በመስማት ድካም እንደተያዝን በነፍሳችን ውስጥ ሃብት ሆነው የተቅመጡ ውድ መንፈሳዊ ነገሮችን ነፍሳችን እንደምታጣ አይተናል። መንፈሳዊ ድካም ውስጣችን ገንግኖ እንደሆንበተለይ የመስማት ጉልበትን በመብላት አማኝ ወገን ከእግዚአብሄር ጋር እንዳይቀራረብ ያደርጋልና ነገሩ ቸል መባል የሚችል አይነት አይሆንም፤ የችግሩ ጽናት ብዙ ጉድለታችንን አመልካች ነውና፤ በየትኛውም አቅጣጫ የሚፈጥረው ተጽእኖም ቀላል አይደለም፦ በርሱ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ነገር መርጠን፣ ለእኛ የሚመጥን ነገር ለይተንና ተጠንቅቀን በመስማት እንዳንባረክ ትልቅ እንቅፋት ይፈጠራል። ለመስማት ድካም ምክኒያት ሆነው ከሚታዩት መሃል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
ጆሮዎች ሲፈዝዙ
‘’ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።’’ (እብ.5:11-12)
ፈዛዛነት ሃይል የማጣት ውጤት ነው፤ ማንም ሰው ያለእግዚአብሄር ጉልበት ከሆነ በመንፈሱ አለም ፈዛዛ ነው፤ የትኛውንም መንፈሳዊ ጥቃት መመከት አይችልምና። በተለይ ለመንፈሳዊ ነገር ምላሽ መስጠት ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ ከሆነ ምን እየሆነ እዳለ አያስተውልም፣ ዘመኑን በተመለከተ የመረዳት እውቀት ስለማይኖረው በዘመን ላይ የሚገለጡ የክፋት አሰራሮችን አይረዳምና ለከባድ አደጋ የተጋለጠ ይሆናል። ጆሮ በሚፈዝዝበት የህይወት ፈተና ውስጥ መንፈሳዊ ድምጾችን መለየት ያዳግታል፣ የውስጥ የመስማት ሃይል ተዳክሞ ወይንም ከመስማት ተደፍኖ ስለሚቆይ በነፍስ ላይ ብዙ ጭንቀት ይመጣል፤ በዚህ ችግር አስቀድሞ ፈተና ውስጥ የሚገባው ግን መንፈሳችን ነው፤ መንፈሳችን ድምጽን እየለየ መገናኘት ስለሚያቆም በእግዚአብሄር መንፈስ መመራት ያዳግተዋል፤ በዚያ ምክኒያትም ነፍስ በጸጋ ድርቀት ትጎሰቁላለች።
ከመታዘዝ መዘግየት
ድምጽን ከመለየት የደከመ ሰው ፣ የሚያስደነግጠው ድምጽ ላያገኘው ይችላል፣ የሚመክረውና የሚያሳስበው መልእክት ላይደርሰውም ይችላል፤ ይሄም በህይወት ላይ ከባድ ችግር የሚያስከትል ነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ በህሊናው የእግዚአብሄር ድምጽ የማይሰማው ስለሆነ ለቃሉ ሊታዘዝ አይችልም፣ ወቃሽ የለውም፣ ቃሉ ወደ ውስጡ አልዘለቀምና።
‘’ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦“ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ነገር ግን፦ እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦“እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ’’ (ሮሜ.10:16-19)
እስራኤላውያን የእግዚአብሄርን ቃል ኪዳን የተቀበሉ ህዝቦች ናቸው፤ የእግዚአብሄር ቃል ከሰማይ የወረደው ወደ እነዚህ የቃል ኪዳን ህዝብ ነበር፤ ህዝቡ ግን እንደሰሙት ቃል መጠን አልተንቀሳቀሱም፣ ወደ እግዚአብሄር መቅረብና መባረክ አልቻሉም፤ ምክኒያቱም ጆሮቻቸው ከመስማት ፈዝዘው ነበር፤ የጠራቸውን አምላክ አልሰሙምና እርሱም እንዳይሰማቸው ሆነ፤ አልታዘዝዙትምና በጠሩት ጊዜ እርሱም አልመለሰላቸውም። ይህ ደግሞ ለእግዚአብሄር ህዝብ ትልቁ የውድቀት ቁልቁለት ነው፤ እግዚአብሄር ከመስማት እምቢ አለ ማለት ሁሉም ነገር አለቀ ጥፋት ተቆረጠ ማለት ነው።
‘’ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።’’ (1ጴጥ. 3:20)
