መንፈሳዊ ድካም(2…)

የመጨረሻ ዘመን

በሮሜ.14:1 ላይ ‘’በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ።’’ ባለው መሰረት በእምነት ድካም ሲመጣ በአማኝ ላይ ከሚመጣ የአስተሳሰብ መናጋት ለመታደግ ጥንቃቄ እንዲኖረን ቃሉ ይመክራል። በተለምዶ እንደምናየው ሰው በአሳብ መናጋት ውስጥ ሲገባ ሌሎች ሰዎች በርሱ ላይ እንዲፈርዱ መንገድ ይከፍታል፤ በተለየ ሁኔታ እንዲገምቱት፣ እንዲተቹትና እንዲፈርዱበትም ያደርጋል። ያ የሚያስተች አመለካከት ደግሞ አድሮ የስነ ልቦና መናወጥ ምንጭ መሆኑ አይቀርም፤ በዚህ አንጻር ነገሮችን ስንመለከት መሰረታዊ የድካም መገለጫዎች የትኛዎቹ እንደሆኑ ማየት እንችላለን፤ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉትን ይመስላሉ፦
1.የመስማት ድካም
-የመስማት ድካም የእግዚአብሄር ቃል ማስተዋል ላይ ተጽእኖ ያደርጋል
-የመስማት ድካም ሳይመርጡ መስማት ይፈጥራል
-የመስማት ድካም ያለበት ሰው የእግዚአብሄርን ቃል መስማት ያዳግተዋል
-የደከመው ድምጽን አይለይም፣ ማየት ይሳነዋል
-ያልሰማ አያምንም፣ ምን አውቆ ያምናል፣ ምን ሰምቶስ ልቡ ይዘጋጃል?
-ከመስማት የደከመ እምነቱ እየደከመ ይሄዳል፣ ህያው ቃል ከውስጡ ተሙዋጦ ሊወጣ ስለሚችል
እስራኤላውያን የጌታን ድምጽ ለይተው መስማት በተሰናቸው ዘመናት የአባቶቻቸው አምላክ የገባላቸውን ቃል ኪዳን ዘነጉት፣ የሚሰሙት እስከማይገባቸውም ደረሱ፣ የሚላክላቸውን መለክተኛ ስለማይሰሙና ስለማያከብሩ የሚናገራቸው ላይ እስከመታበይ ደረሱ።
‘’እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ነገር ግን እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦ እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ፦ ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ። ስለ እስራኤል ግን፦ ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።’’ (ሮሜ.10:14-21)
ከላይ እንደምናየው የመስማት ድካም ትልቅ አዘቅት መሆኑን ነው፤ የመንፈሳዊነት ድቀት ጅማሬ ከመስማት መደናቀፍ ላይ ይነሳልና። በብዙ መልኩ አማኞች ድምጽን መለየት እየተሳናቸው ሲሄዱ የህይወት ትርምስ እየገጠማቸው ማንከስም እየተከተላቸው ይሄዳሉ። መስማት ተስኖናል ስንል የውስጥ ሰውነታችን ከሚሰማው ብዙ ድምጽ መሃል የእግዚአብሄርን ድምጽ መለየት አቁሞአል ማለታችን ነው፤ በመስማት ምክኒያት የእግዚአሄር ቃል በውስጣችን ሃይል ይፈጥር ነበር፤ ነገር ግን ሰው ባለመስማት ምክኒያት ይዝላል። አቅም ያለው መስማት እጅግ አስፈላጊ ልምምድ በመሆኑ የእግዚአብሄር ቃል በትኩረት ያነሳዋል፦
‘’ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።’’ (ዮሃ. 8:42-44)
