መንፈሳዊ ሪቫይቫል- ከሴኬም ወደ ቤቴል ተመለስ!

የእውነት እውቀት

እግዚአብሄር ያእቆብን ስለወደደው ወደ በረከቱ ስፍራ እንዲመለስ አስታወሰው፡-
ዘፍ.35:1-10 እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፡- ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤ ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ። በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው።ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት። በዚያም መሰውያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።… እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።እግዚአብሔርም፡- ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው።”
ሪቫይቫል ወይም መንፈሳዊ ልምላሜ/ተሃድሶ እግዚአብሄር ሲያመጣ በአማኙ/በማህበሩ ህይወት ውስጥ የተከማቸውን ስጋዊ ጥርቅም/ ግሳንግስ ነገር በመጥረግና ህይወትን በዝገትና በብል የሞላውን የህይወት ጉዋዳ በማንጻት ነው፡፡ተሀድሶ ያረጀብንን መንፈሳዊ ልምምድ በአዲስ ይተካል፣የጣልነው ወይም የዘነጋነው የእግዚአብሄር ጸጋ እንደገና በውስጣችን እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል፣ የተውነው ወይም ከልባችን የወጣው የተስፋ ቃል በውስጣችን ማብራት እንዲጀምር ያደርጋል፣ ንሰሃ ያመጣል.. ለያእቆብም ያን ሊያደርግ እግዚአብሄር ወሰነ፡-
ሪቫይቫል በያእቆብ ህይወት እንዲጀምር ያእቆብ ወደ ቤቴል መመለስ ነበረበት፡፡እግዚአብሄር ያእቆብን ከተቀመጠበት የህይወት አዘቅት መሀል ጠራውና ቀድሞ ወደተገናኘውና ተስፋ ወደገባለት ስፍራ ወደ ቤቴል እንዲመለስ አመለከተው፡፡ያእቆብም እንደታዘዘው ወጣ፣ እንደወጣ ግን ቆይታውን በሴኬም አደረገ፡፡ሆኖም እግዚአብሄር የነገረው አቅጣጫውን ወደ ቤቴል ማረፍያውንም በዚያው እንዲያደርግ ነበር፡፡
የተኛን ሰዎች ወደ መንቃት ስንመጣ እንደመባነን ብለን ባገኘነው አቅጣጫ እንድንሮጥ አይደለም ጥሪው፡፡ካንቀላፋንበት ስንነቃ ከመራመዳችን በፊት ቀና ማለት፣ ዙርያውን ማየት፣ያለንበትን ሁኔታ ማገናዘብ፣ ለጉዞ ማቀድ፣ የምንጉዋዝበትን አቅጣጫ ማስተዋልና መጨረሻችንን ማለም፣ እግዚአብሄርን በማስቀደምና በመጠየቅም ወደዚያው መጉዋዝ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
ለያእቆብ ከተያዘበት የአጎቱ አገዛዝ ስርአት መውጣት ለህይወቱ የነጻነት ብስራት ነበር፡፡ያእቆብ ለብዙ ዘመናት በአጎቱ ቤት በባርነት አገልግሎአል፡፡ዘመኑን ሁሉ ለራሱ ፈቃድ መፈጸም ሲል አገልጋይ ከሆነበት ክልል ውስጥ ስለከረመ እግዚአብሄር የነገረውን ዘንግቶ ነበር፡፡ስለዚህ የእግዚአብሄር የጉብኝት ጊዜ ሲደርስ እግዚብሄር አነቃውና ከአጎቱ እንዲለይ ነገረው፡፡
ያእቆብ ወደ ቤቴል እንዲሄድ የታዘዘው በዚያ እንዲኖርና ለእግዚአብሄር መሰዊያን እንዲሰራ ነበር፡፡ወደ መሰዊያው መጠጋቱ ምህረትንና ጥበቃን እንዲያስገኝለት ሲያስችለው በመንፈሳዊ ህይወቱ ተነቃቅቶም ለአባቶቹ የተነገረውን የተስፋ ቃል እንዲያነሳ፣ እግዚአብሄርን እንዲያመልክና እንዲያገለግል ነው፡፡
ያእቆብ ግን ወደ ቤቴል በሚያደርገው ጉዞው መሀል ከሴኬም ጎራ አለ፡፡ያእቆብ በእግዚአብሄር ድምጽ ለመጉዋዝ ተነሳ እንጂ የምሪት አቅጣጫውን በራሱ እየቀየሰ ነበር፡፡ስለዚህ ሴኬም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ቆም አለ፡፡በሴኬም ድንኩዋኑን ተከለ፣መሰዊያም ሰራ፣ኑሮውም በዚያ የተቃና መሰለ፡፡ብዙም ሳይቆይ ግን ሴኬም ያእቆብ የተዋረደበት ስፍራ ሆነ፡- ልጁ ዲና በሀገሬው ሰው ተነውራ ለያእቆብ እፍረት የሆነበት፣ ልጆቹ ስምኦንና ሌዊ በበቀል ደም አፍስሰው መከራ በቤተሰቡ ላይ የፈጠሩበት ስፍራ ሆነ፡፡
ዘፍ.34:30 ”ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፡- በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።”
እግዚአብሄር አንስቶ ሲያንቀሳቅሰን በምሪቱ ካልቀጠልን በመሀል የምናስገባው የራሳችን ነገር ይፈጠራል፣ ያም ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ሴኬም ያእቆብ እንዳሰበው የሚያርፍበትና መሰዊያ ሰርቶ የሚያመልክበት ስፍራ ሳይሆን ቀርቶ ለህይወቱ የሚሰጋበት ስፍራ ሆነበት፡፡እግዚአብሄር ግን ጣልቃ ገብቶ ሲመራው እናያለን፡-
ዘፍ.35:1-5 እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፡- ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።
በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው።ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም።
የሚሻለው ወደ ተነገረው ወደ ቤቴል መውጣት ነው፡፡ከማይበጀው ከዚያ አገር የሰበሰቡትን የአመጽ በረከት እዚያው ቀብረው በታደሰ መንፈስ አምላካቸው ወደ ወሰነው ስፍራ መጉዋዛቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡
በዚህ ዘመን ግን እግዚአብሄር በዙሪያችን ሞገሱን አድርጎ ለጠላት ፍርሀት እንዳንሆን የሚያደርገው ነገራችን ምንድ ነው ብለን ብንጠይቅስ?
• መንፈሳዊ ሪቫይቫልን የሚከለክለው ከሴኬም የሚሰበሰብ አላስፈላጊ ነገር በህይወታችን ሲኖር
• ቃሉን በማስተዋል ለመተግበር አለመቻል
• የራስን አሳብ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር መቀላቀል
• በማየት መመላለስ
• የአለም ምኞትና የአይን አምሮት እኛነታችንን መውረስ ጥቂቶቹ ምክኒያቶች ናቸው፡፡
እኛስ በዘመናችን እንዴት እንድንጉዋዝ ትሻለህ ብለን እግዚአብሄርን ብንጠይቀው በቃሉ የሚለን ምንድነው? ለምሳሌ ያህል የሚከተለው ጥቅስ አካሄዳችን እንዴት መሆን እንዳለበት ያሳያል፡-
ምሳ.2:6-15 ”እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል።የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተው፥ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው” ይላል፡፡
ከአፉ/ከቃሉ እውቀትንና ማስተዋልን በታዛዥነት በመቀበል ያለ ነውር መሄድ፣ ጽድቅን፣ ፍርድን ቅንነትና መልካም መንገድን መከተል መንፈሳዊ ልምላሜን የሚያስጠብቁ መሳርያ ናቸው፡፡