የኖህ ትውልድ እግዚአብሄር ማስጠንቀቂያ እየተናገረ አልሰሙም፣ የሚድኑበትን መፍትሄ እንዲያዘጋጁ ሲመከሩም አልተቀበሉትም፣ እግዚአብሄር በኖህ በኩል በቃልም በስራም መዳኛውን ቢያሳይም የመቶ አመቱ ጥረት መታዘዝ የፈጠረው ኖህ ቤተሰብ ላይ ብቻ ነበር፤ ለቀረው አለም ግን መጥፊያ የውሃ መቅሰፍትም ታዘዘ። እንዲህ ያለ አለመታዘዝ ጥፋትን አሳዘዘ።
2. የመለየት ድካም
የሰማነው ማንን ነው፣ ድምጹስ የማን ነው? እግዚአብሄርን ማወቅ የሚሆንልን ድምጹን በቅርብ ስናውቀው፣ ስንሰማውና ለድምጹ መልስ ስንሰጥ ነው። እግዚአብሄርን የቀረበና የርሱን ድምጽ የተለማመደ እግዚአብሄር እንደብዙ ውሃዎች ባለ ታላቅ ድምጽ ይናገር ወይም እጅግ ዝቅ ያለ ድምጽ ይላክ ያ ሰው የእግዚብሄርን ንግግር ይለያል፣ ለድምጹም ፈጣን ግብረ-መልስ ይሰጣል።
‘’…ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ።እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆም፦ ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ።እርሱም፦ ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።እርሱም፦ ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም።ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ፦ ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። እርሱም፦ ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።’’ (1ነገ.19:8-14)
ነቢዩ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ እግዚአብሄር ተራራ ደርሶ እግዚአብሄርን ያነጋግር ዘንድ በተራራው ጫፍ ላይ ቆመ፤ በቃሉ ላይ እንደምንመለከተው ነቢዩ ኤሊያስ ታላላቅ ክስተቶች በፊቱ ሲገለጡ ቢያይም እግዚአብሄር በነርሱ ውስጥ እንደሌለ በመረዳት መልስ ከመስጠት ይልቅ ትክክለኛውን ጊዜ ይጠብቅ ነበር፤ በመጨረሻ በዝምታ ውስጥ የእግዚአብሄር ድምጽ ሲመጣ የእርሱ ትክክለኛው ድምጽ እንደሆነ ስለተረዳ ነቢዩም ተንሳቀሰ፤ ይህ የመገለጥ እውቀት የእግዚአብሄርን ማነነት ከማወቅ የተነሳ የሚገኝ እውቀት ብቻ ነው።
እግዚአብሄርን ያለማወቅ እግዚአብሄርን እንደ እግዚአብሄርነቱ ባለመቅረብ የሚመጣ ችግር ነው፤ እርሱን እስካልቀረብነው ድረስ ማንነቱን አናውቅም፣ ወይም አናስተውልም፦ አባትነቱ አይገለጥልንም፣ ማዳኑ አይገባንም፣ እርሱ የሁሉ ነገራችን ምንጭ መሆኑን አናምንም። ባህሪውን ያለማወቃችን ንግግሩን እንዳናውቅ ያግዳል፤ በሩቅ ለመኖር ተገደን ባለንበት በዚህ ጊዜ በመሃል ለሚገቡ እጅግ ለሚበዙ ድምጾች በሙሉ እንግዳ ስለሆንን ማን ምን እንደሆነ፣ የቱ ከየትኛው እንደወጣ ፍጹም መለየት አንችልም። በእግዚአብሄር ቤት ስንኖርም በቃሉ ካላደግን የቃሉን ድምጽ አመጣጥ እንዲሁ አንለይም፣ ስለዚህ በሚሆነው ነገር ድንግርግርታ ይፈጠርብናል።
ነብዩ ሳሙኤል ከህጻንነቱ አንስቶ በእግዚአብሄር ቤት ያደገና እግዚአብሄርን ያገለገለ ታላቅ ነብይ ነበረ፤በለጋነቱ ወራትና የእግዚአብሄርን ድምጽ ባልለየበት ወቅት ወደርሱ ይመጣ የነበረው የእግዚአብሄር ድምጽ የሰው/ የካህኑ እስኪመስለው ፈጽሞ መለየት አልቻለም ነበር (ነገሩ የመንፈሳዊ ድካም ውጤት ባይሆንም የእግዚአብሄርን ድምጽ ለይቶ ያለማወቅ ውጤት ግን ነበር)፦
‘’ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር። በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር። ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም፦ እነሆኝ አለ። ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም፦ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ። ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።’’ (1ሳሙ.3:1-7)