ሰዎች ህያው ቃሉን መስማት ከተሳነን የመንፈስ ጥቃት አግኝቶናል ማለት ነው። በጌታ ኢየሱስ ዙርያ የነበሩ አይሁድ አብዛኛዎቹ ከርሱ በተቃውሞ መንፈስ የቆሙ፣ እርሱን ሊያሳንሱ የሚሞክሩ፣ ደግሞ በባእድ መንፈስ የተያዙ ስለነበሩም ህያው ቃሉን ከመስማት ወደኋላ ያሉ እንደነበሩ ከቃሉ እንመለከታለን።
አንድ ሰው ከጌታ ጋር ፊት ለፊት በተቃውሞ ሊቆም የሚችለው፣ የእግዚአብሄር ሆነ የሰው ጠላት የሆነው መንፈስና ትምህርቱን ሲሞላው ነው፤ እንዲህ ያለው የውስጥ ሰውነቱ በዚያ ባእድ መንፈስ ቁጥጥር ስር ስለሚሆን ባለ አስተዋይ ህሊና ይሆን ዘንድ ያዳግተዋል።
ናፍቆት ሲቀር መሰልቸት
የቀድሞ የመንፈስ ጥማት ቀነስ ሲል፣ እለት እለት እያሰለሰ ሲሸሽ፣ ከህይወታችን ክፍል እያዘገመ ወደ ውጪ ሲሳብና እየተሙዋጠጠ ሄዶ የፍላጎት ጉልበት ሲቀንስ፣ ፍለጋችን እንደዚያው እየቀነሰ፣ የቃሉን ጥፍጥና የመለየት ጥንካሬ እየረገበ ይሄዳል፣ አጥብቀን የያዝነውም እውነት ጉልበቱ እየረገበ ይመጣል፤ ይህ በመንፈስ የሆነ ጥማት መሰረታዊ የመንፈሳዊ እርካታ መንገድ ሲሆን በጎ ልምምዳችን ቀንሶ በህይወታችን ፍላጎት መታጣት ሲታከልበት ተጨማሪ ችግሮችን መጎተቱ አይቀርም። ለምሳሌ የምግብ ፍላጎት ሲቀንስ የስጋ ሰውነት ድካም ድካም ይለዋል፤ በዚያው ቀጥሎ አቅሙ እየተሟጠጠ በሄደ ጊዜ መራመድ እስኪያቅት መውደቅና አልጋ ላይ መዋል አልፎም ራስ እስከመሳት በሚያደርስ የጤና መታወክ ያደርሳል፦ ያ በጊዜ ያልተፈወሰ የምግብ ፍላጎት ችግር። መንፈሳዊ ህይወትስ ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ሲጠናወተውና የህይወት ውሃ ሲያጥረው ደግሞ የህይወት እንጀራን በቸርነት ከሚያቀርብለት ጌታ ፊት ሆኖ በቅጡ መመገብ ሲሳነው ነፍስ መሰልሰሏ መች ቀርቶ?
የእስራኤል ህዝብ ከአምላካቸው ርቀው ባሉበት ዘመን ሁሉ በድካም አረም ስለተወረሱ ቃሉን ለመስማት ተቸግረው እጅግ ዳተኞች ሆነው ይታያሉ፤ የህያው አምላክ ቃል ፍለጋ ተረስቶ ወደ እግዚአብሄር ቤት የሚገሰግሱበት ጊዜ ሲዘነጋ፣ በጥፋት ጎን የቆመውን ቃሉ ሰይፍ ሆኖ ሲቀላ፣ እየወቀሰ ህሊናን ያለረፍት ሲወጋና እንደ ጭንቁር ሲሆን በውጤቱ ልብ ሲከብድና ሲደነድን ማየት የተለመደ ነው። ህዝቡ ጆሮውን አልሰጥ ባለበት ዘመን፣ አይኑንም ከበጎ ነገር በመለሰ ወቅት ልቡ ላይ እንዴት ያለ ክፉ መዝጊያ እንደተቸነከረ ማየት እንችላለን፦
‘’ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።’’ (ማቴ.13:13-15)
ለመንፈሳዊ ነገር ከመትጋት የደከሙ በብዙ ድጋፍ ቢደጎሙም እንዴት ያለ አዳጋች ህይወት እንደሚመሩ ማየት ይቻላል፤ በዋናነት እነዚህ ሰዎች ስለማይሰሙ ማስተዋል እንደማይችሉ ጌታ መስክሮባቸዋል፤ የህይወት ቃል በስጋ ጆሮ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን ክፍት ልቦና እንደሚያስፈልገው ከዚህ በተጨማሪ የሚገባው የእግዚአብሄር ቃል ከሰሚው ጋር ተዋህዶ ህይወት እንዲሆንለት ከመንፈስ የሆነ ትኩረት እንዲያስፈልገው እናያለን። የእግዚአብሄር ቃል የሚሰራውን በጎነት የሰው አይን ማየት ካልቻለ፣ በጆሮው የሚሰማው የህያው አምላክ ድምጽ ወደ ልብ መዝለቅ ካልቻለ፣ ልብ እንደምን ያስተውል፣ ለህዝቡስ ፈውስ እንዴት ይሁን?
