መንገዱን እየተነጋገርን እየተረዳንም

የእውነት እውቀት

መንገድ መንገድ ስንል ምክኒያቱ ምድር ላይ የተዘረጋ አንድ በአቅጣጫ የሚመራ የጉዞ መስመር ላይ ለማተኮር አይደለም። ምድር ላይ በተዘረጋው መንገድ ላይ እለት እለት እንመላለሳለን፣ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፣ ምስጢርም የለውም። በመንፈሳዊ ቋንቋ ውስጥ መንገድ ተብሎ ስለሚጠራው በምድራዊው መንገድ ስለተመሰለው ነው እዚህ ላይ የምናነሳው። በዚህ ርእስ ደጋግመን ብንነጋገር ጠቃሚ ነው፣ በየጊዜው መለስ ብለን ብናተኩርበት ተገቢም ነው፣ ምክኒያቱ መንፈሳዊ ግንኙነትን ስናነሳ በዋናነት ስለምናነሳው፤ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ጉዞ ስናስብ መንገዱ አብሮ ስለሚታሰብም ጭምር ነው።
መንገድ የህይወት ጉዞ መመሪያ ነው፤ መንፈሳዊ የህይወት መስመር ነው፤ ይህ ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም። መንገዱን እናውቅ ዘንድ እየተነጋገርን እየተረዳንም እንሄደዋለን የምንለውም ለዚህ ነው፤ ቅዱሳን ስለዚህ ነገር በጥልቀት ይመለከቱ ነበር፦
‘’አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር።’’ (ሃስ. 19:1-9)
የሃዋርያው ጳውሎስን አትኩሮት እንመልከት፦ ሃዋርያው ወደ መጣበት ከተማ እንደደረሰ ደቀመዛሙርቱን አፈላልጎ አግኝቶአል፤ እንዳገኛቸውም ማወቅ የፈለገውን ነገር ሲጠይቅ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ሲጠይቃቸው የህይወት ይዘታቸውን መመርመር ያዘ፤ በነርሱ መልስ ውስጥ ወዲያው ያገኘው ነገር የመንገዱ ነገር ነው፤ በየትኛው መንገድ ላይ ነበሩ እነዚያ ደቀመዛሙርት? የብሉይ ኪዳን መንገድ ስንመለከት ህግን መሰረት አድርጎ እግዚአብሄር ባስቀመጠው የአምልኮ ስርአት መኖርን ይጠይቃል፤ እያንዳንዱ የሙሴ ስርአት፣ ትእዛዝና የተቀመጠው ህግ በተግባር ይታይ ዘንድ የብሉይ ኪዳን መንገድ ያዛልና። ወደ አዲስ ኪዳን ሲመጣ ኢየሱስ ቦታውን ይረከባል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የእምነት አካሄድ በእርሱ አንጻር ይፈተሻል፣ አካሄዱም በእርሱ ጸጋ በኩል ይመረመራል። ንሰሃና የሃጢያት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ፣ በይሁዳ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ እንዲሰበክ በተነገረበት ልክ ያልሆነ መንገድ እንደሆነ ውድቅ ይሆናል። ለኤፌሶን አማኞችም የቀረበው ጥያቄ አዲሱን መንገድ (በክርስቶስ የተመረቀውንና ወደ ቅድስት በስጋው በኩል የሚያስገባውን) በእውቀት ተቀብሎ በእምነት ዳግም ያልተወለደ ሰው እውነተኛውን መንገድ እንዳልያዘ በእርግጥ መታወቅ አለበት ማለት ነው።
የህይወት መንገድ በክርስቶስ እውቀት ላይ የተመሰረተ ነው። መንገዱ እርሱን አውቆ በማመን ይጸናል። ይህንም ለማረጋገጥ ሃዋርያት በደረሱበት ስፍራ ስለመንገዱ ያስተምሩ እንደነበር እንመለከታለን፤ ሃዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ወደ ምኵራብ ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው መንገዱን ይገልጥላቸው ነበር፤ እንዲሁም አንዳንዶች መንገዱን በተቃወሙ ጊዜና እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ (የአዲስ ኪዳን መንገድ ክርስቶስን በገፉት ጊዜ) ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር ይላል። ምክኒያቱም መንገዱን እየተነጋገርን እየተረዳንም መሄድ የግድ ስለሆነ ያን ማድረግ ተገቢ ነውና። መንገዱን የሚነጋገሩ መረዳት የሚችሉት ዋናው ነገር የመንገዱን ባለቤት ነው፤ ይህን ሲነጋገሩ መንገዱ ወዴት እንደሚያደርስ ያስባሉ ይተማመናሉ፤ ይህም እምነት ያሳድጋል፣ በጭፍን ከመጓዝ ያድናል።