ከላይ ባለው ቃል ውስጥ ከሁለቱ አገልጋዮች የእግዚአብሄር ድምጽ እንደራቀ እንመለከታለን፡ የመጀመሪያው የህጻኑ ሳሙኤል ነው፦ ሳሙኤል ለጋ ስለሆነ፣ በእግዚአብሄር አሰራር ሙሉ እውቀት ስለሌለው የእግዚአብሄርን ድምጽ ሊለይ አልቻለም፤ ካህኑ ኤሊ ግን በአገልግሎት ዘመኑ እስከእርጅና ድረስ ያገለገለ ቢሆንም ከእግዚአብሄር ድምጽ የራቀ ነበር፣ ከእግዚአብሄር ከራሱ የራቀ ስለነበር ድምጹ ቀርቦ ሊያነጋግረው አልመጣለትም።
በእግዚአብሄር ቤት ብዙ አመት አስቆጥረን ሳለ የእግዚአብሄርን ማንነት አልተረዳን እንደሆነ ድምጹን መለየት ከቶ አይቻለንም፤ የእግዚአብሄርን ድምጽ ለመለየት ወደ እግዚአብሄር መጠጋት ይፈልጋል። በሌላ በኩል ካህኑ ኤሊ የእግዚአብሄር አፍ ሆኖ እስራኤልን ያገለግል ዘንድ የተሾመ ብቸኛ የዘመኑ ሰው ነበረ። እርሱ ግን ከእግዚአብሄር በአካል ሳይሆን በመንፈስ ሩቅ ስለነበረ የእግዚአብሄር ድምጽ በርሱ የአገልግሎት ዘመን ሩቅ ነበረ። በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ። አዎ ራእይም አይገለጥም ነበር የሚለው ቃል እጅግ አስፈሪ ነው፤ ምክኒያቱም በኤሊ መራቅ እግዚአብሄር ከህዝቡ ርቆአል፣ በተፈጠረው ክፍተትም ህዝቡ ከአምላኩ ጋር ሳይቀራረብ ቀርቶአል። ያ ህዝብ አምላኩ ስለአባቶቹ ብሎ የመረጠው ወገን ሆኖ ሳለ ከአምላኩ ዘንድ ሊወርድለት የሚገባውን በረከት የተነፈገው ስለህዝቡ በተመረጠው እቃ ዳተኝነት ሰበብ ነበር፤ ያን የአባቶችቹን በረከት ህዝቡ በዚያ ሁኔታ ተነፈገ። አንዱም ሰው እንኩዋን ድምጹን የሚለይበት አጋጣሚ ሳያገኝ ቀረ፤ ቃሉ ከእግዚአብሄር ዘንድ ጨርሶ የተቆረጠ እንዲሆን የተደረገበትይህ ሁኔታ ከባድ የመንፈሳዊ ድቀት መገለጫ ጊዜ ነበር።
3. የንግግር ድካም
በልባችን ያለውን በጎ ነገር ፣ ለአምላክ ለመድሃኒታችን ማፍለቅ የሚገባን የምስጋና መስዋእትም ያለማውጣት ትልቅ ጥቃት ነው። ከሚጠብቀን፣ ከሚመግበን፣ ከሚያኖረንና ከሚያድነን አምላክ ጋር ያለመነጋገር ሌላው ጉዳት ነው። ካላነጋገርነው እርሱስ እንዴት ይመልስልናል? ካልጠየቅነው እንዴት ይሰጠናል? ከአምላክ ልናገኘው ያለው መልስ በምናወጣው ድምጽ ላይ ተወስኖአል፣ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በቃሉ እንዲህ ይላል፦
‘’ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። `ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ‘’ (ማቴ.7:7-9)
ድምጻችንን አውጥተን በምልጃ መጮህ፣ በትህትና በፊቱ በንሰሃ ቃል መነጋገር፣ የልባችንን ስሜት አውጥተን ለእርሱ መግለጥ ወደ እርሱ ያቀርበናል። ከአምላካችን ጋር በነጻነት የመኖር ምልክቱ እርሱን ዘወትር ማነጋገር ላይ የተወሰነ ነው፤ እንደ አንድ አምላኩን እንደሚወድ፣ እንደሚያከብርና እንደሚታዘዝ ልጅ ተቀራርቦ መነጋገር እጅግ ትርፍ የሚያስገኝ መንገድ ነው። የፈጠረውን አምላክ የማያነጋግር አመጸኛ ህዝብ ግን ቃሉን አውጥቶ ወደ አምላኩ መለመን ሳይሆን በኩርፊያ ማልጎምጎም፣ ፣ በክስም የአምላኩን ስም ማርከስና በጥላቻ መክሰስ ይቀናዋል፤ ይህ በአምላክ የተጠላ ባህሪ በመሆኑ ከባድ ቅጣት ይጎትታል፣ ሁኔታውን ከእስራኤል ህዝብ ታሪክ መገንዘብ ይቻላል፦
