መመለሰ – ለእውነት ንሰሀ

የእግዚአብሄር ፈቃድ

መታረቅ፣ መስማማት፣ ሰላም ማውረድ፣ መቀራረብና የመሳሰሉት የሰላም ማስቀጠያ መንገዶች በማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ የሰው ልጅ የአብሮነት እሴትን በልቡ አትሞ ስለያዘ በተለይ እርቅ በሚባል የአንድነት ማሰሪያ ላይ ትልቅ አትኩሮት አለው ሊባል ይቻላል፡፡ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ መታረቅን ይሻና መታረቂያውን የማይስማማበት አጋጣሚ ይገጥመዋል፡፡ሁላችን ብንሆን እርቅ ሰላም እንደሆነ ይገባናል ስለዚህ እንስማማበታለን፡፡የእርቁን ሂደት ወይም አላማ ግን ልንወድደው ካልቻልን አንቀበለውም፡፡ለምሳሌ የእግዚአብሄር ቃል በወንጌል በኩል መጥቶ ፡-
”እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”(2ቆሮ.5:20-21) ብሎ ሲናገር ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እርቁን በመርህ ደረጃ ወደን ሂደቱ ወይም አላማው ላይ ጥያቄ የምናቀርብ ብዙ ነን/ነበርንም፡፡እግዚአብሄር መማለዱ፣እግዚአብሄር ታረቁኝ ማለቱ፣መታረቂያው መንገድም ሰዋዊ ያለመሆኑ እንዲያውም ከአእምሮ በላይ ስለሚሆንብን ጭምር እጃችንን በእሺታ ፈጥነን አንዘረጋም፡፡ከእግዚአብሄር ጋር ምን አገናኘን የሚል ይጠፋል? – ምን አጣላን ብሎ የሚያስብ ብዙ ስላለ ማለት ነው፡፡ይቀጥልና በእኛ የወንጌል ጥሪ እግዚአብሄር እየማለደ ነው የሚሉት ሰዎች ላይ ጥያቄ ይነሳል፤ የክርስቶስ መልእከትም፣ እርሱ በእግዚአብሄር የሰው ልጆች ሁሉ የሀጢያት መስዋእት መደረጉም ጭምር ብርቱ ጥያቄ ሆኖ ትውልዶችን እያቆራረጠ ከዚህ ደርሶአል፡፡
ዋናው የ ”ኑ እንታረቅ” መሰረት መመለስ ከሚለው ራስን ወደ አንድ የህይወት ሰታንዳርድ(መንፈሳዊ ውሳኔ እንበለው) ወደዚያ የመታዘዝ ሂደት ማምጣት መሆኑን በመረዳት በዚያ ላይ ለማተኮር እንሞክር፡-
ኢሳ.30:15-16 ”የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፡- በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ፥ ነገር ግን፡- በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፡- በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ።”
መመለስ የሚለው መርህ ራስን ወደ ልቦና መመለስ፣ ራስን ወደ እግዚአብሄር መመለስና በእኛ ዘንድ ያለ የእኛ ያልሆነ ነገር ካለ ወደ ቀድሞ ባለቤቱ እንዲመለስ የሚቀርብ ጥሪን ሁሉ ያካትታል፡፡ነገር ግን አመጸኞችና ቀማኞች መመለስና ማረፍ በዚህ መንገድ አይሆንልንም ብለው በግልቢያ ሲሸመጥጡ እናያለን፡፡መመለስን የመሰለ የእርቅ በር ግን የለም!
