መዝ.107:11-13 ‘’የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።’’
በእግዚአብሄር ላይ አመጽ የሚሆነው በእግዚአብሄር ምክር ሳንሄድ ስንቀር፣ ተግሳጹን ንቀን ችላ ስንል፣ ማስጠንቀቂያውን ምናምን ስናደርግ ነው። ይህን ባደረግንበት በፈንታው ግን በግልጽ ወይም በስውር የሚመጣ መከራ ያገኘናል፤ በግልጽ በስጋችን ላይ በሚሆን የተለያየ ህመም፣ ደዌ ጉስቁልና ሊሆን ይችላል፣ በውስጥ የሆነ የነፍስ ክሳትና የመንፈስ ድካም ሊሆን ይችላል። ሰው በስጋው አንድ ነገር ሲከሰት ቶሎ መልስ ይሰጣል፣ ለዚያ ለተሰማው ነገር ምላሽ ሊሰጥ ይንቀሳቀሳል (ለቅሶም ይሁን፣ ጸጸትም ይሁን፣ ቅስስ ብሎ መሄድም ይሁን ወይም ማጉረምረምረም… ምንም ሊያደርግ ይችላል)፤ በነፍስ ሲሆን ግን በስጋው ላይ እንደሆነው ላይሆን ይችላል፣ በመንፈስም እንደዚያው ይለያል፣ የሚሆነው ነገር። ስለዚህ መንፈሳዊ ድካምን ስናስብ ሰፊ ክልል የሚያዳርስ የመንፈስ ተጽእኖ፣ ችግርና ውጊያ የሚንጸባረቅበት ፈተና መሆኑን እንመለከታአለን።
ቃሉ ሃጢያት አመጽ እንደሆነ ይናገራል፤ ሃጢያትም የሚስበው ክፉ ነገር አለው፤ በዋናነት ደግሞ እስራትና ስብራት ናቸው፤ በእግዚአብሄር ላይ አመጽ ስናደርግ በቃሉ ላይ ሃጢያት ስላደረግን ሃጢያት የምታደርግ ነፍስ ደግሞ ትሞታለች ስለተባለ በነፍስና በመንፈስ ላይ የፍርድ ጨለማ ይወርዳል፤ አዳም እግዚአብሄር በነገረው ነገር ላይ አምጾ ሃጢያት ላይ ወደቀ፤ የእግዚአብሄርን ቃል ንቆ የሰይጣንን ግን አክብሮ እባብ ያለውን ታዘዘ። በዚህ ስራው ራሱን ሞላውን የሰው ዘር ጭምር ወደ ጨለማ፣ እስራትና ሞት ውስጥ ጎትቶ አስገባ።
የልኡልን ምክር መናቅ ሰው ምክር አድርጎ የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ እንደመናቅ አይደለም፣ የልኡል ምክር ህይወት የሚቀጥልበትን ቃል የያዘ ምክር ነው፣ ምክሩ ከጥፋት የሚያድን ነው፣ ምክሩ መልካም ነገር በህወት ዘመን ሁሉ የሚሰጥ ነው፤ ምክሩ ጸጋን የሚያጎናጽፍ፣ ከእግዚአብሄር ጋር የሚያኖር ነው። ይህን ምክር ችላ ማለት የራስን ጥቅም ችላ ማለት ለጠላት አሳልፎም መስጠትና ወደ ኋላ ሊመለስ ወደማይችል ጥፋት መግባት የሚያስከትል ነው።
የልብ ድካም እንደ አካል ድካም ቀላል አይደለም፦ ሰው ልቡ ሲደክም የማሰብ ሃይሉ ይደክማል፣ መንፈሳዊ ነገር ማስተዋሉ ይጠፋል። የልብ ኩራት የያዛቸው ምን እንደሚያገኛቸው ባላስተዋሉ ጊዜ ጥፋት ያጠምዳቸዋል፤ ኩራት ስብራትን ይቀድማል፣ ኩራት ትህትናን ይጨፈልቃል፣ ኩራት ልብን ያስታብያል። በእግዚአብሄር ላይ አመጽ የሚጀምረው ልብ ኩራት ሲይዘው ነው፤ ይህ መንፈስ የሰውን በጎ አመል የሚዋጋ ነው፤ በትህትና ልባችንን በእግዚአብሄር ፊት አዋርደን ምህረት እንዳንቀበል ኩራት መንገዳችንን ይዘጋል። በኩራት የተሸነፈ ልብ ትእቢት ስለሚቀድመው ከባድ አደጋ ይጋረጥበታል።