‘’አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል። እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።’’ (ዘዳ. 26:16-19)
እግዚአብሄር ከእኛ የሚፈልገውን በግልጽ አስቀምጦአል፣ ያን በምንከተል ጊዜ ከርሱ ዘንድ ተከትሎ የሚመጣ እንዳለም ገልጾአል። አንድ የተሰመረ ሰማያዊ የሆነ መስመር ከፊታችን ስለተዘረጋ ያን ተከትለን በመሄድ ከስህተት የምንድንበትን አጋጣሚ መፍጠር ዋና አላማው ነው። ከዚያ ውጪ ያለው ወደ አህዛብ ልማድ የሚመራ፣ ወደልማዳቸው የሚያስገባና እምነትን የሚያበላሽ ነው።
ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ክርስቶስ ኢየሱስ ጽድቅን የሚገልጥ መንገዳችን ሆኖ እናገኘዋለን፤ የተማርነው ወንጌልም የሚገልጠው እርሱን ሲሆን ለወንጌል የተለዩ በመንፈስ የሚመሩ አስተማሪዎችም የሚያመለክቱት ወደ እርሱ ነው። ሰዎች ስለዚህ መንገድ እንዲያውቁ የመንገድ ጠቁዋሚዎችን፣ አመልካቾችንና ሰራተኞችን እግዚአብሄር በየትውልዱ ያስነሳል። ለዚህ የተሾሙ ሰዎችም መንፈሳውያን ናቸው። በነርሱ ውስጥ የተቀመጠው ሸክም መንፈሳዊ ስለሆነ። መንፈሳዊ መንገድ ወደ መንፈስ አምላክ ያደርሳል። አንዱ አምላክ የአብረሃም አምላክ የይስሃቅና የያእቆብ አምላክ በመንፈስ የሚመለክ ነው፤ በመንፈስ የሚታመን ነው፤ በመንፈስም የሚያገለግሉት ነው።
በዘዳ. 30:15-20 እግዚአብሄር ሁለት መንገዶችን በህዝቡ ፊት አኑሮ ወደፈለጋችሁት ምርጫ ሂዱ ብሎአቸዋል፣ ቸር አምላክ ስለሆነ ግን ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ ይላል። ሰው በህይወት መንገድ ይሄድ ዘንድ እንደሚገባው ሲያስታውቀውም እንዲህ ይላል፦
‘’በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።’’
የሰው ምርጫ ወላዋይ ስለሆነ እግዚአብሄር ከጥፋት የሚከለክል ምህረቱን በማስታወቅ በእምቢተኝነት ምክኒያት የሚመጣውን በማሳወቅ ያስጠነቅቃል፦
‘’ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም፥ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም። በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።’’
በእግዚአብሄር መንገድ ላይ ያሉት የመንገዱ ፍሬዎች በግልጽ ተቀምጠዋል፤ መብዛትን፣ ፍሬያማነትን፣ ከእግዚአብሄር ጋር በምህረት መኖርን፣ በአጠቃላይ በእርሱ ጥላ ስር ማደርን ሊቀበል የሚሻ ያን መንገድ ሊኖርበት ይገባል።
ሁልጊዜ መንፈሳዊነት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ነው። መንፈሳዊ ሰውም የሚረጋገጠው መንፈስ ቅዱስ ያለው ሲሆንና መንፈሱ ፍሬማ ያደረገው እንደሆነ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን በሚገልጠው ፍሬ ስራውን በእኛ ያሳውቃል።
