ሕጉ የሚለውን እንስማ

የእውነት እውቀት

– ህጉ ስለ አምልኮ የሚለውን እንስማ
– ህጉ ስለ አምላክ ማንነት የሚለውን እንስማ
– ህጉ ህዝቡ ከአምላካቸው ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት የሚለውን እንስማ
– ህጉ ለማን እንደተሰጠ እንስማ
– ህጉ ወደ ማን እንደሚመራ እንስማ
ዘዳ.1:1-5‘’በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው።… በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ ይገልጥ ጀመር።’’
ህጉ ከእግዚአብሄር የምህረት መንገድ የሚያወጣና የሚያደናቅፍ የሰው ልጆች ጠላት እንደሆነ የሚያስመስሉ አስተማሪዎች ብዙ ናቸው፤ ህጉ ምን አደረገ? እኛን አጋለጠን እንጂ፤ ስለቅድስና አልባነታችን ፍርዳችንን ጮክ ብሎ ተናገረ እንጂ። በሌላ በኩል ህጉ በራሳችን ሃይል፣ እውቅት፣ ብቃትና ጽድቅ ምንም መሆን እንደማንችል የሚያመለክት፣ እግዚአብሄር ግን የሚሻል እቅድ ወደፊት እንደሚገልጥ አመልካችም ነበር። ህጉ ባይኖር እግዚአብሄር ሊሰራው የወሰነው ባልተነገረ፣ የእግዚአብሄር ህዝብ እግዚአብሄርን ማወቅ ባልቻለ፣ ሊመጣ ያለው መልካም ነገር ባልታወቀም ነበር። ህጉ የአዲስ ኪዳን አመልካችና መነሻ ነው፣ ስለዚህ ሃዋርያው በስብከቱ ከዚያ ይንደረደር ነበር፦
ሐዋ.28:23-24 ‘’ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም’’
እግዚአብሄር ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝቡ ክርቶስን ያስተዋወቀውና አይሁድ ስለክርቶስ ማንነት እንዲረዱ የተመሰከረላቸው በህጉ በኩል ነው፦
ሐዋ.26:22-23 ‘’ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።’’
የክርስትና ትምህርት እንደ አህዛብ ሁሉ መነሻውን ከሰዋዊ አስተሳሰብና ፍልስፍና የሚያደርግ ሳይሆን እግዚአብሄር ህግን ሲሰጥ አስቀድሞ እንደተናገረው እንዲሁ የሆነ ነው።
ሐዋ.24:10-16 ‘’ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል፦ ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።’’
ነገር ግን ህግ ሊመጣ ለነበረው የልጅነት ስልጣን ሞግዚት ሆኖ አገልግሎአል፤ ጸጋ የምንድንበት ስጦታ ሆኖ የተገለጠው በእግዚአብሄር ቸርነት ቢሆንም ይህን መልካም ጸጋ የሰጠ አምላክ በሙሴ እጅ ህግንም የሰጠ እርሱ ራሱ ነው። ልዩነታቸው ጸጋ ማንነታችን አጉልቶ በእግዚአብሄር ፍርድ ፊት የሚያቀርበን ያለመሆኑ ሲሆን ህግ ግን ያለምንም አጋዥ ስጦታ ብቻችንን ለፍርድ የሚያጋልጠን ነበር። ጸጋ ሲጋርደን ህጉ ገላለጠን፤ ጸጋ ጉልበት ሲሰጠንና በሃጢያት ላይ ሲያሰለጥነን ህጉ ያለምንም አጋዥ መፍትሄ ለስራችን ወደሚገባን ፍርድ የሚያንደረድር ቁልቁለት ሆነ። ሁለቱም ግን በጽድቅ ከአምላካችን ወጥተዋል።
የእግዚአብሄር ቃል በገላ.4:21 ላይ እንዲህ ይላል፦
‘’እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ…’’ ይላል። እስኪ ህጉ ስለእኛ ምን ይላል ነው ዋናው ነገር። ህጉ ስለ እኛ ብዙ ይናገራል፤ በእኛ ህይወት ስላለው ይናገራል፤ ስለምናደርገው ይናገራል… ሁሉንም ይናገራል። ሰዎች ግን ህጉን አልሰማም ሲሉ ከህጉ በታች ይሆናሉና፤ ቸልተኛ በመሆን ትእዛዙን ሲጥሉ፣ አልስማ ብለው በአለም ውስጥ እንደ ፈቃዳቸው ይኖራሉ፣ ህጉም ሳይተዋቸው በተላላፊነት አስሮ ያስቀምጣቸዋል፤ ማናችንም በህግ ደስተኞች አይደለንም፣ ነቀፋ ስላለብን ያንንም ህጉ ያለ ምህረት ስለሚገልጠውና ለፍርድ አሳልፎ ስለሚሰጠን ተስፋ እንቆርጥበታለን።
ሮሜ.7:7-16 ‘’እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ፦ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር። ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።’’
ሰዎች የእግዚአብሄርን ህግ ሲተላለፉና አልጠብቅም ሲሉ ከህግ በታች ራሳቸውን ያኖራሉ፤ በእርግማንና በሃጢያት ምክኒያት የሚሞቱ የሰው ልጆች እየጠፉ ያሉት ህግን ከግምት ውስጥ ስላላስገቡ ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ እምነት ስፍራዎች ሲያዘወትሩ ቢታዩም በምግባርና በህይወታቸው ይዘት ምክኒያት ከህግ በታች እንደወደቁ አያስተውሉም። በመልካም ባህሪያቸው ውስጥ እየተመላለሱ እንዳሉ ልበ-ሙሉ ሆነው ቢቀርቡም የእግዚአብሄርን ቃል ባለማወቃቸው የሚጠበቀው መታዘዝ ላይ አይደርሱም።