የልብ ኩራት ነፍስን ለጥፋት ያዘጋጃል፤ የመንፈሳዊ ጉዞን ያደናቅፋል፤ ከእግዚአብሄርም ከባልንጀራም ጋር ያለያያል። እግዚአብሄር ንጹህ ልብ ይፍጠርልን፤ ትህትና የሚገዛው ልብ ይስጠን። የታበዩ የሚረዳቸው ስለማያገኙ መከራቸውን የሚካፈል የላም፤ በቃሉ ላይ የኮሩም ከእግዚአብሄር ዘንድ እርዳታ አያገኙም፤ ጸሎታቸው አይሰማም። በመከራ የተያዘች ነፍስ ጩእት ብርቱ ነው፣ አምላክን የማታውቅ ብትሆን መከራዋና ጭንቀትዋ እንዴት ይበረታ?
መዝ.31:10-12 ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፤ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ።በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ።እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ።የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፤ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፤ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ።
ዳዊት ግን በአምላኩ ላይ ልቡን ስላበረታ ጸሎቱ የምትሰማ ነበረች፣ ልመናው መልስ ታገኛለች፣ የእግዚአብሄር ማዳን ትፈጥንለታለች። በእምነት ሳይደክሙ ለመጽናት በእግዚአብሄር ቃል መደገፍ ያስፈልጋል፣ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊሰጠው ይገባል፤ ያ ካልሆነ እንዴት ያሸንፋል?
ሮሜ.6:17-20 ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ፦ ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና።
የስጋ ድካም ጎልቶ የሚወጣበት ጊዜ አለ፤ የስጋ ድካምም ከንቱ የሆነ የህይወት ልማድ ያለው ማንነት ስለሆነ በዚህ ህይወት ውስጥ በእግዚአብሄር ዘንድ አመጽ የሆኑ መተላለፎች ገዢ ይሆናሉ። ባለመታዘዝ የሚከሰቱ መዘዞች አሉ፤ ባለመስማት የሚገጥም ፈተና ከነዚህ ይወጣል፡ ባለመፍራት የሚጋፈጥ ብርቱ ፈተና አለ፤ አመጻ የለመደ ልቦና ቅን በሆነ በእግዚአብሄር የቃሉ ምክር አይገራምና በስጋ ሆነን እግዚአብሄርን ማስደሰት አንችልም፣ የስጋ ፍላጎት ከመንፈሳዊ ተቃርኖ ስለሚቆም በመንፈስ ሊሆኑ የተገባቸው ነገሮችን ያወሳስብብናል። እምነት በሌለበት ልብ ውስጥ መታዘዝ ስለማይኖር የስጋ ስራዎች በቀላሉ ልብን ወዳሻው መንገድ ይመሩታል። የእግዚአብሄር አገልጋዮች በመንፈስ እንደሚመሩ ሁሉ ስጋቸውን የሚያገለግሉ የስጋ ስራን ያስቀድማሉ።
