር የሚያደርግለትን ሳይሆን እርሱ የፈለግነውን ብቻ የሚያስብ ሆኖ አጉረምራሚነት ይበረታበታል። እግዚአብሄርን የሚያውቁ ግን ምስጋና የተሞሉ ናቸው፤ በእግዚአብሄር ህልውና የሚደሰቱ ናቸውና፤ በጌታ ሁልጊዜ ደስ የሚሰኙትም እነርሱ ብቻ ናቸው።
‘’ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።’’ (2ሳሙ.22:4-7)
ምስጋና የሚጀምረው በእግዚአብሄር ፊት መሆናችንን ገና ስናስተውል ነው። በታላቅነቱ ፊት መሆናችንን ስንረዳ እናመሰግነዋለን፤ የእርሱ ማንነት የእኛ አለኝታ መሆኑን ስለምናውቅ እናመሰግነዋለን፤ ሳንነግረው ገና የሚያስፈልገንን ስለሚያውቅ፣ እርሱ ተገቢውን ነገር በሙሉ እንደሚፈጽም ስለምናስተውልም እናመሰግናለን። ከማመስገን ደክመን እንደሆን ደግሞ የእርሱ ህልውናም ስለማይታየን ብዙም አይደንቀንም፤ በአምላክ ፊት እንዲህ ስሜት አልባ መሆን ግን እጅግ ጸያፍ ነው። የማይገባ መስዋእት የሚከተለውም በዚህ ሰበብ ነው። አንካሳ መስዋእት (ተገቢ ያልሆነ ምስጋና የሚመስል መደዴ ንግግር) አጸያፊ መሆኑን መረዳት ይገባል።
መዝ.72:18-19 ‘’ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። ይሁን፤ ይሁን።’’
6. ከአምልኮ መድከም
እስራኤላውያን የእግዚአብሄር እጅ ተገልጣ ባህሩን እንዳደረቀች ጠላቶቻቸውም በሃይሉ በባህሩ ሰጥመው እንዲጠፉ እንዳደረገ አይተው እግዚአብሄርን ሊያመልኩ ተነሱ፣ ያ አጋጣሚ እንደምን የሚያስደስት እንደነበር እንመልከት፦
ዘጸ.15:19-24 ‘’…የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕርገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ።የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ።’’
ማጉረምረም የሆነባቸው ብዙ ሳይቆይ ታምራት ከሆነላቸው ስፍራ ብዙም ሳይርቁ ነበር፣ የአምላካቸውን ማዳን ፈጥነው በዘነጉ ጊዜ አምልኮአቸው ወዲያው ተቆረጠ።
እንዲህ ነፍስ ስትደርቅና በክፉ አሳብ ስትወጋ እግዚአብሄርን በደስታ ለማምለክ ያዳግታታል፤ መንፈስም እግዚአብሄርን ከመከተል ይደክማል፤ የተሳሳተ አምልኮ የሚከተለው የእግዚአብሄርን ማንነት በዚህ ህይወት ውስጥ ፈጥኖ በመዘንጋት ነው፣ ይህም አስደንጋጭ የድካም ውጤት ነው። የእግዚአብሄር ህዝብ ቸልተኛ ከሆነ እግዚአብሄር እንደምን ያዝን?
መሳ.2:16-21 ‘’እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፥ ከሚማርኩአቸውም እጅ አዳኑአቸው። ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ አባቶቻቸውም ይሄዱበት ከነበረ መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ አባቶቻቸው ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ታዘዙ እንዲሁ አላደረጉም። እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው። መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ይመለሱ ነበር፥ ሌሎችንም አማልክት በመከተላቸው እነርሱንም በማምለካቸውና ለእነርሱ በመስገዳቸው አባቶቻቸው አድርገውት ከነበረው የከፋ ያደርጉ ነበር፤ የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር። የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ እንዲህም አለ። ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ አባቶቻቸውም እንደ ጠበቁ፥ ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም።’’
እውነተኛው አምላክ አብርቶልን እንደሆን እርሱ ሊመለክ የሚገባው በእውነትና በመንፈስ ብቻ ነው፣ ነገር ግን ያን ያላስተዋሉና እግዚአብሄርን ያልፈሩ በስሙ የተጠሩ ወገኖችና ነገስታቶቻቸው ብዙ ቅጣትና ጉስቁልና እስከ ህይወታቸው ዘመን ፍጻሜ ተከትሎአቸዋል። የእስራኤል ታሪክ በዚህ ዘመን ላለን ለእኛ የመስተካከያና የመታረሚያ ምሳሌ ሊሆንልን እንዲህ ተጽፎአል፤ የነርሱ ታሪክ የፍርድ ታሪክ እንደሆነ አስበን እንዳናቀልለው፤ ታሪክ ብቻ እንዳይሆንብን አስተማሪ ትምህርትነቱ እንዳይዘነጋን ይሁን፦
1ቆሮ.10:1-11‘’ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።እነዚህም ክፉ ነገር እንደተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደሴሰኑ በአንድቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደተፈታተኑት በእባቦቹም እንደጠፉ ጌታን አንፈታተን።ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።’’