ሮሜ.7:7-14 ‘’እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ፦ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር። ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ።’’
የህጉ ድካም
እብ.7:18-24 ‘’ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን:- ጌታ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው።’’
እግዚአብሄር ህጉ ብቁ እንዳልሆነ በቃሉ አመልክቶአል፤ ስለዚህ ሲናገር ‘’ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች’’ በማለት ይህን እጥረት በሚሻል ሊተካ እንደወሰነ አሳይቶል፤ ህጉ ፍጽምና ጠይቆአል፣ ነገር ግን ሰውን ወደ ፍጻሜ ሊያመጣ አልቻለም። ይህ ግን የሆነው እግዚአብሄር ሰውን ቸል ብሎ ሳይሆን በሰው በኩል ላለው መንፈሳዊነት ሰዋዊ ችሎታ የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንደማይሞላ ሲያመለክት ነው። ህጉም ሰውን እንዲገልጥ እንጂ ሰውን ፍጹም እንዲያደርግ አላደረግም። ይህን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሄር ራሱ የፍጽምና ስራ ውስጥ ሊገባ ፈቀደ፤ ይህም ሰውን መውደዱን የገለጠበት መንገድ ነው።
ሰዎች ሊያስተውሉ የሚገባው ነገር በህጉ መንፈሳዊ መሆን እንደማይቻል መሆኑን ነው፤ ህጉ እግዚአብሄር በእኛ ህይወት ሊያይ የሚፈልገውን የህይወት ይዘት ይናገራል እንጂ ሰውን የሚያግዝ አልሆነም።
‘’ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ’’ እንዳለው ህጉ ምንም ጻድቅ ቢሆን፣ ምንም እንኳን ከእግዚአብሄር የተሰጠ ጻድቅ ትእዛዝ፣ ስርአትና ፍርድ ያለው ቃል ቢሆንም ማንም ሰው በርሱ በኩል ወደ ፍጹም አምልኮና ህይወት ሊደርስ አልቻለም፤ ህጉን የተቀበሉ ሁሎችም ወደ እግዚአብሄር ክብር በርሱ በኩል ሊመጡ አልበቁም። ህጉ አብቅቶ፣ አበርትቶና ሙሉ አድርጎ የሚያቀርብ አልነበረምና፣ የሰውን ድካም የሚገልጥ፣ ለፍርድ አሳልፎ የሚሰጥ ነበር እንጂ።
ሮሜ.4:14-17‘’ከሕግ የሆኑትስ ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኖአል የተስፋውም ቃል ተሽሮአል፤ ሕጉ መቅሠፍትን ያደርጋልና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም። ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።’’
እግዚአብሄር ህግን የሰጠው የሰውን ልጅ ያጠፋ ዘንድ ፈቅዶ አልነበረም፣ ሰው በራሱ ምንም እንደሆነ እንዲያውቅና፣ በርሱ ተስፋ መዳን እንዳለበት አጥብቆ እንዲረዳ ለማድረግ፣ ወደሚሻል የእግዚአብሄር የምህረት ስራ እንዲመለከት ነበር እንጂ። ስለዚህ የቀደመች ትእዛዝ ስትሻር ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋን ገብቶ ነው። የሚሻል የመዳን ተስፋ ተገለጠ፣ መድሃኒት ተገለጠ፣ ጸጋን ሰጠ!
እብ.10:1-6 ‘’ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ:- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም።’’
ከላይ እንደተመለከትነው የእግዚአብሄር ህግ ሰውን መንፈሳዊ አድርጎ እንዲለውጥ አልተሰጠም፤ በህጉ በኩል ግን የእኛ ህይወት በእግዚአብሄር ፊት ምን መሆን እንዳለበት አሳይቶናል፤ ምክኒያቱም ህጉ ሰውን የሚለውጥ ሃይል አልሰጠምና። ይህ የሚያሳየው ህጉን በመፈጸም ጽድቅን ያገኙ ዘንድ የሚደክሙ ድካማቸው ከንቱ እንደሆነ ያሳያል ማለት ነው። የጳውሎስ የቀድሞ ልምምድ ብናይ ምሳሌ ይሆናል፦
ፊል3:3-11 ‘’እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።’’
ህግ የጠየቀንን እያንዳንዱን ስራ ክርስቶስ ኢየሱስ ሰርቶ ፈጽሞልናል፣ ህግ እንዲያየን የሚፈልግብንን የህይወት ቁመና ጌታ ስላሳየልን ኢየሱስን የእኛ በማድረግ ያንን የህይወት ቁመና እንጎናጸፋለን፤ ጌታ ያን አንዴ ካደረገልን በእኛ ህይወት ውስጥ እርሱ መገለጡ ብቻ ከህጉ በላይ እንድንቆም ያደርገናል፤ በርሱ ያለው የህይወት መንፈስ ህያው አድርጎ ሊያቆመን በእኛ እንዲኖርም የእርሱ ፈቃድ መሆኑ ምንኛ አስደናቂ ነገር እንደሆነ ተመልከቱ፦
‘’እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም።በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና።ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ።’’ (ሮሜ 8:1-4)