‘’ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ’’ ባለው መሰረት ያን ባደረግንበት ስፍራ መንፈሳችንን ለሚያደክም ሃይል እያቀረብንና ለጥቃት ራሳችንን እያጋለጥን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከብልቶቻችን አንዱን ወይም ሁለቱን በእግዚአብሄር ቃል ላይ እንዲያምጹ ብንጋብዝ ሙሉ ሰውነታችንን አስወርሰንና ለአመጽ አሳልፈን ማቅረባችን እሙን ነው፦ ጆሮአችንን ለክፉ የምክር ድምጽ አሳልፈን ልንሰጥ እንችላለን፣ አይናችንም እንዲሁ፤ ወይም አንደበታችን ክፋት ቢያወጣ ወይም አንዱ የአካል ክፍላችን ለየት ያለ ሃጢያት እንዲሰራ ብንፈቅድለት መላ ሰውነትችንን (ስጋችን፣ ነፍሳችንና መንፈሳችንን ) ለአመጽ አሳልፈን ሰጠን ማለት ነው። ይህ ሲሆን በመንፈሳዊ አሰራር ብርታትና ሃይል ከእግዚአብሄር መንፈስ የተቀበልንበት ጊዜ እየሸሸና የያዘን እጅ እየለቀቀ ይሄዳል ማለት ነው፤ ያኔ ከአመጽ ጋር እድል ፈንታ የሌለው ቅዱስ መንፈስ ለቅቆ ይሄዳል፣ የውስጥ ሰውነታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ መሆኑ ቀርቶ የሃጢያት ማደሪያ አልፎም የድካም መንፈስ መናሀርያ ይሆናል። በተለያየ አሰራር በኩል ጎራ ያለ ክፉ መንፈስ ሲከራርም በቀጥታ ከመንፈሳችን ጋር እየተዋጋ ይቅጥልና ህይወታችንን ጨርሶ በማድቀቅ ለጠላት ሙሉ ቁጥጥር አሳልፎ የሚሰጠን ይሆናል።
የአካል ክፍሎች ለእርኩሰት ተላልፎ ከመሰጠት በላይ የመንፈስ ድካምን የሚያመጣ ነገር የለም፤ ደግሞ ራስን ለእግዚአብሄር ነገር አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ለአመጽ አሳልፎ ቢሰጥ እንደምን ያለ እርካታ ይሆናል፣ በረከትስ፣ ምህረትና ተስፋስ?
ማቴ.11:28-30 ‘’እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።’’
ቃሉ በሮሜ.3:20 የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና ስለሚል የሃጢያት ቀንበርና የህጉ ጫና የከበደባቸውን፣ በልቦናቸው ምጥ የተጨነቁትንና በአይሁድ ልማድ የተሰላቹትን እስራኤላውያን በነፍስ ምጥ ውስጥ ሆነው አያቸውና ደካሞችና ሸክማችሁ የከበደ እናንተ ሁላችሁ ወደ እኔ (ወደ ባለጸጋ ጌታ) ኑ ሲል ይጋብዛቸው ነበር፤ አህዛብም በጣኦት አምልኮ፣ በከንቱ ስርአት፣ ግራ በሚያጋባ ሰዋዊ ስራ፣ በሰይጣን እስራትና በፍልስፍና ትምህርት በጨለማ ውስጥ አሉና ኑ ከሃጢያት ባርነት ወደ ጽድቅ ነጻነት ልመልሳችሁ እያለ ይጣራል። ድምጹን የሚሰሙ ሁሉ ያኔ እንደሆነው ዛሬም ጭምር በቃሉ ብርታት ተስበውና ቀርበው በመስማት ሸክማቸውን ከእግሩ ስር በመጣል አርነት እየታወጀላቸው ይገኛል፤ የጌታ ኢየሱስ ደም ትምክህታችን ስለሆነ ማናችንም ብንሆን ለነጻነት በርሱ ብቁ እንሆናለን። በጌታ በሚሆነው ነጻነት ደስተኞችና የተፈታን እንሆን ዘንድ የድምጹን ጥሪ ልብ ልንል ለርሱም ልባችንን ልናፈስ ተገቢ ነው። የተቆረሰው ስጋውና የፈሰሰው ደሙ ወደ አምላክ የማቅረብ፣ ከርሱም ጋር የማስታረቅ ለመንግሱቱም ብቁ የማድረግና የሰማያዊ አገር ወራሽ የማድረግ ችሎታ አለው።