የመጨረሻው ዘመን መንፈሳዊነት ላይ የሚከሰት አንደኛው ችግር ትግስት-የለሽነት ሆኖ ይታያል፤ ታግሶ እግዚአብሄርን መጠበቅ ያለመቻል፣ ቃሉ ላይ መቆየት ያለመኖር፣ በጸሎት መልስ መጠባበቅ ያለመቻል፣ ለቃሉ ክብር መንፈግ፣ ትኩረትን በሚታየው አለም ጉዳይ ላይ ማድረግና ራስን በእግዚአብሄር ቃል ከመመልከት ይልቅ በአለማዊ ነገር መመዘን ከፍተኛ ችግር እየሆኑብን ነው፦
‘’በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።’’ (2ጢሞ.4:1-4)
ስለዚህ የመስማት ችሎታችንን ለማስመለስ መፍትሄው የቃሉ ትምህርትና ምክር ላይ ማትኮር እንደሆነ አጽኖት መስጠት ይገባል፤ እግዚአብሄር ቃሉ በሚተላለፍበት ትምህርት ውስጥ ስለሚገለጥና ጸጋውን በዚያ በኩል ስለሚሰጠን ዳግም በሃይል እንድንነሳ ትኩረታችንን ወደ እርሱ ማቅናት የግድ ነው፤ ያኔ ከፍ ብለን በመነሳት ከድካማችን እንበርታለን፤ ቃሉ ለጆሮቻችን ጣፋጭና ከሁሉም በፊት ተመራጭ እንዲሆንል የሚያስችለውን የሚያቀርብ ጉልበት እንቀዳጃለን፣ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመከተል የምንመርጥበትን ማስተዋል በማግኘት እውነትን ለመስማት ጆሮቻችንን የምናዘነብልበትን ትጋት አግኝተን በዚያ ላይ ተመስርተን እንኖራለን፤ ይህ በርሱ ችሎታ ካልሆነልን በቀር ከወዴት ልናመጣው እንችላለን።
ጉጉት ሲቀር አለመፈለግ
ሃዋርያቶች ከጌታ ያልተለዩት ብዙ ነገር ስላደረገላቸው፣ ብዙ ነገራቸውም እርሱ ራሱ ስለነበረ ነው፤ በዋናነት ደግሞ እርሱ የህይወት ቃል ስላለው እለት እለት ከርሱ ቃል እየሰሙ ህይወታቸውን ማለምለም ስለመረጡም ነበር፤ ስለዚህ ጉጉታቸውና ውሳኔያቸው እርሱን ብቻ መስማት ሆነ፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውም ከጌታ ኢየሱስ አሳብ ጋር የተስማማ ነበር። የአይሁድ ነገር ደግሞ ተቃራኒ ነበር (በተለይ እርሱን ሲከተሉት ከነበሩት ደቀመዛሙርት ውጪ ያሉቱ)፤ ጥላቻቸው በገሃድ የሚታይ፣ ስለርሱ የነበራቸው አሳብ ዝቅ ያለ በሰው ደረጃ የወረደም ነበር፤ አንድ ታላቅ ነገር የተደረገለት አይነስውር ግን እስኪያፍሩ ድረስ ድካማቸውን ሲገልጥባቸው በሚከተለው ቃል ውስጥ እናያለን፦