‘’ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት መካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች። ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች። የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ።’’ (ዘሁ. 11:1-6)
ሁኔታዎች በህዝቡና በሙሴ መሃል ልዩነት እንዳለ ያሳዩናል፦ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚያውቅ ሙሴ የልቡን መሻት በጸሎት ወደ አምላኩ ሲያቀርብ፣ ልቡ ከአምላኩ የራቀ ይህ ህዝብ ግን በቁጣ ያጉረመርማል፣ በምኞት ከመቃጠሉ ብዛት ያለቅሳል፣ ይህም በእግዚአብሄር ፊት የማያስደስት ድርጊት ነበርና መቅሰፍት አምጥቶባቸዋል።
እግዚአብሄርን በቅርበት የሚያውቅ ማንም ሰው በማህበር ይሁን በግል ህይወት ላለው ጉዳይ ከአምላኩ ምሪት ይጠይቃል፤ ከእንቅስቃሴው በፊት በልቡ ያለውን የትኛውንም አሳብ እንደሚሰማ እርሱ ያስተውላልና አምላኩን ይፈራል፤ሆኖም የእስራኤል ህዝብ አካሄድ የተለየ ነበር፦ በእግዚአብሄር ላይ አድማ ጠርቶ በፊቱ እንደ አንድ ሰው ቆሞ ሲያጉረመርም፣ በአመጽ ሲናገርም በአምላኩ ዘንድ ሞገስ አጥቶ ነበር፤ አምላኩ ይቀበለው የነበረው ጊዜ አልፎ ከርሱ ጋር ጥል ውስጥ ገብቶ ነበርና አስቀድሞ እንደነበረው ጊዜ አሁን አልታየም። ይህ ክፉ ህዝብ አጉረምራሚ ሆኖ ያዳናቸው አምላክ ፊቱን እንዲያከብድባቸው አደረገ፤ የእግዚአብሔር ቁጣ መአት ስለሚያፈስ እሳት መካከላቸው በርትታ ነደደች፣ ምንም አልተወችም መበላት የነበረባትን የአመጽ ደጅና ጉልበት በላች። በመካከላቸውም የነበሩ ከግብጽ አብረዋቸው የወጡ ድብልቅ የሆኑ ልዩ ልዩ ሕዝብ የግብጽን ነገር እያነሱ በመጎምጀት ሲናገሩ የእስራኤል ልጆች በዚያ ስፍራ ከስጋዊ መሻታቸው ብዛት ያለቅሱ ነበር እንጂ ሁሉን የሚሰጠውን አምላክ በትህትና አልጠየቁም፣ ይህም የእግዚአብሄርን ቁጣ አነሳሳ።እንዲህም ሆነ፦
‘’ሕዝቡንም በላቸው፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ። ሙሴም፦ እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም። ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ። እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን። በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው።’’ (ዘሁ. 11:18-23)
ይህን ሁሉ ምስቅልቅል በህዝቡ ላይ ያመጣው የህዝቡ ብልሃተኛ ያለመሆን፣ ታጋሽ ያለመሆን፣ እንዲሁም አንደበታቸውን በአምላካቸው ፊት መጠበቅ ተስኖአቸው እንዳልተደረገለት ተራ ሰው በእርሱ ላይ ክፋትን ስላሰቡና ስላጉረመረሙ ነው። ሞገስ ካስፈለገ ግን መሆን ያለበት ከምን ግዜውም በላይ የእግዚአብሄርን ነገር ማስቀደም፣ በሃያሉ አምላክ በርሱ ፊት ስንፍና ከመናገር መቆጠብ፣ ለእግዚአብሄር ፈቃድ ስፍራንና ጊዜን መልቀቅ፣ መናገር ግድ ከሆነም ምህረቱን በመሻት ላይ የተመሰረተ ጥያቄ ማቅረብ ነው። የእምነት አባት የሆነውን አብረሃምና ሚስቱ ሳራን በእግዚአብሄር ፊት በነበሩ ጊዜ ያደረጉትን እንይና መናገር የማይገባን ነገር በመናገር የሚመጣብንን ነቀፌታእናስተውል፦
‘’እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር።ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች?በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች። ሣራም ስለ ፈራች፦ አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም። አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት።’’ (ዘፍ.18:10-15)