በዘፍ.49:15 ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ እንደሚል በመንፈስ የሚሆን እረፍት የህሊና እረፍት አለበት፣ የነፍስም ጉትጎታ የሚቀርበት ነው፣ በሞት ጥላ ከሚመጣ የነፍስ ምጥ በርሱ ነጻ መሆን አለ፦ የልብ መፈታት ቢሆን የመንፈሳዊ ህይወት ከፍታ ሁሉ በርሱ ይቻላል። የአምላክ የይቅርታ ጸጋ ህይወትን ይሞላል፣ በክርስቶስ የሆነው የጽድቅ ስራ በጸጋው ተካፋይነት የሚገኝበት ነው። በኢየሱስ ሞት የተገኘውን ህይወት በሙላት የምንቀበልበት አንድ መንገድ ስለሆነ የመንፈስ እረፍት ታላቅ የእግዚአብሄር ጸጋ የሚታይበት ነው። ሰዎች ነፍሳቸው ስታርፍ ደህንነት ይሰማቸዋል፣ ማረፍያዋ የአብረሃም እቅፍ መሆኑን ትረዳለች፣ የዳንን ሁላችን በጌታ ክንድ ስር ሆነንም እንመካለን::
በእርግጥም ማስተዋል ያገኘ ሃጢያተኛ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ያለ የማስተዋል መንቃት ሆኖለት ቢሆን ከበረታበት ድካም ተላቅቆ ይበረታል፤ እግዚአብሄር እየቀሰቀሰው ስለሚሆን ወደ ብርቱው ጌታ ያዘነብላል፤ ህሊናው እየጎተጎተው ስለሚንቀሳቀስ፣ በታደሰው ክፍሉ እየተዘረጋ ስለሚያስስም ፈጽሞ እስኪረካ ድረስ እንደቀድሞ ባለበት አይደበትም፣ የጣፈጠ እረፍቱ ያለው ጌታ ኢየሱስ ዘንድ ብቻ ነውና ወደ እርሱ የመድረስ ግቡ እንደገና ተጠናክሮ ሊነሳሳ የግድ ነው፤ ሆኖም ወደ እርሱ እስካልደረሰ ድረስና ለቅዱሱ ጌታ ጥሪ ትክክለኛ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ ግን ያው እንደለመደው ውስጡ በመንፈስ ጥቃት እንደቆረቆዘ፣ በአዚም እንዳንቀላፋ፣ በአጋንንት እውቀት እንደተሳከረና በህሊና ክስ እንደታወከ ይቀጥላል። የምስራች! ምንም ደካማ ብንሆን የጠራን ጌታ ይራራልናል፣እንዲህ እንደተባለ፦
‘’እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤’’ (መዝ.103:8-13)
ስለዚህ የሚራራልን አምላክ ሊያተርፈን አስቦልን ታላቅ ስራ ሰርቶአል፤ ከለበሰው ሥጋ የተነሣ ጽድቅ ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ የሰው ዘር ደክሞአል፤ ለሙሴ የተሰጠው ሕግም የሰውን ነፍስ ከሞት ሊያድን ስላልቻለ እግዚአብሔር ቃሉን ስጋ አድርጎ የሰው ልጅ በእግዚአብሄር ፊት በምህረት ይታይ ዘንድ መባና መስዋእት አደረገው፣ እንዲሁም ጻድቅ ሥጋውን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ አቀረበው፤ ኃጢያት ባስከተለው ሞት ምክኒያት የሰው ልጅ በሙሉ ከፍርድ በታች ስለተደረገ እግዚአብሄር ስለ አዳም መዳን ልጁን ላከ፣ በአዳም ኃጢአትም ምክንያት በርሱ ምትክ ልጁን ልኮም መዳንን አድርጎአል፤ ስለዚህ በተሰራልን የመስቀል ስራ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንድንመላለስ የሕግ ትእዛዝ ተፈጽሞ ኃጢአትን በክርስቶስ ሥጋ ተኰንኖአል።