‘’ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው፦ እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት። እርሱም መልሶ፦ ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ። ደግመውም፦ ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት። እርሱም መልሶ፦ አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው።’’ (ዮሃ. 9:24-27)
የህያው አምላክ ድምጽ ህያው አድርጎ የሚያኖር ነው፣ ድምጹን የሚሰሙ በጎች አቅጣጫቸው በእረኛቸው የሚቃኝ ነውና ወጥመድ ውስጥ አይወድቁም፣ በጠላት ከበባ ስር አይሆኑም፣ መንገዳቸውንም አይስቱም። ተኩላ የተነጠለችን በግ እንደሚያጠቃ፣ አማኞች ከመንጋው ተነጥለው የአምላካቸውን ምሪት እስከማይሰሙ ቢርቁ የጠላት ወጥመድ ላይ ከመውደቅ አያመልጡም። እውነተኛ አምላክ ግን ለበጎቹ ዘወትር ድምጹን ያሰማል፣ በጎቹም ድምጹን ተከትለው ይሄዳሉ። መጥፎ አካሄድ ተፈጥሮ የመስማት አቅማቸው ሲዳከም ግን እመንገድ ላይ ዝለው ከሚከታተላቸው ተኩላ እጅ ላይ ይወድቃሉ። የመስማት ድካም በአንዴ የሚከሰት ችግር ሳይሆን እያዘገመ መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ የሚገባ ቆይቶም የሚደነድን ችግር ነው። ከመንፈሳዊ ህይወት በዝግታ እየተንሸራተተ ያለ ሰው ድምጽን የመለየት አቅሙ በዚያው ልክ እየደከመ ይሄዳል፤ የጌታ ድምጽ በሩቅ እንዳለ ንግግር ጉልበቱ ይደክምበትና የድምጹን ምንነትና የመልእክቱን ትርጉም ያጣል። ድምጾች የሚደበላለቁት ለይተን ስንሰማው የኖርነው ጥሪ እየራቀብን ሲሄድ ነው፤ የወዳጃችን ድምጽ ለምን ይርቃል? እኛው ራሳችን እየራቅን በመሆኑ አይደለምን?
በእግዚአብሄር የጥበብ ቃል የተሳበች አንዲት የአህዛብ ንግስት ታሪክ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ አለ፤ ንግስቲቱ ጌታ ለእስራኤል ንጉስ የሰጠውን ጥበብ ልትሰማ ጉጉት አድሮባት ረጅም ርቀት እንደተጓዘችና ኢየሩሳሌም እንደመጣች በታሪኳ ላይ ይታያል፦
‘’ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።’’ (ሉቃ.11:31-32)
ንግስተ አዜብ ረጅምና አስቸጋሪውን መንገድ ሳትደክም ያስጓዛት የሰማቸው ዝና ታላቅነት ነው፣ ህያው አምላክ በእስራኤል ንጉስ በኩል የሰራውን ስራ አይታም ለመመስከር ነው። የአማኝ ጉጉት ደግሞ ከርስዋ ቢልቅ እንጂ አያንስም፤ ምክኒያቱም አማኝ የተጠራው በጌታ ኢየሱስ ነውና። እንግዲህ ከሁሉም ይልቅ ከፍ ያለ ጌታ እንደጠራን መጠን ከቃሉ የሰማነውን አውቀን ፍላጎታችን ሳይበርድና ጉጉታችን ሳይቀንስ ልንከተለው ይገባል።