ወደ እግዚአብሄር በመመለስ መታረቅ
መመለስ መርህ ነው ብለናል፡፡መርህ እንደመሆኑ በመመለስና ባለመመመለስ ምክኒያት የሚገኘውን ትርፍና ኪሳራ ማስላት ያስፈልጋል፡፡
ሐዋ.15:3-4 ”ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፥ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው።ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ።”
መመለስ ወደ እግዚአብሄር አሳብ ሲሆንልን ተከታዩን የመመለስ ፍሬ ተረካቢ ነን፡፡ስንመለስ እግዚአብሄርንና ክብሩን እናያለን፤በርሱ ቃል በኩል ራሳችንንም እናያለን፡፡እናይና የሳትንበትን፣ የበደልንበትንና ሀጢያት የሰራንበትን አካሄድ እናስተውላለን፣ ያ ብቻ አይደለም፣ የበደልነው በደልና ከርሱ ጀርባ ያለው ቅጣት ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡
1ነገ.8:47-49 ”በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው፡- ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ”
ወደ ራስ በመመለስ መታረቅ
በመመለስ ለመታረቅ በእግዚአብሄር ፊት አቀራረቡን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡እግዚአብሄር ትሁት አምላክ ነው፣ትሁታንንም ይቀበላል፡፡ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር ብቻ ሳይሆን ወደ ራሳችን እንድንመለስ ይፈልጋል፡-
ኢሳ.46:8-10 ”ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።”
መመለስ የፈቃድ ጥያቄ ነው፡፡ሰው ከፈቀደ መመለስ ይችላል፣ያለመመለስም ይችላል- የሚደርስበትን መቀበል ከቻለ፡፡መቀበል ቢፈቅድም መቁዋቁዋም አይችልምና ምርጫው ስህተት ይሆናል፡፡
ሕዝ.14:6፤18:30 ”ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ።ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፤… የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።” ይላል፡፡
እግዚአብሄርን እናውቃለን የሚሉ መመልከት ያለባቸው
ማቴ.3:1-2፣8‹10፡13፣9፡13 ”በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ፡- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። … እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤በልባችሁም፡- አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፡- ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። … ነገር ግን ሄዳችሁ፡- ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።”
ራሳቸው መመለስ የቻሉ የሌላውን መመለስ ይችላሉ
ሉቃ19:4-10 ”በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ።ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና፡- ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው።ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው።ሁሉም አይተው፡- ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ።ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው።ኢየሱስም፡- እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።”
በማይመለሱ ላይ የሚመለስባቸው ምንድነው?
ዘሌ.18:25-27 ”ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች።ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና”
አንድ አገር ለህዝቦችዋ ምሬት ለምን ትሆናለች? የአገሩ ልጆችና እንግዶች በሚሰሩት ርኵሰት ምድሪቱ ስለምትረክስ ሀጢያትዋ በተመለሰባት ጊዜ ጭንቀትዋ ይወጣል፡፡ እንዲህ አይነት መዘዝ ውድመትና ጥፋት በህዝብ ላይ በማመላለስ ዘመን ከዘመን የሀዘን ድባብ ያለብሳል፡፡
በንሰሀ የተመለሰ የሀጢያት ስርየት ያገኛል
ወደ እግዚአብሄር የተመለሰ ምህረትን ያገኝ ዘንድ በስሙ የሀጢያት ስርየት ይቀበላል፡፡የሀጢያት ስርየት በተስፋ የተጠበቀ፣ በነብያት የተነገረ የእግዚአብሄርና የሰው እርቅ ማህተም ነው፡፡በንሰሀ ተመልሰን ያለስርየት መቆም አንችልም፡፡ለእስራኤል ነቢያት የበራ ይህ እውቀት ለአህዛብ ሁሉ እንዲታወቅ ያስፈልጋል፡፡
ሉቃ24:47-48 ”በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።”
መጥምቁ ዮሀንስ በነበረው ምሪት የንሰሃ ጥምቀትን እየሰበከ ህዝቡን ወደ ጌታ አቀረባቸው፡፡ሀዋርያቶች ግን ሲጠበቅ የነበረውን በስሙ ጥምቀት የሚገኘውን የሀጢያት ስርየት በግልጽ ሰበኩ፣እንዲህ አሉ፡-
ሐዋ.10:43 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።”
በእውነት የተመለሱና የንሰሀ ፍሬን ያሳዩ የሀጢያት ስርየት ተሰብኮላቸው ጽድቅን አግኝተዋል፡፡ይህን መዳን በማይሰብኩና ፍሬን በማያፈሩ ግን ሰማይ ዝግ እንደሚሆንባቸው መገንዘብ ተገቢ ነው(ሀሥ2፡38)፡፡