የሃጢያትና የሞት ህግ የሙሴ ህግ ነው፤ ህጉ የሃጢያት ህግ የተባለው ሃጢያትን የሚደግፍ፣ የሚያበዛ ወይም የሚያበረታታ ሆኖ አይደለም፣ ነገር ግን በሃጢያተኛው ስጋ ላይ የሚያስተላልፈው ቅጣት ከፍ ያለ ጭካኔውን ስለሚያሳይና ይቅርታ ስለሌለበት ብቻ ነው፤ በተረፈ ህጉ ጻድቅ ነው፣ የሚጠብቀው እስካለ ድረስ በህይወት መኖር ይችላል። ሰው ግን ሃጢያት የተሸከመ ስጋ ስላለው በተዋለደው መጠን ሃጢያትና ሃጢያተኛ እየበዛ ሄደ፤ የሰው አእምሮ በሃጢያት እውቀት እየረቀቀ እለት ከእለት እየጨመረም በመሄዱ ሃጢያት እየበረታና ውስብስብ እየሆነ ቀጥሎአል። ሰው የሚሰራው ስራ ጽድቅ የለውም፣ ሰው የሚፈጥረው ነገር ደግሞ የሰውን ሃጢያት የሚያባዛና የሚያወሳስብ ሆነ እንጂ አንድ ኢንች አልቀነሰለትም። በኛ ዘመን የተፈለሰፉ ቴክኖሎጂዎች ቢሆኑ የሃጢያት መባዣ መንገድ ሆኑ እንጂ ሰውን በነፍሱ በኩል አልረዱትም፤ እንዲያውም በእውቀቱ አስታበየው እግዚአብሄር ማነው? አሰኙት እንጂ አምላኬ ይህን አደርግ ዘንድ አስቻልከኝ እንዲል ፈጽሞ አላስቻሉትም።
የሙሴ ህግ የሞት ህግም ተብሎአል፤ ሃጢያት እየበረታ በሄደ መጠን በህጉ እየሞቱ የሄዱት ሰዎች በዚያው መጠን ጨምረዋልና። በአለመታዘዝም ምክኒያት ሞት በአለም ላይ ነገሰ፤ በዚያው ልክ የህጉ ጉልበት ብርታቱ እየተገለጠ ሄደ፣ ሞትም ከመቀነስ ይልቅ ተስፋፋ፤ ሞት የመኖርን ተስፋ እየገደለ፣ ሰዎችን ተስፋ ቢስ እያደረገ፣ ሰውም ለእግዚአብሄር በፈቃደኝነት ከመታዘዝ ይልቅ ወደ አምላክ መመልከትን እንዲተው አደረገ። ህጉ ሰውን ባገኘው ልክ ይገድለው ነበር እንጂ ህይወትን ወይም የህይወትን ተስፋ አልሰጠም፣ ማንንም አላስተረፈም። ስለዚህ በህግ ማንም ተስፋ የሚያደርግበት ሳይሆን የሚቀጣበት በመጨረሻም የሚሞትበት ነበር፣ የህይወት ተስፋ ስላልነበረው ህጉን በመፍራት በፍርዱም በመሳቀቅ ሁሉም ይኖር ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ግን የህይወት ራስ በመሆን ሰው የዘላለም ህይወት ተስፋ እንዲኖረው የእርሱንም መገለጥ እንዲናፍቅ አደረገው፤ በዚህ እግዚአብሄርን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ተስፋ በማድረግ የሰጠውን አዲስ ኪዳን እንዲመለከት አስችሎአል ።
ጌታ ኢየሱስ ህይወታችን በመሆን፣ ከባርነት ነጻ ሊያወጣን በመቻሉ፣ በወንጌል መታዘዝ ከእርሱ ጋር ለዘላለም የምንኖርበትን አዲስ የህይወት አሰራር በመፍጠሩና መንፈሱን በእኛ አሳድሮ በህይወት ተስፋ እንድንለመልም በማድረጉ የህግን ሸክም አራግፎታል። ነፍስን ከሚያደክመው ከሞት ህግ ነጻ በመውጣት ከእግዚአብሄር ጋር የሚያኖረንን የህይወት ህግ ሊሰጠን ችሎአል። በደሙ በማጠብ ዳግም የምንወለድበትን ጸጋ የሰጠን ዋጋ ከፍሎ ነው። ስለዚህ አሁን ሃጢያት የሰለጠነበት መንፈሳዊ አለም አይገዛንም፣ አርነት ያለበት የእግዚአብሄር መንግስት ይገዛናል እንጂ፤ በዚያ መታዘዛችን የሚታይበት ሁሌ በህይወት የምንኖርበት በር የተከፈተበት በመሆኑ ደስተኞች ነን።