የሰው ልጆች ሁለት ነገር ስለጎደለን ከእግዚአብሄር ርቀናል፤ የመጀመሪያው ከእግዚአብሄር ጋር ያለን አቀራረብ በግልጽ ልንገነዘበው ያለመቻል ነው። በሌላ በኩል ራሳችንንና አቅማችንን ራሱ በቅጡ አላወቅንም። በነዚህ ሁለት ስህተቶቻችን እግዚአብሄርን እንገዳደራለን፤ ያውም በማያዛልቅ ሙግት። ያም መጨረሻችንን እያከፋው በፍርድ ውስጥ ትውልዶች ተፈራርቀዋል። የርሱ መንገድ ሲገለጥ ግን ወደ እግዚአብሄር ዞር ያደርገናል፣ በእውነት ወደ እርሱ ያቀርበናል፤ የሃዋርያው ጳውሎስ የቀድሞ ማንነቱ ለእኛ ትልቅ ምሳሌ ነው፤ የርሱ ታሪክ በተለይ አውቀናል ብለው የራሳቸውን መንገድ ላሰመሩ፣ በርሱ በስህተት ለሚጉዋዙ፣ ሌሎችንም በዚያ ለሚመሩ የንሰሃ መንገድ የሚሆን ነው። እንዲህ አለ፦
‘’ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ።ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው።’’ (ሃስ. 9:1-5)
አንዳንድ መንገዶች የጌታ መገኘት ያለባቸው ሳይሆን የመቅሰፍት ሰይፍ የቆመባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሳንረዳና ሳናስተውል በነዚያ ላይ ስንጉዋዝም እድሜያችንን ሊያሳጥሩ ይችላሉ። እግዚአብሄር በመንገዱ ላይ እንቅፋት የሆነን ሰው ሊያስወግደው ጫፍ ላይ ሳለ ተገለጠለትና እንዲመለስ አስጠነቀቀው፤ ይህ ሰው ከጥፋት የተመለሰ፣ መንገዱን አጥብቆ የተማረ ከዚያም አልፎ ለጌታና ለመንገዱ እውነተኛና ታማኝ አገልጋይ የሆነ ነው። መንገዱን መቃወም የመንገዱን መሪ ያስቆጣል፤ መንገዱን የሚያደናቅፍ አይጠፋም፣ የመንገዱ ባለቤት ግን በቅርበት ይቆጣጠረዋልና ድንገት ደርሶ ያጠፋዋል፤ ደቀመዛሙርት ባመኑበት መንገድ ያመኑትን ጌታ የሙጥኝ ብለው ሲኖሩ መውጣትና መግባታቸውን እየተከታተለ የሚያሳድድ የሳኦል መንፈስ ነበር (አሮጌው የጳውሎስ ማንነትና ሃይማኖቱ ነበር)። ኢየሱስ ግን ተገለጠለትና መንገዱ ማለት እኔ ስለሆንኩ የምታሳድደኝ እኔን ነው የሚል መልእክትን ገለጠለት፤ መልካሙ የሳኦል ልብም ተመልሶ ተረፈ፤ የመንገዱን ባለቤት አወቀ፣ አመነው፣ ወደደው፣ ተከተለው፣ ሰበከው፣ ተሰዋለት፣ በክብር ወደ እርሱም ተሰበሰበ።
በፊል. 3:1-10 ውስጥ በቅን ወንድሞች መሃል ለሚከሰቱ አጥፊዎች፣ መንገዱን ከሚያበላሹ ክፉ ሰራተኞችም አጥብቀን እንድንጠነቀቅ ያሳስባል፤ እነዚህን ሰዎች ከውሾች ጋር ያመሳስላቸዋል፣ ከነዚህ ትፋት ተጠበቁ ይላል፣ በህዝቡ መሃል እግዚአብሄር የሾማቸው አስመስለው ከሚያስቱ ከክፉዎችም ሠራተኞችም ተጠበቁይላል፤ ሃሰተኞች የእግዚአብሄርን አሳብ በማገልገል ፋንታ የመሰላቸውን በማድረግ ወገኖችን ያሰናከላሉና ከነርሱ ሁሉ እንድንጠበቅ ይመክራል፤ እነርሱን በተመለከተ ከጌታ መላካቸውን በሚያጠናክር ሁኔታ ሲያሳስብ ይህን ተናግሮአል፦
‘’እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ’’
ሃዋርያው ከአሮጌ መንገድ የወጣው በስጋ ከሚታመንበት አይሁዳዊ ስርአት በመውጣቱ ነበር፤ በዚያ መንገድ ውስጥ የነበሩ እንደምን በስጋ በሆነ ዕብራዊነት ይመኩ እንደነበር የምንመለከተው ነገር ነው፤ ነገር ግን ከዚያ የሚልቀው የጌታ አዲስ መንገድ ሃዋርያውን ትምክህቱን እንዳስጣለውና በርሱ ምክኒያት የተከተለውን መከራ በደስታ እንዲቀበል አድርጎታል፣ ይህም የሆነው በሌላ ሳይሆን ‘’ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ’’ ባለው የውሳኔ ጉልበት ምክኒያት ነው።
‘’እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ’’ (እብ. 10:19-23)